Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow ያልተገሩ አደጋዎች
ያልተገሩ አደጋዎች Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
ማንኛውም አገር እንደ አገር ለመቀጠል በየወቅቱ የሚፈታተኑት የተለያዩ አደጋዎች እንዳሉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ከነዚህ አደጋዎች መካከል ቀኝ ገዥነት፣ የእርስ በርስ ግጭትና መበታተን፣ ሃይማኖትና የብሄር ፖለቲካ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች እነዚህ ችግሮች ሳይፈታተኑባት አልቀሩም፡፡ ፈተናዎቹ ለመፍታት የሚወሰዱ እርምጃዎች የችግሮችን ጉዳት ለመቀነስ ከተቻለም ለማጥፋት ወይም ለማባባስ ያለው ድርሻ ትልቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በቅኝ ገዢነት ለመግዛት እንዲሁም በሌሎች ስትራቴጂክ ጥቅሞች ተገፋፍተው ኢትዮጵያን ለመውረር የሚያደረጉት ሙከራዎች የኢትዮጵያ የቆዩ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ጣልያን፣ ግብፅ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ ወዘተ ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክረዋል፡፡ እነዚህ ከውጭ የመነጩ ፈተናዎች ቢሆኑም ከአገር ውስጥ የሚነሱ ችግሮች በርካቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የእርስ በርስ ግጭትና የሃይማኖት ቅራኔዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚዎች ከተደቀኑባት ከባድ ፈተናዎች መካከል አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ የተወገዱ ቢሆንም አብዛኛዎቹ አሁንም የሚያሰጉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለእርስ በርስ ግጭት መንስኤ ሆኖ የቆየው የብሄር ፖለቲካ አሁንም ዕልባት ያገኘ አይመስለኝም፡፡ እንዲሁም በአገሪቱ የሃይማኖት ግጭት በታሪክ ትልቅ ስጋት ያሳደረ ባይሆንም አንዳንድ የሃይማኖትና የፖለቲካ ተመራማሪዎች አስጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ችግሩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ተገቢ ቦታ አግኝቶ፣ ትኩረት ተሰጥቶት አስፈላጊ መፍትሄ ማፈላለግ እንዳለብን ይመክራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ስለኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ችግሮች ደፋርና ቁርጠኛ ምናልባትም ገለልተኛ የሆነው አስተያየት የሚሰጡት ከኢትዮጵያ ምሁራን ይልቅ የውጭ ምሁራን ናቸው፡፡ ስለአገሩ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ሊጠቁም የሚችል ምሁር ማግኘት ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ “በዚህ (የአገር ውስጥ ፖለቲካ) ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም” የሚል ኢትዮጵያ ምሁር መታየቱ ሕዝቡ ስለአገራዊ ፖለቲካና ወቅታዊ ትንተናዎች የሚያገኝበት ዕድል እየነፈገው እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ በተቃራኒው የውጭ ምሁራን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ሌሎች ትላልቅ ጉዳዮች ላይ የጥናት ጽሁፎችን ማቅረብ፣ ግልፅና የመሰላቸውን አስተያየት መስጠት የተለመደ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት በማድረግ ጥናት ከሚያቀርቡና ነፃ የሆነው ክርክር በማድረግ የመሰላቸውን አስተያየት በመስጠት ወይም አቋማቸውን በማሳወቅ ከሚታወቁት አገር (ኢትዮጵያ) ወዳጅ የውጭ ተመራማሪዎች መካከል ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንና ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤርሊክ ግንባር ቀደም ይጠቀሳሉ፡፡

ፕሮፌሰር ዶናል ሌቨን ቀደም ሲል ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የሚተነብይ ትንተና “ማሻስ promise of Ethiopia" በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጥናታዊ ፅሁፍ ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናቶች ወዳጆ ማህበርና በእስራኤል ኤምባሲ አዘጋጅነት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል በተካሄደው ውይይት ፕ/ር ሀጋይ ኤርሊክ በርካታ የታሪክ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ጉዳዮችን በማንሳት ንግግር አድርገዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሃጋይ በኢትዮጵያ ታሪክ የአገሪቱ ከፍተኛ ፈተና ያሉትና ሙሉ ለሙሉ ሊወገድ ችለዋል ያሉት የቅኝ ገዢነት ፈተና ነው፡፡ አውሮፓውያን የአፍሪካ አገሮች ለመቀራመት ባደረጉት ዘመቻ መሰረት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በባዕድ አገሮች ተሸንፈው በቅኝ ገዢነት ስር እየወደቁ በነበሩበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ አደጋ በተደጋጋሚ ጊዜ ማስወገድዋ “ትልቁና ዘላለማዊ ድል” ብለውታል፡፡ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ማንነታቸውን፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን ጠብቀው የመቆየታቸው ምስጢር በአገር ነፃነት ላይ ያካሄዱት ጦርነቶች ድል በመንሳታቸው እንደሆነ ይናገራሉ ፕሮፌሰሩ፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ሃጋይ አባባል በወቅቱ ድልዋን እያከበረች (Celebrating her victories) የነበረች ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ ለእሳቸው ኢትዮጵያ ልዩ ከሚያደርጓት መገለጫዎች ሁሉ ይህ ትልቁ ነው፡፡ በምሁሩ ዓይን ኢትዮጵያውያን በወቅቱ የነበራቸው የአመራር፣ የፖለቲካና የወታደራዊ ስልጣኔ ከአውሮፓውያን የተሻለ እንደነበር አረጋግጠዋል ማለት እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ስልጣኔና የአገር ወኔ የከፋ የውጭ ወረራም መቋቋም የቻለ እንደነበረ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሃጋይ የዚህ "The challenge of Independence" በማለት የሚጠሩት “የኢትዮጵያ የወቅቱ ትልቁ ፈተና የመመከት ምስጢር ራስ አሉላ ናቸው” ብለዋል፡፡

"Ras Allula and the Scramble for Africa”." በሚል የምርምር መፅሀፋቸው ላይ እንደጠቆሙት ራስ አሉላ ከውጭ ወራሪዎች ጋር ባደረጉዋቸው ከ10 በላይ ጦርነቶች ድል የሆኑበት ወቅት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ራስ አሉላ ግብፃውያን፣ ማህዲስቶችና፣ ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረር ባደረጉት ተከታታይና ተደጋጋሚ ሙከራዎች በብቃት መመከት ችለዋል፡፡ ተመራማሪው በአውሮፓውያንና በአፍሪካውያን መካከል የድሎችን መለዋወጥ ምስጢር ብለዋቸዋል፡፡

የውጭ ወራሪዎች በብቃት በመመከት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ነፃነት ተምሳሌት የሆኑት ራስ አሉላ፣ በወቅቱ በተደረጉት ጦርነቶች ሀሉ የሀበሻ ጦር የበላይነት ለማረጋገጥ የበቁት ብቸኛ አፍሪካዊ ጄኔራል እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

ለራስ አሉላ ልዩ ፍቅር እንዳላቸው የሚናገሩት ፕ/ር ሃጋይ፣ ራስ አሉላ የጦር መሪ ብቻ ሳይሆኑ በአስተዳደርም ችሎታቸውም የታወቁ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ ከጦር ጄነራልነታቸው በፍትህ አሰጣጥ፣ አስተዳደርና በእኩልነት እምነታቸው የሚያደንቃቸው የአካባቢው ሕዝብ እንዲህ ሲል በትግርኛ ቋንቋ እንደገጠመላቸው ያስታውሳሉ፡፡
“ፍትሒ ከም አሉላ
 ፅደቂ ከም ላሊበላ
 ጣፍ ከም ተከላ” የሃብኩም፡፡
ይሄም “ፍትህ እንደ አሉላ
   ፅድቅ እንደ ላሊበላ
 ጤፍ እንደ ተከላ (አካባቢ) ይስጣችሁ ለማለት ነው፡፡    

በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የመረብ ምላሽ (የአሁኑ ኤርትራ) ገዢ እንደመኖራቸው መጠን ራስ አሉላ ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ጋር እንዲጋፈጡ ግድ እንደሆናቸው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሃጋይ፣ በአሁኗ አስመራ ከተማ ውስጥ ከ15”000 በላይ ወታደሮች የሰፈሩበት ወታደራዊ ካምፕ እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር አባባል፣ አስመራ የተቆረቆረችው በዚሁ ወቅት በራስ አሉላ መሆኑ ነው፡፡ በፍትህ አሰጣጣቸው እጅግ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ራስ አሉላ፣ ወታደራቸው ለጦርነት የክተት አዋጅ የሚጠሩበት ወቅት ወታደሩና የአካባቢው ነዋሪ በስራ ወቅት እንዳይሆን ጥንቃቄ በማድረግ፣ ወታደሩ ለሚሰጠው ወታደራዊ አገልግሎት ተገቢ ደመወዝ በመክፈል በመኖሩ የሕዝብ ተቀባይነታቸው እጅግ ከፍተኛ እንደነበርና ዘመናዊ ሰው እንደነበሩ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

በምሁሩ ዓይን በዓድዋ ድልም የራስ አሉላ ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሰጡት ወታደራዊ አመራር ባሻገር ከዚያ በፊት በተከታታይ በተለይ ደግሞ በዶግዓሊ ድል በመንሳታቸው ለጣልያንኖች ከፍተኛ የስነ ልቦና ስጋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ንግግር፣ ጣሊያኖች ራስ አሉላን እንደ ሰይጣን ነበር የሚፈሩዋቸው፣ የአሉላን ስም ሲሰሙ ይደነግጡ ነበር ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ራስ አሉላ በኤርትራውያንና በኢትዮጵያውያን ዓይን መነፀር የተለያዩ ናቸው፡፡ የህግሐኤ አባላት ነፃነታቸውን አንደተቀዳጁ ዶግዓሊ ላይ የነበረው የራስ አሉላ ሃውልት አውድመውታል፡፡ አሁንም አንዳንድ ኤርትራውያን ምሁራንና ፖለቲከኞች ራስ አሉላን የሐበሻ ቅኝ ገዢ አድርገው ነው የሚቆጥሩዋቸው፡፡ ሀማሲየኖች በእኚህ አስመራን የቆረቆሩ ጀግና ጀኔራል ላይ ያላቸው ጥላቻ ምሁሩ አሳዝኗቸዋል፡፡ “የኢትዮጵዊያን አሉላና የኤርትራውያን አሉላ የተለያዩ ናቸው” ብለዋል፡፡    

ፕሮፌሰር ሃጋይ ያነሱት ሌላ ነጥብ በአሁኑ ወቅት ያለው “የኢትዮጵያ አደጋን” በተመለከተ ነው፡፡ የፖለቲካ ስርዓት ይልቅ ኢትዮጵያን የሚያሰጋ የሃይማኖት ፀብ ጉዳይ እንደሆነ በንግግራቸው ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች በብሄር ፖለቲካ ዙሪያ ብቻ ተጣብቀዋል” የሚሉት ፕሮፌሰር ሃጋይ፣ የሃይማኖት ጉዳይ ችላ መባሉ የሚያስከትለው አደጋ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

በቅድሚያ ግን በብሄር የተመሰረተው የወቅቱ ፌዴራሊዝም ለአብዛኛው ሰው አንገብጋቢ የሆነበት ምክንያት ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ በአንድ የማንነት መስመር የተመሰረተች ኢትዮጵያ፣ ደርግ ከሚገባው በላይ በመጫኑ ሂደቱ ተሸንፈዋል የሚለት ፕሮፌሰር ሃጋይ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ምሁራን የመጡት ይህንን የአንድ ማንነት ከሚደግፉት ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንደዚያ ዓይነት አለመሆኗ ሂደቱ ሊቃወሙት ችለዋል” በማለት የዚሁ ምንጭ ግን አወንታዊ አመለካከትና ለአገር ህልውና በማሰብ እንጂ ክፋት አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም መፍትሄው እነዚህ የተለያዩ ወገኖች በመወያየት ልዩነታቸውን ማጥበብ ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት አስመልክተው ፕሮፌሰሩ ሲናገሩ ኤትራዊያን በነፍጥ ነፃነታቸውን ያገኙ እንደሆነ ጠቅሰው ኢትዮጵያ ኤርትራን በርካታ ግዚያት አጥታታለች ብለዋል፡፡ ወደፉት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራት የሚችለው ግንኙነት የፌዴራሊዝም ዓይነት ሊሆን እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ከሆነ ሌላው ጭብጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሃይማኖቶች ግንኙነት ነው፡፡ በተለይ በእስልምናና በክርስትና ሃይማኖት መሀል ስላለው ያሁን ግንኙነትና ወደፊት ምን ሊከሰት እንደሚችል በመተገመት መፍትሄ ያሏቸውን ሃሳቦች ተንትነዋል፡፡ በዚህ ንግግራቸው ኢትዮጵያ የ”ክርስቲያን ደሴት” በሚል የተሳሳተ እይታ የተነሳ ኢትዮጵያ የክርስቲያኖች ብቻ አድርጎ የማየቱ ሁኔታ ሥር ሰዶ የቆየ እንደነበር ገልፀው ይህ ደግሞ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል መቃቃር እየፈጠረ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ እርሳቸው ገለፃ በአገራቱ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉ ሙስሊሞች የአክራሪዎች መጠቀሚያ የሚሆኑበት ዕድል የሰፋ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ሃጋይ፣ ፈጣን የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት እንደ መፍትሄ ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች መሀከል ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ የሆነ ውክልና በመንግሥት ውስጥ መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አክራሪዎች ክፍተት እንደሚያገኙና ጫፍ የነካ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ለዚህም አንዳንድ ምልክቶች እየታየ እንደሆነም በማዐከሉ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ጫፍ የነካ ጥያቄ ያሉት አንዳንድ አክራሪ ሙስሊሞች ከአልቃኢዳና ሌሎች ጽንፈኞች ጋር ትስስር በመፍጠር “ኢስላማዊት ኢትዮጵያ” የመፍጠር ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ነው፡፡ ባጠቃላይ መንግሥት የአክራሪዎችን አካሄድና ነቅቶ መጠበቅና የመፍትሄ ርምጃ መውሰድ አለበት፡፡  

ከዚህ ትንታኔያቸው ምሁሩ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች በሶስት ከፍለው ያዩ ሲሆን እነሱም አክራሪ፣ ወግ አጥባቂ፣ እና ለዘብተኛ የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የለዘብተኞች ቁጥር እንደሚበዛ ገልፀው፣ ተገቢው እርምጃና መፍትሄ ካልተወሰደ አክራሪዎቹ ሌሎቹ ላይ ጫና በማሳደር የነሱን አመለካከት ሊጭኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >