Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow አይጠየፍ
አይጠየፍ Print E-mail
Tuesday, 08 January 2008
ወሎ ጐንደር ጐጃምና ትግራይን ይገዙ የነበሩትና በአቤቶ እያሱ ከራስነት ወደ ንጉስነት የተሾሙት ሚካኤል በ1907 ዓ.ም ጀሜ ኮረብታ ላይ ትልቅ የግብር ማብያ አዳራሽ ማሠራት ፈለጉ፡፡ ወዲያውኑ አይጠየፍ ን አስገነቡ፡፡

አይጠየፍ የተገነባው ከ50 እስከ 60 ኪ.ሜ ቁልቁለትና ዳገት እየተወጣ አልቡኮ ሳልመኔ ከሚባል ቦታ የጥድ እንጨት እየመጣ በሰው ጉልበት ነው፡፡ 1230 ካሜ ስኩዌር ላይ የተገነባው አይጠየፍ አንድ የጭነት መኪና ከነተሳቢው ያለምንም ችግር ማዘር ይችላል፡፡ እንቁላልና አጃ ዱቄትን እንደ ሲማንቶ በመጠቀም ድንጋዩን አጣብቀው ሠርተውታል፡፡ የደሴ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ እንደገለፁልን ሥራው የፈጀው ጊዜ አንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡

ዘጠና ሶስት ዓመት ያህል ዕድሜ ያስቆጠረው አይጠየፍ በ1965 ዓ.ም በአፄ ኃይለሥላሴ ከተደረገለት የቆርቆሮ ጥገና ውጭ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ጥገና ተደርጐለት አያውቅም፡፡

አይጠየፍ ውስጥ ሌሎች አዳራሾች ይገኛሉ፡፡ የልጅ እያሱ አዳራሽ፣ የንጉሥ ሚካኤል የፀሎት ቤትና ሌሎችም የሚገኙ ሲሆን በተለይ የልጅ እያሱ አዳራሽ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለፃ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት በመሆኑ ጥገና ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ሲባል በቅርቡ በሚሌኒየሙ የአይጠየፍ እጣፈንታ ምን ይሆናል.. በሚል ከባለሀብቶች፣ ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ላይም ኮሚቴ ተቋቁሞ የአይጠየፍን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቀየርና እንደ ቅርስነቱ ለጐብኝዎች ምቹ ለማድረግ ጥረት እየተደገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አይጠየፍ የንጉሥ ሚካኤል አዳራሽ ተብሎም ይጠራል፡፡ ያኔ በንጉሥ ሚካኤል የንግሥና ጊዜ ሶስት ዓይነት የግብር ስርዓቶች ነበሩ፡፡ በግብር ስነ - ስርዓቱ ላይ የአካባቢውን ደህንነት ችግርና የመሳሰሉት ሃሳቦች እየተነሱ ንጉሡ ከሕዝቡና ባላባቶች ጋር ይወያዩና መፍትሄ ይፈልጋሉ፡፡ በመጀመሪያው የግብር ስርዓት የሚበሉት ንጉሡና ቀማሾቹ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ባላባቶች ሲሆኑ በሶስተኛው ስርዓት ደሃው ሕዝብ ይመገባል፡፡ በእነዚህ በሶስቱም ሥርዓቶች የበር ጥበቃውን ጥሶ ቢገባ ለምን ጥሰህ ገባህ ብሎ ማንም አይናገርም፡፡ የንጉሡን ክብር አዋረድክ ተብሎ የሚቀጣውና የሚቆጣው የለም፡፡ በዚህም ምክንያት ደሃው ኗሪ ሕዝብ ..አይጠየፍ.. ብሎ ሰየመው፡፡ ሁሉንም ያለማዳላት የሚያስተናግድ ማለቱ ነው፡፡

የደሴን ስያሜ አስመልክቶ የተለያዩ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ ቀዳሚው ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው ከሌሎች ሰራዊታቸው በተለየችው ቀይዋ /ደስታ/ ድንኳን በመነሳት በሆጤ ሜዳ ልምላሜና በቦርከና ወንዝ ተማርከው አፄ ቴዎድሮስ ደሴ አሏት የሚለው አፈታሪክ ሲሆን ሁለተኛው ወደ ሰኞ ገበያ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ወ/ሮ ደስታ የሚባሉ ጠላ ሻጭ ነበሩ፡፡ በርካታ ነጋድራሶች፣ ሲራራ ነጋዴዎች ያልፉ ስለነበር ገራዶ ሜዳ ላይ ከነግመሎቻቸውና በቅሎዎቻቸው ሲያድሩ ለነሱ ጠላ ይሸጡ በነበሩት በወ/ሮ ደስታ ስያሜ ደሴ ተባለች ይላሉ፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ወሎ /ደሴ/ ላኰመልዛ ተብላ ትጠራለች፡፡ ቃሉ ኦሮምኛ እንደሆነ ያጫወቱን አቶ ገዛኸኝ ላኰ ማለት ማሰሪያ ሲሆን መልዛ ማለት ..ውበት.. ነው፡፡ የውበት ማሰሪያ መሆኑ ነው፡፡ በተፈጥሮ ውበታቸው የሚያማልሉት የወሎ ቆነጃጅት የበቀሉበት ምድር መሆኑን ለማመልከት የተጠቀሙበት ነው፡ እንግዳ አክባሪዎቹ የወሎ ሕዝቦች ውጫቸው ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ባህሪያቸውም ይመቻል፤ በርከት ያሉ ብሄሮች /የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሞ፣ የአገውና በመጠኑም የአርጐባ ብሄሮች/ መኖሪያ ናት፡፡ እስላምና ክርስቲያኑ ተቻችሎ የሚኖርባት ምድር መሆኗም ላኰመልዛነቷን ይመሰክራል ብለዋል ኃላፊው፡፡

ከ1920ዎቹ ጀምሮ በማዘጋጃ ቤት የምትተዳደረው ደሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ከ1990ዎቹ ወዲህ ከእንቅልፏ መባነኗን ይናገራሉ ነዋሪዎች፤ ታሪካዊ ቅርሶችም ይገኙባታል፡፡ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የወሎ ባህል አምባ አዳራሽ፣ አይጠየፍ፣ የንጉስ ሚካኤልና ወ/ሮ ስህን ት/ቤቶች እንዲሁም የልዑል አልጋ ወራሽ አሰፋ ወሰን ቤተ መንግሥት /መርሆ ግቢ/ ይገኝባታል፡፡

የመሪዎች መኖሪያ በመባል የሚታወቀው መርሆ ግቢ በቆንሰላ ፅ/ቤትነት እንዳገለገለ ይነገራል፡፡ በ1926 ዓ.ም አልጋ ወራሹ ወሎን ሲያስተዳድሩ ያሰሩት ሲሆን የተለያዩ መሪዎች ሲያርፍበት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት መርሆ ግቢ ወደ ኮሌጅነት ተቀይሯል፡፡ ጉዳት አይደርስበትም ወይ የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው አቶ ገዛኸኝ ኮሌጁ አፍርሶ ሊጠግነው ሳይሆን ቋሚ ቅርሱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት በማይደርስበት መንገድ እንዲጠቀምበት የክልሉ መንግሥትም አምኖበት እንደተሰጠ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኃይለስላሴ ቤተ መንግሥት እንደሚገኝ ሁሉ መርሆ ግቢም ኮሌጅ ቢሆን ተማሪዎቹ ስለ ታሪኩ የበለጠ እንዲያውቁ ያግዛቸዋል የሚል ማብራሪያም ጨምረዋል፡፡

ማንኛውም ቤተመንግሥት በዋናው ቤተመንግሥት ስር መተዳደር ይገባዋል በሚለው ህግ መሠረትም በቤተ መንግሥቱ /መርሆ ግቢ/ ውስጥ ይገኙ የነበሩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች በሙሉ ወደ ዋናው ቤተመንግሥት /አዲስ አበባ/ ተልከዋል፡፡

ወሎ የግሸን ደብረከርቤ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ረእየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል የሚገኝበትሪ፣ የሃይቅ እስጢፋኖስ ገዳም /የመጀመሪያው የእምነት ዩኒቨርሲቲ/፣  የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የመቅደላ አምባ ረየአፄ ቴዎድሮስ ሴፖስቶፓል መድፍ የሚገኝበትሪ፣ የውጫሌ ውል የተካሄደበት  ረበጣሊያንና ኢትዮጵያ መካከል ተደርጐ ለነበረው የአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው አንቀፅ 17 የተፈረመበትሪ እና የመሳሰሉት የሚገኙበት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ እንደነ ቦረና ጋስጫ አባጊዮርጊስ፣ ገዛዛ አቦ፣ ደብረ ፅጌ ድንግል ገዳም ያሉት ጥንታዊ ገዳማትም ይገኛሉ፡፡

ደሴ ደግሞ ወሎ ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች የተሻለ እንቅስቃሴ የሚስተዋልባት ከተማ ነች፡፡ ይሁን እንጅ በውስጧ ለሚገኙት ቅርሶች በተለይ ለአይጠየፍ አዳራሽ ትኩረት የሰጠች አትመስልም፡፡ ምንም እንኳን /ከላይ እንደገለፅነው/ የከተማው የባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቢናገርም ተጨባጭ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በስፍራው ተገኝተን እንዳስተዋልነው አዳራሹ ከአይጠየፍነቱ ወደ አስጠያፊነት ለመየቀር ጥቂት ቀርቶታል፡፡ ታዲያ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ይሁኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ..የእኛ ነው.. የሚል ስሜት ሊሰርፅባቸው ይገባል፡፡

በደመቀ ከበደ

 
< Prev   Next >