Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow የኑሮ ውድነትን ለመከላከል መንግስት...
የኑሮ ውድነትን ለመከላከል መንግስት... Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
Imageከዛሬ ጀምሮ በምግብ እህል ላይ የጣለውን ቫት እና ተርን ኦቨር ታክስ ያነሳል

- ህገወጥ ነጋዴዎችን መቅጣት ይጀምራል
- ድጎማውን ይቀጥላል



በአገሪቱ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ መንግሥት ተከታታይ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ትናንት መጋቢት 9/2000 ዓ.ም. ሪፖርት ያቀረቡት አቶ መለስ የዋጋ ግሽበቱ በተፈለገው መጠን ስላልተረጋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርበው ስንዴ እንዲቀጥልና በምግብ እህል ላይ ሲከፈል የነበረው የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ ከዛሬ ጀምሮ እንዲነሳ መንግሥት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩም የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ልክ ዋጋውን ወዲያው ወደ ተጠቃሚው ከማስተላለፍ ይልቅ ደረጃ በደረጃ ወደ ዓለም ገበያ እየተጠጋ እንዲሄድ የማድረጉ ፖሊሲ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡

በቀላሉ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉትን እንደምግብ ሰብሎችና ሲሚንቶ የመሳሰሉትን ምርቶችም በበቂ መጠን ለማምረት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በነዳጅና በተለያዩ ምርቶች ላይ የታየው የገበያ ዋጋ ጭማሪ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የማይቀየር መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለመቋቋም የሚቻለው ኢኮኖሚው በፍጥነት እንዲያድግና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡ ገቢ እንዲጨምር በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ለበጀት ማሟያ ብሎ ከባንክ የሚበደረው ገንዘብ ከብሔራዊ ገቢው 2.7 በመቶ ብቻ እንዲሆን መደረጉንና የመንግሥት ብድር በተቀመጠው እቅድ መሠረት ብቻ እየተፈፀመ መሆኑን የገለፁት አቶ መለስ የገንዘብ መጠኑ እድገት ግን በተፈለገው መጠን ሊቀንስ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የገንዘብ መጠን እድገትን ለመገደብ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ አቶ መለስ እንዳሉት ይህንኑ የብሔራዊ ባንክ እርምጃ ለማጠናከር በገንዘብና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሚኒስቴርም በኩል ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡

“እድገታችን እጅግ በሚያበረታታ አኳኋን እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱም እየተባባሰ በመምጣቱና በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማ ነዋሪ እጅግ የሚፈታተንበት ሁኔታ በመፈጠሩ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ራሱን እንደቻለ መሠረታዊ ግብ ማስቀመጣችን ተገቢና አስፈላጊም ነው” ያሉት አቶ መለስ ግሽበቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠረና እጅግ የተወሳሰበ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ በጥንቃቄ መተግበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

አቶ መለስ በሪፖርታቸው ላይ እንደገለፁት በጊዜያዊ የማርገቢያ ስልቶች ኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለነዳጅ ድጐማ 3.52 ቢሊዮን ብር ለስንዴ ድጐማ ደግሞ 372 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ከውጭ ከሚገባ የሲሚንቶ ምርት ላይ የሚከፈለውን ቀረጥ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት መንግሥት ከፍተኛ የሰው ኃይል ቁጥር የሚያስተዳድረው የኮንስትራክሽን ሥራ እንዳይስተጓጐል የ387.8 ሚሊዮን ብር ድጐማ ማካሄዱን በጠቅላላው መንግሥት 4.2 ቢሊዮን ብር መደጎሙን ተናግረዋል፡፡

ስግብግብና ህገወጥ ነጋዴዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚጥሉትን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት አቶ መለስ በአሁኑ ወቅት በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ሲከተል የነበረውን ስልት በመሰረቱ ለመቀየር መወሰኑንና ህገ ወጥ ነጋዴዎችን የሚያስታግሳቸው እያንዳንዳቸውን ነቅሶ በማውጣት ያለማመንታት በመቅጣት መሆኑን እንደታመነበት ገልፀዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በቋሚነት በቅርብ በመከታተል በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ፈጣንና የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ በተከታታይ ለመውሰድ ይቻል ዘንድ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርት ተከትሎ ጥያቄና አስተያየት ያቀረቡት ዶ/ር መረራ ጉዲና በመንግሥት በኩል እየታየ ነው ተብሎ የተገለፀው የኢኮኖሚ እድገት “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ከሚለው ተረት ጋር የሚመሳስል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው እውነታም ድህነት እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ መሄዱን አመልክተዋል፡፡

ድርቅ ብዙ አካባቢዎችን እየጐዳ እንደሚገኝ፣ በቦረና አካባቢ ከብቶች እያለቁ መሆናቸውን ዶ/ር መረራ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም አገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት እያሳየች ነው ተብሎ የሚነገረውን ጉዳይ “ኢህአዴግ ይቅርና እግዚአብሔርም ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳመን የሚችል አይመስለኝም” ብለዋል፡፡

እስከአሁን ድረስ ኢህአዴግ በአኮኖሚው በኩል እንዳልተሳካለት የጠቆሙት ዶ/ር መራራ ባሌስትራ ወርቅ ነው ብሎ ያስቀመጠው ብሔራዊ ባንክም በኢኮኖሚው ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ መገለፁ ለመቀበል የሚያስቸግር ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

መንግሥት በምግብ እህል ላይ የተጣለውን ተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ እንደሚያነሳ ማሳወቁን ግን በደስታ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም “የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ሊበላ ይችላል” የሚለውን ጥቅስ በመጥቀስ ኢህአዴግ መድረክ አመቻችቶ ከተቃዋሚዎች ጋር ብሔራዊ ውይይት እንዲከፍት አሳስበዋል፡፡

የኢዴአፓ መድህን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት ጉድለቶች ቢኖሩትም አበረታች የሆኑ ጠንካራ ጐኖች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

“በሪፖርቱ ላይ የኑሮ ውድነት ዋና የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ተገቢ ነው” ያሉት አቶ ልደቱ ኢዴአፓ መድህን የኑሮ ውድነት ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ሲጠይቅ ሁለት ዓመት ቢያልፈውም በጊዜው ተቀባይነት አለማግኘቱን ጠቁመው ጉዳዩ ዘግይቶም ቢሆን አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የዋጋ ግሽበቱን ችግር ለመፍታት መፍትሄው ምርት መጨመር ነው የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ ገዢው ፓርቲ ሲያቀርብ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ልደቱ በኢዴአፓ መድህን በኩል ግን ለመፍትሄው በዋናነት የሸማቹን ህብረተሰብ የገቢ መጠን ማሳደግ ነው የሚል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የደመወዝ ጭማሪ፣ ድጐማና የመንግሥት አገልግሎት ቅናሽ መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ሲያቀርብ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ይህንን ሀሳብ ፓርቲያቸው በአጀንዳ ደረጃ ለፓርላማ አቅርቦ ውድቅ የተደረገበት ቢሆንም ፓርቲያቸው ሲያነሳቸው የነበሩት ጉዳዮች አሁን መፍትሄ ሆነው መቅረባቸው የሪፖርቱን በጐ ጐንነት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ መነሳት ተገቢ መሆኑ አቶ ልደቱ ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ታክስ ሲነሳ ነጋዴው አሁን ካለው የእህል ዋጋ የተነሳለትን የታክስ ጭማሪ እንደሚቀንስ እርግጠኛ መሆን የሚያስችል አሰራር መኖር እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ “በህገ ወጥ ነጋዴዎችም ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ህዝቡ መተባበር አለበት” ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረበው ሪፖርት ላይ አቶ ልደቱ ያልተቀበሉት “ኢኮኖሚያችን በመሰረቱ ጤናማ ነው” የሚለውን አገላለፅ ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ጉድለቶች አሉበት፡፡ የዘላቂነትና የፍትሀዊነት ችግርም አለበት፡፡ “ረየኢትዮጵያ ኢኮኖሚሪ የደም ብዛት ያለበት ኢኮኖሚ ነው” ያሉት አቶ ልደቱ አሁን የሚታየው የግሽበት ችግር እስካልተፈታ ድረስ ኢኮኖሚው ጤናማ ነው ሊባል እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

በተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል ቢባልም በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ለውጥ አለመታየቱን የገለፁት ደግሞ አቶ ተመስገን ዘውዴ ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ ውሀ መጠጣት አለመቻሉን የመብራት አገልግሎት አለማግኘቱንና የምግብ እህሎችን መግዛት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ አገር ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ዓይነት የኢኮኖሚ ችግር ሲታይና የአመራር ድክመት ሲኖር ሥራ አስፈፃሚው አካል ስራዬን ለቅቄያለሁ ብሎ ምክር ቤቱን እንደሚጠይቅ ያመለከቱት አቶ ተመስገን “ረአቶ መለስሪ ይህንን ያደርጋሉ ብዬ ባልጠብቅም ሊያደርጉት ይገባል” ብለዋል፡፡

በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ይወሰዳል የተባለውን እርምጃ በተመለከተም የአንድ ሰው ህገ ወጥነት የሚረጋገጠው በፍርድ ቤት ሆኖ ሳለ ሰዎችን በጥቆማ ማሰርና በአማላጅ መፍታት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በዓለም አቀፍ ግሽበት ምክንያት ብቻ የተከሰተ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የሚታየው አስጊ የዋጋ ግሽበት ከኢትዮጵያ የፈለቀ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቡልቻ ኢትዮጵያውያኖች ብቻ በሚጠቀሟቸው የምግብ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ንረት ህዝቡ ከማይችለው ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡ ..ለዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ነገር መደረግ አለበት.. ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አቶ ቡልቻ እንደሚሉት በአሁኑ ሰዓት በምግብ ላይ የታየውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ በገበያ ውስጥ የጠፋን የምግብ ምርት መንግሥት ከውጭም ሆነ ከውስጥ ገዝቶ ለታላላቅ ነጋዴዎች በማከፋፈል የዋጋ ንረቱን መቀነስ ይችላል፡፡ ይህም አሰራር በሌሎች አገሮች ሲተገበር መቆየቱንና ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“አንድ ኢኮኖሚ አደገ ወይም አላደገም ለማለት የህዝብ ቁጥር መታየት አለበት” ያሉት አቶ ቡልቻ የህዝብ ቁጥራችን ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተገልፆ የኢኮኖሚው እድገት ከህዝብ ቁጥሩ ጋር መታየት እንደነበረበት አመልክተዋል፡፡ በጉጂ ኦሮሚያ ያለው ድርቅም በሪፖርቱ ላይ አለመጠቀሱ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከተቃዋሚዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሸ የሰጡት አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያደገ መሆኑን ለማወቅ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ10 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቡ አይነተኛ ማረጋገጫ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


ፍትሀዊነትን በተመለከተም ሁሉም የገጠር ነዋሪ በኢኮኖሚ እድገቱ ተጠቃሚ መሆኑን በከተማ አካባቢም ባለሀብቱና እወቀት ያለው የህብረተሰብ አካል፣ ሠራተኛው ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሚያስቆጨውና የሚያሳዝነው በእናቶች የሚመሩ ጥቃቅን ሥራዎች ላይ ለውጥ አለመታየቱ ነው፡፡

ከዶ/ር መረራ ጉዲና ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መሞከር የፓርላማውን ክብር ሊነካ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ መለስ ከግሽበቱ ጋር ተያይዞ በኤርትራና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ለተነሱት ጥያቄዎችም መልስ አልሰጡም፡፡

ከውጭ ስንዴ ገዝተን አምጥተን ለነጋዴ ሰጥተን ገበያ ላይ ብናፈስሰው ገበያው ራሱ ያወርደዋል በሚል ለቀረበው ሀሳብ ምላሽ ሲሰጡ “በጣም ቀላል ሀሳብ ነው በጣም ስህተት ከመሆኑ በስተቀር” ብለዋል፡፡

እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ አሁን ባለው የዓለም ገበያ ስንዴ ከውጭ አገር ተገዝቶ አዲስ አበባ ለማድረስ 5ዐዐ ብር ይፈጃል፡፡ ስንዴን በ5ዐዐ ብር ገዝቶ በርካሽ መሸጥ እንደማይቻል አቶ መለስ ያለው አማራጭ የስንዴ መጠንን በአገሪቱ መጨመር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >