| የአሜሪካን ሴኔት የምስራቅ አፍሪካን... |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
የአሜሪካን ሴኔት የምስራቅ አፍሪካን ያለመርጋጋት ችግሮች አዳመጠ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለስልጣኖች ሰኞ ዕለት በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ፊት ቆመው በሰጡት ቃል፣ በምሥራቅ አፍሪካ ለተፈጠረው አለመረጋጋት ኤርትራ ዋነኛ ምክንያት መሆኗን ጠቅሰው በኤርትራ ውስጥ ለሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛ ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታወቁ፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ክልል ውስብስብ ችግር ትኩረት በተሰጠበት በዚህ የሴኔቱ ጉባኤ ላይ ስድስት ምስክሮች ተገኝተው የምሥራቅ አፍሪካ ክልል ሁኔታ ከዩናይትድ ስቴትስ ሀገራዊ የደህንነት ጥቅም አንፃር ምን እንደሚመስል ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ የምትከተለውን ፖሊሲም መርምረዋል፡፡ የመጀመሪያው ፓናል አራት ከፍተኛ የቡሽ አስተዳደር ተወካዮችን የያዘ ነበር፡፡ እነዚሁ የቡሽ አስተዳደር ተወካዮች ስብሰባውን ሲመሩ ከነበሩት የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ሩስ ፊንጐልድ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በክልሉ የሚከተለው ስትራቴጂ ፊንጐልድ ተችተዋል፡፡ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ ጀንዴይ ፍሬዘር በበኩላቸው የምሥራቅ አፍሪካን በተመለከተ መንግሥታቸው እየተከተለው ያለው ጠቅላላ ስትራቴጂ ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን ያጠፉት ግን በክልሉ መረጋጋት ለመፍጠር እየታየ ያለውን መሻሻል በማብራራትና በመሀል ያጋጠሙ ችግሮችን በመዘርዘር ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ጅቡቲ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ያደነቁት ፍሬዘር “ኤርትራ ግን የዚህ ምስል ተቃራኒ ገጽታ ነች” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “በኢትዮጵያ፣ በዳርፉር ሶማሊያ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ድጋፍ ይሰጣል፣ በተመድ የሰላም አስከባሪ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል” በማለት የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አውግዘዋል፡፡ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ኤርትራ የምትከተለውን ስትራቴጂ የተቹት ፍሬዘር የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ሪከርድ አስከፊ ሆኖ እንደቆየና ከጊዜ ወደጊዜም እያሽቆለቆለ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ኤርትራን ለቀጠናው ስጋት እንደሆነች አድርጋ ኢትዮጵያ የምትወስዳት ከምን ተነስታ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፍሬዘር “ኤርትራ የኡጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን ታሰለጥናለች፣ በገንዘብ ትደግፋለች ታስታጥቃለች፣ የሶማሊያ ዜጐችን ታግታለች፤ የጦር ሀይሏን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አስጠግታለች” በማለት ኤርትራ ለምን ስጋት እንደሆነች አብራርተዋል፡፡ ከሶማሊያ ውጭ በሚንቀሳቀሱት የአልሸባብ ሽብርተኛ መሪዎችና በአልቃይዳ ኔትወርክ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተም ፍሬዘር በርካታ ምሳሌዎችን ሰጥተዋል፡፡ በኤርትራ ድገፍ የሚንቀሳቀሰውን የአልሽባብ የተሰኘውን ቡድንም በአካባቢው ለተፈፀሙ የተለያዩ ጥቃቶች ተጠያቂ አድርገውታል፡፡ የአፍሪካ መከላከያ ምክትል ረዳት ፀሐፊ ቴሬሳ ዌላንም ኤርትራ እየፈፀመች ባለው ተግባር ላይ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ ኤርትራ በክልሉ አለመረጋጋት የሚፈጥሩ አካላትን መደገፏ የሚያሳስብ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዌላን ኢትዮጵያ በኡጋዴን አካባቢ ትክክለኛ የሆነ የፀጥታ ችግር እንደተጋረጠባት አመልክተዋል፡፡ ኤርትራ ለኦብነግ የታጣቂ ቡድን ድጋፍ እንደምትሰጥ ጠቁመው ቡድኑ በኡጋዴን አካባቢ በፈፀመው የሽብር ጥቃት 70 ኢትዮጵያውያኖችና ዘጠኝ ቻይናውያኖች መገደላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኛው የዌላም ንግግር በዩናይትድ ስቴትስና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሚሊታሪ ግንኙነት የሚቃኝ ነበር፡፡ “ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያና በክልሉ የፀረ ሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር ከሆነው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን እርዳታ የገለጹት ዌላም ኢትዮጵያ የጸረ ሽብርተኝነተ ዘመቻዋን ስታካሂድ በአካባቢው ህዝብ ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ይሆናል ብላ ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታስብ አመልክተዋል፡፡ የዩኤስ.አይ.ዲ ርዳታ ሀላፊ ካትሪን አልምኪዩስት በበኩላቸው በሰጡት ምስክርነት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ፕሮግራም ቃኝተዋል፡፡ አልምኪዩስት ትኩረት የሰጡት በኡጋዴን የእርዳታ ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ በአካባቢው የምግብ ዋስትና በመሻሻል ላይ መሆኑን የገለፁት አልምኪዩስት በድርቅ ለተጎዱት አካባቢዎች ርዳታ የሚደርስበት መንገድ እንዲመቻች አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካ ሪፎርም ለማካሄድ፣ ሲቪል ማህበራትን ለማጠናከርና የጎሳ ግጭትን ለመቀነስ ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ፕሮግራም መንደፏን አስረድተዋል፡፡ የሰብዓዊ እርዳታ ቡድን በሶማሌያ ክልል አሁን እያካሄደ ያለውን የመስክ ጉብኝት እንደሚቀጥልና የኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስትሮች ፕሮግራሙን ለማስፈፀም ለሚያደርጉት ጥረትም እርዳታ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ በስሚው ሁለተኛ ክፍል አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመወከል ምስክርነታቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ናቸው፡፡ ሰዓት ለመቆጠብ ሲባል በሁለተኛው ፓናል ላይ ንግግራቸውን ያቀረቡት ሰዎች ቃላቸውን ሲሰጡ የነበሩት በፍጥነት ነበር፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጸረሽብርተኝነት ዘመቻ በኦጋዴን፣ ሶማሊያን የማረጋጋት ጥረት፣ ጸረ ሽብርተኝነትን በመደገፍና የሰብዓዊ እርዳታ መስጠትን በተመለከተ የአሜሪካ ሀይል ትክክለኛ ሚና የሚሉት ጉዳዮች በውይይቱ ላይ ተነስተዋል፡፡ በመጨረሻ ንግግር ያደረጉት በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ በሴኔቱ የተካሄደውን ጉባኤ “የተጠናና አስተዋይ እይታ” በማለት አድንቀዋል፡፡ የሽብርተኝነትን ዋነኛ መሠረት ለመቅረፍ፣ ድህነትን ለመቀነስና ዴሞክራሲን ለማጐልበት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልና በክልሉም ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ቁልፍ ሚና እንደምትጫወትም ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም “እንደነዚህ ዓይነቶቹን የተለያዩ ሰፊ ጉዳዮች ኮሚቴው ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ በአሁኑ ሰዓት ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጉዳዮች እውቅና መስጠቱን የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |