| ሰው አውሬ ሲሆን |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
ሰው አውሬ ሲሆን
የአምስትና የሦስት አመት እህትማማቾች ቤት ውስጥ የነበራቸው ፀባይ ከተቀየረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ያለቅሳሉ፣ ይነጫነጫሉ፣ ሌሊት ከእንቅልፋቸው ይባንናሉ፣ ትምህርት ቤት አንሄድም ይላሉ፣ ገላቸውን ለመታጠብ ፍቃደኛ አይሆኑም፣ ወንድ እንግዳ እቤት ውስጥ ሲመጣ ይሸሻሉ. . . እናት በልጆቿ ላይ የታዩት እነዚህን የፀባይ ለውጦች ቢያሳስቧትም ምክንያቱ በግልጽ ማወቅ አልቻለችም፡፡ "ልጆቼን በድህነት ነው ያሳደግኳቸው፡፡ ዳቦ ቆሎ ሰርቼ እየሸጥኩ፣ ሰው ቤት ልብስ እያጠብኩ፡፡ እስከ ምሽቱ 2፡30 ድረስ እቤት የማልገባበት ጊዜ አለ" የ34 ዓመቷ የልጆቹ እናት እንደምትለው ከልጆቿ ጋር ለመዋልና እነሱን ጊዜ ሰጥቶ ለመንከባከብ ጊዜ የላትም፡፡ ህፃናቱ ከትምህርት ቤት መልስ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በግቢው ውስጥ እንደነሱ ተከራይ ሆኖ ከሚኖር አንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ነው፡፡ እናት እንደምትለው ግለሰቡ ልጆቹን ያቀረባቸው በፍቅር ነው፡፡ "ልጆች እወዳለሁ፣ አትከልክሉኝ ከእኔ ጋር ይዋሉ" በማለት ወላጆችን አስፈቅዶ አብሮ ይጫወታል፡፡ ከረሜላ፣ ማስቲካና ብስኩት እየገዛ ከቤቱ እንዳይወጡ ያደርጋል፡፡ ፊልምም ያሳያቸዋል፡፡ እናት ይህንን ሰው "እግዚአብሔር የሰጠኝ ወንድሜ" እያለች ታወድሰዋለች፡፡ ማታ ከሁለት ሰዓት በኋላ ከስራ ስትመለስ ልጆቿን የምታገኛቸው እሱ ቤት ውስጥ እንቅልፍ ወስዷቸው ነበር፡፡ እቤቷም ስትውል ሥራ ከበዛባት ወደዚሁ ጎረቤቷ ቤት ትልካቸዋለች፡፡ አንድ ቀን ሁለቱም ተከራዮች የሚኖሩበት ግቢ ውስጥ የመልስ ጥሪ ነበር፡፡ ግቢው ተተራምሷል፡፡ ሁለቱ ህፃናት ግን ዛሬም ፊልም የሚያሳያቸው የጎረቤት ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ ከቆይታ በኋላ የአምስት አመቷ ህፃን እያለቀሰች ስትወጣ እናቷ አይታት ምን እንደሆነች ብትጠይቃትም ልጅቷ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ "ስትወጣ አይኗ በጣም ቀልቷል፡፡ የሳግ አይነት ድምጽም አላት፡፡ ምን ሆነሽ ነው ስላት ፣ፊልም በቅርበት ስላየሁኝ ነው፣ አለች፡፡ እሱንም ሳነጋግረው ምንም አልሆነችም አለኝ፡፡ ልጆቼ አንተ ላይ እንደሚቀብጡ አውቃለሁ፡፡ ሲያጠፉና ሲረብሹህ ቅጣቸው፡፡ እንደባዳ ዝም አትበል ብዬው ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ልጆቹ የፀባይ ለውጥ ቢያሳዩም፣ እያለቀሱ ከግለሰቡ ቤት ቢወጡም ምን እንደሆኑ ግን የተነፈሱት ነገር አልነበረም፡፡ በስልክ ትልቋ ልጅ ከምትማርበት ትምህርት ቤት ለእናት የደረሳት መልዕክት ደግሞ ሌላ የልጇን ችግር የሚያሳይ ሆነ፡፡ "ልጅቷ መጥፎ ጠረን አላት፡፡ በፊት ጫማዋ መስሎን ነበር ግን አይደለም፡፡ ልጆቹ አብረናት አንቀመጥም እያሉ ተጽዕኖ እያሳደሩባት ነው፡፡ ለምን አታጥቢያትም" የሚል ነበር፡፡ አንድ ቀን ልጆቹ ምስጢራቸውን ለአንድ ዘመዳቸው ተናገሩ፡፡ እናት ወደ ክፍለ ሀገር በሄደችበት ወቅት ልትጠይቃቸው የመጣችው ዘመድ የመጀመሪያ እርምጃዋ ልጆቹን አጣጥባ ልብሳቸውን አጥባ ማልበስ ነበር፡፡ ልብሳቸውን ስታወልቅ ያየችው ደም ግን አስደነገጣት፡፡ ልጆቹ ለሷ ምስጢር አልሸሸጓትም፡፡ ለእናታቸው እንዳትናገርባቸው በመማፀን በተደጋጋሚ ሲፈፀምባቸው የከረመውን በደል ዘረዘሩላት፡፡ "ለእማማዬ እንዳትነግሪብን፡፡ ካካችንን አወጣውና በሶፍት ጠርጎ ፖፖ ውስጥ ጣለው፡፡ ካካችን የሚወጣበት ውስጥ ሽንት መሽኛውን ከተተብን" አሏት በልጅነት አንደበታቸው፡፡ በደሉን የፈፀመባቸው ፊልም እዩ እያለ የሚወስዳቸው ጎረቤታቸው መሆኑን ገልፀውላታል፡፡ ለእናታቸው ብትናገር እናታቸውን ስለሚገድልባቸው እያለቀሱ እንዳትናገር ተማፀኗት፡፡ ይህ የተነገራት ዘመድም ፈርታ የሰማችውን የህፃናቱን በደል ለማንም ሳትተነፍስ ወደ ቤቷ ሄደች፡፡ ከሳምንት በኋላ እናት ወደ ቤቷ ስትመለስ ትንሿ ልጇ ታማ አገኘቻት፡፡ በፊንጢጣዋ ደም ይወጣ ነበር፡፡ እናት አሁንም አልጠረጠረችም፡፡ አሜባ ወይም ሆድ ድርቀት ይዟት ይሆናል በሚል ጥርጣሬ አለፈችው፡፡ እሷ እንደምትለው እጇም ላይ ገንዘብ ስላልነበረ ሐኪም ቤት አልወሰደቻትም፡፡ ትንሿን ልጅ አስተኝታ እየተንከባከበች እያለች የግቢው ሌላ ተከራይ ሠራተኛ ትልቋን ልጅ ገላዋን ስታጥብ ቆይታ ያመራችው ወደ እናቷ ነበር፡፡ ልጅቷ መጥፎ ሽታ እንዳላትና የውስጥ ሱሪዋም በፈሳሽ እንደሚርስ፣ ሐኪም ቤት ብትወስዳት ጥሩ እንደሆነ አስረዳቻት፡፡ ይሄኔ ሁለቱንም ልጆቿን እያባበለች የሆኑትን እንዲነግሯት አግባባቻቸው፡፡ ጎረቤታቸው በእግሩ ብልታቸውን እንደሚነካካቸውና አፋቸው ውስጥና ፊንጢጣቸው ውስጥ እንደሚያስገባባቸው ትልቋ እያለቀሰች አስረዳቻት፡፡ እግር መሆኑን እንዴት አወቅሽ? የእናት ጥያቄ ነበር፡፡ ህፃኗም ብልቷን እየጠቆመች እዚህ ጋ ፂም ያለው እግር አለው ምንድን ነው? ስንለው እግር ነው ይለናል፡፡ እግሩ ትንሽ ናት፡፡ ሳሙልኝ ደባብሱልኝ ይለናል፡፡ ስንስምለት ግትርትር ብሎ እግሩ ትልቅ ይሆናል፡፡ በኋላ አፋችን ውስጥ አስገብቶ ሞቅ ያለ ነገር ያፈስብናል፣ ቋቅ ሲለን ዋጡት እያለ ያስውጠናል" "እግዚአብሔር የሰጠኝ ወንድሜ" የምትለው ጎረቤቷ አስባው የማታውቀውን በደል ልጆቿ ላይ እንደፈፀመ ስትሰማ ያመራችው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ነው፡፡ ተከሳሽ ወዲያው በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ቢሆንም በ10 ሺህ ብር ዋስ ተፈቶ አሁን ያለበት እንደማይታወቅና ከአመት በኋላ ባለፈው ጥር ወር ፍርድ ቤቱ የ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንደፈረደበት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የውሳኔ ወረቀት ያስረዳል፡፡ የፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ በከፊል እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ "ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ዳባ ጥፋተኛ የተባለበት ወንጀል በህፃናት ልጆች ላይ በሚፈፀም የግብረስጋ ግንኙነት በደል ሙከራ ወንጀል ሥራ እና በሽታን በማስተላለፍ ሲሆን ተከሳሽ በህፃናቱ ላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በደል ሙከራ ብቻ ሳይሆን የፈፀመው አፀያፊነቱን በሚገልጽ ሁኔታ ብልቱን ለህፃናቱ ያስጠባቸው እና የዘር ፍሬውን በአፋቸው ውስጥና በየብልቶቻቸው ውስጥ ያፈስባቸው እንደነበር በዚሁም ምክንያት ህፃን . . . . . የተባለችው የግል ተበዳይ የጨብጥ በሽታ በተደረገላት ምርመራ የታየባት መሆኑ የቀረበው ማስረጃ ያስረዳል፡፡ ስለሆነም ፍ/ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት አስተያየት ከግምት በማስገባት ተከሳሽ ሊቀጣ ሊያርመው እና ሊያስተምረው እንዲሁም ለሌሎች ማስጠንቀቂያ ይሆናል በማለት የወ/መ/ሕ/ቁጥር 88 ሥር የተመለከተውን መሰረት በማድረግ ተከሳሽ ጥፋተኛ በተባለባቸው በሁለቱም ወንጀሎች በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እንዲሁም በ17 ዓመት ጽኑ እስራት የተቀጣ በመሆኑ ተከሳሽ ቅጣቱን ከፈፀመ በኋላ ለ5 ዓመት ምስክር ከመሆን፣ ከመምረጥ ከመመረጥ ከመሳሰሉት ህዝባዊ መብቶች እንዲሻር ፍ/ቤቱ ወስኗል" አመት ያህል ከፈጀ የፍርድ ቤት ቆይታ በኋላ በቀረቡ የሐኪም ማስረጃዎችና የልጆቹ ምስክርነት አማካይነት የፍርድ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ተከሳሽ ግን የደረሰበት አይታወቅም፡፡ እናት እንደምትለው ፍርድ ቤት በ10ሺህ ብር ዋስ ከለቀቀው በኋላ የተወሰኑ ቀጠሮዎችን ተከታትሎ በኋላ ጠፍቷል፡፡ በፍርድ ሂደቱ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ውጣ ውረዶችን እንዳለፈች የምትናገረው የህፃናቱ እናት የሆስፒታል ማስረጃ ለማግኘት ከሚደረገው ምርመራ ጀምሮ ብዙ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልፃልናለች፡፡ "ልጆቹ የተደፈሩበትን ትክክለኛ ቀን ካላመጣሽ ብለው ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ እጅ ከፍንጅ አልያዝሽም፡፡ ህፃናት ልጆች ናቸው እንዲህ ተደረግን ብለው የሚናገሩት መቼ ስትያቸው ከሥራ ሲመጣ፣ እሁድና ቅዳሜ እቤቱ ኑ እያለን ይላሉ፡፡ ድርጊቱ በተደጋጋሚ ሲፈፀምባቸው በዚህ በዚህ ቀን ብለው ህፃናቱ ማስታወስ አይችሉም፡፡ የሆስፒታል ማስረጃ ለማግኘትም ችግር አለ፡፡ በተለይ ወንድ ዶክተሮች ይህ ቁስል የተሰማቸው አይመስልም ይሰድቡሻል፡፡ ህፃናት ልጆችሽን ያጉላላሉ፣ ምንሽ ጋ ነው የነካሽ በእግሩ ነው በእጁ አልነካሽም እያሉ ልጆቹን ይበልጥ ያሳቅቋቸዋል፡፡ ከተከሳሽ ወገን የሚደርስብሽ ዛቻ አለ" ስትል እነዚህንና ሌሎችንም ፍትህ ለማግኘት ትግል ላይ እንቅፋት የሆኑባትን ነገሮች ዘርዝራለች፡፡ ጥቂት ቢሆኑም ነገሮች በትክክለኛው መስመር ተጉዘው እውነተኛ ፍትህ እንዲያገኙ የተባበሯትና በቀናነት ያስተናገዷት እንዳሉም ገልፃለች፡፡ ከእናታቸው አንደበት ለመረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ልጆቹ የጤና መሻሻል የሚታይባቸው ቢሆንም የስነልቦና ጉዳታቸው ግን መጠገን አልተቻለም፡፡ አሁንም ወንድ እንግዳ ሲያዩ ይደበቃሉ፡፡ ጨለማ ውስጥ ለብቻ መቀመጥና መገለል ይታይባቸዋል፡፡ በየጊዜው የሚነሳባቸው የማህፀን በሽታ እንዳለባቸው ከሕክምና ጣቢያ የተነገራት ሲሆን እየተመላለሰች እንደምታሳክማቸው ተናግራለች፡፡ በትዕግስት ዘሪሁን |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |