Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow ብልጥ ለብልጥ
ብልጥ ለብልጥ Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
“በዱሮ ዘመናት በአንድ መንደር ውስጥ ከአንድ አባት ከአንድ እናት የተወለዱ እህትና ወንድም ባንድነት እየተጋገዙ ይኖሩ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ እህቲቱ ባል አገባች፡፡ ወንድምዬው ብቻውን መኖር አቃተው፡፡ እህቱ ዘንድ ሄዶ ደባል ሆነ፡፡ ሁለት ዓመታት አለፉ፡፡ ወንድምዬው የግል ሥራውን እየሰራ እህቲቱ ባሏንና ወንድሟን እያገለገለች በመከያው ሴት ልጅ ወለደች፡፡
ወንድምዬውም የሙያ ሥራውን እየሰራ የሚያገኘውን አንዳንድ አሞሌ እህቱ ዘንድ በማስቀመጥ ብዙ እንደሆነ አወቀ፡፡ በወለድ ሊያበድረው መፈለጉንም ለእህቱ ነገራት፡፡ ወንድምዬው አንድ ቀን ጧት ይነሳና አሞሌው ወደ ነበረበት ጐታ ሄዶ ቢመለከት በቦታው ድንጋይ ተሞልቶበት አገኘ፡፡ ተደናግጦ እህቱ ዘንድ ሄዶ አሞሌው ወደ ድንጋይ ተለውጦ እንዳገኘው ነገራት፡፡ ሞኝ ነህና አሞሌ ብዙ ጊዜ ሲቆይ ወደ ድንጋይነት መለወጡን አታውቅም ብላ ትመልስለታለች እሷም፡፡ ያዝናል፣ ይተክዛል፣ ጥርጣሬ ይገባዋል፡፡ በርግጥ ወደ ድንጋይ መለወጡንም ለማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡

ጥቂት ቀናት ካወጣ ካወረደ በኋላ ወደ ጫካ ሄዶ ዝንጀሮ ይገድላል፡፡ ከዚያም እቤት አምጥቶ የዝንጆሮውን ሬሳ የእህቱ ልጅ ተኝታበት እነበረው መደብ ላይ አስተኝቶ ልጅቷን ሩቅ ቦታ ወስዶ ይደብቃታል፡፡ እናቲቱ ልጄ ካሁን አሁን ትነሳለች እያለች ብትጠባበቅ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ይጠፋል፡፡ ወደ መደቡ ጠጋ ትላለች፡፡ ገለጥ አድርጋም ብትመለከታት ወደ ዝንጀሮነት ተለውጣ ታገኛታለች፡፡ ከመጠን በላይ ትደነግጣለች፡፡ አይኖቿንም ልታምን ያቅታታል፡፡ የጐረቤት እርዳታ ልትሻ ሮጣ ትወጣለች፡፡ ካንዲት ጓደኛዋ ጋር ትመለሳለች፡፡ ጓደኛዋ ግን የሆነውን ባየች ጊዜ የበለጠ ትደነግጣለች፡፡ ውርጅብኝ ነው ትላታለች፤ መላ ካልተበጀለት እስከ መጨረሻው ስም የሚበክል፡፡ ሰው ሳይሰማ ሞተች ብሎ መቅበሩ የሚሻል መሆኑንም ታማክራታለች፡፡ እንደ መከረቻትም ደህና አድርጋ በጨርቅ ጠቅልላ ቁቁ በማለት ለአካባቢው ጐረቤት ጭንቅና ድንጋጤዋን ታሰማለች፡፡ ጐረቤት ይሰበሰባል፡፡ ልቅሶ ይጀመራል፡፡ አልፎ አልፎም የሀዘን ግጥም መወራወር-
እህት- ወይ ዘንድሮ! ወይ ዘንድሮ!
      ልጅቷ ሆነች ዝንጀሮ
ወንድም- አወይ ጉባይ! አወይ ጉባይ!
        አሞሌው ሆነ ድንጋይ!
እህት-  አሞሌው አለ ባዲስ ጐታ
       የልጄን ነገር እንዴታ?
ወንድም- አሞሌው ካለ ባዲስ ጐታ
        ልጅቷም አለች ካጐቷ!
የየራሳቸውን ተንኮል ያወጡታል፡፡ እሷም ልጅዋን፣ እሱም አሞሌውን ያገኛሉ.......”

(ዳኛው ወርቁ፣ የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ፣ 1985)


እርካታ

እየቀጠነ ሄደ እየቀጠነ
ጭብጥ እየመጠነ
ውፍረቱ፣
እየተቀረደደ ቅርፊቱ
እየሰለለ ክርክራቱ
ግንድ ንጣቱ፡፡
ቀቅ-ቀቅ-ቀቅ!
እና ው-ድ-ድቅ!
ዛፍ ግርስስ! - ተገረሰሰ
ሣር - ቅጠሉን ደመሰሰ!
እና ቆሞ ያየው ጀመር
ደገፍ ያለው ደገፍ
ምሣሩን
እየጠራረገ ግንባሩን፡፡

(ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ውስጠት፣)

ከጐንጥ ተውኔት

“አንደኛ - ካሁን በፊት ለማንም መቀነቷን ፈትታ የማታውቅ ማለትም ክብረ-ንፅህና ያላት፣
ሁለተኛ - የወገቧ ውፍረት ከወንድ ልጅ እቅፍ ሞልቶ የማይተርፍ፣
ሦስተኛ - ቁመቷ ከኔ ከጐንጥ በረደድ ቁመት ያልዘለገ፣
አራተኛ - እኔ ባሏ ከሥራ ውዬ ስገባ ፈገግታ በማሳየትና ከተቻለም ጉንጬን በመሳም የምትቀበለኝ፣
አምስተኛ - በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ ልብስ አቀያይራ መልበስ ልማድ ያላደረገች፣
ስድስተኛ - ከተቻለ ጥርሶቿ ፍንጭት የሆኑና ጉንጮቿም ላይ ድንብል ያለባቸው ቢሆኑ፣
ሰባተኛ - ከጉልበት በላይ ያጠረ ቀሚስ በመልበስ ጭኗን ለአላፊ ለአግዳሚው እያስመረቀች መሄድ ልማድ ያላደረገች፣
ስምንተኛ - የኔን አባወራነት አምና የምትቀበልና ትዕዛዜን በሙሉ ያለማቅማማት ለመፈፀም ፈቃደኛ የሆነች፣
ዘጠነኛ - ያለሠርግና ያለጥሎሽ ከቤቴ ድረስ ሰተት ብላ ለመግባት ፈቃደኛ ሆና የተገኘች”
አሥረኛ - “ማንኛውንም የቤት ዕቃ ባል ገዝቶ ይጠብቀኝ” የሚል ሰባራ ሰንካላ ትዕዛዝ ከመስጠት ይልቅ ፣በጋራ ገንዘባችን እንግዛ፣ የማለት በጐ አስተሳሰብ ያላት፣
አሥራ አንደኛ - የአስካሪ መጠጦች ምርኮኛ ያልሆነች፣
አሥራ ሁለተኛ - ቁንጅናዋን በማሳመር ጊዜዋን ጉልበቷንና ገንዘቧን የማታባክን፣
አሥራ ሦስተኛ - ወሬ ማነፍነፍ ከሚወዱ የሴት ወይዛዝርት ጋር በምንም ታምር ጓደኝነት የማትገጥም፡፡

(ፋንታሁን እንግዳ፣ የተውኔት ድርሰት አፃፃፍ ዘዴ፣ 1992)

መወድስ

መዓተ ሥላሴ ዘኮነ አረጋዌ ዕድሜ
ድኅረ እማየ አይኅ መፅአ እመ ኢክህለ ቁረተ
በምድረ ገሞራ ተረክበ እንዘ ይስሕን እሳተ፣
ወአመ ተጸውዐ ለበሊዕ
ውስተ ቤተ ሎጥ ዘቀርበ ምሕረት
እመ ለስሐ ጣዕመ ዝንቱ
ለተወክፎ ጼው ሰአለ ወአማኅፀነ ብእሲተ፡፡
መዓትሂ አረጋዊ በጊዜ ሰአለ ዘንተ
ብዙኅ ያኅዝን ወያቴክዝ ዓለማተ፤
እምድኅረ ውእቱ ፈትሐ በምድረ ሰናዖር ቤተ
ቅድመ ሎጥ ጸላኢሁ እስመ ተዋረደ ወተትሕተ፡፡

ትርጉም

የእድሜሽ ሽማግሌ የሆነ የስላሴ ቁጣ
ከጥፋት ውሃ ከወጣ በሁዋላ ቅዝቃዜን ባይችል
እሳትን እየሞቀ በገሞራ ምድር ተገኘ፤
በሎጥ ቤት ውስጥ የቀረበ
ምህረትንም ለመብላት በተጠራ ጊዜ
የዚሁ ጣዕም ቢያልጥ (አልጫ ቢሆን)
ጨው ለመቀበል ለምኖ ሴትን አማጠነ፡፡
ሽማግሌ ቁጣም ይህን በለመነ ጊዜ
ብዙውን ያሳዝናል አለሞችንም ያስተክዛል፤
እሱ በሰናኦር ምድር ቤት ከፈታ በሁዋላ
በጠላቱ ሎጥ ፊት ተዋርዷልና፡፡

ምስጢር

ገላውን የታጠበ ሽማግሌ ከመታጠቢያ ቤት ሲወጣ የተሰማውን ቅዝቃዜ ለማስወገድ እሳት እንደሚሞቅ የስላሴ ቁጣ በሰብአ ትካት የጥፋት ውሃን ካዘነበ በሁዋላ በገሞራና በሰዶም እሳትን አዘነበ፡፡ ደግሞ ለግብዣ የተጠራ ሽማግሌ ምግቡ ጨው ሲያንሰው ተጨማሪ ጨው እንደሚጠይቅ የስላሴ ቁጣም ለሎጥ ይቅርታን ሲያደርግ የሎጥን ሚስት የጨው ሀውልት አደረገ፡፡ ከዚህም ሌላ ሽማግሌ ቤት ሲፈታ እንደሚዋረድ የስላሴ ቁጣ በሰናኦር ምድር የተሰራውን ህንፃ ማፍረሱንና መመዝበሩን ቋንቋውንም መለወጡን ባለቅኔው አመስጥረዋል፡፡

(የግእዝ ቅኔዎች፣ የስነ ጥበብ ቅርስ፣ 1980)


ገራገር


ቻይናዊቷ የጓደኛዋን ጡት አስቀነሰች

ቻይናዊቷ ወይዘሮ የወንድ ጓደኛዋ ጡት ትልቅ በመሆኑ የሷን ጡቶች አሳንሶ እያሳየባት ስለሆነ የጡቱን መጠን እንዲያስቀንስ አስገደደችው፡፡

ዘየዋ ፊንግ የተባለችው ይህችው ቻይናዊት ጓደኛዋ ዥንግ ይህን ካላደረገ ግንኙነቷን እንደምታቋርጥ አስጠንቅቃዋለች፡፡

5 ጫማ ከ7 ኢንች ርዝመት ያለውና 95.25 ኪ.ግ የሚመዝነው ዥንግ ከመንገድ ላይ ስትሄድ ሰው ሁሉ የሚያየው የእሱ ጡት በመሆኑ ጓደኛው በዚህ ሀፍረት እንደሚሰማት ብዙ ጊዜ.. እንደምትነግረው፣ የእሱን ጡት ከእሷ ጋራ እያነፃፀረች እንደምትነዘንዘው ተናግሯል፡፡

የቀዶ ሕክምናውን ያደረጉበት የቾንግኪንግ ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ዶክተሮች 200 ሚ.ሊ ስብ ከጡቱ እንዳስወገዱለት ለቾንግኪንግ የቢዝነስ ዜና አስታውቀዋል፡፡

የኩላሊት ለውጡ ባህሪዋን ቀየረባት

የኩላሊት ለውጥ የተደረገላት ሴት ከህክምናው በኋላ ሙሉ እሷነቷን እንዳጣች ተናገረች፡፡ ኩላሊቱን የለገሳት የ59 ዓመቱ አዛውንት “እኔውሪዝም” በተባለ በሽታ የሞተ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የእርሱን ባህርይ እንደወረሰች ተናግራለች፡፡

“ከሕክምናው በኋላ ነጭናጫና ተናዳጅ መሆኔን ልጄ እየነገረኝ ነው” ያለችው ሚስስ ጆንሰን የምታነባቸው መጻሕፍትም በአዲሱ ባህሪዋ ምክንያት መቀየራቸውንም አስታውቃለች፡፡

በአሜሪካ ያሉ ተመራማሪዎች እንዲህ ዓይነት ነገር እንደሚያጋጥም ለምሳሌ የሰባት ዓመቷ ሕፃን በሰው ከተገደለ ሰው ተወስዶ ከተገጠመላት ልብ በኋላ የተገደለች እየመሰላት ትቃዥ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው በሚለብሱትን የሚቀጣ ሕግ

የፍሎሪዳ ስቴት ሴኔት የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሱሪያቸውን ከፍ አድርገው እንዲታጠቁ የሚያስገድድ ሕግ ሊያወጣ ነው፡፡

ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው የሚታጠቁ ተማሪዎች መቀጣት እንዳለባቸው የሚደነግግ ረቂቅ ሕግ በሕግ አውጪው መውጣቱንና የተወካዮች ምክር ቤት ካሳለፈው ሕግ ሆኖ እንደሚፀድቅ ተገልጿል፡፡

የውስጥ ሱሪያቸውን እስኪያሳይ ድረስ እስከ ታች ድረስ ዝቅ አድርገው በሚለብሱ ተማሪዎች ላይ ቅጣት የሚያስጥለው ህግ በተለያዩ ከተሞች የወጣ ሲሆን ፍሎሪዳም እነሱን እየተቀላቀለች ነው፡፡ የሕጉ ደጋፊዎች፣ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ የሚለብሷቸውን ልብሶች ሥርዓት ያላቸው እንደሆኑ ቤተሰብም መከታተል እንዳለበት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

66 ኪሎ ዓሣ በእጅ

በናይጄሪያ በተዘጋጀው የዓሣ ማጥመድ ውድድር ቤለ ሃኩባ የተባለ የ48 ዓመት ጐልማሳ 66 ኪ.ግ የሚመዝን ዓሣ በሁለት ቀላል መረቦች በመታገዝ በእጁ ያዘ፡፡

ውድድሩ 17,000 ፓውንድ እንደሚያስገኝም ታውቋል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ የዓሣው ክብደት ሰውየውን የሚያህል ነው ብሏል፡፡ በናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛት ኬባኪ በተደረገው በዚሁ ውድድር ከ20,000 በላይ ዓሣ አጥማጆች መሳተፋቸውንም ቢቢሲ አመልክቷል፡፡

ያኩቡ እንዳለው ከ30 ጊዜ ሙከራ በኋላ የአሁኑን ሲያሸንፍ የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህ ትልቁ ዓሣ “ጊዋን ሩዋ” ወይም የውሃ ውስጥ ዝሆን ተብሎ ተሰይሟል፡፡
 
< Prev   Next >