| ከቻይና በኮንቴነር ሲገባ የተያዘ ብር የለም |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
![]() ኮማንደር ደምሳሽ ኃይሉ ![]() የፖሊስ ድንገተኛ አሰሳ ቻይና ተሰርቶ በኮንቴነር ወደ አገር ውስጥ የገባ ፎርጅድ ብር በየትኛውም የአገሪቱ ኬላ ላይ እንዳልተያዘ የፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግነኙነት ኃላፊ ኮማንደር ደምሳሽ ኃይሉ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ በጥቁር ገበያ ዶላር በሚመነዘር ገንዘብ ላይ ሐሙስ ዕለት በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተያዘ፡፡ ከአሁን በኋላ ስግብግብ ነጋዴዎች በዝምታ እንደማይታለፉ ተገለፀ፡፡ ኮማንደር ደምሳሽ እንዳስታወቁት በአዲስ አበባም ሆነ በመላው አገሪቱ “ከቻይና በኮንቴነር ፎርጅድ ብር ተሰርቶ ሲገባ ተያዘ በሚል በስፋት የተሰራጨው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው” ስግብግብ ነጋዴዎች በስልክ ወሬ አናፍሰው የጨው ዋጋን በአዲስ አበባ 10፣ በክልል ከተሞች እስከ 28 ብር ድረስ እንዲሸጥ ማድረጋቸውን የገለፁት ኮማንደር ደምሳሽ “ከቻይና ሁለት ኮንቴነር ፎርጅድ ብር ሲገባ ተያዘ የሚለው ወሬም እንደጨው ገበያ ተመሳሳይ ይዘት አለው” ብለዋል፡፡ ኮማንደር ደምሳሽ ሲያብራሩ በየትኛውም ኬላ ፎርጅድ ብር አልተያዘም፡፡ ይህን ያህል መጠን ያለው ብር በፎርጅድ ደረጃ ይገባል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ የውጪ ምንዛሪን በመሰብሰብ የማጠራቀምና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር በስውር የሴራ ሥራ እንዳለ ከግምት ባለፈ የሚናገሩት ኮማንደር ደምሳሽ መንግሥት ቢዘገይም ከትናንትና በስቲያ ርምጃ መውሰዱ አግባብ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ “የተጠና” ነው በተባለው ዘመቻ ሐሙስ ዕለት በ25 የጥቁር ገበያ መመንዘሪያ ሱቆች የተገኙ የውጭ አገር ገንዘቦች ተይዘዋል፡፡ 35 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ እንደ ኮማንደር ደምሳሽ ገለፃ ህገወጦቹን የማሰስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኮማንደሩ የተያዘውን የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ይፋ ባያደርጉም ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደተያዘ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በዕለቱ በተመሳሳይ ሰዓት በአውሮኘላን ማረፊያ በተደረገ ፍተሻ ከአንድ ግለሰብ 4ዐ ሺ ዶላር መያዙ ታውቋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ የጥቁር ገበያ ዶላር መንዛሪዎችን ሲይዝ በአካል ተገኝተን በተመለከትንበት ወቅት አስተያየት የሰጡ እንደገለፁት በከፍተኛ ደረጃ የውጪ ምንዛሪ ሲዘዋወር እየተመለከተ መንግስት የጥቁር ገበያውን ዝም ማለቱ እንደጐዳው ተናግረዋል፡፡ በአንድ ተራ መስኮት ብቻ ባሉት ሱቅ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የውጪ ምንዛሪ ሲገኝ፣ በዶላር ምንዛሪ በየቀኑ ሲያሻቅብ መንግሥት የት ነበር? በማለት የጠየቁ በርካታ ናቸው፡፡ “በአዲስ አበባ 25 የዶላር መመንዘሪያ ሱቆች ብቻ አሉ ማለት ያስቃል” ያሉት አስተያየት ሰጪ ቡቲክ ቤቶች፣ ውስኪ ቤቶች፣ የቅርሳ ቅርስ መሸጫ መደብሮች፣ አነስተኛ የችርቻሮ መሸጫ የሚመስሉ ሱቆች የጥቁር ገበያ መናኸሪያ መሆናቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አያውቅም ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡ ኮማንደር ደምሳሽ የቀረበውን ቅሬታ ባይቃወሙም ፖሊስ የወሰደው ርምጃ ቀጣይነት እንደሚኖረው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ዋጋ በማናር ተጠቃሚውን ህብረተሰብ ክፉኛ ስለሚያማርሩት ነጋዴዎች መንግሥት ምህረት የሌለው ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ኮማንደር ደምሳሽ አስታውቀዋል፡፡ “ከአሁን በኋላ ስግብግብ ነጋዴዎች በዝምታ አይታለፉም” ያሉት ኮማንደሩ በጨው ነጋዴዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ዓይነት የንግድ ዘርፍ ግርግር እየፈጠሩ በአቋራጭ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ከንግድ ሥራ እስከማስገለል የሚደርስና ከዚያም በላይ በከባድ የወንጀል ድርጊት የሚጠየቁበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ “ጤፍ 750 ብር ገብቷል መባሉን ሲሰማ ህብረተሰቡ ከመደናገጥ ይልቅ ለምን? ማለት አለበት” በማለት ኮማንደር ደምሳሽ ምንም ነገር በተፈጠረ ቁጥር ህዝቡ የሌቦች ሰለባ ከመሆን ራሱን እንዲቆጥብ፣ ለፖሊስ በመደወል መረጃ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ህዝብን እያነጋገረ ስላለውና ወንጀለኞቹ በጥብቅ ሊቀጡ እንደሚገባ አስተያየት በሚሰጡበት የወርቅ ማጭበርበር ጉዳይ በተመለከተ ኮማንደር ደምሳሽ “ወንጀሉ በአገር ላይ የተፈፀመ ከባድ ወንጀል በመሆኑ ደህንነት፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ዋናው ኦዲተርና ፌደራል ፖሊስ በጥብቅ ይዘውታል” ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል፡፡ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ 8ዐ ከመቶ የሚሆን የተሳካ ሥራ እንደተሰራ ያመለከቱት ኮማንደር ደምሳሽ “የተዘረፈው ሃብትና ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ይመለሳል፡፡ ፖሊስ ህዝባዊነቱን በዚህ የምርመራ ስራ ያረጋግጣል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በባንክ እንዲታገድ ከተደረገው ገንዘብ በአጠቃላይ ከ10 ሺህ ብር በላይ አልተገኘም ለሚለው “በትክክል አሀዙ የለኝም፡፡ ግን የሚጠበቅ ነው” በማለት ኮማንደር ደምሳሽ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም ብረት ወርቅ ነው እያለ ገንዘብ ሲወስዱ አንድ ቀን እንደሚያዙ ስለሚያውቁት የዘረፉትን ገንዘብ ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ በየግድግዳውና ኮርኒስ ውስጥ ማስቀመጥን መርጠዋል” ብለዋል፡፡ ኮማንደር ደምሳሽ “አሳፋሪ” ባሉት የወርቅ ማጭበርበር ወንጀል ተመጣጣኝ ርምጃ እንዲወስድ የርሳቸውም ፍላጐት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |