| “ብዙ ፕሮጀክቶቻችን ተጫራች... |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
“ብዙ ፕሮጀክቶቻችን ተጫራች አጥተው እየቸገርን ነው”አቶ ዛኢድ ወ/ገብርኤል፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛኢድ ወ/ገብርኤል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ እያከናወነ ስላለው ሥራ እንቅስቃሴና በአገሪቱ የመንገድ ግንባታዎች ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ እየተሰራ ነው? የፕሮጀክቶቹ የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? አቶ ዛኢድ፡- በ2000 በጀት አመት በአጠቃላይ 180 የሚሆኑ ፕሮጄክቶች አሉን፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በውስጣቸው ሌላ ፕሮጄክቶች ይኖራቸዋል፡፡ እነዚህ 180 ፕሮጄክቶች በተለያየ የእርከን ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ 100 የሚሆኑት የግንባታ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ስራዎችም አስፖልት ማሻሻያ ሥራዎች ናቸው፡፡ የአስፓልት ማጠናከሪያ ስራዎች፣ ጠጠር የነበረውን ወደ አስፓልት ኮንክረት መለወጥ፣ አዳዲስ አስፓልት መንገዶችን ጭምር የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡ ወደ 80 የሚሆኑት ፕሮጄክቶች ደግሞ በሚቀጥለው በጀት ዓመትና እንዲሁም በ2002 በጀት አመት ድረስ ባለው ዲዛይናቸው ተጠናቅቆ ወደግንባታ የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህን ፕሮጄክቶች ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፈነው በመንግሥትና በመንግሥት ሥር ሊካተቱ የሚችሉ የውጭ አበዳሪዎችና እርዳታ ሰጪዎች የሚሸፈን ነው፡፡ ሌላው የገንዘብ ምንጭ ደግሞ የመንገድ ፈንድ ነው፡፡ ከዚህ ፈንድ የሚገኘው ገንዘብ ለመንገድ ጥገና የሚውል ነው፡፡ ስለዚህ በ2000 በጀት ዓመት ለነዚህ ፕሮጄክቶች የተተከለልን በጀት 5.6 ቢሊዮን ብር ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከመንግሥት ወደ 3.58 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ከአበዳሪዎች 1.29 ቢሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ ተገኝቷል፡፡ ከእርዳታ ሰጪዎች የተገኘው ደግሞ 0.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከእርዳታ ሰጪዎች የተገኘ ገንዘብ ሲባል በእርዳታ መልክ ነው ወይስ በብደር? አቶ ዛኢድ፡- 1.29 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ብድር ነው፡፡ ይህም ብድር ከአለም ባንክ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከመሣሠሉት የሚገኝ ነው፡፡ 0.8 ቢሊዮን ብሩ ደግሞ በእርዳታ የተገኘ ነው፡፡ ይህም እንደ ጀርመን ጃፓንና የመሣሠሉት አገሮች ቀጥታ የሰጡት ገንዘብ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በዚህ ገንዘብ ምን ያህል ሥራ እየተሰራበት ነው? አቶ ዛኢድ፡- ከመንግሥት ከተመደበው 3.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከሞላ ጎደል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ተጨማሪ ወደ 3.5 ቢሊዮን ብር ተጠይቆ ወደ 1.7 ቢሊዮን ብር ተፈቅዶልናል፡፡ እንግዲህ ይህ ሲደመር ወደ በበጀት አመቱ ባለሥልጣኑ ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ ያገኘው 7.3 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደርገዋል፡፡ ይህ ማለት የተጠየቀው ገንዘብ በሙሉ አይፈቀድም ማለት ሳይሆን እንደ ፕሮጀክቱ ሂደት እየታየ የሚለቀቅበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- የአገሪቱ መንገዶችን በተመለከተ በቀድሞውና በአሁኑ መካከል ምን ያህል ልዩነት አለ? የጥራት ደረጃስ? አቶ ዛኢድ፡- የጥራት ጉዳይ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል እንጂ እየባሰበት የሄደ አይመስለኝም፡፡ እውቀትና ችሎታው ቀደም ብሎ ከነበረው የተሻለ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምንሠራው መንገዶች ዲዛይን ተሰርቶላቸውና ተጠንተው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ቁጥጥሩም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየጠበቀ ነው የመጣው፡፡ ጥራቱ እየተሻለ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ መንገዶች የጥራት ደረጃ የላቸውም እየተባለ ነው፤ አቶ ዛኢድ፡- የአስተያየት ሰጪው ፍላጎት መታየት አለበት፡፡ የዛሬ አስር እና ሃያ አመት የነበረው የመንገድ ፍላጎትና አስተያየት አሁን ካለው ጋር የተለየ ነው፡፡ አሁን ይበልጥ መንገድ ተጠቃሚዎች መንገዶቻቸው ጥሩ እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የአመለካከት ለውጥ መጥቷል፡፡ ስለዚህ የጊዜ ክፍተት አለ፡፡ የህብረተሰቡ ንቃት እያደገ መጥቷል፡፡ ከፍ ያለ ነገር ይፈለጋል፡፡ ትንሽ ስህተት ካየ ይህ ለምን ሆነ እያለ ነው፡፡ ሌላው ነገር አንድ ሲሰራ ጥሩ ነገር ከማይት ይልቅ ትንሽ የተበላሸች ነገር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ለምሣሌ ከዚህ ድሬዳዋ ከተሠራው መንገድ ውስጥ (የ550 ኪ.ሜ ነው) የተወሰነ ቦታ ላይ መንገዱ ከተበላሸ ህብረተሰቡ የሚያተኩረው ያቺ የተበላሸችበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ማለት ሁሉም የሚያሳይ አይደለም፡፡ ለማንኛውም የመንገዱ ጥራት ተሻሽሏል፡፡ ይህ ማለት ግን ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ችግሮች ምንጫቸው ሁለት ነው፡፡ አንዱ የዲዛይን ችግር ነው፡፡ ዲዛይኑ ትክክለኛውን የአፈር አይነት ባመላከተ መልኩ ተሰርቷል ወይ? የትራፊክ መጠኑ ሊሸከመው በሚችል መልኩ መንገዱ ተሰርቷል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ዲዛይን ካለው የትራፊክ መጠን ጋር ሊመጣጠን በሚችል መልኩ አለመሰራቱ የተወሰነ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ሌላው ችግር አንዳንድ ከኛ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮችም ያጋጥሙናል፡፡ ሪፖርተር፡- እነዚህ ችግሮች ምንድናቸው? አቶ ዛኢድ፡- ለምሳሌ ያህል የመሬት መንሸራተት አንዱ ነው፡፡ አዲስ መንገድ ተሰርቶ ወዲያው በመሬት መንሸራተት ምክንያት ሊበላሽ ይችላል፡፡ ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ነው፡፡ ለምሣሌ ከጣርማ በር ኮምቦልቻ መንገድ ሥራ ላይ የተንሸራተተ መንገድ አለ፡፡ ይሄ የአፈር አይነቱ አስቸጋሪ ነው ማለት ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱን በቀላሉ ዲዛይን አሰርተህ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ ለመቆየት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ ሪፖርተር፡- ታዲያ እንዲህ አይነት ችግሮችን ቀድሞ በማወቅ ዲዛይኑን ማስተካከልና ችግሩ እንዲቀነስ ማድረግ አይቻልም ነበር? አቶ ዛኢድ፡- እኛ አገር ባለው አሰራር የመሬት መንሸራተት የሚያጋጥማቸው ቦታዎች በደንብ አይታወቁም፡፡ የለሙ አገሮች ግን የሳተላይት መረጃ ነው በመጠቀም መገመት ይችላሉ፡፡ በኛ አገር ግን ያስቸግራል፡፡ ብዙ ወጪ ይጠይቀናል፡፡ ያም ሆኖ ግን ችግሩ ሊከሰት ይችላል፡፡ በቅርቡ እንኳን ከውጭ ባለሙያዎች መጥተው እንዲህ አይነቱን ጥናት በአንድ መንገድ ላይ በጣም ውድ በሆነ ዋጋ ሰርተው ነበር፡፡ ነገር ግን አልተቻለም፡፡ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አልተቻለም፡፡ ጎሃጺዎን መንገድም እየገጠመን ያለው ይሄነው፡፡ በጣም ከፍተኛ ወጪ ነው የሚጠይቀው፡፡ እዚያ ያሉ የጃፓናውያን ባለሙያዎችም ሊቋቋሙት አልቻሉም ባይባልም በጣም ውድ ዋጋ እየጠየቀ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ህብረተሰቡ የሚመለከታቸው ሁኔታዎችና ላለፉት ሦስት አራት አመታት መንገዱ ከተሠራ በኋላ እነዚህ የመንገድ መንሸራተት የሚታይበት ቦታዎች ላይ በህብረተሰቡ ጭንቅላት ላይ ትተውት የሚሄደት አሻራ አለ፡፡ ስለዚህ ይሄ መንገድ ጥራቱን ጠብቆ አልተሰራም የሚል አስተያየት እንዲሰነዘር ያደርጋል፡፡ የዲዛይን ችግር ያጋጠመናል፡፡ ለዚህ አቅማችንን መገንባት አለብን፡፡ አሁን ያለን አቅም በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኮንትራክተሩ የራሱ የሆነ ድክመት ይኖረዋል፡፡ ድክመቱን መቆጣጠር ይኖርብናል፡፡ እነዚህም ነገሮች ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ አብዛኛው መንገዶች ግን ጥራታቸውን ጠብቀው እየተሰሩ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- እንደተጠቀሰው የመንገድ ጥራት ችግር የለም ማለት አይቻልም፡፡ በግንባታ ወቅት ከደረጃ በታች የሰሩ ኩባንያዎች ላይ የወሰዳችሁት እርምጃ አለ? በቁጥጥርስ ወቅት የምታገኙትን ስህተት እንዴት ታርማላችሁ? አቶ ዛኢድ፡- ሁልጊዜ እርምጃ እንወስዳለን አንድ የመንገድ ፕሮጄክት በመስፈርቱ መሰረት ተቆጣጣሪ መሃንዲሱ እያንዳንዱን የሥራ እንቅስቃሴ የሚያይና እያንዳንዱን የሥራ እንቅስቃሴ በመከታተል ያፀድቃል፡፡ ስለዚህ በተቀመጠው ስፔስፍኬሽን ካልተሰራ የላብራቶሪ ሙከራ ማለፍ ካልቻለና ማሃንዲሱ አይቶ ካላፀደቀው መንገድ ዝም ብሎ ከተሰራ እንዲፈርስ ነው የሚደርገው፡፡ ይሄ ጥቂት ጊዜ ብቻ የሚያጋጥም ሳይሆን በተደጋጋሚ ያጋጥማል፡፡ በዚህ መልክ ብዙ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተደርገዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ የመንገዶች ስራ ከተያዘባቸው የጊዜ ገደብ በላይ ይወስዳሉ፤ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመጠናቀቃቸው ደግሞ ለተጨማሪ ወጭዎች እየዳረገ ነው፤ ይህ ችግር ለማስተካከል ምን አድርጋችኋል? አቶ ዛኢድ፡- የመንገድ ፕሮጀክቶች ይዘገያሉ ወይም አይዘገዩም የሚለው ነገር ብዙዎቹ እንደምናስበው አይደለም፡፡ ብዙዎቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገድብ የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ግን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ የማይጠናቀቁ መንገዶች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሰላ የናዝሬትን መንገድ ብንወስድ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በፊት የተጠናቀቀ ነው፡፡ ሌሎችም ፕሮጀክቶች እንደዚሁ የተጠናቀቁ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ሰዎች የሚያዩዋቸው መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ጅማ ያለውን መንገድ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ችግር ሁሉም ላይ የሚንፀባረቅ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ጅማ መንገድ መዘግየት እንቀበላለን፡፡ ግን እሱም ከዲዛይን፣ ከአሠራር ችግር፣ ከኮንትራክተሩ ጋር በነበረው ችግርና በመሣሠሉት የመንገዱ ሥራ ከሁለት አመት በላይ የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህ መንገድ ከርዝመቱ አንፃርም በአንድ ፓኬጅ መሰጠት እንዳልነበረበት እናምናለን፡፡ ይህ 340 ኪ.ሜ የሚሸፍን መንገድ በአሁኑ ወቅት ቢሆን ለአንድ ኮንትራክተር በአንዴ አንሰጥም ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ጅማ መንገድ ለሁለት ለሦስት ኮንትራክተር መሰጠት ነበረበት፡፡ ስለዚህ ይህም ችግር መታየት አለበት፡፡ በጥቅሉ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አንድ ፕሮጀክት መቼ ነው የሚያልቀው ሲባል በሦስት አመት እንዲያልቅ ተፈራርሞ ሥራው በሦስት አመት ውስጥ ያልቃል ማለት አይደለም፡፡ በመሃከል ያልጠበቅናቸው ችግሮች ሲፈጠሩ ጊዜውን ሊያራዝመው ይችላል፡፡ ከተተመነው ዋጋ በላይ የሚያስወጡ ስራዎች ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ አዲስ የጊዜ ኮንትራት ማራዘሚያ ለኮንትራተሩ ይሰጣል፡፡ ሪፖርተር፡- ስለዚህ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሥራን አለማጠናቀቅ ተጨማሪ ወጪ ይጠየቃል ማለት ነው? አቶ ዛኢድ፡- ተጨማሪ ወጪ የሚጠየቀው በሁለት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው ምክንያት የሥራ መጠኑ ሲጨምር ተጨማሪ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የጎላ ችግር አልታየም፡፡ ብዙ ጊዜውን የሚራዘመው ከተጨማሪ ሥራ መጠን መስጠት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ባለሥልጣኑ ብዙ የመንገድ ፕሮጄክቶች አሉት፡፡ እነዚህን ሥራዎች እንዲሰሩለት በማድረግ ላይ ያለው በውጭ ኩባንያዎች ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለቻይና ኩባንያዎች እድሉን እንዲያገኙ የሚደረገው ለምንድነው? አቶ ዛኢድ፡- በኔ አመለካከት እኛ አገር ያለው የመንገድ ግንባታ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ በርካታ ኮንትራክተሮች ያስፈልጉናል የሚል አመለካከት ነው ያለን፡፡ እኛ አገር ያሉት ኮንትራክተሮች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ አቅማቸውም ቢሆን በርከት ያለ ፕሮጄክቶች እንዲይዙ የሚያስችላቸው አይደለም፡፡ በርካታ ፕሮጄክቶች ካሉ ሰፊ ስራ አለ ማለት ነው፡፡ ብዙ ተጫራቾችን ሊጋብዝ ይችላል፡፡ ለነገሩ እኛ አገር ያለውን የግንባታ እንቅስቃሴ ካየን ብዙዎቹ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሦስትና አራት ስራዎችን ያልያዙ የሉም፡፡ ይህ ከአቅማቸው በላይ ነው፡፡ የተወሰኑት ናቸው ይህንን ያህል ፕሮጄክቶች የመያዝ አቅም የላቸውም፡፡ ይህም ከአቅማቸው በላይ ሥራ እየሰጠናቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ ሌላ መሰመር ያለበት ጉዳይ ብዙ የመንገድ ፕሮጄክቶች ፋይናንስ የሚደረጉት በውጭ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪዎች ነው፡፡ እነሱ ደግሞ የራሳቸው አካሄድ አላቸው፡፡ ለኮንትራክተሮች የሚያስቀምጡት መስፈርት አለ፡፡ እነዚህ መስፈርቶች መሟላታቸውን ይቆጣጠራሉ፡፡ የኛ አገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እነዚህን መስፈርቶች ማሟላት አይችልም፡፡ መስፈርቶቹ የአውሮፓና የኢዥያ ኮንትራክተሮች አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ይህ ለኛ አገር ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ በውጭ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪዎች የሚሰሩ መንገዶች ለውጭ ኩባንያ መያዛቸው ይህን ያህል የሚያስገርም አይደለም፡፡ በመንግሥት ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጄክቶች ደግሞ እነሱንም ቢሆን የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚፈለጉትን መስፈርቶች ሊያሟሉ አይችሉም፡፡ ከባድ ነው፡፡ አንድ መስፈርት ሲወጣ ለዚያ ፕሮጄክት ዋስትና ነው የምትሰጠው (አንዳንዴ መንገድ ሊበላሽ የሚችለው እኮ ከኮንትራክቶች ልምድ ጋር በተያያዘ ነው) እና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ስራ ስትሰጥ ልምድ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በኛ በኩል ግን ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እነዚህ መስፈርቶች እና ስጋቶችን ወደኛ በማምጣት መስፈርቶችን ዝቅ አድርገናል፡፡ ስለዚህ የአገራችን ኮንትራክተሮች ብዙዎቹ ማለት ይቻላል፡፡ እንኳን በውጭ ፋይናንስ የሚደረጉትን መንገዶች ይቅርና በመንግሥት የሚሰሩትን መንገዶች መስፈርት የአገራችን ኮንትራክተሮች አሟልተው የሚገኙ አይደሉም፡፡ በትክክለኛው መስፈርት እንጓዝ ብንል ኖሮ ብዙዎቹ በመንግሥት ፋይናንስ የሚሠሩ መንገዶች ለውጭ ኮንትራክተሮች ይሰጥ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ኮንትራክተሮች የሚሰጡ መስፈርቶችን ለይተናል፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ግን ብቃት አለን ልንሠራ እንችላለን መስፈርቱንም እናሟላለን ይላሉ፤ አቶ ዛኢድ፡- የመቻልና ያለመቻል ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ነገር እችላለሁ ማለት ሳይሆን በተግባር መታየት አለበት፡፡ 500 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሥራ እችላለሁ ስለተባለ ብቻ አይሰጥም፡፡ እንደ መንግሥት፣ እንደመስሪያ፣ ቤት እንደ ሕዝብ መንገዱ በተባለበት የጊዜ ገደብ ስለመጠናቀቁ ዋስትና ያስፈልጋል፡፡ ጥራቱን ጠብቆ ስለመሠራቱ ዋስትና ያስፈልጋል፡፡ በቂ መሳሪያ እንዳለው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በቂ የሰው ሃይልና የገንዘብ አቅም ሊያሳይ ይገባል፡፡ ተመሣሣይ መንገድ ስለመገንባቱም መረጃ መቅረብ አለበት፡፡ ከፈረሰና ከተበላሸ በኋላ ሃላፊነቱን ማን ይወስዳል? ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መቼ ሥራ አጡ? የሚለው ነገር ላይ ማስመር ያስፈልጋል፡፡ ለእነርሱ የሚሆን ብዙ ሥራ አለ፡፡ ብዙዎቹ የምናወጣቸው ጨረታዎች ላይ ሁለትና ሦስት ተጫራቾች ብቻ የሚወጡበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በእጃቸው ያሉ ፕሮጄክቶችን በአግባቡ መስራት ያልቻሉ ናቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ስራው አለ፡፡ ስራ አላጡም ነው፡፡ እንደውም ለውጭዎቹ 200 እና 300 ሚሊዮን ብር ተርንኦቨር ስንጠይቅ ለኛዎቹ 40 እና 50 ነው፤ የምንጠይቀው፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ ከሰጣቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ምን ያህሉን ለአገር ውስጥ ምን ያህን ለውጭ ኩባንያዎች ሰጥቷል? የገንዘብ መጠኑስ? አቶ ዛኢድ፡- በአጠቃላይ ካሉት ጠቅላላ ሥራዎች ሃምሳ በመቶ በአገር ውስጥ ሃምሳ በመቶ ደግሞ በውጭ ኮንትራክተሮች የተያዘ ነው፡፡ በአጠቃላይ 18 የሚሆኑ ትላልቅ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ከኛ ጋር እየሰሩ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቶቹ በሚፈጁት የገንዘብ መጠን ሲተመን የውጭ ኮንትራክቶች ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛሉ፤ አቶ ዛኢድ፡- ይህንን ያህል ልዩነት የለውም፡፡ የውጭዎቹ ስልሣ የአገር ውስጥ ደግሞ አርባ ከመቶ ድርሻ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በውጭ ገንዘብ ለጋሾች የሚሰሩ ስራዎች ትላልቆች ናቸው፡፡ ዋጋቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ልዩነቱን ሊያመጣ ይችላል ግን ይሄ ችግር ሆኖ አይታየኝም፡፡ እንደውም ብዙዎቹ ፕሮጄክቶቻችን ተጫራች አጥተው እየተቸገርን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ለቻይና ኩባንያዎች ያለ ጨረታ ሥራ ይሰጣል ስለሚባለውስ? አቶ ዛኢድ፡- ምናልባት ይህንን ኢንፎርሜሽን ስሰማ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፡፡ እንደዚህ አይደረግም፡፡ ያለ ጨረታ የተሰጠው የቻይና ኩባንያም ሆነ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር የለም፡፡ የኛ የጨረታ አካሄድ ግልፅና የመንግሥትን መመሪያ ተከትሎ የሚሄድ ነው፡፡ ይልቁንስ የውጭ ኮንትራክተሮች ለአገራችን ኮንትራክተሮች እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን በማመን ልናመሰግን ይገባል፡፡ እነሱ ባይኖሩ ይህንን ሁሉ መንገድ ማን ይገባው ነበር የሚለውን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከአቅሙ በላይ ስራዎች የተደራረበበት ስለሆነ በሦስት ተከፍሎ እንዲሠራ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ ነበር፡፡ ይህ ጥናት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? አቶ ዛኢድ፡- መስሪያ ቤቱ የቁጥር ሥራን ይሰራል፤ የመንገዶች ባለቤትም ነው፡፡ የግንባታ ስራንም ይሰራል፡፡ ይሄ አሰራር ግጭት ያስከትላል፡፡ ተቆጣጣሪም ቁጥጥር የሚደረግበት መስሪያ ቤትም ሆኖ መስራቱ ከባድ ነው፡፡ በሥራ ጥራትም ላይ የተወሰነ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህንን አሰራር መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው መስሪያ ቤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና መምጣቱ ከቁጥር አንፃር እንዲሁም ከኦፕሬሽን ስራ ጋር በተያያዘ መስራቱን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን በሚመለከት አሁን እያካሄድን ያለነው መሠታዊ አሰራር ለውጥ ላይ የሚረግ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ ጥናት መሰረት የሚገኘው ውጤት ለመንግሥት ቀርቦ መወሰድ ያለበት እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ሪፖርተር፡- በየአመቱ ለኮንስትራክሽን ግንባታዎች ግብአት የሚሆኑ እቃዎች ዋጋ መጨመር ያስከተለው ችግር አለ? አቶ ዛኢድ፡- ዋና ዋና የሚባሉ የኮንስትራክሽን ግንባታ ግብዓቶች ውስጥ እንደ ነዳጅ ያሉ ምርቶች ዋጋ ጨምረዋል፣ አስፓልት ጨምሯል፣ የሰራተኛ ደሞዝ ጨምሯል፣ ይህ ግንባታ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የፕሮጄክቶች ቁጥር መብዛትና የኮንትራክተሮች ቁጥር ያለመመጣጠን እና ውድድር አለመኖሩ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ያለው ዋጋ ትክክለኛ የገበያውን ዋጋ ያንፀባረቀ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነገር በደንብ መታየት ይኖርበታል፡፡ በአጠቃላይ ግን የመንገድ ግንባታ ዋጋ ጨምሯል፡፡ ይህ በሁሉም አገር እየተከሰተ ነው፡፡ እኛ ጋር ብቻ ያለ አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- ይህ የዋጋ ውድነት በመገንባት ላይ ያሉ ሥራዎችን አያስተጓጉልም? እቃ ተወደደ ብለው የዋጋ ጭማሪ የጠየቁ ኮንትራክተሮች የሉም? አቶ ዛኢድ፡- ከኮንትራክተሮች ጋር ባለን ውል መሰረት ይህ የዋጋ ጭማሪ ብዙ ችግር አይፈጥርም፡፡ ምክንያቱም የግብዓት እቃዎችን መጨመር በሚመለከት በራሱ በኮንትራት ውሉ ውስጥ በግልፅ የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ ነዳጅ ሲጨምር የአስፓልትና የመሣሠሉት ነገሮች ሲጨምር እንዲስተካከል ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ይህ ጭማሪ የመንግሥትን በጀት ሊጎዳው እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ ምናልባት ቀደም ብሎ ሦስትና አራት መንገድ የሚሰራበትን ገንዘብ አሁን አንድ መንገድ ሊሰራበት ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- መስሪያ ቤቱ ብዙ ሰራተኞች አሉት፡፡ የሰራተኞችን የሥራ ዋስትና በመጠበቅ ረገድ ምን እያደረጋችሁ ነው፡፡ ሠራተኛው ኢንሹራንስ ለምን የለውም? አቶ ዛኢድ፡- በህብረት ስምምነት ነው የምንተዳደረው፡፡ የሰራተኛን መብትና የሰራተኛውን ጥቅማ ጥቅም በሚመለከት በየጊዜው በምናደርጋቸው በማኔጅመንትና በሰራተኛ ማህበሩ በኩል በሚደረግ ድርድር ተደርጎ የሚቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አነሰም በዛ የሰራተኛው መብት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የሄደበት ሁኔታ የለም፡፡ ምናልባት ኢንሹራንስ የተባለው ነገር አስፈላጊው ነገር ታይቶ የሚታይ ይሆናል፡፡ እስካሁን ግን በዚህ ዙሪያ ገፍቶ የመጣ ነገር የለም፡፡ ሪፖርተር፡- የውጭ ኮንትራክተሮች ከሰራተኞች ጋር ብዙ ጊዜ ግጭት ይፈጥራሉ፡፡ ይህም በስራ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ይባላል? በዚህ ጉዳይ የናንተ ሚና ምንድነው? አቶ ዛኢድ፡- ይህ የኮንትራክተሩና የሰራተኛው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ኮንትራት የምንገባው ከኮንትራክተሩ ጋር ነው፡፡ ከሰራተኛው ጋር ስላለው ግንኙነት የሚወሰነው ኮንትራክተሩ ከሰራተኛው ተወካዮች ጋር ወይም ከፕሮጄክቱ የሰራተኛ ማህበር ጋር በሚያደርግ ውል ሊሆን ይችላል፡፡ በኛ በኩል እንደ አንድ አሰሪ እዛ ውስጥ የምንገባበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የኮንትራክተሩና የሰራተኛው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የሚነሳ ግጭት የለም ማለት አይደለም፡፡ ይነሣል፡፡ ግን ይህንን ያህል የጎላ አይደለም፡፡ እነዚህም ግጭቶች የሚነሱትም ብዙውን ጊዜ በጥቅም ግጭት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን አንድ ሥራ እየተጠናቀቀ ሲሄድ ሰራተኞች ሊቀንስ ይችላል... ምናልባት እኛ መግባት ካለብን ለመምከር ያህል ከመግባት ውጭ ኮንትራክተሩን ይህንን አድርግ አታድርግ ማለት አንችልም፡፡ ሰራተኞቹንም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን በሚመለከተው አካል በኩል ሰላማዊ መንገድ እንዲፈጠር ጥረት እናደርጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የመንገድ ግንባታ ደረጃና ስብጥር ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል? አቶ ዚያድ፡- ያለን የመንገድ ስርጭት በተለያየ መንገድ ሊታይ ይችላል፡፡ መለኪያውም ሊለያይ ይችላል፡፡ ለማንኛውም ከአገራችን የቆዳ ስፋትና ካለን የሕዝብ ቁጥር አንጻር አሁን ያለን የመንገድ ስርጭት ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ምን ያህል መንገድ አለን የሚለውም ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ አሁን እኛ ያለን መንገድ 46 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ኬንያ ብትሄድ 60 እና 70ሺህ ኪሎ ሜትር ሊደርስ ይችላል፡፡ የመንገድ ብዛቱን ወይም ስርጭቱን የሚጎዳው ሌላ ምክንያት አለ፡፡ እኛ መንገድ የምንለውና እነርሱ መንገድ የሚሉት ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህ የኛ አሃዝ የከተሞች መንገዶችን አያጠቃልልም፡፡ እነርሱ ግን ይህንን ሁሉ አጠቃለው የሚያዩት ነገር አለ፡፡ ዋናው ነገር ይሄ መንገድ አይቆጠርም፡፡ ይሄ ይቆጠራል ማለት ሳይሆን በአገራችን ያለው የመንገድ አነስተኛ መሆኑን መገምገሙ ነው የሚሻለው፡፡ ስለዚህ ይህንን አነስተኛ መንገድ እንዴት አድርገን ነው የምናሻሽለው የሚለውን ነገር የምንጨነቅበትና የምንሠራበት ነው የሚሆነው፡፡ ያሉት መንገዶች በቂ አይደሉም፡፡ 70 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ ገና በቂ በሆነ ሁኔታ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ያለን የአስፓልት ብዛት ከጠቅላላው መንገድ ጋር ስናነፃፅረው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ይህንን አነስተኛ የመንገድ ሽፋን ለማስፋፋት በመንግሥት የተያዘው እቅድ ምንድነው? አቶ ዛኢድ፡- አሁን እያካሄድን ያለነው የአምስት ዓመት የመንገድ ልማት ፕሮግራም ነው፡፡ በተመሣሣይ የመስሪያ ቤቱም የሦስት ዓመት እቅድ እየተካሄደ ነው፡፡ እስከ 2002 የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ስለዚህ የ3 ዓመቱን እቅድ ካየኸው በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተቻለ መጠን አሁን ያሉትን መንገዶች በተሻለ መጠን ማሻሻል ሥራ ይሰራሉ፡፡ የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያየ መረጃ ያቀርባሉ፡፡ እዚህ አገር 200ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ያስፈልጋል የሚሉ አሉ፡፡ 120 ሺህ ኪሎ ሜትር ያስፈልጋልም የሚሉ አሉ፡፡ ከመንግሥት ፖሊሲ አንፃር ካየነውና በመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች መሰለፍ ካለብን የአገራችን የመንገድ ሽፋን 200 ሺህ ኪሎ ሜትር መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ደረጃ ያሉ አገሮች ከ200 ኪ.ሜ በላይ የሚሆን መንገድ አላቸው፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ ጥረት ይደረጋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |