| በእሳት ያልተፈተነ ወርቅ ዓለም አቀፍ.. |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
በእሳት ያልተፈተነ ወርቅ ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ አይሆንም
በባስሊ የወርቅ ነገር ቆሽታችንን ማሳረር ከጀመረ ከሁለት ወር በላይ ሆኖናል፡፡ በሕሊና ቢሶች የተዘረፈው የገንዘብ መጠን ድሃው ወገናችን የሚታከምበት ስንት ጤና ጣቢያ ወይም የሚማርበት ስንት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ስንት ድልድይ፣ ስንት መንገድ፣ ግድብ፣ ኮንዶሚኒየም ወዘተ. ሊገነባ ይችል እንደነበረ ሲታወስ ያምማል፡፡ ሪፖርተርና ሌሎች ጋዜጦች በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሰፊ ሽፋን በመስጠት ለሕዝብ ዓይንና ጆሮ እንዲደርስ ማድረጋቸው ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሕዝብ የሚደርሰው መረጃ ትክክለኛና ያልተዛባ መሆን አለበት፡፡ ይህችን አጭር ጽሑፍ እንድፅፍ ያነሳሳኝ በሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 13 ቁጥር 25/816 በወጣው ርዕስ አንቀጽ ላይ በብሔራዊ ባንክ ያለ ወርቅ ሁሉ የውጭ “ሪዘርቭ” ወይም ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ እንደሆነ ተደርጎ የተፃፈው ስህተት በመሆኑ እንዲታረምና ከፋይናንስና ኢኮኖሚክስ ሙያ ውጭ የሆኑ አንባቢዎችም ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲይዙ ለማገዝ ነው፡፡ ሪፖርተር በርዕሰ አንቀፁ ላይ “በብሔራዊ ባንክ የሚገኘው ወርቅ ግን የወርቆች ሁሉ የበላይና ልዩ ወርቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የፒያሳው ዓይነት ለጌጣ ጌጥ ተብሎ የሚሸጥ ወርቅ ሳይሆን የሀገር ሀብትን ወክሎ የሚቀመጥ ፣ሪዘርቭ፣ ማለትም መጠባበቂያ ወይም የዋስትና መያዣ ሀብት ነው፡፡ አንድ አገር ምን ያህል ፣ሪዘርቭ፣ አላት ሲባል የመጠባበቂያው መለኪያ ወርቅ ነው፡፡ ስለሆነም የብሔራዊ ባንክ ወርቅ ተጭበረበረ፣ ባሌስትራ ሆኖ ተገኝ ሲባል ለጉትቻ የሚሆን ወርቅ ጠፋ ማለት ሳይሆን የሀገር የመጠባበቂያ ዋስትናና የመያዣ ሀብት ጎደለ ጠፋ ማለት ነው . . . በሀገራችን ጠላት ቢነሳ ጦርነት ቢቀሰቀስ ለሚያስፈልጉን ሁሉ የምንገለገልበት ሀብት ይህ መጠባበቂያ ነው” በማለት አስፍሯል፡፡ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠ ወርቅ ወይም ወርቅ መሰል ነገር የዓለም አቀፍ መጠባበቂያ አካል ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በአጭሩ አይደለም ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ያለ ወርቅ ወይም “ወርቅ መሰል ነገር” የሀገር ሀብትን ወክሎ ..ሪዘርቭም..፣ መጠባበቂያም፣ የዋስትና መያዣ ሀብትም አይደለም፡፡ አንድ ሀገር ምን ያህል መጠባበቂያ አላት ሲባል መለኪያ ሆኖም አያገለግልም፡፡ በብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ነጋዴዎች ተገዝቶ የተቀመጠ ወርቅ ወርቅ ከሆነ ፒያሳ ለጉትቻ እንደሚውለው ዓይነቱ ተራ ወርቅ ነው፡፡ ወርቅ መሰል ብረት ከሆነም ለቢላዎ ወይም ለቆንጨራ መሥሪያ እንደሚውለው ተራ ብረት ነው፡፡ ከመርካቶ ቅቤ ገዝተው ወደ ቤታቸው የገቡ አንዲት ወይዘሮ የገዙትን ቅቤ ለወጥ ማጣፈጫነት ከመጠቀማቸው በፊት በእሳት ይፈትኑታል፡፡ ቅቤ ከሆነ ፈተናውን አልፎ ተነጥሮ ለታሰበለት የወጥ ማጣፈጫነት ዓላማ ይውላል፡፡ የእሳት ፈተናውን ሳያልፍ ቀርቶ የተገዛው ቅቤ ሳይሆን ሌላ መሆኑ ከታወቀ ለታሰበለት ዓላማ ሳይውል በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ይጣላል፡፡ እርግጥ ነው ወይዘሮዋ ገንዘባቸውን ይከስራሉ፡፡ ነገር ግን ያልሆነ ነገር በግድ ይሆናል ብለው ወጥ ውስጥ አይጨምሩም፡፡ በተመሳሳይ ከነጋዴው የተገዛው ወርቅም ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ከመሆኑ በፊት በእሳት መፈተን መነጠር አለበት፡፡ ማንኛውም የባንክ ባለሙያ እንደሚያውቀው የዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ወርቅ ብቻ አይደለም፡፡ የመጠባበቂያው ዋና ዋና ዓላማዎች አንደኛ በሪፖርተር ጋዜጣ እንደተጠቀሰው በክፉ ቀን (ጦርነት ቢነሳ፣ ድርቅ ቢመታን፣ ረሃብ ቸነፈር ቢገባ ወይም ሕዝብ የሚጨርስ ወረርሽኝ ቢከሰት) እንዲህ ዓይነቱን ቀን ለመውጣት የሚረዱ ከውጭ ሀገር ሸቀጦችን፣ መድኃኒቶችን፣ የጦር መሳሪያዎችን ወዘተ. ገዝቶ ማስመጣት መቻል ነው፡፡ ሁለተኛ የሀገሪቱ ገንዘብ ማለትም የብር ዋጋ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አባባል የብር የመግዛት አቅም ከሌሎች ሀገሮች ገንዘቦች ጋር ሲወዳደር ከመጠን በታች እንዳያሽቆለቁል ወይም ከመጠን በላይ ጠንካራ እንዳይሆንና ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የብር የመግዛት አቅም ከሌሎች ሀገሮች ገንዘቦች ጋር ሲወዳደር ከመጠን በታች እንዳያሽቆለቁል ወይም ከመጠን በላይ ጠንካራ እንዳይሆንና ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው የብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆልም ሆነ መጠንከር ከመጠን ካለፈ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት ስላለው ነው፡፡ ሦስተኛ ሀገሪቱ (ኢትዮጵያ) በሌሎች የዓለም ሀገሮች እይታ በውጭ ሀገር ያደረገቻቸውን ማናቸውንም የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የብድር ወይም በአጠቃላይ የክፍያ ስምምነቶችን ልትወጣ እንደምትችል እምነት የሚጣልባት እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡ ለእነዚህ ዓላማዎች ማስፈፀሚያ የሚውል መጠባበቂያ ደግሞ የግድ ወርቅ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እንዲያውም ወርቅ በዓለም ደረጃ ለዓለም አቀፍ መጠባበቂያነት ወይም ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ለመወጣት የሚጫወተው ሚና እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ከውጭ ሀገር ሸቀጥ ወይም መድኃኒት ወይም የጦር መሳሪያ ለመግዛት ወይም ማናቸውንም ክፍያ ለመፈፀም የሚያስፈልገን የውጭ ምንዛሪ እንጂ ወርቅ አይደለም፡፡ ወርቅ ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ከሆነ ለዚህ ዓላማ ከመዋሉ በፊት ተሸጦ ወደ ውጭ ምንዛሪ መቀየር አለበት፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት መሥፈርት መሠረት ማናቸውም ለሌሎች ሀገሮች ክፍያ ለመፈፀም የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ (convertible currency) የዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ሊሆን ይችላል፡፡ ወርቅ የዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ለመሆን ወደ ገንዘብ ወርቅነት (monetary gold) መቀየር አለበት፡፡ ወደ ገንዘብ ወርቅነት ለመቀየር ደግሞ (ከላይ የጠቀስናቸው ወይዘሮ ከመርካቶ የገዙትን ቅቤ ለወጥ ማጣፈጫነት ከመጠቀማቸው በፊት እንዳደረጉት) ወርቁ ተነጥሮ፣ የጥራት ደረጃው ታውቆ፣ የወርቁ ባለቤት በሆነ ባንክ ውስጥ ሳይሆን በሌላ የውጭ ሀገር ባንክ ውስጥ መቀመጥ አለበት፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ ወደ ገንዘብ ወርቅነት አይቀየርም፡፡ በመሆኑም ከወርቅ ነጋዴዎች ተገዝቶ ብሔራዊ ባንክ የተቀመጠ ወርቅ ወይም ወርቅ መሰል ነገር ውጭ ሀገር ተልኮ ተነጥሮ ደረጃው ታውቆ በሌላ የውጭ ሀገር ባንክ እስካልተቀመጠ ድረስ ፒያሳ ለጉትቻ መሥሪያ ከሚውለው አይለይም፡፡ በነገራችን ላይ ፒያሳ ያለው ወርቅ መሰል ነገርም ቢሆን ጉትቻ የሚሆነው ተነጥሮ ወርቅ ሆኖ ከተገኘ ነው፡፡ ባሌስትራማ ከሆነ ጉትቻ አይሆንም፡፡ በብሔራዊ ባንክ ያለው ወርቅ ወይም ወርቅ መሰል ነገርም ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ የሚሆነው መነጠር ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በተሳሳተ አኳኋን ተወስዶ ሁሉም ብሔራዊ ባንክ የገዛው ወርቅ ወይም “ወርቅ መሰል ነገር” እንደ ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ተደርጎ በሪፖርተር ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ሰፍሯል፡፡ ዓለም አቀፍ መጠባባቂያ በባህሪው መጠባበቂያውን የያዘው ሀገር ሳይሆን ሌሎች ሀገሮች ለክፍያ የሚቀበሉት ነው ካልን እንዴት ብሔራዊ ባንክ ራሱ ወርቅ መሆኑን ያላመነበት በመሆኑ “ወርቅ መሰል ነገር” እያለ ከነጋዴው ገዝቶ ያስቀመጠው ንብረት በሌሎች ሀገሮች ተቀባይነት አግኝቶ ለክፍያ የሚውል መጠባበቂያ ሊሆን ይችላል ብሎ ሪፖርተር ገመተ የሚል ጥያቄ ጋዜጣውን ሳነብ አቃጭሎብኛል፡፡ ምንም እንኳ ብሔራዊ ባንክ በሰሞኑ የወርቅ ቅሌት ከፍተኛ ገንዘብ የከሰረ ቢሆንም የሀገር መጠባበቂያ ተዘርፏል የሚለው አባባል ትክክል ባለመሆኑ መታረም አለበት፡፡ በተሳሳተ መነሻ ወይም አረዳድ አንባቢን ሥጋት ውስጥ መጣልም ተገቢ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ባሉ አገሮች ወርቅ በዓለም አቀፍ መጠባበቂያነት የሚጫወተው ሚና እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ አሳትሞ ባወጣው ቅጽ 22 ቁጥር 3 2006/07 አራተኛ ሩብ ዓመት ቡለቲን መሠረት እ.ኤ.አ በሰኔ 2ዐዐ7 መጨረሻ ላይ ብሔራዊ ባንክ ብር 12 ቢሊዮን በውጭ ሀገር የተያዘ ንብረት ነበረው፡፡ ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ የሚባለውም ይሄው ንብረት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ብር 11 ቢሊዮኑ (ወይም 92 በመቶ) በውጭ ምንዛሪ፣ ብር 0.4 ቢሊዮን (ወይም 3 በመቶ) በወርቅ፣ ቀሪው ብር 0.6 ቢሊዮን (ወይም 5 በመቶ) ደግሞ በተለያዩ የውጭ ሀብቶች የተያዘ ነበር፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |