Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow የቴሌቪዥን ቦርድና ሠራተኛው ይተዋወቃሉ?
የቴሌቪዥን ቦርድና ሠራተኛው ይተዋወቃሉ? Print E-mail
Sunday, 16 March 2008
(ከኢቲቪ ሠራተኞች አንዱ)

“አቤቱ ቦርዳችን ሆይ በቴሌቪዥን ሕንፃ ላይ የምትኖር ስምህ ይታደስ ግልፅነትና ተጠያቂነትህ ትምጣ ፈቃድህ ደመወዝ መቀበል ብቻ እንደሆነች ሁሉ የተገፋነውንም በግንባር እየን፡፡ መልካም አስተዳደርን አስፍንልን፡፡ ዛሬ በመዋቅር ሽፋን የሚያፈናቅሉንን ሃይ በልልን፡፡ እኛም ሰርቶ የመኖር ዋስትና አለን እንደምንል ሁሉ ቤተሰባዊና ቡድናዊ ከሆነ ፈተና አታግባን፡፡ ዴሞክራሲያዊ አሰራርን አስፍንልን እንጂ ኃላፈነት ያንተ ናትና ፍትሃዊ አመራር ውሳኔ በስልጣን ዘመንህ አሜን!”

ቋንቋቸውና የአለማመን ዘዬአቸው የተለያየ ይሁን እንጂ ግልፅነትና ተጠያቂነት በሌለበት አሠራር እየታሹ ያሉት አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሠራተኞች ለመግቢያ የተጠቀምኩበትን ማለት ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡

ጥቂት ከእኛ ወዲያ ፖለቲከኛና ለኢሕአዴግ ታማኝ ለአሳር የሚሉ ስብስቦች በሚያቀርቡት ተራ ወሬ ያልተነካና ያልተጠለፈ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሠራተኛ ቢኖር ህልናውን ለእነዚህ ኃይላት ሸጦ ወሬ ያቀበለ፣ ጫማቸው ሥር የወደቀ፣ እነሱን ሲያስነጥሳቸው መሃረብ ያቀበለ፣ በራሱ የማይተማመን ብቻ ለመሆኑ እኔም ሆንኩ በውስጡ ያለፉ ያውቁታል፡፡

ባለፉት ዓመታት የነበረው ቦርድ ያጋባበት በሽታ ነው መሰል ሥራ ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር በወራት የሚቀር ጊዜ የቀረው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ቦርድ በበርካታ የመገናኛ ብዙኃን የሠራተኛው መገፋት፣ የአስተዳደር በደል፣ በተለይም በአዲሱ የሠራተኛ አደረጃጀት መዋቅር ሽፋን የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት በሚነገርበት በዚህ ፈታኝ ወቅት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሏል፡፡

አንድም ቀን ሠራተኛው ጋ ድርሽ ብሎ አያውቅም፡፡ ተፈጥሯል በተባለው በሠራተኛው ችግር ዙሪያም አላወያየም፡፡

ሚዲያውን ተቆጣጥሬዋለሁ ማን የደፈረ ነው የሚናገረኝ በማለት አብጠው ሪፖርተር ጋዜጣ ለምን ህገወጥ ድርጊቴን አጋለጠ በሚል በሚመሩት ቴሌቪዥን ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ የተደመጡት የቴሌቪዥን ምክትል ሥራ አስኪያጅ በነጋታው ከኃላፊነት ተነሱ ተባለ፡፡ ጥቅምት 10 ቀን 1999 ዓ.ም ውሳኔው ፀንቶ ደብዳቤ ደረሳቸው፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል የተነሱበት ምክንያት እንኳ ግልፅነትን በተከተለ ሁኔታ ለሌላው አስተምህሮ እንዲሆን ለሠራተኛው አልተገለፀለትም፡፡

ያም በመሆኑ “እርሳቸው የከለከሉአቸው ወደ ቦታቸው ሊመለሱ ነው፡፡ እንዲያውም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሊመደቡ ነው…” በማለት በሠራተኛው መሃል ውዥንብር ሲፈጥሩ ቤቱ የእከክልኝ ልከክልህ ነውና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት መኪና ይዘው ነዳጅ እየተሞላላቸው፣ የሞባይል ካርድ እየተከፈለላቸውና ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አድርሶ የሚመልስ መኪና ይመደብላቸው እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ዛዲያ እርሳቸው ተነሱ እንጂ እርሳቸው የፈፀሙትን ስህተት የሚያራምዱ ሹመኞችና ተከታዮች ለመኖራቸው ምን መጠራጠር ያስፈልጋል?

ሕዳር 1 ቀን 2000 ዓ.ም ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ እንደተገለፀው በብዙ መስሪያ ቤቶች አቅም እንገነባለን እያልን በተቃራኒው ግን አቅም እያጣን ለመሆኑ የኢትየጵያ ቴሌቪዥን ጥሩ መገለጫ ነው፡፡

በአዲሱ የሠራተኞች መዋቅር ሽፋን በቂ ትምህርት ያካበተ የሥራ ልምድ ያላቸውን ካሜራ ማኖች፣ ቴክኒሽያኖችና የስቱዲዮ ሠራተኞች “ውሳኔ እስኪሰጣችሁ ዘወር በሉ” ማለቱ በራሱ አንዱ መረጃ ነው፡፡

ይህ ደብዳቤ ከደረሳቸው 25 ባለሙያዎች ውስጥ  ደግሞ ሁለቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጃ ምሩቃን ናቸው፡፡ አንዱን ድርጅቱ ራሱ ከአገር ውጭ ልኮ አስተምሮታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ባለሙያ ከገፉ ወዲህ ሰሞኑን ደግሞ ደብዳቤ ፅፈው ጠሯቸው፡፡ የእነሱ ምላሽ አንመጣም ሆነ፡፡  ኮምፒውተሮችን ማን ያንቀሳቅስ? ሰዶ ማሳደድ ይሏል ይህ ነው፡፡

ይኸው ቤተሰባዊ፣ ቡድናዊና ፖለቲካዊ ይዘት የተላበሰው የኢቴቪ መዋቅር ከተገለፀ ወዲህ ባለፈው ዓመት የረዥም ጊዜ የካበተ የሥራ ልምድ ያላቸው የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቃን ጥለው ሄደዋል፡፡ ከአራቱ ሁለቱን ድርጅቱ ራሱ ነው ለማስትሬት ዲግሪ ያስተማራቸው፡፡ አንዱን በአገር ውስጥ አንዱን በውጭ አገር፡፡

በቀንም ይሁን በምሽት እየሰራን እንማር በማለታቸው ከተማራችሁ መሥሪያ ቤቱን ልቀቁ የተባሉ ሰባት ጋዜጠኞች ዛሬ ከሰባቱ አምስቱ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው ሌላ ጋ እየሰሩ ነው፡፡ እድልዎ በተሞላውና ግልፅነት በጎደለው መዋቅር ተማርረውም 6 የመጀመሪያ ዲግሪና የካበተ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች 2 ፊልም አንሺዎች ኤዲተሮች ቴክኒሽያኖች ለቀዋል፡፡

የካበተ የሥራ ልምድ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋጋ ካጣ ከራርሟል፡፡ ለምን ቢሉ የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞችን አዋጅና ደንብ በሚጥስ መልኩ ለቦታው የሚመጥን ሠራተኛ ከውስጥ ሞልቶ እያለ “ዝውውር” በሚል ማሳበቢያ ከአማራና ከደቡብ ክልል እንዲሁም ከሬዲዮ ፋና፣ ከዋልታና ከሜጋ ለመሰግሰጋቸው እነርሱም ዐይናችንን ግምባር ያድርገው ብለው የሚክዱት አይደለምና!

ለማንኛውም ዛሬ ማንም ወጣ ማንም ወረደ የሠራተኛው ኪስ ጠብ የሚል ቅንጣት ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሰለጠነ በተማረና የካበተ ልምድ ባለው አዲስ የሠራተኛ አደረጃጀት እንዲዋቀር ፍላጎቱና ምኞቱ ነበረን፡፡ ይህንን ምኞታችንንና ህልማችንን ግን በቤተሰብ፣ በቡድን፣ በፖለቲካ የተሳሰሩ እያደናቀፉት ነው፡፡

ለሥራ የቆመውን ለማበረታታት፣ በእውነትም ቴሌቪዥን በብቁ አሠራር ጥሩ የሕዝብና የመንግሥት አገልጋይ ሆኖ በገበያ ላይም ጥሩ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሙያዊ አመራር ለባለሙያዎች ይለቀቅ፡፡ ሁሉም ሠራተኞች እኩል ይታዩ፡፡ ሕግና ፍትህ በወሬና በፖለቲካ ሽፋን እየተጣሰ ነውና ቦርዱም ሆነ መንግሥት ትኩረት ይስጡ፡፡

ሕገ መንግሥታዊውን ስርዓት ተቀብሎ የመንግሥት ፖሊሲ የሚያስፈፅመው ሠራተኛ በሥራው ታታሪነቱን ተነሳሽነቱን ከማስመስከር በላይ ምን እንዲሆን ይፈለጋል?!

ከሕግ ውጪና ከኤዲቶሪያል ቦርዱ መመሪያ ውጭ አይሆኑትን ሁን ለሚሉት ትናንሽ የቴሌቪዥን ንጉሦች መፍትሄውን በማህበር መደራጀት መሆኑን ጋዜጠኛው ቢያምንም ጋዜጠኛውን መጠቀሚያ የሚያደርጉት እንጂ የሚጠቅሙት ከቶም አልተፈጠሩለትም፡፡

መብትና ጥቅሙን የሚያስከብርለት ማህበር እንዳይፈጥር ደግሞ ከራሱ ውስጥ የሚወጡ ልወደድ ባዮች ጋሬጣ እየሆኑበት በሙያቸው ሳይሆን በወሬ፣ በችሎታቸው ሳይሆን በማደግደጋቸው ለቴሌቪዥን ስክሪን ይበቃሉ፡፡ እነዚህን መታገል ለጋዜጠኛው የሚተው ሆኖ ግን የመኖሪያ ቤት ቦታ የወሰዱና የቸበቸቡ እንደገናም ኮንዶሚኒየም ቤት የወሰዱ ዕውን በቦርዱና በመንግሥት ይታወቃሉ?!
 
< Prev   Next >