| “ራበን” |
|
|
| Wednesday, 19 March 2008 | |
|
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ ተማሪዎች
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ ተማሪዎች “በወር የሚከፈለን የኪስ ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ ለረሃብ፣ ለችግር ተጋልጠናል” በሚል መጋቢት 8 ቀን 2000 ዓ.ም ሠንጋተራ አካባቢ በሚገኘው የኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመሰብሰብ ቅሬታቸውን ለትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ማቅረባቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ እንደ ተማሪዎቹ ገለፃ አዲስ ከአበባ ወደ ኮሌጁ ለገቡ ተማሪዎች ብር 240፣ ከክፍለ አገር ለመጡ ብር 300 በየወሩ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ “የሚሰጠን ገንዘብ እንኳን ቀለባችንና የቤት ኪራያችንን ሊችልልን ቀርቶ ከመምህራኖቻችን በሚሰጠን ትዕዛዝ መሠረት ከተለያዩ መጽሐፍቶች ኮፒ ለምናደርግበት ክፍያም አይበቃንም” ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከሦስት ወራት በፊት “ፒቲሽን በመፈራረም” የሚከፈላቸው ገንዘብ በቂ አለመሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን ለኮሌጁ አስተዳደር ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ ባለማግኘታቸው፣ ቅሬታቸውን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ሕዝቡ እንዲረዳላቸው ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በግቢ ውስጥ ሠላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ “ኑሮው በከፍተኛ ሁኔታ አስቸጋሪ በሆነበት በአሁኑ ሰዓት ቤት ተከራይተን፣ ምግብ ተመግበን፣ የተለያዩ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ገዝተንና ትራንስፖርት ተጠቅመን እንዴት 300 ብር ይበቃናል?” በማለት የሚጠይቁት ተማሪዎቹ፣ እንኳንስ ከክፍለ አገር መጥተው ለሚማሩትና አዲስ አበባም ከቤተሰብ ጋር ለሚኖሩት ገንዘቡ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኮሌጁ የበላይ ኃላፊዎችና መንግሥት ያለብንን ችግር ተመልክተው አስቸኳይ ውሳኔ ካልወሰኑልን፣ በቅርብ ቀናቶች ውስጥ ትምህርታችንን ለማቆም እንገደዳለን የሚሉት ተማሪዎቹ መንግሥትም ሆነ ነዋሪው ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የኑሮ ውድነት “ልብ ሊሉት ይገባል” በማለት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ በአንድ ላይ በመሆን ለኮሌጁ ኃላፊዎች ያቀረቡትን ጥያቄ፣ የኮሌጁ ዲን በማዳመጥ በሰጡት ምላሽ፣ ጥያቄአችሁን ተቀብለን ዝም አላልንም፣ ለበላይ አሳውቀን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው፡፡ አሁንም በድጋሚ እናስታውሳለን የሚል ምላሽ እንደሰጡዋቸው ተማሪዎቹ አሰረድተዋል፡፡ የኮሌጁ ኃላፊዎች የተማሪዎቹን ጥያቄ በምን መልኩ እያስተናገዱት እንደሆነ እንዲያብራሩልን፣ በኮሌጁ ተገኝተን ለማጣራት ብንሞክርም፣ “ሙሉ ቀን በስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ምላሽ በጥበቃ ሰራተኞች በመከልከላችን ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |