Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow ኑሮ ከተወደደ ሳሎንም አይሞቅም
ኑሮ ከተወደደ ሳሎንም አይሞቅም Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
Imageኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል፤ እያልን ስንቴ ራሳችንን እያፅናናንና ራሳችን ለራሳችን ማስተዛዘኛ እያሰማን እንኑር?
ኑሮ ከተወደደ አይደለም መቃብር፣ ሳሎንም አይሞቅም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የዓለምን የኑሮ ሁኔታ እያናጋው ነው፡፡ ትራንስፖርትን ብቻ ሳይሆን ከፔትሮሊየም የሚሰሩ በርካታ የምርት ውጤቶች፣ ከነዳጅ የሚሰሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ስላሉ ነው፡፡ በነዳጅ የሚሰራው የሲሚንቶ ፋብሪካችን በከሰል እንደሰራ ሆኖ ካልተቀየረ የሲሚንቶ ዋጋ ሲንር ይኖራል፡፡

የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመናሩ በአገራችን የኑሮ ውድነትን አስከትሏል፡፡ ሆኖም ግን በአገራችን ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ሁሉ ከነዳጅ ዋጋ ንረት ጋር አይያያዝም፡፡

መንግሥት የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ ሊሰራቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ፡፡ መጀመሪያ ከዓለም የነዳጅ ዋጋ ንረት ጋር ተያይዘው በአገራችን የሚከሰቱት የኑሮ ውድነቶችን በተገቢ ጥረት አስደግፎ ለሕዝብ ግልፅ ያድርግ፡፡ በቁጥጥር ማነስ ወይም  በነጋዴዎች ስግብግብነት ብቻ ሳይሆን ተወደደም ተጠላም በዓለም የሚታይ ችግር በእኛ አገርም መታየቱ በግልፅ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብም ግልፅ ይሆንለታል፡፡ መንግሥትም ከአቅሙ በላይ ነውና አይወቀስበትም፡፡

ሁለተኛ፣ ራሱ መንግሥት በፖሊሲው ምክንያት የተከሰቱ የኑሮ ውድነቶችን ይመርመር፡፡ ሱር ታክስ ያስከተለው የኑሮ ውድነት እንዳለም በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ በቅንጦት እቃዎች ሱር ታክስ ቢጣል ተቃውሞ የለንም፡፡ ገቢው ለልማት ይፈለጋልና፡፡ ነገር ግን የቅንጦት እቃ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ይሁን፡፡ ይለይ፡፡ በኒዶ ወተት ላይ ሱር ታክስ ተጨምሯል፡፡ ኒዶ ወተት የቅንጦት ዕቃ አለመሆኑን ለመረዳት ግን ባለሙያ መሆንን አይጠይቅም፡፡ መንግሥት የሱር ታክስ ፖሊሲውን ይፈትሽ፡፡

ሦስተኛ፣  ስግብግብ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠርና ሕዝብን ከጉዳት ለመከላከል በአስፈላጊ ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን ያስቀምጥ፡፡ ነፃ ገበያ ማለት እንዳለ በሁሉም ነገር ላይ ዋጋ አለመተመን ማለት አይደለም፡፡ መሠረታዊ በሆኑ ፍጆታዎች ላይ ዋጋ መተመን ነፃ ገበያን አይፃረርምና መንግሥት ይህንን ያድርግ፡፡ ገበያ ይወስነው ተብሎ የቤንዚን ዋጋ ለነዳጅ ማደያዎች አልተተወም፡፡ መንግሥት ወሰን አስቀምጧል፡፡ በሌሎች ተፈላጊ ዕቃዎች ላይም እንደዚያ ይደረግ፡፡ ከዚያ ዋጋ በላይ የሸጠ ይቀጣ፡፡

አራተኛ፣  ምርት ይጨመር፡፡ ምርት ሲጨምር ዋጋ ይቀንሳል፡፡ የኑሮ ውድነትን ይከላከላል፡፡ የበርበሬ፣ የጤፍ፣ የስንዴ ምርት መጨመር ይቻላል፡፡ አሰራርና ፖሊሲን ማስተካከል ነው፡፡ ማበረታቻ እየሰጡ ምርት ማሳደግ ለኢትዮጵያውያን የሚሳነን እርምጃ መሆን የለበትም፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች በግሉ ዘርፍ የማይመረቱ ከሆነ መንግሥት ይጀምራቸው፡፡ ከትናንሽ የገበሬ መሬቶች በተጨማሪ ሰፋፊ ኮሜርሻል እርሻዎችም ይኑሩ፣ ይቀጥሉ፣ ይበረታቱ፡፡

አምስተኛ፣ የሸማቾች ማኅበር እንዲፈጠሩና እንዲጠነክሩ መንግሥት ድጋፍ ያድርግ፡፡ መንግሥት ብቻውን ዋጋ መቆጣጠር አይችልም፡፡ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ የኅብረተሰቡን ድጋፍ ማግኘት የሚቻለውም በተናጠል ሳይሆን በተደራጀ መልኩ ሲሆን ነው፡፡

ስድስተኛ፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ቅድመ ዝግጅትና ትንበያ ይደረግ፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ የተባለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ስለሆነ መንግሥት እየተዘጋጀ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር ሲታይ ግን ሊደረግ የሚገባው ቅድመ ዝግጅት ከአንድ መሥሪያ ቤት ኃላፊነት በላይ ነው፡፡ በርበሬ ጠፋ፣ ጤፍ  አነሰ፤ እየተባለ ኅብረተሰቡ መደናገጥ የለበትም፡፡

ሰባተኛ፣  ሥራ መፍጠርና ገቢ መጨመር ሌላው መወሰድ ያለበት እርምጃ ነው፡፡ ሥራ አጡም ሥራ ካገኘ፣ ባለአነስተኛ ገቢም ገቢው ከጨመረ በተሳካ ሁኔታ ሊቋቋመው ይችላል፡፡ ሳሎን ሊሞቅ የሚችልበት አንዱ መንገድም ገቢን በማሳደግ ነውና በድህነት ላይም ከማጭበርበር ውጭ የሆነ ገቢ ሊጨምር ይገባል፡፡

እነዚህ የጠቃቀስናቸው ነጥቦች አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ሁኔታው ይበልጥ እንድናስብበትና እንድንከታተለው የሚያስገድደን ግን የበልግ ሁኔታ ነው፡፡ እስከአሁን ድረስ መታወቅ የነበረበት የበልግ ዝናብ አልታየም፡፡

የበልግ ዝናብ ካልዘነበ ለእንስሳት የሚሆን ሳርና ለሰው የሚሆን ምግብ ይቀንሳል፡፡ ለተጨማሪ የኑሮ ውድነት እንዳረጋለን፡፡ ስለዚህ በልጉ ቀይ ካርድ እያሳየ ስለሆነ ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅት ይደረግ፡፡

ፖሊሲዎች ተአምር ይሰራሉ፡፡ በትክክለኛ ፖሊሲና ተግባር ኑሮአችንን አሻሽለን፣ አስተካክለንና ተቆጣጥረን ሳሎናችንን ማሟሟቅ እንችላለን፡፡
 
< Prev   Next >