መነሻ ገጽ - ቢዝነስና ኢኮኖሚ - የአልማዝ መዳቡ ቱሪዝም እንዲነቃ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
07 April 2013 ተጻፈ በ 

የአልማዝ መዳቡ ቱሪዝም እንዲነቃ

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የተፈለገውን ያህል መራመድ አለመቻሉ፣  ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር ሲታይ ብዙ የሚቀረው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የሚወሳ ነው፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታየው ችግር በርካታ ቢሆንም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ግን አናሳ ሆኖ እንደሚገኝ ይታመናል፡፡ ይህንን ዘርፍ በተመለከተ፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የምክክር መድረክ ጽሕፈት ቤት ያስጠናው ጥናት እንዳመለከተው፣ የአገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የተወዳዳሪነት ዕምቅ ዕድል ያለው መሆኑ ቢታመንም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡

የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለመመልከት የሞከረው ይህ ጥናት፣ በዘርፉ የሚታዩ አሥር ያህል ችግሮችንም በዝርዝር አመላክቷል፡፡ እነዚህ ችግሮችና ተግዳሮቶች መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ያሳሰበ ነው፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት  መቻል፣ የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ እንዲያሳይ ያስቻላሉ ተብሎ እንደሚታመንም ይገልጻል፡፡ ችግሮቹን ከነመፍትሔዎቻቸው በመርመር የቀረበ ጥናት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ከእነዚህ መፍትሔዎች መካከል፣ የቱሪዝም ስትራቴጂ መቅረጽ ቀዳሚው እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፖሊሲ ቀደም ሲል ተቀርፆ እንደነበር የሚያስታውሰው ይኸው ጥናት፣ ፖሊሲውን ለማስፈፀም የሚረዱ ስትራቴጂዎች  እስካሁን አለመውጣታቸውን ይዘክራል፡፡

ስትራቴጂ ቢዘጋጅ፣ ያልተመለሱ የቱሪዝም ጥያቄዎችን በመመለስና ባለድርሻ አካላትን ለአንድ ዓላማ የማስተባበር ሚና እንደሚጫወትም ጥናቱ አስገንዝቧል፡፡ ስትራቴጂው በአንድ ወገን ተግባርን በመምራት፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ የቀረፃ ሒደቱን በአሳታፊነት በማስኬድ ሊያስከትል የሚችለውን ንቅናቄ ግምት ሰጥቶታል፡፡

ከዚህ ሌላ እንደመፍትሔ የቀረበው ነጥብ፣ የቱሪዝም ቦርድ ማቋቋምን ነው፡፡ በበርካታ አገሮች ውጤታማነቱ እንደታየው፣ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ፖሊሲም እንደሰፈረው፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ የቱሪዝም ቦርድ ቢቋቋም፣ ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚጠቅም ያትታል፡፡ በዘርፉ የሚታዩ የታክስ፣ የአገር ገጽታ፣ የቅንጅት ሥራ፣ የአቅም ግንባታና የቪዛ እንዲሁም ሌሎች ችግሮች በጥናቱ ተዳስሰዋል፡፡ ቦርዱ ለእንዲህ ዓይነት ችግሮች ሀሳብ ያቀርባል፤አፈጻጸማቸውንም ይከታተላል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ እንደሚነበበው፣ በርካታ ችግሮች ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው ባለመወያየታቸው የተነሳ ተንጠልጥለው የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሶ፣ የቱሪዝም ቦርዱ ቢቋቋም፣ ቅንጅት በመፍጠር መፍትሄ አመንጪ አካል ሊሆን እንደሚችል አስገንዝቧል፡፡

የቱሪዝም ቦርዱ በ2005 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ተቋቁሞ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራውን በይፋ ቢጀምር ተመራጭ እንደሚሆንም ጥናቱ ይገልጻል፡፡

የቱሪዝም ፈንድ መቋቋሙ ደግሞ የጋራ ሥራዎችን በመሥራት ረገድ የሚታዩ ልዩነቶችን መቅረፍ ስለመቻሉም ያራራል፡፡ የቱሪዝም ፈንድ፣ የአቅም ግንባታ፤ አገርን የማስተዋወቅ፤ብራንድ የማድረግና ሌሎችም (በጥናት የሚደረስበት) መስኮቶች ተካትተውበት፣ በቱሪዝም ቦርድ በጀት አመዳደብ መሰረት ሥራ ላይ እንዲውል ሃሳብ ቀርቧል፡፡

የግሉ ዘርፍ ለቱሪዝም ፈንድ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑም ጥናቱ አስፍሯል፡፡ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን መገምገም እንደሚገባም አሳይቷል፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ክፍተት ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ የማበረታቻዎች ፖሊሲ፣ሕግና አተገባበር እንደሆነ የሚገልጸው ይኸው ጥናት፣ ማበረታቻዎች ከማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ከቱሪዝም ስትራቴጂዎች ጋር ተቆራኝተው መታየት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ በቦታ ተራርቀው የሚገኙ የቱሪዝም ተቋማት (ሆቴል፣ ሎጅ የተከለሉ የደን ቦታዎች ወዘተ) የመሰረተ ልማት ዝርጋታቸው የሳሳ ቢሆንም፣ በውስጣቸው ያቀፉት የቱሪዝም ሃብት ግን ከፍተኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በብሔራዊ ፓርኮች አካባቢ፣ሆቴልና ሎጅ ለሚገነቡ ባለሃብቶች የሚሰጠው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እጅግም ነው፡፡ በማበረታቻ አሰጣጡ ላይ የሚታየው አፈጻጸም ወጥነት ማጣቱና የሕግ አተረጓጎም  ችግሮች፣ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ሃብታቸውን ያፈሰሱትንም ሆነ ለማፍሰስ የሚያስቡትን ባለሃብቶች መተማን አሳጥቷቸዋል፡፡ በመሆኑም፣ የቱሪዝም ማበረታቻዎች ከሚቀረጸው የቱሪዝም ስትራቴጂ አንጻር በጥልቀት መታየትና መገምገም እንደሚኖርባቸውም ጥናቱ አመላክቷል፡፡ 

ከዚህም ሌላ በውጭ አገር የኢትዮጵያን ቱሪዝም ስለማስተዋወቅ ተግባር በተመለከተ፣ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መሠራት እንደሚኖርባቸው ያሳስባል፡፡

አገሮች የቱሪዝም ሀብታቸውን ለማስተዋወቅና ከቱሪስቶች ጋር በመገናኘት ቱሪስቶችን አነቃቅተው ለመጎብኘት የሚመጡት ቁጥራቸው አንዲጨምር ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ፣ የቱሪስቶች ቢሮዎችን በውጭ አገር መክፈት ነው፡፡ ይህም ቱሪዝምን በማስፋፋት ዓበይት ስኬት ያስመዘገቡ አገሮች የተጠቀሙበት ፍቱን ዘዴ ወይም ስትራቴጂ ነው፡፡ በተለይ እነዚህ የቱሪዝም ማዕከላት ለቱሪስቱ በቀላሉ መረጃ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡

ከአፍሪካ አገሮች ውስጥ በቱሪዝም መስህብነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉትን አገሮች በምሳሌነት የጠቀሰው ይህ ጥናት፣ ኢትዮጵያ አንድም የቱሪዝም ማስፋፊያ ስትራቴጂ የሌላት መሆኑን ያሳያል፡፡ በምሳሌነት ከቀረቡት አገሮች ግብፅ 21፣ ቱኒዝያ 23፣ ደቡብ አፍሪካ 10 የሚሆኑ የቱሪዝም ቡድኖች በኬንያ እንዳላቸው አሳይቷል፡፡

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት ሙያዊ ደረጃውን ጠብቆ ለማስተዋወቅ፣ በልዩ ሁኔታ ጥረት ባለሙያዎችን በዋና ቱሪስት አመንጪ አገሮች መመደብ ግድ እንደሚል የሚያትተው ጥና፣ በአጭርና መካከለኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አማካይነት፣የቱሪዝም የቀን ተቀን ተልዕኮውን የሚያከናውን ባለሙያ ቢመደብ፣ ከወጭ አንጻር አግባብነት ይኖረዋል፡፡ አገሪቱ ለቱሪዝም የሚኖራትን የአቅርቦት አቅም ከማሻሻሉ ጎን ለጎን፣ በረዥም ጊዜም (ከ5-7 ዓመታት) የቱሪስት ቢሮዎችን በቱሪስት አመንጪ አገሮች መክፈቱ ሊሳት የማይገባው ጉዳይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

በክልልና በፌዴራል መንግሥታት መካከል ከፍተኛ የቅንጅት ጉድለት ይታያል፡፡ በተግባርም አንዱ ከሌላው ጋር ከመደጋገፍ ይልቅ ወደ መወዳዳር ያዘነበለ ግንኙነት እንዳላቸው ይታያል፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት መካከልም እንዲሁ ከፍተኛ የቅንጅት ክፍተት አለ፡፡ አስጎብኚ ባለሙያዎች፣ለትርጉምና ለገለጻ የሚያስከፍሉትን  ዋጋ፣ ራሳቸው በዘፈቀደ የሚተምኑና ከአካባቢ አካባቢ ምክንያታዊ ያልሆነ ልዩነት ያለው ሆኖ ይገኛል፡፡

የመንግሥት ኃላፊዎች በየአካባቢው ያሉ አስጎብኚ ባለሙያዎችና ተርጓሚዎች ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆኑን ቢገነዘቡም ከሥራ ፈጠራ ጋር ብቻ ስላገናኙት፣ ሳይለወጥ ለመቀጠሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የቱሪስት ሥፍራዎችንና ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚከፈለው የመግቢያና የማስጎብኛ ክፍያ ባልተጠና ሁኔታ በአካባቢው አስተዳደሮች/የእምነት ተቋማት ውሳኔ ብቻ የሚተመን በመሆኑ የተነሳ፣ በአገር ደረጃ የተቀናጀ አይደለም፡፡ በቅርቡ የላሊበላ ቅዱሳን መካናትና ሌሎች በሰሜን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት የተጣለው የሦስት እጥፍ አዲስ የክፍያ ተመን እንደጥሩ ማስረጃ ሊጠቀስ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡ ይህም አስቀድመው ለቱሪስቶች ስለክፍያው መረጃ የሰጡ የአስጎብኚ ድርጅቶችን ለኪሳራ የሚዳርግና በቀጣይም ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖረንን ተወዳዳሪነት የሚጎዳ ነው በማለት ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

የታሪክና የቅርስ ገቢ የአካባቢውን ማኀበረሰብና መንግሥትን በሚጠቅም አኳኋን መተመኑና ጥቅም ላይ መዋሉ አግባብ ቢሆንም፣ የታሪፍ መጣኔው በተፈለገ ጊዜ የሚለወጥና የሚስተካከል ከመሆኑም በላይ የገቢው ከፊል መጠን የታሪክንና የባህል ቅርሶችን በሚያድስና በሚጠቅም መልክ የሚመደብ ስለመሆኑ የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡ የቅርስና የቱሪስት ቦታዎች የጉብኝት ታሪፍ በአገር ደረጃ ተቀናብሮና ተቀናጅቶ የቱሪዝም ዘርፉን በማይጎዳ መልክ ሊተገበር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያቱ፣ ቱሪስቶች ወጪያቸው ገና ከአገራቸው ሳይነሱ ተገማች እንዲሆንላቸው ስለሚፈልጉ ነው፡፡  

 ይኸው ጥናት አገራዊ የቱሪዝም ጥራትና ብቃት ደረጃዎች አለመውጣት ወይም አለመተግበር ለዘርፉ ጉዳት ሆኖ መታየቱን ሳያመላክት አላለፈም፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም አንዱ ዋና ችግር የጥራትና የስታንዳርድ ችግር እንደሆነም የጥናት ውጤት ያመላክታል፡፡ በሆቴሎች፣ በምግብ ቤቶች፣ በቁርስ ቦታዎች፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በሌሎችም መስኮች የሚሰጡት አገልግሎቶች፣ ደረጃቸው የወረደ እንደሆነ ቱሪስቶች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በንጽህናና በሳኒቴሽን ላይ አሳሳቢ ሁኔታ ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሆቴልና የመስተንግዶ ደረጃዎችን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ላይ ከፍተኛ ጉድለት ይታያል፡፡ የኮከብ ማዕረጎችንና የተለያዩ ደረጃዎችን በማያሟሉ የቱሪዝም ተቋማትን ተከታትሎ ማረቅና እንደሁኔታው ፈቃድ እስከመንጠቅ ሊደረስ እንደሚገባም ሀሳብ ቀርቧል፡፡

የተለያዩ የቱሪዝም ደረጃዎች ሲታሰቡ፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ገና ከግንባታቸው ጀምሮ በጥንቃቄ እንዲያቅዱና አስገዳጅ ደረጃዎችን እንዲተገብሩ መታገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ግንባታቸውን ያጠናቀቁ ድርጅቶች የተጓደላበቸውን ስታንዳርድ መልሳችሁ አሟሉ ማለቱ፣ ሒደቶችን እንደገና መቀልበስን ሊጠይቅና ከፍተኛ ኪሳራ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ለባለሀብቶች ደረጃዎችን ማስተዋወቅንና ቀረብ ብሎ መርዳትን የሚጠይቁ ብዙ አጋጣሚዎች እንዳሉ መታዘብ ይቻላል ተብሏል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገነቡት ባለኮከብ ሆቴሎች፣ የአካባቢዎቹን ታሪክ፣ ወግና ባህል እንዲሁም መገልገያ ቁሳቁስ ወደ ጎን በመተው፣ በአውሮፓውያን የሥነ ሕንፃና የግንባታ ደረጃ ሆቴሎችንና ማረፊያ ቤቶችን ስለሚገነቡ ለቱሪስቱ ተገቢውን ገጽታ ይነሱታል፡፡     

የሳኒቴሽን፣ የንጽህናና የደኅንነት ደረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጰያ ከምትተችባቸው መስኮች ከፍተኛውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ የዓለም የቱሪዝም ተወዳዳሪነት ቀመርን መመልከቱ ጠቃሚ እንደሆነ ተመክሯል፡፡ በዚህ ቀመር መሠረት እ.ኤ.አ. በ2011፣ ኢትዮጵያ ከ139 አገሮች 139ኛ በመውጣት የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች፡፡ ከዚህ ባላነሰ፣ ድክመት የሚታይባቸው የአስጎብኝነትና የአስተርጓሚነት ደረጃዎች ናቸው፡፡

አገራዊ የስታትስቲክስ መረጃ ድክመት የዘርፉ ሌላው ክፍተት ነው፡፡  የኢትዮጵያ ተወዳዳሪነት የሚጎዳበት አንዱ መልክ የተሟላና ወቅቱን የጠበቀ የቱሪዝም መረጃ አለመኖሩ ነው፡፡ የቱሪስቶች ፍሰት ጥቅል አኀዝ እንኳ ትክክለኛነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡  በዘለቄታዊ መንገድ የተገነባ፣ በክልልና በፌደራል መንግሥታት መካከል የመረጃ ፍሰትን በብቃት የሚያረጋግጥ አገራዊ የቱሪዝም የመረጃ ስርዓት መዘርጋት እንደሚኖርበት በመፍትሄነት ቀርቧል፡፡ የቱሪዝም የመረጃ ሥስርዓት ብቃት በተመለከተ አሁንም የአለም የኢኮኖም ፎረም የጉዞና ቱሪዝም ተወዳዳሪነት ቀመርን ብንወስድ፣ ኢትዮጵያ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም መሠረት በ2011፤ ከ139 አገሮች በቱሪዝም መረጃ ሙሉዕነት 123ኛ ስትወጣ፡ በቱሪዝም መረጃ ወቅታዊነት ደግሞ 109ኛ ወጥታለች፡፡ጥናቱ ጠንካራ ጐን የሚላቸውንም ያሰፈረ ሲሆን በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ችግሮችንም አስቀምጧል፡፡

ከዚያ አኳያ፣ጥናቱ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ካላቸው ነጥቦች መካከል የሆቴል ቅደመ-መያዝ ስረዛን የሚመለከት ሕግ መቅረጽ አንዱ ነው፡፡ በጥናት አቅራቢዎቹ እምነት መሠረት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ተቆጣጣሪው ምህዳር ውስጥ፣ በጉድለት የሚታየው አንዱ የሆቴል ቅደመ ምዝገባ አስገዳጅ ህጎች አለመኖር ነው፡፡  አስጎብኝ ድርጅቶች የጉብኝት መደባቸውን ከረዥም ጊዜ በፊት አስቀድመው አዘጋጅተው ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዱ ከስድስት እስከ ስምንት ወራት በፊት ተደራድረው ይጨርሳሉ፡፡ በመሆኑም በገቡት ግዴታ መሠረት ለሚመጡት ቱሪስቶች ያዘጋጁትን የጉብኝት መርሃ ግብር ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለመደው ተግባር ግን ሆቴሎች የተሻለ ዋጋ ሲያገኙ ግዴታቸውን ትተው ለሌላ አዲስ ደንበኛ መኝታ ቤቶችን ማከራየት ነው፡፡ ብዙ ዕቅድ አዘጋጅቶ በጉጉት ሲጠብቅ ቆይቶ ወደ አገር ለሚገባው ቱሪስት ቅር የሚያሰኝ ተግባር ከመሆኑም በላይ የአገሪቱ የቱሪዝም ገጽታን እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቱሪስቱ ክፍያ ጨምሮ አዲስ ሆቴል ለመከራየት ይገደዳል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ትግባራትን ለመቆጣጠር፣ በአገር ደረጃ ተግባራዊ የሚሆን የሆቴል ቅደመ-ምዝገባና የኮንትራት ስረዛን በተመለከተ (በፍትሐ ብሄር ህጉ የተቀመጡት ጠቅላላ የውል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው) አስገዳጅ ቅጣትን የያዘ ግልጽ መመርያ በአፋጣኝ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል ተብሏል፡፡ በጣም ብዙ አገሮች እንዲህ ዓይነት ልዩ መመሪያ (protocol) ስላላቸው ችግሩ አይታይባቸውም ይላል፡:

የቱሪስት ቪዛ አለአግባብ መዘግየት ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በቦሌ አለም-አቀፍ ኤርፖርት በኩል መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡ ለቱሪስቶች የመጀመሪያው የግንኙነት ተሞክሮ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት የሚያገኙት መስተንግዶ ነው፡፡ ይሄ ተሞክሮ አስደሳችም ቅር የሚያሰኝ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የዚህም ውጤት፣ ቱሪስቶች በቆይታቸው ወቅት የአዎንታ ወይም የአሉታ ጥላ እንዲያጠላበት ያደርጋል፡፡ አገሪቱን ጎብኝተው በማያውቁ  ጎበኚዎች ላይ የጋባዥነት ወይም በተቃራኒው የገፊነት ውጤት ሊኖረው ይችላል ተብሏል፡፡ በቅርብ ዓመታት የተጀመረው ለተወሰኑ አገሮች ዜጎች ኤርፖርት ላይ ቪዛ የመስጠት አሠራር በራሱ አመርቂ ዕርምጃ የመሆኑን ያክል ከውጭ የሚገቡ ቱሪስቶች/ተጓዦች የኢሚግሬሽን ሥነ ሥርዓት እስኪፈፅሙ ድረስ ለረዢም ጊዜ በሰልፍ እንደሚጠባበቁ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህን ስርዓት ለመፈጸም እስከ አንድ ሰዓት ድረስ እንደሚወስድባቸው ቱሪስቶች የሚገልጹ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ከሁሉም በላይ የችግሩ ምንጭ ቪዛ የሚሰጥባቸው መስኮቶች ቁጥር ማነስ ነው፡፡ ምንም እንኳ” መስኮቶቹ በተግባር ቢኖሩም በአንድ ወቅት የሚሰሩት ግን ግማሽና ከግማሽ በታች የሚሆኑበት ወቅቶች በርካታ ናቸው፡፡ ሰለዚህ መጠነኛ ማስተካከያዎችን በማድረግ ችግሩን ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነስ ይቻላል፡፡ ሁሉም እንደሚገነዘበው ከረጅምና አድካሚ ጉዞ በኋላ ከላይ ለተገለጸው ያህል ጊዜ ኤርፖርት ላይ መጠበቅ ለተጓዡ አስደሳች ተሞክሮ አይደለም፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ የቪዛ አገልግሎት በአሜሪካን ዶላር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች ተመጣጣኝ የውጪ ምንዛሪ የሚሰጥበት ዕድል ማስፋት ይኖርበታልም ተብሏል፡፡

ይህንን በብሔራዊ ደረጃ የሚቀርበው ጥናት የንግድ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት አካላት ጋር የሚያወያዩበትና ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡