Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
May 10th
Home arrow Sections arrow በሠራተኛው ሥም የሚፈጸሙ..
በሠራተኛው ሥም የሚፈጸሙ.. Print E-mail
Sunday, 16 March 2008
በሠራተኛው ሥም የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራት

ጥር 28 እና 29 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. 24ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን ለማድረግ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን እንጨት ብረታ ብረት ሲሚንቶና የመሳሰሉት ሠራተኛ ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን አባል የሠራተኛ መሪዎች ከየመሰረታዊ የሰራተኛ ማህበራችን ተገኝተን ነበር፡፡
በዕለቱ ምዕላተ ጉባዔ ተሟልቷል ተብሎ መክፈቻ በኢሠማኮ ምክትል ኘሬዚደንት ስብሰባው ተከፈተ፡፡ በመቀጠልም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ያከናወነውን የሥራ እንቅስቃሴ በንባብ በፌዴሬሽኑ ኘሬዚዳንት ተነቦ ያለወትሮው የኦዲት ኮሚቴ ሪፖርት ሳይቀርብ የሻይ እረፍት እንድንወጣ ተደረገ፡፡ ይህን ጊዜ ነው አንድ ችግር እንዳለ የጠረጠርኩት፡፡ ሌላ ጊዜ የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ከተነበበ በኋላ የሻይ እረፍት ተወጥቶ ከሻይ እረፍት በኋላ በሁለቱም ሪፖርቶች ላይ ውይይት ይደረግ ነበር፡፡

ከሻይ እረፍት በኋላ ተጋባዥ የአቻ ማህበራት (ፌዴሬሽን) የሥራ አስፈፃሚዎች ሪፖርቱን በእጃቸው ይዘው ከእረፍት በኋላ ሳይመለሱ የቀሩ ቢሆንም ሪፖርቱን ተገኝተው እንዳያዳምጡ የተደረገ ሴራ በመሆኑ ሪፖርቱ ለምክር ቤቱ አባላት ቀረበ፡፡

ለምክር ቤቱ አባላት የኦዲት ኮሚቴው ሪፖርት የታደለው በአዳራሹ ውስጥ ገብተው ቦታ ቦታቸውን ለያዙት የምክር ቤት አባላት በእጅ በመስጠት ሲሆን፣ ሪፖርቱ ቀልብን ስቧል፡፡ አብዛኛው የምክር ቤት አባላት የፌዴሬሽኑን ኘሬዚዳንት ሪፖርት በንባብ እየተከታተለ ማዳመጥ ትቶ የኦዲት ሪፖርት ነበር ሲያነብ የቆየው፡፡

የኮንስትራክሽን ፌዴሬሽን የምክር ቤት አባል ከሆንኩ ለሦስት ጊዜ የተሰበሰብኩ ሲሆን የአሁኑ የኦዲት ሪፖርት ግልጽ የሆነና ትንታኔው የሚማርክ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ሪፖርቱ በመጀመሪያ ገፁ ላይ ኦዲት ስህተት ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ስህተት እንዳይፈፀም ማረም፣ ከተፈፀመም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው የሚለውን አባባል በመጥቀስ ነበር ለምክር ቤቱ አባላት ሪፖርቱ የቀረበው፡፡ ሪፖርቱ ብዙ ጭብጦች ያሉት ሲሆን በተለይም ግዥን አስመልክቶ በበቂ ሁኔታ ጥናት ሳይደረግ በጀት ሳይያዝ ከመጠባበቂያ ገንዘብ በመውሰድ ግዥን መፈፀም አግባብ ያለመሆኑን አስረድቶ ፌዴሬሽኑ የሚያከናውነው የአላቂና የአሮጌ ዕቃዎች ሽያጭ በቂ የዋጋ ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የፌዴሬሽኑን የገንዘብ አያያዝ ንብረት ምዝገባና ቁጥጥርን አስመልክቶ በቼክና በጥሬ ገንዘብ የሚወጡ ወጪዎች የሰነዶችን ሕጋዊነት፣ አግባብነት፣ ለውሎ አበል፣ ለትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ ለነዳጅ፣ ለልዩ ልዩ ሥራ ማስኬጃዎች የሚወጡ ወጪዎች ደረሰኝ የሌላቸውና በፌዴሬሽኑ ፎርማት እየተሞሉ የሚወጡ ወጪዎች ትክክል አለመሆናቸውን፤ አጠራጣሪ ሰነዶች እንዳሉ ትንታኔ በመስጠት የቀረበው ሪፖርት ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ባለ መልኩ ግልፅ ሆኖ ቀርቦልናል፡፡

በተለይም በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ግርምትን የፈጠረው ፌዴሬሽኑ አባል የሆነበት ብዩልዲንግ ዎርከር ኢንተርናሽናል ከሚባል ዓለም አቀፍ የሕንፃ የሠራተኛ ማኀበር ለሴት ሠራተኞች ስልጠና እንዲሰጥበት የተላከውን ብር 46..952.99 በሚመለከት የማያስገርም ሪፖርት ቀርቧል፡፡

በሪፖርቱ ለሦስት ስልጠናና ለ5ዐ ሴት ተሳታፊዎች ብር 9..220.00 ለውሎ (ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ብር) አበል ወጪ ሲደረግ ለፌዴሬሽኑ ሦስት ሥራ አስፈፃሚዎችና ለአምስት የፅህፈት ቤት ቅጥር ሠራተኞች ብር 11..715.00 (አሥራ አንድ ሺህ ሰባት መቶ አሥራ አምስት ብር) አስተባባሪ በመባባል ገንዘቡን እንደየሥልጣናቸው ደረጃ የተከፋፈሉት መሆኑን ተገልጿል፡፡ ለነዳጅ ብር 8..098.94 ለሦስት ቀናት ሥልጠና ወጪ መደረጉ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ሲሆን፣ ለጽህፈት መሳሪያም አንድ ስክሪቢቶና ማስታወሻ ወረቀት ለሃምሳ ሰልጣኝ ተሰጥቶ 6632.00 ብር ወጪ ሆኗል፡፡ ለግብዣ 3..676.85 ብር፣ ለፎቶ ግራፍ፣ ለስልክ ብር 1..637.20 ወጪ ሆኖ ሂሳቡ እንዲወራረድ ለለጋሹ ተልኮለታል፡፡

ለመስክ ሥራ ወደ ባህር ዳር የሄደ መኪና አዲስ አበባ ላይ ነው ተብሎ የነዳጅ ደረሰኝ ማቅረብ፣ ፊትና ኋላ የሆነ የቀንና የቁጥር ዝብርቅርቆሽ ያለው ደረሰኝ መቅረቡን ኦዲት ኮሚቴው በሂሳብ ምርመራው አግባብ ያለመሆኑን ተችቷል፡፡ ኦዲት ኮሚቴው በየዕለቱ ወጪዎችን በመቆጣጠር መከላከል ሲገባው ይህ ሁሉ ዝም ማለቱና ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ ሪፖርት ማቅረቡ ቅሬታን አሳድሮብኛል፡፡

በሪፖርቱ የቀረበውና ሌላው አስገራሚው ጉዳይ የፌዴሬሽኑ መኪናዎች የነዳጅ አጠቃቀም ከተከናወነው ሥራ ጋር ያልተጣጣመና በየዕለቱ የሚቀዳላቸው ነዳጅ ከሚሄዱበት ርቀት ጋር ተገናዝቦ የቀረበው ትንታኔ ነው፡፡ ይኸውም ለመኪናዎቹ የተያዘው የነዳጅ ዋጋ በጀትና የተጠቀሙት ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን በሂሣብ ስሌት ተሰርቶ ቀርቦ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ብስጭትን ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ በወጪ ደረጃ የሚፈጥረው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ስለሆነም በአግባቡና ለተገቢው ሥራ ነዳጅ በቁጠባን በመጠቀም የሠራተኛን ጉዳይ ማስፈፀም ሲገባ ለሠራተኛው ጥቅም ላልሆነና ለግል ጥቅም የነዳጅ ደረሰኝ ብቻ በማቅረብ መገልገል ተገቢ አይደለም፡፡ መኪናዎቹ በየቀኑ የተጓዙት ኪሎ ሜትር ተቀዳ ከተባለው ነዳጅ ጋር ሲነፃፀር የማይታመን ነው፡፡ ወሩን ሙሉ ያለእረፍት እየተሽከረከሩ ነበር ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ የትርፍ ሰዓት አጠቃቀም ነው፡፡ ለቅጥር ሠራተኛ ከወር ደመወዙ በላይ መክፈል አግባብ አለመሆኑን በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል፡፡ በመደበኛ የሥራ ሰዓት ሥራዎች ሳይከናወኑ ይቀሩና ጥቂት ሠራተኞችን ለመደጐም ሲባል የትርፍ ሰዓት እየተባለ መክፈል አግባብነት የሌለው መሆኑን በሂሳብ ስሌት ተሰርቶ በሪፖርት መቅረቡ የአሰራር ግድፈት መኖሩን ያስገነዝባል፡፡

የውሎ አበል አከፋፈል ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ሲሆን ዩፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚዎች በመደበኛ የሥራ ቀንና ሰዓት ማኀበራትን ለመጐብኘት ሄደናል፤ ግብዣ ላይ ተገኝተናል..፤ ..መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች ስብሰባ ጠርተውናል..፤ ..የመክፈቻና የመዝጊያ ጥሪ ላይ ተገኝተናል..፤ እንዲሁም ..ቅዳሜና እሑድ ፅህፈት ቤት ተገኝተናል.. ወዘተ. እያሉ ፎርም እየሞሉ በማቅረብ መሠረት የሠሩት ሥራ ምን እንደሆነ በትክክል ሳይታወቅ በወር የሚከፈላቸው ቀላል ያልሆነ ብር ነው፡፡

ሌላው ለፌዴሬሽኑ ግዢ የሚደረጉ ወጪዎች ከበጀት በላይና ዋጋቸውም የተጋነነ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ በአግባቡ የግዢ ደንብና መመሪያ ተከትሎ ግዥ እንዳልተፈፀመና ተገዝተውም በዕቃ ግምጃ ቤት ገቢ ለመደረጋቸው አጠራጣሪ መሆኑን በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የንብረት ቁጥጥር ካርድ ምዝገባ እንዳልተከናወነና መረጃም በአግባቡ እንዳልተያዘ ተጠቅሷል፡፡ የጥገና ወጪን በተመለከተም ከበጀት በላይ እየወጣ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን ወደፊት በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ የፌዴሬሽኑን አቅምም ያሳጣል፡፡

የዓመት እረፍትን በገንዘብ እየቀየሩ መክፈል ለፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ወጪ ከመሆኑም በላይ ሠራተኛው አእምሮውን አዝናንቶ በአዲስ መንፈስ ወደ ሥራው እንዳይመለስ የሚያደርግ አሠራር በመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንፃርም ሕገወጥ መሆኑንና ለአብነት ያህልም ለሦስት ሥራ አስፈፃሚዎች ብር 13..100.66 ብር በዓመት እረፍት ስም ወጪ መደረጉ ተቆጣጣሪና ሃይ ባይ የሌለ መሆኙን አመላክቷል፡፡

ለምክር ቤቱ የቀረበው የኦዲት ኮሚቴ ሪፖርት የፌዴሬሽኑ አመራሮች በተመረጡበት በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ላይ ከተከናወነው የሥራ ሪፖርት የተገኘ የአሠራር ግድፈት መነሻ ነው፡፡ ለሚቀጥለው ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በዚህ ሁኔታ ከተቀጠለ ይህ ፌዴሬሽን አለ ለማለት አያስችልም፡፡

በአጭር ጊዜ (በስድስት ወራት) የዚህ ዓይነት የሥነ ምግባር ጉድለት መታየቱ ለሠራተኛው ጥቅም ያልቆሙ የማኀበር መሪዎች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

ሠራተኛው ከቤተሰቡና ከኑሮው ላይ ቀንሶ መብቱ እንዲከበርለት ያዋጣውን 40 በመቶ መዋጮ ለዚህ ተግባር ማዋሉ ወደፊት ተጠናክሮ ለመታገል እንዳይችል የሚያደርግ፣ ሞራሉን የሚነካ በመሆኑ ምግባረ ብልሹ የማኀበር መሪዎች እንዲታረሙ ማድረግ ተገቢ ሲሆን ሠራተኛውም ለሌላው አርአያ እንዲሆኑ ተገቢው የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡

በዕለቱ የኦዲት ሰብሳቢው ብቻቸውን መድረክ ላይ ሲጮሁ የዋሉ ሲሆን የመናገር እድልም ተነፍጓቸዋል፡፡ ሌሎች የሥራ አጋሮቻቸው ሲያግዟቸውም አልታየም፡፡ ለምን ዝምታን እንደመረጡ አልገባኝም፡፡

ምክር ቤቱ በአንድ ቀን የውይይት ውሎው የሥራ አስፈፃሚው ሪፖርት ላይ ብቻ በማይጠቅም መልኩ ጊዜ እንዲወስድ ተደርጐ የተወያየ ሲሆን የኦዲት ሪፖርቱን ግን የምክር ቤት አባላት እንዳይወያዩበትና ጊዜ እንዲባክን ተደርጐ የደረሰው ጥፋት ወደፊት በውጭ ኦዲተር ጉዳዩ ተጣርቶ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብለት ውሳኔ በማሳለፍ ሁሉም በተጣደፈበት ስብሰባው እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡

የኮንስትራክሽን ፌዴሬሽን የምክር ቤት አባል
 
< Prev   Next >