| ከሥራ የታገዱት የባህር ትራንዚት... |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
ከሥራ የታገዱት የባህር ትራንዚት ሰራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ ነን አሉ
ከሥራ የታገዱ የባህር ትራንዚት አገልግሎት ሰራተኞች ከስራ ከታገዱበት ከግንቦት ወር 1999 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ መታገዳቸውን ተከትሎ ደሞወዛቸው በመቆሙ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ሰራተኞቹ እንደገለፁት፣ ከግንቦት 28 ቀን 1999 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ “የመዋቅር ለውጥ አድርጌያለሁ” በሚል ሰበብ የሁለት የሁለት ወር ደመወዝ እየተሰጣቸው ከስራ ሲሰናበቱ፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የገቡላቸውን ቃል ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ላለፉት ሰባት ወራቶች ያለምንም ገቢ በችግር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ከስራ ሲፈናቀሉ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የድርጅቱ ሰራተኛ ማህበርና የኢሠማኮ ባለሥልጣናት ባሉበት ሰብስበዋቸው 20 ዓመት አገልግሎትና ዕድሜያቸው 45 እና 55 ዓመት የሞላቸው ዘላቂ ጡረታ እንዲያገኙ እንደሚያደርጉ፣ ከ20 ዓመት በታች ለሠሩት ደግሞ ለዘለቄታው የሚቋቋሙበት ፕሮጄክት እንደሚያቋቁሙ፣ ይህ ሂደት እስከሚያልቅ ድረስ ድርጅቱ በየወሩ ደመወዝ እንደሚከፍላቸው ቢናገሩም “እንኳንስ ጡረታና ፕሮጄክት ሊቋቋም የወር ደመወዛችን ከቆመ ከስድስት ወራት በላይ ሆኗል” ብለዋል፡፡ ሠራተኞቹ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢያመለክቱም “እኛን አይመለከተንም” የሚል አጭር ምላሽ በማግኘታቸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የድርጅቱ መዋቅር ሲጠና መሰረት ያደረገውና ከሥራ ይሰናበታል የሚለው ከ12ኛ ክፍል በታች ያሉትን ሠራተኞች ሆኖ ሳለ፣ ከሥራ የተቀነሱት በሙሉ 12ኛ ክፍል የጨረሱና ከዚያ በላይ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው መሆናቸውን የገለፁት ሰራተኞቹ በመዋቅሩ መሰረት መመደብ የማይገባቸው የተመደቡበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ የኑሮው ውድነት ጣራ በነካበት ባሁኑ ጊዜ እንኳንስ የማይሰራውና የሚሰራም ቢሆን መኖር ባልቻለበት ሰዓት “እንዴት እኛ እንቻለው” በማለት ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ቤት ተከራይተው የሚኖሩት በየዘመድ ቤት መጠጋታቸውን፣ አንዳንዶቹ ልጆቻቸው ትምህርት እንዳቋረጡና ቀሪዎቹም በልመና ላይ የተሰማሩ እንዳሉ ሰራተኞቹ ገልፀው፣ “መንግሥት ህይወታችን ከማለፉ በፊት ሊታደገን ይገባል” በማለት ተማፅነዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ከድርጅቱ ከተቀነሱት 65 ሰራተኞች መካከል ሁለት ሰራተኞች በብስጭትና በችግር ምክንያት ህይወታቸው ማለፉንና፣ እነሱም የሟቾቹ እጣ ፋንታ ሳይደርሳቸው የሚመለከተው አካል ሊደርስላቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት የሕግ አገልግሎት ኃላፊ (ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጁ ተወካይ) አቶ ገብረወልድ ተሰማ የተፈጠረውን ችግር እንዲያስረዱን ጠይቀናቸው፣ “ድርጅቱ 20 ዓመት አገልግሎትና ዕድሜያቸው 45 እና 55 ዓመት የሞላቸውን ጡረታቸው እንዲከበርላቸው ለመንግሥት ልማት ድርጅት አስተላልፈን፣ እሱ ደግሞ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቅርቦት ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡ ከ20 ዓመት በታች አገልግሎት ላላቸው ሰራተኞች የአገልግሎት ክፍያ በመስጠት ውላቸውን እያቋረጡ መሆናቸውንና፣ ያልወሰዱም ካሉ እየመጡ መውሰድ እንደሚችሉ አቶ ገብረ ወልድ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |