Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Monday
Oct 13th
Home arrow Sections arrow የስድብ ፖለቲካን ቅበሩት
የስድብ ፖለቲካን ቅበሩት E-mail
Wednesday, 09 January 2008
ዝማም ማርዬ
 
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በኢንተርኔት ካስተላለፉት ንግግራቸው፣ ምን ጊዜም የምስማማበት፣ ከቶውንም ለሌላውም ትምህርት ሊሆን ይገባዋል፤ ብዬ የማምንበት መልዕክት አዳምጪያለሁ፡፡ ማንም የፈለገውን መስመር ይከተል፣ ቢያንስ ስድቡን ይተወው፤ የብልግና ፖለቲካ አናካሂድ፤ ነውረኛ አነጋገሮችን ትተን በየፊናችን እንሂድ ነበር ያሉት፡፡

በየፊናችን እንሂድ ማለታቸው ከተለያዩ ቡድኖች፣ ከራሳቸው ..ሰዎች.. ጭምር ነቀፋ እንዳስከተለባቸው አስታውሳለሁ፡፡ ነገር ግን ማንኞቹም ቢሆን በስድብና በብልግና ፖለቲካ መከተል እንደማይገባ በተናገሩት ላይ ሲነቅፏቸው አልሰማሁም፡፡ ሊነቅፏቸውም አይችሉም፡፡ ይኸ አስተያየታቸው እንደ አጠቃላይ እውነት የሚታይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ተቃዋሚን በተራ ቃሎች መሳደብ፣ ግለሰቦችን የወረደና የዘቀጠ ቃል እየተጠቀሙ መዝለፍ፣ አሳፋሪና የሚያስገምት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በሃሳብ ላይ ከመከራከር ይልቅ የሰዳቢውን ዳራ የሚያጠያይቁ ዘለፋዎችን መጠቀም፣ የፖለቲካ አንዱ መገለጫ ነው፤ የሚል ደፋር ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ በተመረጡ ..የባለጉ.. ቃላት ድርጅትን ወይም ግለሰቡን ማጣጣል የጨዋነት ምልክት አድርጐ የሚወስድ ግድየለሽ አለ ብዬ ማመን ይቸግረኛል፡፡

ይልቁንም እድሜያቸው ገፍቶ ለተከታዮቻቸው የመልካም ሞራል አስተማሪ ሊሆኑ ይችላሉ፤ የሚባሉ አዛውንቶች፣ በዚህ የወረደና የላሸቀ የዘለፋ ምልልስ ለመቦጫጨር ጥፍራቸውን ሊመዙ ያስደነግጣል፡፡ ይልቁንም ትላንት ለአንድ ዓላማ ቆመው ድሉንም ሽንፈቱንም አብረን እንካፈላለን፤ ያሉ ሰዎች፤  ልዩነት ሲጣሉ ..አንድ ነን.. እያሉ በሚያታልሉት ሕዝብ ፊት ለመራገጥ እግራቸውን ሲያነሱ፣ ምን ያህል እንደሚያሳፍሩ ከማንም የተሰወረ አይሆንም፡፡ በስድብ ናዳ፣ በነውረኛ የአገላለፅ ወርጅብኝ አንጀቴን አረስሁት የሚል ሰው ግቡን የሚያውቅ አይደለም፡፡

በተለይም ፖለቲካውን አንጠርጥረን እናውቃለን፤ ሕዝቡ የምንለውን ይሰማናል የሚሉ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና አቶ አባይነህ ብርሃኑ ያሉ ሰዎች በዚህ አረንቋ ሲላቁጡ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ዕድሜ ትምህርትና ልምድ ብዙ አሳውቆናል፤ እያሉ የሚገደሩ ሰዎች፤ ትላንት እኛን በሚያታልሉበት ወቅት አንድ አካል አንድ አምሳል ነን፤ ሲሉ የነበሩ የፖለቲካ አመራሮቻችን፣ በተራ ስድብ ሲወራረፉ ማየት ያሳፍራል፡፡ ያስደነግጣል፤ ያስፈራል፤ ያስገምታል፤ ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ለመስዋዕትነት መዘጋጀታችንም ሊያስቆጨን ይችላል፡፡

ከአለፈው አንድ ወር ወዲህ በሚታተሙ ጋዜጦች እንደአውሬ ድመት ለመዳመት የሚፎክሩባቸውን ነውረኛ ቃላት አንብባችኋል፡፡ ከፍ ብዬ የገለፅሁዋቸው ሁለት ሰዎች አንዱ በሌላው ላይ በሚሰጡት አስተያየት፣ የታጀቡባቸውን ቃላት፣ ልብ ሳትሉ አትቀሩም፡፡ እነዚህ ሰዎች ባለፈው ዘመናቸው እንዲህ ዓይነት ቃላት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ሳስብ አንገቴን አቀረቅራለሁ፡፡ ይበልጥ የሚያስቀረቅረኝም አንደኛው ለሌላው የሰጠውን የስድብ ናዳ ሃስትነት የኛን ያህል እንኳ የሚያውቁ አለመሆናቸውን ስላሳየኝ ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ስለመኢአድና ስለሌሎቹ የሚያውቁትና ያልገባቸው ነገር መኖሩን የተረዳሁት ..ስድባቸው.. ፍሬ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ስረዳ ነው፣ አቶ አባይነህ የተናገሩት፣ ፕሮፌሰር መስፍንን የኛን ያህል እንኳ የማያውቋቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ናቸው፤ አንዱ ሌላውን የሚያውቅ መሰለው፣ አንዱ ሌላውን የሚያከብር መሰለው፣ ቅንጅትን ያህል ታላቅ የሕዝብ ድጋፍ የጎረፈለትን ድርጅት፣ በጋራ ይመሩና ያስተባበሩ የነበሩት? አለማወቃችን እንዴት አሳስቶን ኖሯዋል?

አስተያየቴን ለማብራራት ሁለቱ አዛውንቶች /ይኸን ቃል የምጠቀመው ቢያንስ በዕድሜያቸው ሊናገሩት የማይገባ ነው ብዬ ስለማምን ነው/ የተጠቀሙበት አገላለፅ ምን ያህል ገደቡንና ልኩን የሳተ መሆኑን ለማሳየት ልሞክር፡፡

አቶ አባይነህ ብርሃኑ፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለምልልስ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ከወሬ በስተቀር ውጤት አምጥተው የማያውቁ፣ እድሜያቸውን ሙሉ ወሬ እንጂ ቁም ነገር ሰርተው የማያውቁ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የሚያወሩትን ያህል የማይሰሩ፣ የሆነ ያልሆነውን ማውራት የሚያስደስታቸው፣ ስልጣን ፈላጊ... እያሉ ይወርፏቸዋል፡፡ ይኸ ሁሉ ኃይለ ቃል የመጣው፣ ፕሮፌሰሩ በጋዜጣ ላይ ስለመኢአድና ስለአባሎቹ ለተናገሩት አፀፋ ለመመለስ ነው፡፡

ፕሮፌሰር የተናገሩት የቱንም ያህል ..የወረደ.. ነው ብለው አቶ አባይነህ ቢያምኑ እሳቸውና ድርጅታቸውን አስመልክቶ ጨዋ በሆኑ ማስተካከያ ሊሰጡበት የሚያዳግታቸው አልነበረም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እልህ የሚፈጥረውን ..ስሜት.. ተከትሎ የሚመጣ ንግግር ዋናው ሃሳቡን ትቶ ሌላ ጭራ ያወጣል፡፡ አቶ አባይነህ የተባለባቸውን ማስተባበል ትተው ፕሮፌሰር መስፍንን ቢዘልፉ አንዳች ነገር አያተርፉም፡፡ ድርጅታቸውን ይጎዳሉ፤ ራሳቸውንም ያስገምታሉ እንጂ፣ በሳቸው ንግግር ተመርቶ ፕሮፌሰር የነበራቸውን ክብር ይቀነሳል ብዬ አልገምትም፡፡

ለመሆኑ ፕሮፌሰርን ከወሬ በቀር የማይሰሩ ብሎ ለመዝለፍ አቶ አባይነህ ብርሃኑ ማን ናቸው? የሚል ጥያቄንም እንደሚያስከትል መረዳት ብልህነት ነው፡፡ የኋላ ጀርባቸ ሲገላበጥ ባለፉት መንግሥታት ማ ምን እንደሰራ አይታወቅብኝም እያልን የምንናገር ከሆነ ስህተት ይሆናል፡፡ ንስሐ ገብተን ተለውጠናል፤ የሚሉ ሰዎች ደግሞ አፋቸው እንዳመጣ ከመናገር መቆጠብ አለባቸው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፣ አቶ አባይነህ እንደሚሏቸው ዓይነት ሰው አለመሆናቸውን አብዛኛው ሰው ያውቅላቸው ይመስለኛል፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምረው ባሉ መንግሥታት አግባብ ያለው ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ ናቸው፡፡ ስለዴሞክራሲ፣ ሰለሕዝብ መብት በራሳቸው መንገድና አተያይ በአደባባይ ሲናገሩ የቆዩ ናቸው፡፡ በደርግ ጊዜ አሁን በቅንጅት ውስጥ ስለታቀፉ ታጋይ መስለው እንደሚታዩት የንግድና የካድሬዎች ዕቃ አቀባባይ ሆነው በመቆየት አይታወቁም፡፡ ለመሾም ብለው የወታደሮችን ጫማ ሲሰሙ አይታወቁም፡፡ ፈልገው ቢሆን ኖሮ በሩ የተከተላቸው እንደነበር እናውቃለን፡፡ ስልጣን በመፈለግ አይታወቁም፡፡ በቅንጅት ውስጥ እንኳ ራሳቸውን ያገለሉት የስልጣን አባዜ የተጠናወታቸው የሚሰሩትን ስላዩ መሆኑን ከኔ ይልቅ አቶ አባይነህ ማወቅ አለባቸው፡፡

ለመሆኑ ውጤት ማለት ምን ማለት ነው? እንኳን ግለሰብ ድርጅትም ቢሆን ውጤት ለማምጣት በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፍና ትውልድን የሚጠይቅ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አንድ አላማ ቢዘገይ፣ የሃሳቡን ቀስቃሽ ውጤት የማያመጣ ብሎ መዝለፍ ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ መኢአድ ሥልጣን ሳይዝ ዓመታት ቢቆጠሩ ኢንጂነር ኃይሉና አቶ አባይነህ ውጤት የማያመጡ ተብለው ሊዘለፉ ይገባልን?

ፕሮፌሰር መስፍን ያመኑበትን ለመናገር ወደ ኋላ የማይሉ ብዙዎች በፍርሃት በሚብረከረኩበት ወቅት ብቅ ብለው ያሰቡትን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስ፡፡

ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ እየተቃረበ ሲመጣ ብዙ ምሁር እንኳንስ ለሀገሩና ለሕዝቡ ሊያስብ፣ ቤተሰቡን እረስቶ ለራሱ ብቻ በሚያስብበት ወቅት፣ ደርግ ስልጣኑን እንዲያስረክብ፣ ምርጫ  መንግሥት ለሽማግሌዎች በአደራ እንዲሰጥ በዩኒቨርሲቲ ተደርጐ በነበረው የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ ላይ ፊት ለፊት ሃሳብ ሲያቀርቡ አስተውያለሁ፡፡ ኮሚቴ ሲቋቋም አንድ ምሁር ሰግተው ሲወጡ ሌላው ሲጠቆሙ እጃቸውን  አርገብግበው እንቢ ሲሉ አይተናል፡፡ ጥቂት ቆራጦች ምሁራን ተመርጠው ኮሚቴ ሲቋቋም ፕሮፌሰር ሰብሳቢው ነበሩ፡፡ ጊዜውን አስቡት፡፡ በኮሌኔል መንግሥቱ ጊዜ እንዲህ ይሞከር ነበር ወይ? ያን ጊዜ አቶ አባይነህ ምን ይሰሩ እንደነበረ ወደፊት ይነግሩን ይሆናል፡፡

ይኸ አቋማቸው ኮሌኔል መንግሥቱ ደማቸውን አፍልቶባቸው እንደነበርና ..እኛ እዚህ ወንበር ላይ እያለን እንዲህ አይሞከርም ብለው በስብሰባ እስከመናገር መድረሳቸውንና ከንፈራቸውን እንደነከሱባቸው እናስታውሳለን፡፡ እና ይህ እራስን አሳልፎ መቆም ውጤት ስላላመጣ፣ ፕሮፌሰር መናገር ብቻ ነው ሊያስብላቸው ይችላል?

ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ማቋቋም መቻላቸው በቀላሉ ..ካልሆነ በቀር.. ተብሎ የሚነገር አይመስለኝም፡፡ ከፍተኛ መስዋዕትነትን የጠየቀ ብዙ ሥራም የሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ አቶ አባይነህ አያውቁም ማለት ነው?፡፡ ምን አልባትም የእሳቸው ሙሉ ድጋፍ ባይኖረው የቅንጅት መዋሃድ እውን ባልሆነ ነበር፡፡ ግን ውህደቱ ባለመዝለቁ፣ የፕሮፌሰር መስፍን ውጤት ያለማምጣት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

እነዚህን ለምሳሌ አቀረብኩ እንጂ በግላቸው በርካታ የሚያስመሰግን ተግባር ያከናወኑ መሆናቸውን ብዙዎች ያውቁ ይመስለናል፡፡ አቶ አባይነህ የፕሮፌሰርን ሽምግልና ላይወዱት ይችላሉ፡፡ ግን ሽማግሌ በዋለበትም አልዋሉም ብሎ መናገር ክፉኛ መዳፈርና ነውርም ነው፡፡

የፖለቲካ ሽምግልና፣ አቅጣጫ አሳይቶ የተወጠረን ስሜት አርግቦ ለማነጋገር የሚደረግ እንጂ የባልና ሚስት ሽምግልና ዓይነት አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን መሸምገል ቢፈልጉ እንኳ፣ የሚያስታርቁት በመሰላቸው መንገድ እንጂ አቶ አባይነህ በፈለጉት መንገድ ብቻ አይሆንም፡፡ በልማዳችንም ሽማግሌ ሃሳብ አቅርቦ ተሸምጋዮቹ ሳይደግፉት ..አንፈልግም.. ብለው ይሄዳሉ እንጂ አይዘለፍም፡፡

አቶ አባይነህ፣ ወሬ ብቻ እንጂ ሲሉ ፕሮፌሰርን በጭራሽ የሚያውቋቸው አይመስለኝም፡፡ እስከዛሬ በቅጡ ሊያውቃቸው አለመቻላቸውም ያስተቻቸዋል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አቶ አባይነህ ብርሃኑ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ መኖራቸውን የሚያውቀው የድርጅቱ አባል ከሆኑ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንንስ... አንባቢ - ይገምተው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ሁልጊዜም ለሚቃወሟቸው የፕሮፖጋንዳ ሰለባ መሆን እጣ ፈንታቸው የሆነ ይመስለኛል፡፡ የኮሌኔሉ መንግሥት ደንፍቶባቸዋል፣ ኢህአዴግ ከመጀመሪያው ጀምሮ ባገኘው አጋጣሚ ሊያሳጣቸው ሞክሯል፡፡ በተለይ በሁለት ኤርትራዊያን /አቶ ተስፋዬ ገብረአብን፣ አቶ አረፋይኔ ሃጐስ/ ዋና አዘጋጅነትና ምክትል ዋና አዘጋጅነት በሚያሳትመው የእፎይታ መፅሔት የቤተሰባቸውን ታሪክ ሳይቀር ለማጣመም ሲሞክር ቆይቷል፡፡ ግን የሕዝቡን ከበሬታ ሊቀንስባቸው አልቻለም፡፡

አቶ አባይነህ፣ ፕሮፌሰርን የመሰለ የ76 ዓመት አዛውንት፣ የተመሰከረላቸውን ምሁር፣ በራሳቸው መንገድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቆማቸውን በተግባር ያሳዩ ሰው /አቋማቸው ላይ ላንስማማ ይችላል/ ሲዘልፉ ራሳቸውን እንደሰደቡ፣ ራሳቸውን እንደዘለፉ ሊቆጥሩት ይገባል፡፡ ይኸ ደግሞ እኛን አንባቢዎቹንም ያሳፍረናል፡፡ የቅንጅት ደጋፊዎችን ያሸማቅቃል፡፡ የበለጠ ቀድሞ የመኢአድ አባላት የነበሩትን ያሳፍራል፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ይወዱላቸው አይመስለኝም፡፡

በሌላ በኩል የታወቁ ምሁራችን አድርገን የምንቆጥራቸው ፕሮፌሰር መስፍን ..አዲስ ነገር.. ለተሰኘ ጋዜጣ የተናገሩት ዕድሜና ትምህርት አልቆታል፤ ከሚባል ሰው የሚጠበቅ ሆኖ አይታይም፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፣ የመኢአድ አባላት ግንኙነት ..የጌታና የሎሌ.. ዓይነት መሆኑን ደፋር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የሚደንቀው መኢአድን ያህል ድርጅት የጌታና የሎሌ ነው ሲሉ ለምን እንደዚያ እንዳሉ መገለጫውን አላሳዩንም፡፡ አልተጠየቅሁም ይሉኝ ይሆን? ተሳዳቢ ዝም ብሎ ስድቡን ይለጥፋል እንጂ ለስድቡ ምክንያቱን ዘርዝሮ እንደማያስረዳ አውቃለሁ፡፡ በፕሮፌሰርነት ደረጃ ግን ምክንያቱን ሳያስረዳ፣ የነሲብ ዘለፋ የሚናገር ከሆነ ከመተቸት አያመልጥም፡፡

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያለ ታዋቂ ሰው፣ የሚናገረውን እየለካ ጊዜያዊ ስሜት እየቀሰቀሰ የሚያሳስት ሳይሆን ሰርስሮ የሚገባ እውነት ይናገራል እንጂ በተራ ስድብና ዘለፋ እድፍ ራሱን አያቆሽሽም፡፡

ለመሆኑ መኢአድ የጌታና የሎሌ ግንኙነት ተብሎ የሚያቃልሉት ድርጅት ነው? አይመስለኝም፡፡ መኢአድ በድርጅታዊ አወቃቀር ተንተርሶ ዘለግ ያሉ መስዋዕትነትን የሚጠይቁ አስጨናቂ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ፕሮፌሰር እንደሚሉት በአሽከርና በጌታ ግንኙነት የተዋቀረ ድርጅት አስጨናቂውንና ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቀውን ድፍረትና ፅናት አያገኝም፡፡ በፈቃደኛነት ላይ ያልተመሰረተ አባልነት፣ እንኳን በጭንቅ ወቅት በሰላሙም ጊዜ ውጤት አያመጣም፡፡ በመኢአድ ውስጥ ያሉ አባላት፣ ፕሮፌሰር እንደመሰረቱት ቀስተ ደመና ወደውና ፈቅደው የገቡበት እንጂ የእጅ መንሻ እያገኙ..ለመኖር ሲሉ የገቡበት አይደለም፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ፕሮፌሰር ላለማየት አይናቸውን ካልሸፈኑ በስተቀር፣  ከፈጠሩት አራት ድርጅቶች፣ የደረጀ የፖለቲካ ፓርቲ ወግ ይዞ ድርጅታዊ ሥራውን በጥሩ ውጤት ፈፅሞ የሰራ እንደመኢአድ የለም፡፡

መቼም ፕሮፌሰር እርሳቸው ያሉትን እጅ ነስቶ ያልተቀበለና የተቃወማቸውን፣ እገሌን የሚከተለው አሽከር ስለሆነ ነው፤ የሚሉ ከሆኑ ክፉኛ ተሳስተዋል፡፡ የእርሳቸው መንገድ ሁልጊዜም ትክክል ነው፤ ብለው ሊደነፉብን አይችሉም፡፡ ፕሮፌሰር ሁሉ የተናገረው ያላንዳች ጥያቄ መደመጥ አለበት የሚባል ከሆነ ይኸ ሌላ ነገር ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፣ ወ/ት ብርቱካንን አጎላምሰው በሕዝብ ፊት ለማስወደድ ያላቸውን መጠን የለሽ ፍላጎት፣ የሚገልፁት መኢአድን በመስደብና አባላቱን በማዋረድ እንዲሆን መፈለጋቸው ለሕዝቡ ያላቸው ግምት የተሳሳተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

የአቶ አባይነህን ውክልና የድርጅቱ ደንብ እንደሚፈቅድ መኢአዶች የሚናገሩትን ለማስተባበል ከፈለጉ ደርዝ ያለው ንግግር ከመናገር ይልቅ ስድብ ምን አመጣው? በዚህ እድሜያቸው የሚጠሉትን ለመንቀፍ ሎሌዎች እያሉ ለመሳደብ ለከት ማጣት ይመስለኛል፡፡

የነወ/ት ብርቱካንን ቡድን በአሜሪካ ለማሽመድመድ የበቃው መኢአድ ወግ ያለው የድርጅት አቋም የያዘ በመሆኑ እንጂ በጌታና በሎሌነት ግንኙነት አይደለም፡፡ እንዲህማ ከሆነ ፕሮፌሰር ከብርቱካን ጀርባ ሆነው ያለሙትን ለማሳካት ፈልገዋል እየተባሉ የሚታሙበትን፣ ብርቱካንን ሎሌ ሊያደርጓት ፈልገው ነው ቢባሉ ምን ሊሉ ይሆን? እነ አቶ አባይነህ የፈለጉትን ቢከተሉ በሎሌነት ሊተረጎምባቸው አይቻልም፡፡ የመኢአድ አባል ግንኙነት የሎሌና የጌታ ነው ካሉ ማስረጃውን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል እስኪያቀርቡ እጃቸውን አፋቸው ላይ መጫን አለባቸው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ለከት ያጣ ንግግራቸው በተለይ እንደ እርሳቸው ካለ ታዋቂ ሰው ሲሰማ የሚረጨው መርዝ ብዙ ነው፡፡ በርግጥ ተራና ያልታሰበ አነጋገር፣ ራሱን ተናጋሪውን ያስገምታል እንጂ ተቺውን አንዲትም ነገር አይቀንስበትም፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ 60ዎቹን የአፄ ኃይለስላሴ ሚኒስትሮች እንዲገደሉ ፕሮፌሰር መስፍን ቀስቃሽ እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ እንደዚያ በማለታቸው በራሳቸው ሳቅንባቸው እንጂ ፕሮፌሰርን አላንጓጠጥናቸውም፡፡ ዛሬም ርሳቸው እንደፈለጓቸው ሊነዷቸው ያልቻሉትን የቀድሞ የመኢአድ አባላት ..ሎሌዎች.. እያሉ ቢሳደቡ እንታዘባቸዋልን እንጂ በእነ አቶ አባይነህ ላይ ጣታችንን አንቀስርም፡፡

ሌሎቹንም ቃሎች እየመዘዝን ብንናገር ፕሮፌሰር መስፍን ታናናሾቻቸው የማያደርጉትን ነውረኛ አነጋገር በመናገራቸው የሚስነቅፋቸውና የሚታረሙበት አስተያየት እንዲሰጡ የሚያስገድድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ነገሬን ላብቃላቸው፡፡ ከእነዚህ ከሁለት አዛውንቶች አጠገባቸው ያሉ ወጣቶች ምን ሊማሩ ይችላሉ? ይኸ ራሱ ያሳስባል፡፡ እነሱም በተመሳሳይ ዝቅጠት እንዳይሰጥሙ አሳስባለሁ፡፡ 

ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፡፡ ልዩነታችሁ እንደፍጥርጥራችሁ፡፡ ነገር ግን ስድብና ዘለፋ እንዳያዘቅጧችሁ አትጠቀሙባቸው፡፡ ሃሳብ ላይ በማስረጃ እያስደገፋችሁ ተተቻቹ፡፡ ግን በተራ ስድብ በማጀብ የብልግና ፖለቲካ አታካሂዱ፡፡ የሚያሳፍረውንና የሚያስከብረውን ንግግር እወቁት፡፡

እባካችሁ ጋዜጠኞችም እንዲህ እንዲህ ዓይነት መረን የለቀቀና የተነወረ ቃሎችን እያረማችሁ ብትፅፉ ተናጋሪውንም የወከለውን ድርጅትም ከመገመት ታድኑታላችሁ፡፡

 

Last Updated ( Wednesday, 09 January 2008 )
 
< Prev