እንኳን አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ከመንግሥት ፊት ተደቅኖ እያለ ‹‹በአበረታች››ና በተረጋጋ ሒደት ላይ ተሁኖ፣ እኔ ሁሉንም አውቃለሁ በማለት የተዘጋጋ አስተሳሰብ ይዞ ከመጓዝ ይልቅ፣ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ከጎን በማሰለፍ ጠቃሚ ሐሳብና ምክር እያገኙ መጓዝ ብልህነትንና ትክክለኛነትን የሚያሳይ ነው፡፡
ብልህ የዓለም መሪዎችና መንግሥታትም እንዲህ እያደረጉ አገርን መምራት የተለመደና ተግባራዊ ባህርይ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ ‹‹ቲንክ - ታንክ›› ቡድን ወይም ስብስብ ይሉታል፡፡ አማካሪ ቡድን ወይም ኮሚቴ መሆኑ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያም በአገራችን ውስጥም ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በሰላምና መረጋጋት መስክ፣ በኢኮኖሚው መስክ፣ በፖለቲካው መስክ፣ በማኅበራዊውና በባህላዊው መስክ በአሁኑ ጊዜ ፈታኝ ችግሮች ከበውናል፡፡ ፕሮጋንዳውን ትተን ሀቁ ይኼው ነው፡፡ አላስፈላጊ በጀትና ወጪ ሳይመደብ፣ ጊዜ ሳይባክን፣ እንቅፋትና ችግር ሳያጋጥም፣ የስም መበከልና ግድፈት ሳይደርስ ችግሮችን ለመፍታት እንዲቻል፣ መመካከርና መፍትሔ በጋራ ማፈላለግ እውነተኛ የወቅቱ ጥያቄ አይደለምን?
‹‹መንግሥት ካለ በሰማይ መንገደ አለ›› እያልን ራሳችንን ለአደጋ ከማጋለጥ ይልቅ መንግሥትና ሕዝብ ካለ፣ ባለሙያና ባለዕውቀት ካለ፣ መመካከርና መወያየት ካለ፣ እጅ ለእጅ መያያዝ ካለ፣ በመቀራረብ መንፈስ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲሳተፉ ከተደረገ፣ ‹‹…በሰማይ መንገድ አለ›› ብንል አያስተማምንም ወይ?
እስቲ በየዘርፉ ያለውን ሁኔታ እንዳስስና ለቲንክ - ታንክ አስፈላጊነት አፅንኦት እንስጥ፡፡
1. የኢኮኖሚ ዘርፉ ቲንክ - ታንክ ያስፈልገዋል
መንግሥትም አገርም ሁለት መቶ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር አለባቸው፡፡ በግሽበት በዓለም ቀዳሚውን ስፍራ እየያዝን ነው፡፡ ግዙፍ በጀት የሚጠይቁ በርካታ ዓበይትና ጠቃሚ ፕሮጀክቶችና ዕቅዶች ተነድፈዋል፤ ተጀምረዋል፡፡ የኑሮ ውድነት በጣም እየናረ ነው፡፡ ባንኮች የሚሰጡት ብድር አስተማማኝ አይደለም፡፡ የንግድ እንቅስቃሴው እየቀዘቀዘ ነው፡፡ አዳዲስ መመርያዎችና ደንቦች እየወጡ አለመረጋጋትና አለመተማመን እያስከተሉ ናቸው፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ በከፍተኛ የቀውስ ስጋት ውስጥ ነው፡፡ ቀውሱ እየባሰበትም ነው፡፡ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ብዙ ገቢ ማግኘት አለበት፡፡ ሙስና የአገራችንን ኢኮኖሚያ በአደገኛ ሁኔታ እያመሰው ነው ወዘተ፣ ወዘተ ማለት ይቻላል፡፡
በእንደዚህ ዓይነቱ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና የመንግሥት ኃላፊዎች በጋራ ቲንክ - ታንክ ፈጥረው የኢኮኖሚ ችግሩ እንዴት ይታይ? እንዴት ይፈታ? በማለት መነጋገራቸው በእውነት ለአገራችን አይጠቅምም? የመንግሥትን ችግርና ጫና አያቃልልምን? ቲንክ - ታንክ ይረዳል ይጠቅማል እንጂ፡፡ በእጅጉ!
2. የፖለቲካ ሁኔታችን ቲንክ - ታንክ ያስፈልገዋል
የፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸውን ፖለቲካ በራሳቸው ፍላጎት የሚመሩበትና የሚያንቀሳቅሱበት አካሄድ ቢኖራቸውም፣ በአጠቃላይ የአገር ፖለቲካ ምን መምሰል ይገባዋል የሚለውን ለመመካከር ቲንክ - ታንክ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ የምርጫ ሒደትን በተመለከተ መመካከርና ማሻሻያ ያስፈልገዋል፡፡ ልዩነትን ይዞ እየተቻቻሉ የመጓዝ ክህሎት በባለሙያዎች፣ በባለልምዶች፣ በዜጎች ምክክር ሊመጣ የግድ ነው፡፡ በእጅጉ ከፍተኛ የሆነ አስተዋይነትን በማስፈን በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እየተፈጠረ ያለውን መጠራጠርና መራራቅ ለማጥበብ መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የፕሬስ ነፃነት፣ የመደራጀት ነፃነት፣ ወዘተ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲከበር መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ተቋማት እንዴት እንደሚያድጉ መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዴት እንደሚሰፍን መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥትን ስህተት ለማየትና ለማሳየት፣ የተቃዋሚዎችን ስህተትና ድክመት ለማየትና ለማሳየት መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ቲንክ - ታንክ የግድ ያስፈልጋል፡፡
3. ማኅበራዊና ባህላዊ ዘርፉ ቲንክ - ታንክ ያስፈልገዋል
ራሳችንን አናታልል፡፡ በዚህ ዙሪያም ቲንክ - ታንክ ያስፈልጋል፡፡ ባህል እየተበላሸ ነው፡፡ ወጣቱ አመራር እያጣ ነው፡፡ ፆታዊ ጥቃት እየተባባሰ ነው፡፡ ባህልን፣ ቋንቋን፣ ልምድን በፍቅርና በቅንጅት አዋህዶ ለመምራት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መጠበቅ የለበትም፡፡ መርህ እንጂ ገጠመኝ አይሁን፡፡ አላስፈላጊ የሃይማኖት ግጭት አልፎ አልፎ እየተስተዋለ ነው፡፡ ሐሺሽና ዝሙት እየተስፋፋ ነው፡፡ የጉልበት ሠራተኞችን፣ ዕድሜያቸው ያልደረሱና ሌሎችን ያለ ጥበቃና ከለላ ወደ ውጭ መላኩ የባርያ ሽያጭ እየመሰለ ነው፡፡ የኑሮ ችግርና የሞራል ዝቅጠት አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የልመና ብዛቱና ዓይነቱ ኢትዮጵያችን ምን እየሆነች ነው የሚል ድንጋጤ እየፈጠረ ነው፡፡ ሥራ አጥነትና ወንጀል መወዳጀት ጀምረዋል፡፡ ኧረ ስንቱ?! ለዚህም ባለሙያ፣ ባለልምድ፣ ምሁሩና ባለሥልጣናቱ በጋራ እየተገናኙ እንዲመካከሩና መፍትሔ እንዲያስገኙ የሚያደርግ ቲንክ - ታንክ ያስፈልጋል፡፡ በአስቸኳይ!
4. የሰላም፣ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ጉዳይም ቲንክ - ታንክ ያስፈልገዋል
አሁን እየታዩ ያሉ የኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራ፣ ብልህና ብልጥ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል፡፡ ከምዕራቡና ከምሥራቁ ዓለም ጋር ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መንገድ ውጤታማ ግንኙነት መፍጠር የግድ ነው፡፡ ከክርስቲያኑም፣ ከሙስሊሙም፣ ከአይሁዱም ጋር የተቆራኘ ታሪክና ግንኙነት ስላለን በዚህ መስክ ከሁሉም ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር፣ በእኩልነት እንጂ በአሸባሪነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዳይኖርና ለመመካከር ቲንክ - ታንክ ያስፈልጋል፡፡
ለማሳያ እነዚህን ጠቃቀስን እንጂ መመካከር የሚያስፈልገው በሁሉም ዘርፎች ነው፡፡ ቲንክ - ታንክ የሚያስፈልገው ችግር ሲኖር ብቻ አይደለም፡፡ በመልካም ሒደት ላይ፣ በልማት ወቅት፣ በሰላም ጊዜና በፍትሕ ጉዳይ ጭምር ቲንክ - ታንክ ያስፈልጋል፡፡ ዓለም ስድስት በመቶ ነው የሚለውን ዕድገት ወደ አሥር በመቶ እንዴት እናሳድገው? ብሎ ለመመካከርም ቲንክ - ታንክ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን፣ ወደ የአፍሪካ ሕዝብ የኢኮኖሚ፣ የቱሪዝም፣ የቴክኖሎጂና የስፖርት ማዕከልነት እንዴት እናሸጋግራት ለማለት ቲንክ - ታንክ ያስፈልጋል፡፡
ከአሁኑ በፊትም ደጋግመን ያልነው ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይቻላል፡፡ መቶ ጊዜ ያልነውን አሁንም እየደጋገምነው ነው፡፡ ከሁሉም ዘርፍ የተውጣጣ የጋራ ቲንክ - ታንክ ቡድን ወይም በየዘርፉም ሊሆን ይችላል፡፡ የጥሪው ቁምነገር አንድ ነው፡፡
መንግሥት በአስቸኳይ በእምነትና በቅንነት ቲንክ - ታንክ ያቋቁም!!


