Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
(በቤተሰብ ሰርግ ተገኝተዋል፡፡ ፊታቸውን አሳይተው ድግሱ ከተካሄደበት ትልቁ ሆቴል ውስጥ ወዳለው ባር ሄደዋል፡፡ አንድ የሚያውቃቸው ሰው አግኝተው ማውራት ጀመሩ)
- ስለ ወርቅ መጭበርበር አልሰሙም ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በወርቅ ዙሪያ ችግር እንዳለማ ሰምቻለሁ፡፡ ያጭበረበሩት ሰዎች ግን ናይጄሪያዊያን ይሁኑ ሻዕቢያ አልገባኝም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የምን ናይጄሪያ፣ የምን ሻዕቢያ እነ እንትና እኮ ናቸው ተጠርጥረው የታሰሩት፡፡
- እነ ማን?
- አንዴ ያስታውሳሉ ፎቅ ሲመረቅ የተገናኘንበት ቦታ?
- አዎን አስታውሳለሁ፤ በክብር እንግድነት ጠርቶኝ ነበር፡፡
- እሱ ሰውዬ አንዱ ነው፡፡
- ባለ ፎቁ?
- አዎን እሱ ራሱ፡፡
- ትቀልዳለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ምን እቀልዳለሁ፣ ተቀለደብኝ እንጂ፡፡
- እሱ ሰውዬ አሁን ነው ሃብታም የሆነው አይደል?
- አሁን እንጂ አሁን አሁን በኢሕአዴግ ጊዜ፡፡
- እሱ ወርቅ አጭበረበረ ነው የምትለኝ?
- ተራ ማጭበርበር እኮ አይደለም፡፡ ባሌስትራን ወርቅ ነው ብሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሰርቆ አገሪቷን አከሰረ፣ መሳቂያ አደረገ፡፡
- ወይ ጣጣ..
- አንድ ደህና ነጋዴ ያለ እንዳይመስልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱማ አሉ፡፡ አንድ መጥፎ ስላጋጠመ ሌላው ደህና ነጋዴ ሁሉ መሰደብ የለበትም፡፡ ሽልማት የተሰጣቸው አሉ አይደል? በኤክስፖርት ንግድ የተሸለሙ፣ በግብር መክፈል የተሸለሙ አርአያዎች አሉኮ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ነገሩን አላወቁትም፡፡
- እንዴት አላውቀውም?
- በኤክስፖርት ተሸላሚ ከሆኑት አንዱ፣ በግብር አከፋፈልም ከተሸለሙት አንዱ ናቸው በወርቅ ማጭበርበር የታሰሩት፡፡
- ወይ ጣጣ.. በል በል ምን አሰማኸኝ፡፡ ቤቴ ልሂድ ፍቀድልኝ፡፡
- ቻው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቻው፡፡

(ቤት ገብተው ከባለቤታቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ)
- ወርቅ አጭበረበሩ የተባሉት እነማን እንደሆኑ ሰማሽ?
- ኧረ ወርቅ ገደል ይግባ፡፡ ሰው የቸገረው ጨው፣ ድንችና ሎሚ ነው፡፡
- ጨው ደግሞ ምን ሆነ?
- በኪሎ ብር ከሃምሳ የነበረው አስር ብር ሆነ፡፡
- ትቀልጂያለሽ?
- አንተ ነህ የምትቀልደው፡፡ ሚኒስትር ሆነህ ነገር አለሙን አታውቅም፡፡
- እንዴት አላውቅም የጠላትን እንቅስቃሴ ቀንና ሌሊት በትኩረት እየተከታተልን ነው፡፡
- ወይ ጠላት፡፡ በዚሁ በጨው ማን እንደታሰረ አውቀሃል?
- አላውቅም
- ቢንያም፡፡
- ማነው ቢንያም?
- የባለ ሆቴሉ ልጅ በቀደም እኛ ቤት ለለቅሶ መጥቶ የነበረው፡፡
- እሱ ሃብታም አይደለም እንዴ?
- ነው እንጂ ብዙ መኪኖች አሉት፡፡
- እና በጨው ያጭበረብር ነበር ማለት ነው?
- አዎን፡፡
- ወይ ጣጣ..
- ወይ ጣጣ፣ ወይ ጣጣ፣ ወይ፣ ጣጣ አትበል ሚኒስትር ነህ፡፡ አንድ ነገር አድርግ፡፡
- ይኸው እየተለቀሙ አይደለም እንዴ?
- አዎን እየተለቀሙ ናቸው፡፡ ግን በዚህ ይለቀማሉ በዚያ ይፈለፈላሉ፡፡
- ምን አይተሽ ነው?
- የጨው አጭበርባሪ ታሰረ ሲባል ጨው ቀነሰ፡፡ ግን ጤፍ በኩንታል ሰባት መቶ ብር ደረሰ፡፡
- ሰባት መቶ?
- አዎን፡፡
- የጤፍ ነገር እንኳ አለማወቅ፣ አለመማር ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግ ራስህ ገበያ አውጥተህ ሽጥ ስላለው የገበያ ሁኔታ ባለማወቅ ገበሬው የሚያደርገው ይሆናል፡፡
- ወይ ገበሬ የአቶ ገብረማርያም ልጅኮ ነው ሲያጭበረብር የተያዘው፡፡
- ገብረ ማርያም ማን?
- ገብረማርያም እኝህ በቀደም ቤታቸው ተመለሰላቸው ያልኸኝ፡፡
- ወይ ጣ... ጣ...
- በይ በይ እንተኛ ነው፡፡

(ቢሮ ገብተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡ ከፀሐፊያቸው ጋር ያወራሉ)
- ክቡር ሚኒስትር ጉዳይ አስፈፃሚም ተላላኪም ሆኖ ይሰራ የነበረው የእኛ ሰራተኛ ትናንት ታሰረ ብለው ከቤት ደውለው ነበር፡፡
- ለምን ታሰረ?
- በጥቁር ገበያ በዶላር ምንዛሬ ይሳተፋል መሰለኝ፡፡
- እሱ ባለገንዘብ ሆኖ?
- አይደለም ክቡር ሚኒስትር ይላላካል፡፡ ኮሚሽን ይሰጠዋል፡፡
- አሁን ምን አድርጉ ነው የሚሉን?
- በእጁ አንድ ሚሊዮን ዶላር ስለተገኘ ሌላ አደጋ እንዳይደርስበት ክቡር ሚኒስትሩ ቢያስፈቱልን ብለው እናቱ ደውለው ነበር፡፡
- እጁ ላይ ያን ያህል ዶላር ተገኘ?
- አዎን፡፡
- ወይ ጣ... ጣ..
- እኔ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ውስጥ እንደማልገባ ታውቂያለሽ?
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ዛሬ ቢሮ አይገቡም ብዬ ነው የመለስኩላቸው፡፡
- እንደዚህ ዓይነት ነገር አይሰሩም አትያቸውም፡፡ በይ በይ ማን ነው ስሙ አማካሪውን ጥሪልኝ፡፡

(አማካሪው ተጠርቶ ገባ)

- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና ይስጥልኝ፡፡ እባክህ የምሰማው ወሬ ሁሉ የሚያስጠላ ስለሆነብኝ ስለፕሮጀክታችን ደህና ወሬ ካለህ ንገረኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ቆመኮ፡፡
- ለምን ይቆማል?
- ክቡር ሚኒስትር ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ የሲሚንቶ እጥረት ነው፡፡
- ለሌላው ያጥራል እንጂ እኛ ከሙገር አይደለም እንዴ የምንጠቀመው?
- የሙገር ነው ግን እሱም ሰላሳ ብር ጨምሯል፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ዛሬኮ 260 ብር ደረሰ፡፡
- ለምን?
- ሲሚንቶ ማስገባት ተከለከለ፡፡
- ወይ ጣጣ... ለምን ተከለከለ?
- ሲሚንቶ እንዲገባ ተፈቅዶ የነበረው ውጭ ገንዘብ አለኝ ለሚል ነበር፡፡ በፍራንኮ  ቫሉታ ማለት ነው፡፡
- ምን ሆነ ታዲያ?
- ከውጭ ገንዘብ ሳይኖራችው እዚህ በጥቁር ገበያ እየመነዘሩ ገንዘብ የሚልኩና የሚገዙ ሆነው ስለተገኙና የውጭ ምንዛሬውን ስላሟጠቱት ተከለከሉ፡፡
- ከዚህ በጥቁር ገበያ እየመነዘሩ ነበር ሲገዙ የነበሩት?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሕንዶች ይሆናሉ፡፡
- የምን ሕንዶች ኢትዮጵያዊያን እንጂ፡፡ እዚህ እኛ የዕቃ ግዥ ኃላፊ የነበረው በገዛ ፈቃዱ የለቀቀውን ያውቁታል?
- አዎን..
- ክቡር ሚኒስትር የእነሱ ናቸው፡፡እንዲያውም እሱ ታስሯል፡፡ ቀንደኛ ነው አሉ፡፡
- ወይ ጣጣ.. ጣጣ

(ሂድ ፀሐፊዋን ጥራልኝ)
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ትንሽ ራሴን ስላመመኝ ቤት ሄጄ ልተኛ፡፡
- እንዴ አሁንኮ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተደውሎ አስቸኳይ ስብሰባ አለ ተብሏል፡፡
- ስንት ሰዓት?
- አሁን አሁን ይምጡ ነው ያሉኝ፡፡

(ክቡር ሚኒስትሩ ከሰዓት በፊት እዚያው ስብሰባ ላይ ዋሉ፡፡ ከሰዓት በኋላ ስብሰባው ሲቀጥል የታሸገ ፖስታ ደብዳቤ ደረሳቸው፡፡ ከፍተው አነበቡት)
- ወይ ጣ... ጣ....
- ምንም አይደለም ክቡር ሚኒስትር መበርታት ነው፡፡
- መበርታትማ እበረታለሁ፡፡ ነገር ግን እኔኮ ሁሉም የሚያውቀኝ ንፁህ ሰው ነኝ፡፡
- ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ እርስዎን ሰረቁ፣ ጉቦ ተቀበሉ፣ ዋሹ የሚል አንድም ሰው የለም፡፡
- ታዲያ ለምን ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ተነስተህ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አማካሪ ትሆናለህ የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡
- እሱም ቢሆን ስለሰረቁ፣ ስለዋሹ ጉቦ ስለተቀበሉ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን አድርጌ ነው?
- መወሰን አይችልም፣ እርምጃ አይወስድም፣ ጠንካራ አቋምና እምነት የለውም ተብለው ነው፡፡
- ወይ ጣ... ጣ..
- እና አሁን ስብሰባ እገባለሁ? አልገባም? እረፍት ያድርጉ ነው ያለኝ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት እዚህ እኛ አካባቢ ሥራ ይጀምራሉ፡፡
- እሺ ቤት ልሂድ ቻው፡፡
- ደህና ይሁኑ ክቡር ሚኒስትር፡፡

(ቤታቸው ገቡ)
- ምን ሆነህ ነው ፊትህ ጠቋቆረ?

- ዛሬ ደስ አላለኝም፡፡
- የኃይሉን መታሰር ሰማህ እንዴ?
- ማን ነው ኃይሉ?
- ብሄራዊ ባንክ የሚሰራው ዘመዳችን፡፡
- አልሰማሁም ምን አደረገ ተባለ?
- አዲስ ብር አላስረከብህም፣ የሚሰራ ብር አቃጠልክ፣ ብለው ነው፡፡
- ወይ ጣ... ጣ...
- አንተ ደግሞ ሁሌ ወይ ጣጣ ነው፡፡ ምን ሆነህ ነው?
- ስራ እየቀየርኩ ነኝ፡፡
- ምን የሚሉት መቀየር?
- በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አማካሪ ሆነህ ስራ ተብያለሁ፡፡
- ታዲያ ጥሩ ነዋ፡፡ እድገት እኮ ነው፡፡
- ከሚኒስትርነት አማካሪ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መግባት እድገት ነው ብለሽ ነው?
- ማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበሩት አማካሪ ተብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋ ናቸው፡፡ እድገት ነው?
- እኔ እንጃ እስቲ እናያለን፡፡
- በቃል ነው የነገሩህ በደብዳቤ?
- ደብዳቤማ ሰጥተውኛል፡፡
- እስቲ አሳየኝ፡፡

(ተሰጣቸው አነበቡት)
- ወይ ጣ... ጣ...
- አንቺም ወይ ጣጣ ማለት ጀመርሽ ምን ሆነሽ ነው?
- ደብዳቤውን በደንብ አይተኸዋል?
- አዎን ሳነበው እድገት አይደለም፡፡
- እንዴት?
- አማካሪ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እንዲሰሩ ብቻ ነው የሚለው፡፡
- እና ምን ጎደለው?
- የጎደለውማ በሚኒስትር ደረጃ አይልም፡፡ ዝም ብሎ አማካሪ ብቻ ነው የሚለው፡፡
- እስቲ ስጭኝ እንደገና ላንብበው፡፡

(ክቡር ሚኒስትሩ ደጋግመው አነበቡት)
- እ.. አነበብከው በሚኒስትር ደረጃ አይልም?
- ወይ ጣ... ጣ...

 
< Prev   Next >