Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow “ደንበኞቻችን የሚፈልጉትን ካሟላን...
“ደንበኞቻችን የሚፈልጉትን ካሟላን... Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
Image“ደንበኞቻችን የሚፈልጉትን ካሟላን ውድድር ቢኖርም አንሰጋም”

አቶ አሰፋ ጉያ

አቶ አሰፋ ጉያ ባለፉት 2ዐ ዓመታት በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት ድርጅቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ማገልገል ከጀመሩ በኋላ ዓመታዊ ገቢውን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደጉ የመጡና ለዚህም አስተዋፅኦቸው በሠራተኞቻቸው የተሸለሙ “ውጤታማ” ሥራ አስኪያጅ ለመባል በቅተዋል፡፡ ከድርጅቱ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬው አበበ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከተመሠረተ 43 ዓመት ሞልቶታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጤት እያገኘ መጥቷል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡
- ድርጅታችን በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ድርጅታችን ቀደም ሲል በዓመት ከ60 ወይም ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አያገኝም ነበር፡፡ ከሶስት ዓመት ወዲህ ግን 90 ሚሊዮን፣ ባለፈው ዓመት 110 ሚሊዮን ብር፣ ዘንድሮ ከ110 እስከ 120 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዷል፡፡ በየዓመቱ ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት እያሳየ ነው የመጣው፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ስድስት ወራት 57 ሚሊዮን ብር ከሽያጭ ለማግኘት አቅዶ 67.7 ሚሊዮን (ከዕቅድ በላይ 19 በመቶ) አሳክተናል፡፡ ካለፈው ዓመት በ33 በመቶ የተሻለ ገቢ አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የተሻለ ውጤት እየተገኘ የመጣበት ምስጢር ምንድነው?

አቶ አሰፋ፡
- ባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ልናገኝ የቻልነው የተለያዩ ጥናቶችን አድርገን በመንቀሳቀሳችን ነው፡፡ የሽያጭ አውታሮችን አስፋፍተናል፡፡ አዳዲስ ምርቶችን ለሽያጭ አቅርበናል፡፡ አንዳንድ የሪፎርም ሥራዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ኤክስፖርትን አስፋፍተናል፡፡ ሠራተኛው/ ማኔጅመንቱ እና የሥራ አመራር ቦርዱ በቅንጅት በመሥራታችን ውጤታማ ልንሆን ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከስያሜው ለመረዳት እንደሚቻለው የቱሪስት ንግድ እንደመሆኑ፣ የቱሪስት ንግዱን ለማስፋፋት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ አሰፋ፡-
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡ ይኸን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመናል፡፡ ድርጅቱ ሥራውን ለማስፋፋት በማቀድ በኤርፖርት ባለን ከቀረጥ ነፃ መደብር ቦታ ላይ ትልቅ የገበያ ማዕከል በማዘጋጀት የተሽከርካሪ፣ የቤት ዕቃዎች፣ የኮምፒውተር ዕቃዎችን ለመሸጥ አስበናል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ስብሰባ የሚካሄድባት ሀገር ስለሆነች ለባለመብቶች ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን በብዛት በማቅረብ የቀረጥ ነፃ ንግድን የማስፋፋት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይኸም ድርጅታችን ካከበረው የሚሌኒየም በዓል ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጳጉሜ 3 ቀን 1999 ዓ.ም በቦሌ ኤርፖርት ለግንባታው የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡

አሁን እየሠራን ያለነው ለቱሪስቶች መረጃ የሚሰጡ ብሮሸሮችን ማዘጋጀት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የቱሪስቶች መመሪያ (handbook) አዘጋጅተን አሠራጭተናል፡፡ ዘንድሮም ብሮሸሮች አዘጋጅተን እያሠራጨን ነው፡፡ በተለያዩ ቻናሎች በመጠቀም ቱሪስቶች ተጨባጭ መረጃ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ብዙ ጊዜ የሚታወቀው የቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን በመሸጥ ነው፡፡ ቀረጥ የሚከፈልባቸው ንግዶች ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ አሰፋ
፡- ድርጅታችን በአራት የንግድ ዘርፎች ላይ ተሰማርቷል፡፡ አንደኛው የቀረጥ ነፃ ንግድ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ፣ የተለያዩ ሸቀጦች፣ መጠጦች፣ ሲጋራና ትምባሆ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ሽቶና ቅባት፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳትና የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎችና የመሳሰሉትን ከውጪ ሀገር በማስመጣት የቀረጥ ነፃ መብት ላላቸው ዲፕሎማቶች፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች እንዲሁም ለወጪና ገቢ መንገደኞች የሽያጭ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ሌላው ቀረጥ የተከፈለባቸው ዕቃዎች በመግዛት በድል ገበያ ለኅብረተሰቡ መልሶ ይሸጣል፡፡ ሦስተኛው የዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ምርቶች ሽያጭ ንግድ ዘርፍ ነው፡፡ ድርጅቱ ባለፈው የማምረቻ ማዕከል የዕደጥበብና ሥነ ጥበብ ምርቶች በማምረትና ከሌሎች መሰል አምራቾች በመግዛት ለገበያ እናቀርባለን፡፡ በተጨማሪም የቤት የውስጥ ማስዋብ ሥራዎችን እንሠራለን ሜዳሊያዎችን እንሠራለን፡፡ በመጨረሻም የበሰሉና በከፊል የተዘጋጁ ምግቦችን ማደራጃና ማከፋፈያ ንግድ ዘርፍ አለን፡፡ በዚህ ዘርፍ የበሰሉና በከፊል የተዘጋጁ ምግቦችን እንጀራ፣ ..ዳቦ፣ የወጥ እህሎችና (የመሳሰሉትን አዘጋጅተን በተለይ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ለሆስፒታሎች፣ ለህፃናት ማሳደጊያዎች) መሰል ተቋማት እናቀርባለን፡፡ በጠቅላላው ድርጅታችን ሰባት የቀረጥ ነፃ መደብሮች፣ አምስት ቀረጥ የተከፈለባቸው ሸቀጦች ሽያጭ መደብሮች፣ 14 የዕደጥበባትና ሥነ ጥበብ መሸጫ መደብሮች፣ በምርት ማዕከላቱ ውስጥ የተለያዩ የማምረቻ መሣሪያዎች፣ ሰፋፊ የማከማቻ መጋዘኖች አደራጅቷል፡፡ የምግብ ምርቶችን ለደንበኞች ለማድረስ የሚያስችል የትራንስፖርት አቅም ፈጥሯል፡፡ በቂ የፋይናንስ አቅም ያለው ሲሆን በዓለም ታዋቂ ከሆኑ ከ200 በላይ የዕቃ አቅራቢዎች ጋር የረዥም ጊዜ መልካም ግንኙነት ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀረጥ ነፃ ንግድ ሥራ ፈቃድ ለሌሎችም ተቋማት እየተሰጠ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ውድድሩ ጠንከር እያለ መጥቷል፡፡  በአሸናፊነት ለመወጣት ምን አስባችኋል?

አቶ አሰፋ፡-
ዋናው ነገር ደንበኞቻችንን በተገቢው ሁኔታ በመያዝ፣ የሚፈልጉትን ማሟላት ከቻልን ውድድሩ ቢኖርም በጣም የሚያሰጋን ሁኔታ አይኖርም፡፡ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ዓይነት የገበያ ስልት እየተከተልን ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ንግድ (ሞል) አንዱ ነው፡፡ እኛ ለብዙ ዓመታት ሥራ ውስጥ በመቆየታችን የምናስመጣቸው ዕቃዎች በደንበኞቻችን የታወቁና ጥሩ ተአማኒነትን ያገኘንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ሠራተኞች ናቸው ያሉት?

አቶ አሰፋ፡
- በአጠቃላይ 900 ገደማ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- የሠራተኛ ዓመታዊ በዓል በቅርቡ ሲከበር በሠራተኞች ተሸልመዋል፡፡ ለምን?

አቶ አሰፋ፡
- የድርጅቱ 43ኛ ዓመትና የሠራተኞች ዓመታዊ በዓል በቅርቡ በሜታአቦ ቢራ ፋብሪካ አክብረናል፡፡ ሠራተኛው የተደሰተበት በዓል መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ከበዓሉ በኋላም ሠራተኛው የዚህ ዓይነት ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል ቀጣይ እንዲሆን ስምምነት ተፈራርሞ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በዚህ በዓል ላይ በድርጅቱ በኩል የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ አማካይነት 30 እና ከዚያ በላይ ዓመታት አገልግሎት ላላቸው በጡረታ ለተገለሉ ሠራተኞች፣ በጃፓን ኤክስፖ ላይ ለተሳተፉ ሠራተኞችና ልዩ አስተዋፅኦ ላላቸው ሁለት ሠራተኞች ሸልሟል፡፡ የድርጅቱ መሥራች ለነበሩት ለአቶ ሀብተ ስላሴ ታፈሰ የመታሰቢያ ስጦታ ተበርክቷል፡፡ በሠራተኛ ማኅበር በኩል ደግሞ ለአቶ ሀብተ ስላሴ ታፈሰ፣ ለእኔ እና ለሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢያችን ሽልማት ተበርክቷል፡፡ ከሽልማቱ በኋላም የድርጅቱ መሥራች አቶ ሀብተ ስላሴ ታፈሰ የምስጋና ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡ ለእኔ ሠራተኛ ማኅበሩ ሲሸልመኝ በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ትስስርን በማጠናከር ድርጅቱ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋፅኦ አድርገሃል ተብዬ ነው፡፡ በዚህ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ እንዴት ነበር የተመሠረተው?


አቶ አሰፋ፡
- ድርጅታችን በ1957 ዓ.ም (የዛሬ 43 ዓመት ገደማ) በአነስተኛ የገፀበረከት መደብር፣ በስድስት ሠራተኞች ሥራ መጀመሩን የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በወቅቱ ሲቋቋም የአገሪቱን ባህል፣ ቅርሶች የሚያንፀባርቅ የተለያዩ ሕትመቶችን ለቱሪስቶች ለማቅረብና የቱሪዝም መስህብ ለመፍጠር በማቀድ ነበር፡፡ በኋላም አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችን፤ እንቅስቃሴዎችን ማስተናገድ ስትጀምር የቀረጥ ነፃ ንግድ በ1959 ዓ.ም ገደማ የሚጀምርበት ሁኔታ ተመቻቸ፡፡ አንድ መጋዘን ተከፈተ፡፡ የአሁኑን ስሙ መሠረት የሆነው ተብሎ እንደገና የተቋቋመው በ1963 ዓ.ም ነበር፡፡ በ1967 የአሁኑን ስያሜ ከማግኘቱ በፊትም የተለያዩ መስሪያ ቤቶች አካል እየሆነ ሲዋቀር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሥር በመንግሥት ልማት ድርጅትነት በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡
 
< Prev   Next >