Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow “ተቋማት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተጽዕኖ...
“ተቋማት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተጽዕኖ... Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
“ተቋማት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ አንድ እርምጃ መሄድ ነው”

አቶ ደረሰ ጌታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶስዮሎጂ ትምህርት ክፍል የፖለቲካ ሶስዮሎጂ መምህር ናቸው፡፡ በፖለቲካ ተቋማት ምንነትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ እንዲሁም ተያያዥነት ባላቸው ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሪፖርተራችን ሔኖክ ሥዩም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ተቋም ምን ማለት ነው?

አቶ ደረሰ፡-
የፖለቲካ ተቋም ከማለታችን በፊት በመጀመሪያ ተቋም ራሱ ምን ማለት ነው የሚለውን ብንመልስ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥነ-ማኅበረሰብ ወይም ሶሽዮሎጂ የሚባለው የጥናት መስክ እንደሚያስገነዝበን አንድን ማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ከሚያሰኙት ነገሮች ዋናዎቹ ተቋማት ናቸው፡፡ እነሱም ቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የኢኮኖሚ ተቋማት እና የፖለቲካ ተቋማት ናቸው፡፡

የፖለቲካ ተቋማት ምንድን ናቸው ብለን ስንጠይቅ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሥርዓትን ለማስፈን እና የተፃፉም ሆኑ ያልተፃፉ ህግጋትን ለማስፈፀም ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የፖለቲካ ተቋማት ሲኖሩ ሕግና ሥርዓትን የማስፈን ሚና የሚጫወቱ ናቸው ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡-እነኚህ የፖለቲካ ተቋማት ለአንድ ማኅበረሰብ የፖለቲካ ዕድገት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

አቶ ደረሰ፡-
የመንግሥት የስልጣን ቅርጽ ወይም ክፍፍል እና የፖለቲካ ዕሳቤ ወይም ፍልስፍና በሌሎች ማኅበረሰብ ተቋማት ይወሰናል፡፡ የቤተሰብ፣ የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ እና የትምህርት ተቋማት በአንድ አገር ፖለቲካ ላይ ዓብይ ተጽዕኖ አላቸው፡፡ ስለ ፖለቲካና የፖለቲካ ሂደት ስናወራ ከእነዚህ ተቋማት ነጥለን ማውራት አንችልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ተቋማት በተራቸው ለኅብረተሰቡ የሚያደርጉት ነገር አለ፡፡ ይህ ማለት የፖለቲካ ተቋማት የሌሎች ማኅበረሰባዊ ተቋማት ድምር ውጤት ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውም ሌሎች ተቋማት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ፖለቲካ በቤተሰብ፣ በሃይማኖት፣ በትምህርት እና በኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ተቋማት በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት የሚኖራቸው ሚና ምንድን ነው? ሊበራል ዴሞክራሲ እንደ ብቸኛ የዴሞክራሲ ዓይነት መውሰድና ለተግባራዊነቱም የመንቀሳቀስ ነገር በብዙ አገሮች ይታያልና የአፍሪካ አገራት ከዚህ አንፃር ተቋሞቻቸውን እንዴት ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ?

አቶ ደረሰ፡-
ሊበራል ዴሞክራሲ በ1989 ከሶቭየት ካምፕ እና ከበርሊን ግንብ መፍረስ በኋላ የአለማችን ብቸኛ የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራም ሆኗል፡፡ ቀንደኛ የሊበራል ዴሞክራሲ ደጋፊዎች ቀኝ አክራሪዎች ከሊበራል ዴሞክራሲ የተሻለ ሌላ ርዕዮተ ዓለም የለም እያሉ የትንቢት ያህል መናገር ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነን ፍራንሲስ ፋኩያማ የተባለ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር “ዘ ኢንድ ኦፍ ሂስትሪ ኤንድ ዘ ላስት ማን” የሚል መጽሀፍ በ1990ዎቹ አውጥቶ ነበር፡፡ መጽሀፉ በዋነኝነት የሚያነሳው የፖለቲካ ተቋማት ዕድገት የመጨረሻው ነጥብ ሊበራል ዴሞክራሲ መሆኑን ነው፡፡

ሊበራል ዴሞክራሲ መነሻው ከፈረንሳይ ሲሆን ዋና ዋና እሳቤዎቹም የሚያጠነጥኑት በግለሰብኝነት ላይ ነው፡፡ የግለሰብ ነፃነት እና መብት በመሳሰሉት ማለት ነው፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ጥሩም ሆነ ጥሩ ያልሆኑ ገጽታዎች አሉት፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ይህንን በአውሮፓ ወይም በምዕራባውያን የወጣ የዴሞክራሲና የርዕዮተ ዓለም አመለካከት በሌላው ዓለም ላይ በጥቅሉ መጫን በጣም ያስቸግራል፡፡ የሚያስቸግርበት  ምክንያት የፖለቲካ ተቋማት ባህሪ በሌሎች የማኅበረሰብ ተቋማት ባህሪ የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የካፒታሊስት የኢኮኖሚ ሥርዓት ባልዳበረበት፣ ሰዎች የፖለቲካ ምርጫቸውን በሚደግፉት የርዕዮተ ዓለም ወይም መደብ በማያስተጋቡበት፣ የፖለቲካ ዕሳቤዎች በትክክል ባልለዩበት ሁኔታ ሊበራል ዴሞክራሲን ማስፈን በጣም ይከብዳል፡፡ በምዕራቡ ዓለም ለምሳሌ ቀኝ ጫፍ፣ መሃል ቀኝ፣ ግራ ጫፍ እና መሃል ግራ በማለት የፖለቲካ ዕሳቤዎቻቸውን ያንፀባርቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሚታወቅ አይደለም፡፡ በአፍሪካ የመደብ ሳይሆን የብሄር እና የጎሣ አመለካከትና ስሜት በጣም ጨምሮ እናያለን፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ይመቸናል ብለው ፖለቲካቸውን በዚያው የቃኙ እንደ ኬንያ አይነት አገሮች በቅርቡ እንዳየነው ምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይሆን የጎሣ እና የብሔር ምርጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ “ህ” is no more an election, it is an Ethnic ሰስቃቋበቋ” ብሔርተኝነት ለምን በአፍሪካ ውስጥ ይጎላል ብንል ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሊበራል ዴሞክራሲ በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ እንደማይሰራ ትንሹ ማሳያ ነው፡፡ አገራት እንደ ማኅበረሰባቸው ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ ተቋማቸውን ማስተካከልና መቃኘት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የቱ ይቀድማል? ዴሞክራሲያዊ ባህልና ፖለቲካ ወይስ የፖለቲካ ተቋማት፡፡ የዴሞክራሲ ባህል የፖለቲካ ተቋማትን ዴሞክራሲያዊ ያደርጋል ወይስ የፖለቲካ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ባህልን ይገነባሉ?

አቶ ደረሰ፡-
ባህልና ተቋማትን ነጣጥሎ ማየቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ተቋም ራሱ ባህል የምንለው ነገር ነው፡፡ የእኛ ማኅበረሰብ ተቋም የሚለውን ቃል አሳክሮ ነው የሚያውቀው፡፡ ተቋም ማለት ቢሮክራሲ ማለት አይደለም፡፡ ተቋማት የእሴቶችና የደንቦች ጥንቅር ናቸው፡፡ ተቋም አይዳሰስም አይጨበጥም፡፡ ተቋማት ድርጅቶች አይደሉም፡፡ ባህል ደግሞ የተቋማት ስብስብ ነው፡፡ ባህልን ከተቋማት ለይቶ ማየት አይቻልም፡፡ በዚህ መሠረት ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ባህል ይገነባሉ ወይስ ዴሞክራሲያዊ ባህሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ያመጣሉ የሚለው ጥያቄ የእንቁላል እና የጫጩት ዓይነት ጥያቄ ነው፡፡ ሁለቱም ለዴሞክራሲ ግንባታ በእኩል መጠን አስፈላጊ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲ አለ የሚያሰኙትን ተቋማት ለምሳሌ የምርጫ ቦርድ ከመንግሥትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ አንድ እርምጃ መሄድ ነው፡፡ ተቋማትን ነፃ የማድረግና የማጠናከር ሥራ መሥራት ወደፊት ለምናስበው የተሻለ ዴሞክራሲ መፍትሄ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን የምናደርገው ግን ሰዎች በዴሞክራሲ ሲያምኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲን የምንፈልገው ዛሬ ፋሽን ስለሆነ ወይም ስሙ ስለሚጣፍጥ አይደለም ወይም ፈረንጆች ስለሚወዱት አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ካሉት የፖለቲካ አሰራር ዘይቤዎች በአሁኑ ሰዓት የሚመራውን ሰው የሚመርጥ ማኅበረሰብ የሚሰጠን የፖለቲካ ሥርዓት ስለሆነ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚመነጨው ከህዝቡ ነው፡፡ የህዝብ ሉዓላዊነት የሚባለው ማለት ነው፡፡ በዴሞክራሲ መሪዎች ተጠያቂ ናቸው፡፡ እድሜ ልክ ለመምራት ማንም የስልጣን ኮንትራት ወይም መብት የሰጣቸው የለም፡፡ ጊዜያቸው ሲደርስ ይወርዳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ዴሞክራሲ ስልጣን ለመገደብ የተሻለ የፖለቲካ ዘይቤ ነው፡፡

ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም ብሎ የሚያምን ዜጋ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ምንም አይነት ተነሳሽነት አይኖረውም፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ፀሐፊዎች ለምሳሌ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን እንዳሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል “ወንድነት” ያጠቃዋል፡፡ ሁሌም የእኔ ይበልጣል ማለት ደግሞ ለዴሞክራሲ አይመችም፡፡ ይህ ልማድ ባለበት የዴሞክራሲ ተቋማት በፈለገው መጠን ቢስፋፋ ትርጉም አይሰጡም፡፡ ከዚህ አንፃር መቀየር ያለበት የፖለቲካ ባህላችን ነው የሚሉት ይህ ከሆነ ባህልን እንዴት ነው መቀየር የሚቻለው?

አቶ ደረሰ፡-
በጥያቄው መንፈስ ባህል የሚለውን ቃል የእያንዳንዱ ግለሰብ እምነት እንበለው፡፡ ተቋማትን ደግሞ ቅርጽ እናድርጋቸው እንደ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድ እና ፍርድ ቤት የመሳሰሉት፡፡ በዚህ መሠረት ካየነው የእያንዳንዱ ግለሰብ አመለካከት መለወጥ አለበት፤ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል ብሎ ማመን አለበት፡፡ ልጆቹ አብረውት ምሳ እንዲበሉ የማይፈቅድ፣ ሲናገሩ ዝም በሉ የሚል፣ ሲያጠፉ መደብደብ የሚወድ፣ ሚስቱን የማያመሰግን የቤት አባወራን አገር ብንሰጠው እንዴት አድርጎ ነው የሚመራው? እንዴት ዴሞክራት ይሆናል? ተማሪዎቹ በጥያቄ መምህሩ የተናገረውን ነገር ሲቃወሙት የሚያኮርፍና የሚቆጣ፣ ለሚወዱት “ኤ” ለሚጠሉት “ዲ” እና “ኤፍ” የሚሰጥ አምባገነን መምህር ነገ በፓርቲ ወይም በግለሰብ ደረጃ ቢወዳደር እንዴት ዴሞክራት ይሆናል? ሠርቶ ለመንግሥት ግብር ከፍሎ የሚያገኘውን ትርፍ ለልማት ከማዋል ይልቅ እያጭበረበረ ባሌስትራውን ወርቅ ነው እያለ በመስገብገብ መክበር የሚፈልግ ነጋዴ እንዴት አድርጎ ነው ዴሞክራት የሚሆነው? እነዚህን አብነቶች የማነሳልህ እያንዳንዱ ግለሰብ የእነዚህ ማኅበረሰባዊ ተቋማትና ባህል ውጤት ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ ተቋማት በሙሉ መለወጥ አለባቸው የሚባለው፡፡

ጥያቄው እነኚህ ተቋማት እንዴት ይለወጣሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ ዋናውና ትልቁ አንድን ማኅበረሰብ ሊሞግት የሚችል ተቋም ትምህርት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከፋሽስት ወረራ በኋላ ባሉት 30 ዓመታት ውስጥ ትምህርት በኢትዮጵያ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ተማሪዎች ፖለቲካ፣ ሶሽዮሎጂ፣ ኢኮኖሚክስ ወዘተ. ሲማሩ፣ የአፍሪካን እና የዓለምን ሁኔታ ሲቃኙ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ያረጀ፣ ያፈጀ፣ መለወጥ ያለበት መሆኑን ማመን ጀመሩ፡፡ ዛሬ “ያ ትውልድ” እየተባለ የሚነገርለት ትውልድ እንደዚህ አይነት የለውጥ አመለካከት ያዳበረው በትምህርት ነው፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ ምን አይነት ትምህርት የሚለው ነው ወሳኙ ጉዳይ፡፡ ትምህርት የወሰድናቸው ኮርሶች ብዛት ወይም የሰበሰብናቸው ወረቀቶች ብዛት አይደለም፡፡ ትምህርት የባህሪና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚችል መሆን አለበት፡፡ የተለወጠውም የተማረ ሰው ሌሎችን የሚለውጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከትምህርት የምናገኘው የአመክንዮ አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገሮችን በስሜት፣ በጭፍን ወይም በቲፎዞ መመዘን አያስፈልግም፡፡ ይህን የምንቀይረው ደግሞ በትምህርት ነው፡፡ በጥቅሉ ት/ቤቶች ለባህል ለውጥ ወሳኝ ናቸው ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ የባህል ለውጥ ለማምጣት ረዥም ጉዞ መጓዝ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- በብዙ የአፍሪካ አገራት እየተሞከረ ያለው የዴሞክራሲ ግንባታ እየተሳካ አይደለም፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ለምሳሌ ምርጫዎች የግጭት ምክንያት እየሆኑ ነው፤ ከዚህ ተነስተው የምዕራባውያኑ ሊበራል ዴሞክራሲ ለእኛ የፖለቲካ ባህል የሚመች አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ከሆነ ለእኛ የሚሆን የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት አንችልም?


አቶ ደረሰ፡-
እንችላለን፡፡ ግን አንድ በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ምዕራባውያኑም አንዳንድ አፍሪካውያንም ስለ አፍሪካ መንግሥታት ሲጽፉ የተለያየ ስያሜዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አስተኔ መንግሥት (ቆበሮቋሽ-ቋ”ሮ”ስ”፣ ድኩም መንግሥት (weak ቋ”ሮ”ስ”፣ ያንድ ሰው መንግሥት (strong man state) ይሏቸዋል፡፡ ከዚህ ተነስተን በአፍሪካ ውስጥ መንግሥት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ አለወይ የሚለው ራሱ ትልቅ የጥናት ጥያቄ ሆኗል፡፡ ይህ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ  ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ትተን ማለት ነው፡፡ በሱዳን ዳርፉር የሚገኝ ዛርጋ የሚባል ጎሣ አለ፡፡ የቻዱ ፕሬዚዳንት ሁሴን ሀብሬ የዚህ ጎሣ አባል ናቸው፡፡ ካርቱም የእሳቸውን ተቃዋሚዎች ትደግፋለች፡፡ እሳቸው በበኩላቸው የሱዳንን ተቃዋሚዎች ሲደግፉ ይታያሉ፡፡ የአንድ ጎሳ አባላት በሁለት ዓለም አቀፍ ድንበር ውስጥ በተለያዩ ሁለት መንግሥታት እየተደገፉ ይዋጋሉ ማለት ነው፡፡ ይህን ምን አመጣው ያልክ እንደሆነ ባለፈው የቻድ አማጽያን ወደ አራት መቶ ኪሎ ሜትር በአንድ ቀን ሄደው ነው ከሱዳን ድንበር ኢንጀሚና የደረሱት፡፡ የሚያግዳቸው አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ከተማው ሲደርሱ የፕሬዚዳንቱ የግል ጠባቂዎችና አንዳንድ የውጭ መንግሥታት እሳቸውን የሚወዱ የሞት ሽረት አድርገው ነው የሰውየው መንግሥት የተረፈው፡፡ የሚገርመው ነገር ያን ያህል ሰፊ መሬት ያለምንም እንቅፋት በአንድ ቀን ሲቆጣጠሩት እውነት ቻድ ውስጥ መንግሥት አለ ወይ ያሰኛል፡፡ እዚሁ ቻድ ውስጥ ሌላ የተደረገ አስገራሚ ነገር ነበር፡፡ የመጀመሪያው የቻድ መሪ ባልባዬ ለምሳሌ ከዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ የሆነው መገናኛ ብዙሃን (ሚዲያ) የተጠቀሙበት መንገድ በጣም የሚገርም ነበር፡፡ የቻድ ህዝብ እንዳያምጽባቸው በብሄራዊ ሬዲዮ “ዘ ቮይስ ኦፍ አንሲስተርስ” የሚባል ፕሮግራም ነበራቸው፡፡ ይህ ፕሮግራም ሙታን እየተነሱ እገሌን ታዘዙት እያሉ ለልጅ ልጆቻቸው የሚናገሩበት ነው፡፡ እንዲህ አይነት መሳቂያ የሆኑ መሪዎች እንዴት ነው ዴሞክራሲን የሚያመጡት ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ሌሎች መሪዎች ደግሞ ሙልጭ አድርገው ዘርፈው አገርን በአጥንት ያስቀሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኮንጎ ውስጥ ኪንሻሳ እና ኪሳንጋኒ በሚባሉት ሁለቱ የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች መካከል የአስፓልት መንገድ እንኳን የለም፡፡ የኮንጎ መንግሥት ከኪንሻሳ አስራ አምስት ኪሎ ሜትር በኋላ የለም፡፡ አገሩ እንዳለ በአማጽያን የተያዘ ነው፡፡ የጋምቢያው መሪ ያህያ ጃሚ የሚባሉት አሁን ከመሪነት አልፈው ፈዋሽ ሆኛለሁ ብለው ሐኪም ቤት ከፍተው በሽተኞችን ውሃ ሲረጩ ነው የሚውሉት፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት መሪዎች እያሉ ምን አይነት ዴሞክራሲ ያስፈልጋል ብለን ነው፡፡ የምንጠይቀው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ እነ ጋዳፊ ዓይነቶቹ የአፍሪካን አገራት ሁሉ ጠቅልለው ለመምራት ትልቅ ህልም ያላቸው ናቸው፡፡ ቀስ በሉ ሲባሉ ጥለናችሁ እንሄዳለን ወደ ሜድትራኒያን ፊታችንን እናዞራለን ወደ አረቡ ዓለም ፊታችንን እናዞራለን የሚሉ ናቸው፡፡ እነኝህን ይዘን ነው ምን አይነት ዴሞክራሲ እያልን የምናስበው?  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶቻችንን እንዴት ነው ለዴሞክራሲ ግንባታ ግብዓትነት ልንጠቀምባቸው የምንችለው?

አቶ ደረሰ፡-
ዘመናዊ የመንግሥት ሞዴልና አሰራር ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የመጣ አዲስ አስተሳሰብ ነው፡፡ አሁን ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምትተዳደርበት “ህቃ”ስቈቃሮ”ሽቄቃሮቁ world ቄቈሳስቈ” በአገራት (States) የተመሰረተ ነው፡፡ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የመንግሥት አስተዳደር ዘይቤዎች እና ሌሎች ባህላዊ ተቋማት ቅድመ ዘመናዊነት ናቸው፡፡ ቅድመ ዘመናዊነት የሚለውን ቃል ግን በጥንቃቄ ማየት አለብን፡፡ እነዚህ ቅድመ ዘመናዊ ተቋማት ከዘመናዊዎቹ ያነሱ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ዘመናዊ የመንግሥት ቅርጽና አሰራር ከመጣ በኋላ ራሱ ባህላዊዎቹ ተቋማት አልጠፉም፣ አሉ፡፡ ነገር ግን ያጧቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕዝብን በማስተዳደር፣ ግብር በመሰብሰብ፣ ወታደር በማሰልጠን፣ በደህንነት ጉዳይ ላይ ባህላዊዎቹ ተቋማት አሁን እየሰሩ አይደሉም፡፡ በምትኩ በግለሰቦች፣ በማኅበረሰቦች መሃከል ያሉ ግጭቶችን ለምሳሌ በግጦሽ መሬት ሊሆን ይችላል፣ በደን ላይ ያሉትን ግጭቶች በማስወገድና በመፍታት ላይ በመሳሰሉት ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆነዋል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ችግሮች መፍቻ በጣም አመቺ እና ውጤታማ ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ቅድመ-ዘመናዊ (ባህላዊ) ተቋማትን ለዴሞክራሲ ግንባታ እንደ ግብዓት መጠቀም እንችላለን፡፡ በአካባቢ አስተዳደር ደረጃ በጣም ይጠቅማሉ፡፡ ስልጣንን ወደ ታች ለማውረድ ኅብረተሰቡን መሠረት ላደረገ የልማት ተሳትፎ ለመሳሰሉት ጥሩ መሳሪያ እና ግብዓት መሆን ይችላሉ፡፡ ሊረዱና ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሌሎች የመንግሥት አካላትም መኖር አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት የመቆጣጠር አቅሙ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች እንደ ምርጫ ቦርድ አይነቱ የፖለቲካ ተቋም ገለልተኛ አይደለም እያሉ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ተቋም ገለልተኝነት እንዴት ነው ሊረጋገጥ የሚችለው?

አቶ ደረሰ፡-
ሕገ መንግስቱ ወይም ሌላ ሕግ ስለ ምርጫ ቦርድ አሰያየም ምን እንደሚል በትክክል አላውቅም፡፡ ነገር ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊዎች ተሰብስበው የሚስማሙበት ገለልተኛ እገሌ የሚባል ሰው የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ቢሆን፤ ቦርዱ ውስጥ አባል የሚሆኑት እነማን ናቸው በሚለውም ገዢው ፓርቲም ሌሎችም የጋራ መስማማት ላይ መድረስ ካልቻሉ እና መተማመን ከሌላቸው የሌሎች ፓርቲዎች ቅሬታ እና ስሞታ ሁሌም ይኖራል፡፡ ትልቁ የገለልተኝነት መመዘኛ የሚሆነን የምርጫ ውጤት ነው፡፡ ሁልጊዜ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ አንድ ፓርቲ እያሸነፈ ባለበት ሁኔታ ለተመልካችም ለዜጋም የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ፡፡ ቅሬታው ትክክል ነው ባይ ነኝ፡፡ በሌላ በኩል ፓርላማ የሚገቡት ተመራጮች ቁጥር ብቻ ወሳኝ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ተስፋ የእያንዳንዱ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊነት ነው፡፡ ይህ ሁሌ ይዘነጋል፡፡ ኢህአዴግ በውስጡ ምን ያህል ዴሞክራሲ አለ? ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባል ከእነ ሌሊን የተወሰደ የፓርቲው ሃሳብ ያንተ ሃሳብ ነው፤ ብትስማማም ባትስማማም የፓርቲውን ሃሳብ ማራመድ አለብህ የሚል የተለያዩ ሃሳቦችን አራምዶ ወደ ፓርላማ መምጣት እንደ ድካም እንደ መከፋፈል የሚያይ ግራ ዘመም የሆነ ቅኝት ያለው ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ያህል ለአገሪቱ የሚጠቅም ሃሳብ፣ የፓርቲውን የመንግሥት ስልጣን ጥያቄው ውስጥ የማይጥል ሃሳብ ተቃዋሚዎች ቢያመጡም አንድም የኢህአዴግ የፓርላማ አባል ለድጋፍ እጁን አያወጣም፡፡ እነሱ እጃቸውን የሚያወጡት ለራሳቸው ድርጅት ብቻና ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ ተቃዋሚ በሚባሉት ፓርቲዎችም ቢሆን አብዛኛዎቹ በአንድ ግለሰብ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ ሱቅ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አይመስሉም፡፡ የሚከራከሩ፣ ፖሊሲ የሚያወጡ፣ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው በቅርጹ የተነደፈ፣ ሕዝብ የሚቀሰቅሱ፣ የሚያደራጁ አይደሉም፡፡ ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችም የሚሰሩት ፖለቲካ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፈን ምርጫን ብቻ ማየት የለብንም፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ከዚያም በላይ ነው፡፡ እዚህ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹና መሪዎቻቸው ዴሞክራሲያዊ ናቸው ወይ የሚሰብኩንን ያደርጉታል ወይ ብሎ መጠየቅና መመርመር ያስፈልጋል፡፡
 
< Prev   Next >