መነሻ ገጽ - ቢዝነስና ኢኮኖሚ - ከአፈር የተሠራ ብሎኬት አዲሱ የግንባታ አማራጭ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

ከአፈር የተሠራ ብሎኬት አዲሱ የግንባታ አማራጭ

ሦስት ሆነው የጀመሩት ሥራ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ድርጅቱ ገበያም ማግኘት ጀምሯል፡፡ አፈርን በማሽን ቅርፅ እያበጁለት፣ እንደ ብሎኬት ጥንካሬ ኖሮት ማምረት ተጀምሯል፡፡

በቀን ሦስት ሺሕ ያህል የአፈር ብሎኬት መሥራት የቻሉት ወጣቶቹ፣ ሁለት ቤቶችን በዚሁ ምርት ገንብተው አስረክበዋል፡፡ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የአሜሪካ ኮንክሪት ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ ቻፕተር አካሂዶት በነበረው ዓውደ ጥናት ላይ፣ እነዚህ ወጣቶች የሚያመርቱት የአፈር ብሎኬት የዓውደ ጥናቱ አካል ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡

በአፈር የሚሠሩ ቤቶችን መገልገያዎችንና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ማምረትና መጠቀም ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል ከአምስት ዓመት በፊት በዘመናዊ መንገድ ከአፈር የሚሠራ ብሎኬት በኢትዮጵያ የማምረት እንቅስቃሴ የተጀመረው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ጥናት እያካሄዱበት የሚገኙ መሆናቸው የሚነገርለት ይህ የአፈር ብሎኬት፣ ስለጠቃሚ ጎኑ የሚነገርለትም በርከት ያለ ሆኖ ይገኛል፡፡

ከድረ ገጾች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አፈር በሚገኝበት አካባቢ መሣርያውን በማጓጓዝ የሚመረት በመሆኑ የማጓጓዣ ወጪን ማስቀረቱ አንደኛው ጥቅም ነው፡፡ ብሎኬት ሆኖ እስኪወጣ ድረስ ያለው ሒደት ብዙ ጊዜ የማይጠይቅ መሆኑ፣ በቀላሉ የሚደርቅና የሲሚንቶ ወጪን የሚቀንስ ወይም የሚያስቀር መሆኑ ሳይቀር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ቀላል በሆነ ማምረቻ መሣርያ በቀን ከ5,000 በላይ የአፈር ብሎኬት ማምረት የሚቻል ሲሆን፣ ከፍተኛ አቅም ያለው ማሽን በመጠቀም ግን በቀን እስከ 17 ሺሕ ብሎኬት ሊመረት እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉ የሚልቀው ደግሞ ለአካባቢ ተስማሚነቱና መርዛማ ኬሚካሎችን የማያመነጭ እንደሆነ ተመራጭ አድርጎት፣ በአሜሪካ ደቡባዊ ምዕራብ ግዛቶች በብዛት የሚመረት መሆኑም ይነገራል፡፡ ኒው ሜክሲኮ፣ አሪዞና፣ ካሊፎርኒያ፣ ኮሎራዶና ቴክሳስ ግዛቶች ከአፈር የተሠራ ብሎኬት የሚዘወተርባቸው እንደሆኑ የሚገልጹ መረጃዎች ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ምርቱን በማምረት እያስተዋወቁ ካሉ ድርጅቶች አንዱ ፕሮቴር (በእስፓሽ፣ ይህ ቃል አፈር እንደማለት ነው) ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂስ የተባለውና በሦስት ወጣቶች የሚመራው ድርጅት አንዱ ነው፡፡ በዓውደ ጥናቱ ወቅት ይህ ተቋም ከአፈር ስለሚሠራው ብሎኬት ጽሑፍ ያቀረበ ሲሆን፣ መልዓከሰላም ሞገስና ሰሎሞን ጥበቡ የተባሉ ሁለት የኩባንያው ባለድርሻዎች ለሪፖርተር ስለምርቱ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በቀን እስከ 3,000 ያህል ከአፈር የተሠራ ብሎኬት ማምረት የሚችለው ይህ ድርጅት፣ በቀላሉ በእጅ ሊመረቱ የሚችሉ የአፈር ብሎኬቶችን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡ እስካሁንም በኦሎንኮሚ የዘር ማከማቻ መጋዘን ሲሠራ፣ በጫንጮም ለሌላ ተግባር የዋለ ቤት በአፈር ብሎኬት ገንበቷል፡፡ የቤቶቹ ስፋት 18.5 በ8.5 ሜትር መሆኑን የገለጸው ሰሎሞን፣ ምርቱ ቀስ በቀስ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አስታውቋል፡፡ በዋጋ ረገድ እንደ ብሎኬቱ ስፋትና መጠን ሊለያይ ቢችልም፣ በአማካይ ከሁለት ብር በላይ የሚሸጥ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ ሰሎሞን እንደሚያስረዳው አፈሩ በሚገኝበት ቦታ ላይ ማምረቻ ማሽኑን መትከል ከተቻለ ዋጋው ከዚያም በታች ሊቀንስ ይችላል፡፡

ከ30 በላይ የተለያየ ዓይነትና ቅርፅ የአፈር ብሎኬቶችን ማምረት እንደሚቻል የሚገልጸው ሰሎሞን በሲሚንቶና በእበት ሊያያዝ የሚችል፣ አለበለዚያም ያለ ሲሚንቶም ሆነ ያለእበት እርስ በርሱ ሊገጣጠም የሚችል የአፈር ብሎኬት ማምረት የሚቻልበት ቴክኖሎጂ እንዳለ ያስረዳል፡፡

ከአፈር ስለሚሠራው ብሎኬት ማብራርያ ባቀረቡበት መድረክ ጥያቄዎችንም አስተናግደው ነበር፡፡ ብሎኬቱን ለማያያዝ አልፎ አልፎ ብረትና ሲሚንቶ መጠቀም ሊያስፈልግ ስለሚቻልበት፣ እነሰሎሞን ከሚያመርቱት አንዱ የሆነው እርስ በርሱ የሚገጣጠም የአፈር ብሎኬት፣ ክብደት የመሸከም ብቃቱና እርጥበት ሳያበላሸው ወይም ሳይሸረሽረው ለብዙ ጊዜ ማገለግሉን በተመለከተ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ማብራርያ የሰጠው መልዓከሰላም፣ ከማንኛውም የሲሚንቶ ውጤት ከሆነ ብሎኬት ያልተናነሰ ጥንካሬ እንዳለው፣ ይዘቱ ወደሸክላነት የሚያደላ የአፈር መጠን በመጠቀም የሚመረት በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ማገልገል እንደሚችል አብራርቷል፡፡ የአፈር ብሎኬቱን የተመለከቱ ባለሙያዎች በበለኩላቸው ምንም እንኳ አብላጫ ይዘቱ አፈር ቢሆንም፣ ሳይፈረካከስ እንዲቆይ ለማድረግ መጠነኛ የሲሚንቶ ውህድ የሚጨመርበት መሆኑንና በማሽን እንደሚጠቀጠቅ ሲገልጹ ለመመልከት ተችሏል፡፡ የአፈር ብሎኬቱ ግድግዳም ከውጭ በኩል ብረት ቀለም ቢቀባ በውኃ እንዳይሸረሸር ሊረዳው እንደሚችልም በወቅቱ ምርቱን ሲመለከቱ ለነበሩ ታዳሚዎችና ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡

የአፈር ብሎኬቱ በቀላሉ ከሚገኝ አፈር ከመመረቱ ጀምሮ በቀላሉ በሚሰጥ ሥልጠና ማንም ሰው እንዲያመርተው መዘጋጀት የሚችል ስለሆነ፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ሲነገርለት በውበቱና በዲዛይን ምቹነቱ፣ በአካባቢ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ባለመኖሩ በሌሎች አገሮች ተመራጭ እንደሚያደርጉት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡