Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Tuesday
May 13th
Home arrow Sections arrow ለወጣት ታራሚዎች ተሃድሶ
ለወጣት ታራሚዎች ተሃድሶ Print E-mail
Wednesday, 19 March 2008
Image
አቶ ሞገስ አቤ
ወጣት ታራሚዎች በአፍላነት እድሜአቸው ወደ ማረሚያ ቤት ሲገቡ የመጀመሪያ አልያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ስለሚያቋርጡ፣ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው፣ ያለመዱትና አዲስ የሆነው የማረሚያ ቤት የተለያየ ሁኔታ የሚፈጥርባቸው ጫና ቀጣይ ሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ወጣት ታራሚዎች መደበኛ ትምህርትና የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ከወጣቶች ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በማስመልከት የተቋሙ ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ሞገስ አቤ እንደገለፁልን ተቋሙ በበርካታ ማረሚያ ቤቶች ከሚያከናውናቸው የእናቶችና የሕፃናት ፕሮግራሞች በተጨማሪ የወጣት ታራሚዎች ተሀድሶና መልሶ የማቋቋም ፕሮግራም ዋነኛው ነው፡፡

"ከወጣቶቹ በእድሜ ለጋ ከመሆን አንፃር በማረሚያ ቤቱ ያለውን ሁኔታ መልመድና መቀበል አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ ጊዜአቸው ይባክናል፡፡ ወጣት ጥፋተኞቹ የሚፈጠርባቸውን የስነ ልቦና ጫና ከመቀነስ፣ ማረሚያ ቤት የሚኖራቸውን ቆይታ ለመጪው ሕይወታቸው ጠቃሚ በሚሆን ተግባር ላይ እንዲያሳልፉ በማድረግ ረገድ የወጣት ጥፋተኞች የተሀድሶና የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ትልቅ ጠቀሜታ አለው..ም ብለዋል፡፡

ፕሪዝን ፌሎሺፕ በአገሪቷ ዘጠኝ ክልሎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ሞገስ በአገሪቷ በሚገኙ መቶ ሃያ ማረሚያ ቤቶች ከአንድ መቶ ሁለቱ (102) ጋር በቅርበት እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡ ወጣት ጥፋተኞች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ፣ በማረሚያ ቤት እያሉ መደበኛ ትምህርታቸውን መማር እንዲችሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገርና ከሌሎች ድጋፍ ሰጪ አጋር ድርጅቶች ጋር በአንድ ላይ በመሆን የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፣ በአገሪቱ ያለው ወጣት ጥፋተኞችን መልሶ የሚያቋቁም ማዕከል አንድ ብቻ መሆኑ ወጣቶች በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ የተረጋጋ ስነ ልቦና እንዳይኖራቸውና የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን እንዳያገኙ አድርጓል፡፡ ወጣቶች እንደፈጸሙት ጥፋት በማረሚያ ቤት የሚኖራቸው ቆይታ ስለሚለያይ ለወጣት ጥፋተኞች ሥልጠና የሚሰጠው ፍላጎታቸውን፣ የትምህርት ደረጃቸውንና የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ፕሪዝን ፌሎሺፕ በትኩረት በሚንቀሳቀስባቸው መቶ ሁለት ማረሚያ ቤቶች በሙሉ ለወጣት ጥፋተኞች የሙያ ሥልጠና ይሰጣል ማለት ባይቻልም ወጣት ጥፋተኞች የሥነተዋልዶና ሥነ ልቦና ትምህርቶችን እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

“በማረሚያ ቤቶች በሚሰጡ የወጣት ጥፋተኞች መደበኛ ትምህርት የእኛ ድርሻ የትምህርት መረጃ መሣሪያዎችን ማቅረብ ነው፡፡ የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ማድረግ፣ ድጋፍ መስጠት፣ በመደበኛ የወጣት ጥፋተኞች ትምህርት አሰጣጥ ላይ ግብአቶችን ማሟላት፣ የሙያ ስልጠናዎችን (የእንጨት ሥራ፣ ብረታብረት፣ የዘመናዊ ሽመና፣ ልብስ ዲዛይንና ስፌት) በየማረሚያ ቤቶች ያለውን የወጣት ጥፋተኞች የሙያ ስልጠና ፍላጎትና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የአሰሳ ጥናት አድርገን ወጣት ጥፋተኞቹ በተለያየ ሙያ እንዲሰለጥኑ እናደርጋለን” በማለት ተናግረዋል፡፡

ወጣት ጥፋተኞቹ የሙያ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ስልጠናውን ማግኘታቸውን የሚያሳይ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ይህ ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ በግል ወይም በተለያየ መልኩ ተደራጅተው መሥራት የሚችሉበትን መንገድ እንደሚያመቻች አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ወጣት ጥፋተኞቹ ማረሚያ ቤት የሚያመርቷቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች እዚያው ማረሚያ ቤት ውስጥ ለገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ ከሽያጭ የሚገኘው ገቢ ደግሞ በቀጣይ ለሚመረቱ ምርቶች ግብአቶች መግዣና የወጣቶቹን ሙያዊ እንቅስቃሴ ማጠናከሪያ ይውላል፡፡

በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ያሉ ወጣት ጥፋተኞችን በሙያ ስልጠናዎች እንዲሳተፉ ማስቻልን አስመልክቶም “አብዛኛውን ጊዜ ወጣት ጥፋተኞች ወደ ማረሚያ ቤት ሲገቡ የአካባቢው መቀየርና ሌሎችም ተያያዥ ሁኔታዎች የሥነልቦና ጫና ስለሚያሳድሩባቸው ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወይም የሙያ ስልጠና ለመውሰድ ፍቃደኛ አይሆኑም፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ቆይታ በኋላ ሌሎች ወጣቶችን በመመልከትና ሁኔታዎችን በማመን ፍቃደኝነት  ያሳያሉ” ብለዋል፡፡

በማረሚያ ቤት የተለያየ የሙያ ሥልጠና አግኝተው ከማረሚያ ቤት የሚወጡ ወጣት ጥፋተኞች በቀጣይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መከታተልና ያሉበትን ደረጃ ለመመልከት በተለያየ ጊዜ ማረሚያ ቤት ገብተው የሚወጡ ወጣት ጥፋተኞች ቁጥር በርካታ በመሆኑ እስከ አሁን የዚህ ዓይነቱን ክትትል ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ነገር ግን የወጣት ጥፋተኞች ተሀድሶና መልሶ ማቋቋም አላማ ወጣት ጥፋተኞች በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ ለቀጣዩ ሕይወታቸው ጠቃሚ የሚሆን ልምድና ሙያ ይዘው እንዲወጡ ማድረግ በመሆኑ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች ባሉት ፕሮግራም ኮኦርዲኔተሮች አማካይነት ከማረሚያ ቤት የሚወጡ ወጣቶችን ለመከታተልና የመነሻ ካፒታል እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቧል፡፡

በ1999 ዓ.ም ብቻ ከሰባት መቶ እስከ ስምንት መቶ የሚሆኑ ወጣት ጥፋተኞች በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች መሠልጠናቸውን የሚናገሩት አቶ ሞገስ አሠልጣኝ ወጣት ጥፋተኞች ከተለያየ ክልል ወደተለያየ ክልል በመሄድ የአሠልጣኞች የሙያ ስልጠና የሚወስዱበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቷ ያለው የወጣት ጥፋተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል አንድ ብቻ መሆኑና ወጣት ጥፋተኞች የሚታሠሩት ከአዋቂዎች ጋር አብረው በመሆኑ ይህ ሁኔታ ወጣት ጥፋተኞችን መልሶ በማቋቋም ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ከአቶ ሞገስ ገለፃ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑንም “በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደሮች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ ነን፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት እንደምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው በአማራ ክልል የተጀመረው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው” በማለት ገልፀዋል፡፡

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >