Thu02232012

Go to :English Edition

Back ርዕሰ አንቀጽ ርዕስ አንቀፅ የመንግሥት ሹመኞች ብቃት ማነስ አይምሬ የአገር በሽታ እየሆነ ነው!

የመንግሥት ሹመኞች ብቃት ማነስ አይምሬ የአገር በሽታ እየሆነ ነው!

  • PDF

ስለመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም ሹመኞች ጉድለት፣ ድክመት፣ ችግርና አቅም ማነስ ስናወራ ሁሉም አንድ ዓይነት ናቸው ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡

ሙሰኞች ባለሥልጣኖች እንዳሉ ሁሉ ንጹሃንም አሉ፡፡ ክፉዎችና ማፍያዎች እንዳሉ ሁሉ ቅንና ሃቀኞችም አሉ፡፡ አቅምና ብቃት የሌላቸው እንዳሉ ሁሉ ብቁና ንቁ ባለሥልጣናትም አሉ፡፡

እያሳሰበንና እያሰጋን እየመጣ ያለው ግን ክፉዎቹ፣ ማፍያዎቹ፣ ሙሰኞቹና ብቃተ ቢሶቹ እየበዙና በብቁዎቹ፣ ቅኖቹና ንጹሆቹ ላይ የበላይነት ወደመያዝ እያኮበኮቡ መሆናቸው ነው፡፡ መንግሥት አንድ ወጥ አይደለም፣ ኢሕአዴግ አንድ ወጥ አይደለም እያልን ስንጮህም የተራ ትንታኔ፣ ጥናትና ምርምር ጉዳይ ሆኖብን ሳይሆን በተጨባጭና በተግባር አገርን የሚጎዳ፣ ክፉና አይምሬ በሽታ ስለሆነ ነው፡፡ በሽታው ደግሞ በእነዚህ በደካሞቹና በሙሰኞቹ ምክንያት እየተዛመተ መሆኑን ስለምናይ ነው፡፡

በሙሰኝነት፣ በማፍያነት፣ በክፋት፣ በተንኮለኝነትና በአደርባይነት ምክንያት በሹመኞች እየደረሰ ያለው ጉዳት ብዙ ጊዜ የጮህንበት ጉዳይ ስለሆነ፣ ለጊዜው እዚህ መደጋገሙ ይቅርብንና ለዛሬ በሹመኞች የአቅም ማነስ ምክንያት እየደረሰ ያለው ችግር ላይ እናተኩር፡፡

ኃላፊዎች፣ ሹመኞችና ባለሥልጣኖች ብቃት የላቸውም ስንል አገር እንዲለማ፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲ ሕያው እንዲሆንና መረጋጋት እንዲፈጠር ፍላጎት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ፍላጎት ቢኖራቸውም በተግባር ላይ የሚያውሉበት አቅም የላቸውም፡፡ እውቀትም ልምድም ያንሳቸዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የአሁኑ የመንግሥት ቢሮክራሲ እየተሳከረ ይገኛል፡፡ መመርያዎችና አዋጆችም የ‹‹እርስዎም ይሞክሩት›› መድረኮች እየሆኑ ናቸው፡፡

የመሬት ሊዝ አዋጁ ሲወጣ ራሱ ብቃት ባላቸው ሰዎች የተረቀቀና የተጠና ነው ቢባልም፣ ብዙ የብቃት ማነስ ታይቶበታል፡፡ በማብራራት፣ በማስረዳትና በማረጋጋት አንፃር ሲታይም በርካታ ስብሰባዎችና በርካታ መግለጫዎች ቢሰጡም፣ ሕዝቡን የሚያረጋጋ ብቃት እስካሁን ከሹመኞች አልታየም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ትልቅና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች በጋራ ሊያጠኑት፣ ሊወያዩበትና ሊከራከሩበት በተገባ ነበር፡፡ ሲሮጡ እየተፈታ ያለው ሲሮጡ ስለታጠቁት ነው፡፡ በአረም የተሞው አድበስብሰው ስላረሱት ነው፡፡

የዋጋ ተመን ይውጣ ሲባልም የብቃት ማነስ ያስከተለው አካሄድ ነበር፡፡ በቂ ጥናት ተደርጎለት ነው የተባለው በምሁራንና በወጣቱ ትውልድ ይቅርና በአዛውንቶች ዙርያም ‹‹ቢራ አስፈላጊ ነው ተብሎ ተተምኖ ቡናን የቅንጦት ነው ብለው እንዴት ሳይተምኑት ቀሩ?›› የሚል ስላቅ ደርሶበታል፡፡ ብዙ ሳይቆይም ተመኑ ቀርቷል ተብሎ ተሰረዘ፡፡ ያን ያህል ጥናት የተደረገበት ነው ተብሎ ብዙ የተዘመረለት እንዴት በአንዴ ተሰረዘ? ሲነደፍም፣ ሲፀድቅም፣ ሲዘረዘርም የነበረው በብቃት ማነስ ነበር ማለት ነው፡፡

ቡና ኤክስፖርት ሲደረግ በጆንያ ወይስ በብትን ይሁን የሚል አጀንዳ ተነሳበትና ያልሆነ መመርያ ወጣ፡፡ በዓለም ያሉ የቡና ገዥዎችም በእኛ አካሄድ ተበሳጩ፡፡ እኛን ትተው ከኬንያ ጋር መዋዋል ጀመሩ፡፡ አደጋው መታየት ጀመረ፡፡ ትተነዋል ተባለ፡፡ ይህ ታዲያ ‹‹እርስዎም ይሞክሩት›› አይደል?

በባንኮችና በፋይናንስ ተቋሞች ዙርያ እየታየ ያለው ችግርም እንደዚሁ ብቃት የራቀውና “እርስዎም ይሞክሩት” እየመሰለ ነው፡፡ 27 ከመቶ አስቀምጡ ይባላል፡፡ በኋላ 20 ከመቶ ሆኗል ይባላሉ፡፡ ባንኮች ማበደር ሊጀምሩ ነው ይባላል፡፡ ቆይቶ ብድር የለም ይባላል፡፡ ቦንድ ግዙ፣ ኮላተራልም ይሆናል ይባላል፡፡ ትንሽ ቆይቶ ማበደር ስላቆምን በኮላተራል ማሳያዙ ይቆይ ይባላል፡፡

በባንኮች ያለ ችግርማ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡ መመርያ የሚያወጣውና የሚከታተለው ብሔራዊ ባንክ ራሱ ሌላ መሪ ብሔራዊ ባንክ የሚያስፈልገው ይመስላል፡፡ ዋናውን ሥራ የረሳ ብሔራዊ ባንክም ሆኗል፡፡

ግሽበትን መከታተል፣ ማጥናትና መፍትሄ መስጠት እንዲሁም መቆጣጠር ዋነኛው የብሔራዊ ባንክ ሥራ ነው፡፡ ግሽበት በኢትዮጵያ የታየው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ከራሱ ተነስቶ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ይቅርና ዕርምጃ ይወሰድ የሚል ማሳሰቢያ ከባለሙያዎች ሲሰጠውም፣ ‹‹ጥሪ አይቀበልም››  ነበር ምላሹ፡፡ ዓለም ያስከተለው ችግር ነው እያለ የውስጡን ችግር ማስተዋል አልቻለም፡፡ በአንዴ ግሽበቱ ሰማይ ሲደርስ የብሔራዊ ባንክ ሩጫ ወደ ትክክለኛው መፍትሔ ሳይሆን ወደ ብር ማተም ነበር የሮጠው፡፡ ተደጋጋሚ ችግር በግሽበት ዙርያ እየታየ ያለውና በግሽበት ደረጃ ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚ ቦታ ልትይዝ የቻለችውም፣ ብሔራዊ ባንክ ችግሩን ለመፍታት ብቃት ስለሚያንሰው ነው፡፡

በባንኮች አካባቢ ያለው አቅም ማነስ በብድር አሰጣጥ፣ በአሰባሰብ፣ በጨረታ አወሳሰንና ወዘተ. ዙርያ ይታያል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለው ችግርም ‹‹እግዚኦ›› የሚያሰኝ ነው፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴር ራሱ ‹‹ሕግ የማርቀቅ አቅም የለም›› ብሎ ሲናገር ለራሱ የሚያስገርም ነው፡፡ ንግግሩ በራሱ ‹‹አቅም ማነስ›› ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለስንት ዘመናት ሕግ ስታረቅና ስታፀድቅ የነበረች ናት፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ተግባር ላይ በማዋል ችግር አለባት እንጂ አሉ ከሚባሉ ሕገ መንግሥቶች አንዱን ራስዋ ተወያይታ አርቃ ያፀደቀች አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አቅም ስለጠፋ አይደለም፡፡ ሕጉን የማርቀቅ ኃላፊነትና በሞኖፖሊ የያዙት አቅም የሌላቸው ስለሆኑና አቅም ያለው ስለተገፋ ነው፡፡ በግልጽ እንነጋገርና ፍትሕ ሚኒስቴር ራሱ አቅም የሌለውና እንዲኖረው የማይፈልግ ተቋም ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ዙርያ እየታየ ያለ በሽታም ተራ በሽታ ሳይሆን መቆረጥ ያለበት የ‹‹ጋንግሪን›› በሽታ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሰሞኑን ለቴሌቪዥን ዓመታዊ ክፍያ እናስከፍላለን እያለ ነው፡፡ ድርጅቱም 27 ሚሊዮን ብር እሰበስባለሁ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱ ምን ይባላል? ፕሮግራም ለማሰራጨው አገልግሎት አስከፍላለሁ ቢል ተገቢ ነው፡፡ የሚያስከፍለውም ከተገልጋይ ጋር ተዋውሎ ነው፡፡ የተዋዋለ ይከፍለዋል፣ የማይከታተልና ያልተዋዋለ አይከፍልም፡፡ ጭራሹን በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ ግን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ራሱ በራሱ በዚህ ሳምንት በሰጠው መግለጫ፣ የማስከፍለው ለምሰጠው አገልግሎት ሳይሆን ቴሌቪዥን የተባለ ዕቃ ቤት ውስጥ በመገኘቱ ብቻ ነው  ብሏል፡፡ ለዕቃው ነው የሚያስከፍለው ማለት ነው፡፡ ለዕቃው ማለት ምን ማለት ነው? የቴሌቪዥን ጣቢያው ለአገልግሎቱ ሳይሆን ለዕቃው ነው የማስከፍለው ሲል ምን ማለቱ ነው? በስንቱ እንፈር? በስንቱ እንሸማቀቅ?

የፓርላማችን ብቃት ራሱ ሲፈተሸም አሳሳቢ ነው፡፡ ስንት የመንግሥት ባለሥልጣናት ሪፖርት ሲያቀርቡለት ተገቢ ጥያቄ መጠየቅና መልስ ማግኘት የማይችል ፓርላማ ሆኗል፡፡ ተቀልዶበት የሚሄድ ፓርላማ ሆኗል፡፡

ፓርላማ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢትዮጵያዊያን ማቋቋም ይችላሉ የሚል ዝርዝር ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ካወጣ አሥራ አምስት ዓመት አልፏል፡፡ አዋጁ ለምን ተግባር ላይ አልዋለም? ብሎ ግን ጠይቆ አያውቅም፡፡ ሕግ አውጪው ያወጣውን ሕግ አስፈጻሚው ሚኒስቴር መጥቶ ቴሌቪዥንማ አልፈቅድም ሲለው፣ ኧረ ያወጣሁትን ሕግ አንተ ማፈን አትችልም ብሎ ማንነቱን ማሳየት የማይችል ፓርላማ ነው፡፡

የመሬት ሊዝ አዋጁ ለምን ጊዜ ተወስዶ ውይይት አይደረግበትም? ለምን እንቸኩላለን? የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት እንኳ፣ መንግሥት በአስቸኳይ ስለፈለገው ነው ብሎ ይመልሳል፡፡ ፓርላማ ከመንግሥት በላይና በመንግሥት የማይታዘዝ አካል መሆኑን የሚረሳ ነው፡፡ አቅም ማነስ!!

በአቅም ማነስ ዙርያ የማስረጃና የመረጃ ብዛት እንጂ እጥረት የለም፡፡ አቅም አልባ ሹመኞች፣ አቅም ያላቸውን ሹመኞች በተገቢ ፍጥነት እንዳይሄዱ ቆልፈው እየያዙና እያዘዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም መራመድ እስኪያቅታት ድረስ በዚህ በሽታ ተቆላልፋለች፡፡ ተማሪ ብቃት ሲያንሰው ይደግማል፡፡ ባለሥልጣን አቅም ሲያንሰው ግን አገርንና ሕዝቡን ያወድማል፡፡

የማይፈታ ችግር ግን አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ካንጀት ካለቀሰ፣ መንግሥት ካንጀት ካለቀሰ ሊፈታ ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ ባለፈው የአዳማ ጉባዔው አዲስ ኃይልና ብቁ ኃይል በመተካካት እናመጣለን ብሎ ነበር፡፡ ‹‹አመጣሁ ወይ?›› ብሎ ኢሕአዴግ ራሱን ይገምግም፡፡ ካንጀት ያልቅስ፡፡ የመንግሥት ሹመኞች ብቃት ማነስ፣ አይምሬ የአገር በሽታ መሆኑን ይመን፡፡