Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow የደላው ሙቅ ያኝካል
የደላው ሙቅ ያኝካል Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
Imageጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ወር በባህርዳር ተደርጎ በነበረው የአማራ ተወካዮች ጉባኤ ላይ ከአርሶ አደሩ የቀበሌና የዞን መሪዎች ጋር ተነጋግረው ነበር፡፡ ሁልጊዜ ምንዝሩ አለቃውን ሲያገኝ የሚያቀርበው የችግር ጥያቄ ቀርቦላቸው የመፍትሔ መልሶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡
 
የአማራው ክልል የሚገኙ ሕዝቦችን የሚመሩት የወረዳዎችና የዞን መሪዎች እንደ አቶ መለስ ዓይነት ከፍተኛውን የሃገሪቱን ባለሥልጣን ሲያገኙ ሊፈቷቸውና መፍትሔ ሊያገኙላቸው ያልቻሉትን የተወሳሰቡ ችግሮቻቸውን መጠየቅና መንገዱን እንዲያመላክቷቸው መጠየቅ ጥሩ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ በስንትና አጋፋሪና ከልካይ ማግኘት የማይቻለውን መሪ በግላጭ ማግኘት የውጣ ውረድ መንገዱን ያቃልላል፡፡ ጥሩ አቋራጭ መንገድ የሚሆነው ግን የሕዝቡን ስሜት ተከትሎ፣ የሕዝቡን ብሶት የሚያንፀባርቀውን ችግር ያቀረቡ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

በባህርዳሩ ጉባኤ ላይ የቀረቡት የሰሜን ሸዋና የደቡብ ጎንደር የዞን ሹማምንት ያቀረቡት ጥያቄ ግን ለዛሬው አስተያየቴ መነሻ ሆነውኛል፡፡ የሕዝባቸው የወከላቸው ወይም ይወክላቸዋል ተብሎ ተጠሪ ለሆኑበት ሕዝባቸው ችግር የማይመለከት ጥያቄ እያቀረቡ አቋራጭ መንገዳቸውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡

የሰሜን ሸዋውና የደቡብ ጎንደር የዞኖች ተወካይ በሥራቸው የሚገኙትን ወረዳዎችና ሕዝቦች ወክለው ካቀረቡት ጥያቄ ውስጥ ዋነኛ ችግር አድርገው ያቀረቡት በአንዳንድ ወረዳዎቻቸው የቴሌቪዥን ስርጭትን ሊያገኙ አለመቻላቸውን ነበር፡፡ የቴሌቪዥን ስርጭት ባለመኖሩ የገጠሩ የሰሜን ሸዋና የጎንደር ሕዝብ ከምንም በላይ የሆነ ችግር እንዳጋጠመው አድርገው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለዚህ ከፍተኛ ችግር መፍትሔ እንዲፈልጉላቸው፣ በቴሌቪዥን ስርጭት እጦት የተራበውን ሕዝብ እንዲደርስለት፣ በቴሌቪዥን እጦት ምክንያት በበሽታ የሚማቅቀውን ሕዝብ ስቃይ እንዲያቃልሉለት ሲማፀኑ መስማት ያሳዝነኛል፡፡ እንደ እኛው ሁሉ የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች የመርሐቤቴ፣ የሜዳ፣ የቡልጋ፣ የበረከት፣ የግሼ፣ የአንፃኪያና የደቡብ ጎንደር ወረዳዎችም የፎገራ የእብናት፣". ወረዳ ሕዝቦች ሰምተውት ይሆናል፡፡ አሁን ወጥሮ የያዘውን፣ የተለመደ ግብርና ሕይወቱን እንዳይመራ ቆፍድዶ የያዘውን፣ የእርዛትና የመገናኛ የጤናና የምግብ ችግር ሳይሆን በቴሌቪዥን ስርጭት ችግር እንዲቃለልለት መጠየቁን ምን ያህል እንደሚያሽሟጥጥ አረጋግጠን ለመናገር ጥናት ስላላደረግን ያስቸግረን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያን አካባቢ ለሚያውቅ ወይም እንደ አቶ መለስ በሪፖርት የሚያውቀው እንኳ ቢሆን የዞኑ ኃላፊዎች ጥያቄ የሕዝቦቹን ስሜት ሊጎዳ እንጂ ሊጠግን እንደማይችል መገመት አይከብደውም፡፡

የሰሜን ሸዋና የደቡብ ጎንደር በተለይም አንዳንድ ወረዳዎች ከማንኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች ኋላ ቀር የሆኑ መሆናቸውን ራሳቸው አቶ መለስ ያውቃሉ፡፡ አንዳንድ ወረዳዎች ሌላው ቀርቶ የክረምትና በጋ የመኪና መንገድ የላቸውም፡፡ የአንዳንዶቹ ተሰርቶላቸዋል ቢባል እንኳ የመኪና መንገድ ካገኙ ከሁለትና ሦስት ዓመት አይበልጥም፡፡

በወረዳ ደረጃ አብዛኛዎቹ ሆስፒታል የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በወረዳ ደረጃ አንድ ብቻ የሆነባቸው በርካታ ወረዳዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ተቋሞች የሌሉባቸው ወረዳ ሕዝቦች፣ የቴሌቪዥን ስርጭት ዋና ጉዳያቸው ሆኖ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት ይላሉ ብሎ መገመት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

እጅግ ተራራማና ገደላ ገደል የበዛባቸው የሸሜን ሸዋና የደቡብ ጎንደር ሕዝቦች በተከታታይ ዓመታት በደረሰባቸው የዝናብ እጥረት ወይም የአዝመራ መምከን ጉዳይ ራሳቸውን በምግብ ማስተዳደር ያልቻሉ ወረዳዎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ የክልሉ መንግሥትም ይኸንኑ አውቆ የምግብ ዋስትና ላላረጋገጡት ወረዳዎች የተለያዩ እገዛ እያደረገ መሆኑን የዞኖቹ ኃላፊዎች አያውቁትም፤ ተብሎ ሊገመት አይችልም፡፡ አቶ መለስም ቢሆን በአማራው ክልል አንዳንድ የምግብ ዋስትናቸውን ላላረጋገጡ ወረዳዎች እገዛ እንደሚደረግ ያውቃሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ያሉ  

እነዚህ ወረዳዎች የቴሌቪዥን ስርጭት አለማግኘታቸውን ቀዳሚ ጉዳያቸው አድርገው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንገሩልን ይላሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡

እንደ በረከትና ግሼ ወረዳ ዓይነቶቹ ዛሬ በአብዛኛዎች የኢትዮጵያ ወረዳ የተደረሰው የማይክሮዌቭ የስልክ ግንኙነት እንኳ የላቸውም፡፡ በዚያ ፋንታ የሚጠቀሙበት የቪ.ሳት ሳተላይት ስልክ ነው፡፡ አብዛኛዎች የደቡብ ጎንደርና የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች የመብራት አገልግሎት አያውቁም፡፡ አብዛኛዎቹ የወረዳው ከተሞች የውሃ ጥም ሊጨርሳቸው ተደርሷል፡፡ ግን ኃላፊዎቻቸው የሚናገሩት የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘት ዋነኛ ፍላጎታቸው መሆኑን ነው፡፡ የደላው ሙቅ ያኝካል የሚባለው ለእንዲህ ዓይነቱ ሥራ ነው፡፡  

ከሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ የምለውም ለዚህ ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የክልል ወረዳዎች ብቻ ሳይሆን ቀበሌዎች እየተዳረሰ ላለው የስልክና የመብራት አገልግሎት በአማራ ክልል ለሚገኙት የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ብርቅ ነው፡፡ ንፅፅሬም ከሌሎቹ ክልል ወረዳዎች ጋር እንጂ የተለየ አቅርቦት ሊደረግላቸው ይገባል ከሚል መነሻ አይደለም፡፡

የቴሌቪዥን ሥርጭት ይድረሰን የሚለው የሰሜን ሸዋና የደቡብ ጎንደር ዞን ኃላፊዎች ጥያቄ በሌላ በኩል አስቂኝ ሊሆን ይችላል፡፡ የተሟላ የመብራት አገልግሎት የሌለበት ሁኔታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሊኖር የሚችልበት መንገድ እንዴት ነው? መባልን ያስከትላል፡፡

በእርግጥ የዞኑ ተወካዮች የሚቀመጡት፣ በደብረብርሃንና በደብረታቦር ከተሞች ስለሆኑ የቴሌቪዥን ሥርጭት ወይም የመብራት አንዳንድ ጊዜ መቆራረጥ ላይመቻቸው ይችላል፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት ግን የሚመለከት አይደለም፡፡

በሁለቱም ዞኖች ያሉት በምግብ ሰብል ራሳቸውን ያልቻሉ ወረዳዎች፣ ባለፈው የመኸር ወቅት በቂ ምርት አላገኙም፡፡ ይባስ ብሎ ከጥር መጨረሻ ጀምሮ የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ በመቅረቱ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡

በበልግ ዝናቡ መቅረት እህሉን ብቻ ሳይሆን በከብቶቹ መኖር ላይ ጥርጣሬ አሳድሩዋል፡፡ በተለይ በጎች አርቢ በሆኑት የሰሜን ሸዋና የደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ከፍተኛ እልቂት ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተፈርቷል፡፡ በእንደዚህ ያለ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ያለ ሕዝብ የቴሌቪዥን ስርጭት "የነፍስ አድን" ጥያቄ ሆኖ ሲቀርብ የሚያስገምት ይሆናል፡፡ አስፈሪ ለሆነው ድርቅ የተጋለጠ ሕዝብ፣ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲኖረው የሚያሳስብለትን ኃላፊ ይወክለኛል ብሎ የሚያምን አይመስለኝም፡፡

በዚህ አስተያየቴ አርሶ አደሩ ቴሌቪዥን ማየት አስፈላጊው አይደለም፤ እንዳልሁ ተደርጎ እንዳይተረጎም ያስፈልጋል፡፡ አርሶ አደሩ የቴሌቪዥን ሥርጭት ማየቱ ሊዝናናበትና ምናልባትም ትምህርት ሊያገኝበት ይችላል፡፡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የበለጠ ማግኘት የሚቻለውን ትምህርት የመሪዎቹን ምስል ለማየት ይረዳዋል፡፡

አሁን እየተሸለሙ እንደምናያቸው ዕድገት ያገኙና ሃብት ያተረፉ ገበሬዎችም እስከ ዲሽ መትከል እንደደረሱ አይተናል፡፡ ከቴሌቪዥን ስርጭት አልፈው ወደ እርሻ ንግድ አልፈዋል፡፡ ይኸ የሚያስደስት ዕድገት ነው፡፡ ነገር የምንነጋገረው ስለእነዚህ ዓይነቶቹ ገበሬዎች አይደለም፡፡ ሃገራችን በቴሌቪዥን ሲሸለሙ ባየናቸው ዓይነት ገበሬዎች ተጥለቅልቃለች ብለን ራሳችንን ካላታለልን በቀር አሁንም የድሃው ገበሬ መቶኛ ይበልጣል፡፡

አብዛኛዎቹ የደቡብ ጎንደርና የሰሜን ሸዋ ገበሬዎች በቴሌቪዥን ሊያገኙት የሚችሉትን መረጃ በሬዲዮ ሊያገኙት ስለሚችሉ አሁን ባላቸው አቅም ቴሌቪዥን የማግኘት ቅብጠት ዋና ጥያቄያቸው ሊሆን አይችልም፡፡ መጀመሪያ መኖር ይበልጥባቸዋል፡፡ ሬዲዮ 100 ብር ባነሰ ዋጋ ለመግዛት ከቻለም በቂው ሆኖ ሳለ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ አውጥቶ የቴሌቪዥን ሳጥን ለመግዛት ትችላለህ ሲባል የብሽቀት ሳቅ መሳቁ አይቀርም፡፡ ከዚያ በፊት ክሊኒክ ሄዶ እንዲታከም የቃሬዛ ሸክም መንገድ ተቀንሶለት በአቅራቢያው መታከሚያ እንዲኖረው የሚያመለክቱለት ኃላፊዎች ቢኖሩት "ይደሰታል፡፡ ከቀበሌዎች በ6፡00 ሰዓት የእግር መንገድ በታች በሆነ ርቀት መኪና እንዲያገኝ እንዲያስቀድሙለት ይመርጣል፡፡ የመሠረታዊ ልማት የችግሮቹ መፍቻ ሊሆን የሚችለው መብራት እንዲገባለት ይመኛል፡፡ የወረዳ ከተሞች በውሃ ጥም ከማለቃቸው በፊት ደጋግሞ የሚያመለክትላቸው ሹማምንት ይፈልጋሉ፡፡ የዞንና የወረዳዎቹ ሹማምንት ችግሩን የሚያውቁ ከሆኑ የክልሉ መሪዎች ወደታች እየወረዱ ሕዝቡን አግኝተው የተቸገሩበትን ለአቶ መለስ ቢያመለክቱላቸው ይፈልጋሉ፡፡ አቶ መለስ አሁን የጀመሩትን ከሕዝብ ጋር መገናኘት ወደገበሬው ሄደው ራሱን ቢያነጋግሩት የተሻለ ይሆናል፡፡ ከማንም ጋር ቢሆን ፊት ለፊት መነጋገር ጥቅም ያለው መሆኑን በተግባር ያረጋገጡበት ጊዜ አሁን በመሆኑ ገበሬውን በተወካዩ ሳይሆን ራሱን ቢያነጋግሩት የሚፈልገውን ይነግራቸዋል፡፡  

ለነገሩ በአካባቢው ኖረው የሕዝቡን ፍላጎት ያውቁታል ከሚባሉት ተመራጮች ይልቅ፣ አቶ መለስ ስለአካባቢዎቹ የበለጠ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ለሕዝቡ ስሜት የበለጠ ቅርበት ወይም የተሻለ መረጃ ያላቸው ይመስላሉ፡፡

ለጠያቂዎቹ በሰጡት መልስ የቴሌቪዥን ስርጭት ወደወረዳዎች ለማዳረስ ትኩረት ያልሰጡት ገበሬው ከሬዲዮ በላይ አልፎ ቴሌቪዥን በመጠየቅ ደረጃ ደርሷል፤ ብለው ስላልገመቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ገበሬው የበለጠ ትምህርት ቤት ጤና ጣቢያ ቢቋቋምለት የሚመርጥ ነው ብለው ስለገመቱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ግምታቸው ትክክል ነው፡፡

"ለወደፊቱ ግን" ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ፍላጎቱ በዚህ ደረጃ ከደረሰ በቀጣዩ በጀት ተይዞ ጥያቄው እንደሚሟላ ተናግረዋል፡፡

ይሄ አነጋገራቸው ለዞንና ለወረዳ መሪዎች የሰጡት አግቦኛ መልስ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ የነዋሪው ፍላጎት እርሳቸው እንዳሉት አለመሆኑን የዞን መሪዎች ተከራክረው ሊረቷቸው አይችሉም፡፡ ሊረቷቸው ካልቻሉ ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት ሳይሆን የራሳቸውን ስሜት እንዳንፀባረቁ ይታመናል፡፡ ተወካዮችም በዚያ መልክ ቢገባቸው ጥሩ በሆነ ነበር፡፡

ተወካዮቹ የሕዝባቸውን ስሜት እንዳላንፀባረቁ የገባቸው መለስ፣ የድርጅታቸው አባላት የሆኑት እነዚያ የዞንና የወረዳ መሪዎች በሰጧቸው መልስ እንዳይደነግጡባቸው የወደፊቱን በጀት እንደሚያስፈቅዱላቸው በመንገር እንዲበረታቱ አድርገዋል፡፡ የተናገሩት ከዚህ በላይ ካለፈና የጠየቁዋቸውን አምነውበት ከሆነ የሳቸውም መሳሳታቸው አይቀርም፡፡ ለእነዚያ ዞኖች ምግብ ጠግበው እንዲበሉ የሚያደርግ በጀት እንዲፈቅድ ቢያደርጉላቸው ምንኛ የታደሉ ይሆናሉ፡፡ ውሃ ጠጥተው እንዲያድሩ መብራት አብርተው እንዲያመሹ የሚያስችል በጀት ቢፈቀድላቸው ምስጋናቸው የትየለሌ በሆነ ነበር፡፡".

እግረ መንገዴን በአማራም ክልል ሆነ በሌሎች በልግ አብቃይ የክልል አካባቢዎች አደገኛ የድርቅ ሁኔታ እየታየ በመሆኑ ካሁኑ በግልፅ ማስጠንቀቅ ይገባል፡፡ በልማት ጀግንነት የሚሸለሙትን ብቻ እያየን ገበሬው ለዕለት ጉርስ እየተቸገረ መሆኑን አለማየት ክፋት ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ በከፍተኛ የሚያስደነግጥ መሆኑን የመንግሥትም የሚዲያዎች ሁሉ ትኩረት ሊሆን ይገባል፡፡

አቶ መለስ የኑሮ ውድነቱ ገበሬውን አይነካውም፤ የሚሉት የበልግ ዝናብ ካላገኘን ከሚመጣብን ችግር ገበሬው ለአንድ ዓመት ሊግደረደር የማይችል ከሆነ መረጃዎቻቸውን እንደገና መፈተሽ አለባቸው፡፡ የጤፍ፣ የቡናና የሌሎች የገበያ ምርቶች መወደድ ለጤፍ አምራቾቹና ለቡና አብቃዮቹ የተመቸና ለዕድገታቸው የሚጠቅም መሆኑን ብቻ በማየት 85 በመቶ የሚሆነው ገበሬ የኑሮ ውድነቱ አይነካውም፤ ማለት ስህተት ይመስለኛል፡፡

በእስካሁኑ ምርቶቻቸው በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ ገበሬዎች የበፊታቸውን እየሸጡ ወይም በብድር የሚያገኙትን ገንዘብ መሸመቻ አድርገውት ሳለ፣ የሃገራቱ ገበሬ ሁሉ የኑሮ ውድነቱ ተጎጂ አይደለም ሲባል ትክክል ነው ብሎ መቀበል ያስቸግራል፡፡ ደጋው የሃገሪቱ ክፍልና የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሰብላቸው ጠፍቶ ባለበትና ችግረኞች በሆኑበት በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ገበሬ ሆዱን ሞልቶ ልብሱን ለብሶ አትርፎና ተመችቶት እንደሚኖር ተደርጎ መናገሩ ምን ማለት ይሆን?

ለማንኛውም እንደዞን መሪዎቹ የቴሌቪዥን ቅንጦት ለማያምረው ገበሬ፣ አሁን ከአንዣበበበት አደጋ ቶሎ መታደግ የሚቻልበት መንገድ በፍጥነት ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዝናብ አንጋጦ በሚያመርት ማህበረሰብ ውስጥ ዝናብ ሲጠፋ ማስደንገጡ አይቀርም፡፡  
ሃብታሙ በቀለ
 
< Prev   Next >