መነሻ ገጽ - ቢዝነስና ኢኮኖሚ - የኢትዮጵያ ፍራፍሬ ምርቶች ትንሳዔ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
23 October 2013 ተጻፈ በ 

የኢትዮጵያ ፍራፍሬ ምርቶች ትንሳዔ

በላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ሥር ከነበሩ ትላልቅ የመንግሥት እርሻዎች መካከል ቲቢላ እርሻ ልማት አንዱ ነው፡፡

ሦስት ንዑስ እርሻዎች ያሉትን ቲቢላ እርሻ ልማትን ወደ ግል ለማዛወር ወይም በሽርክና ሊሠራ ከሚችል ኩባንያ ጋር ለመሥራት ታስቦ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት እንቅስቃሴ ተደርጐ መንግሥት መጨረሻ ላይ የደረሰበት ድምዳሜ እርሻ ልማቱን በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) እንዲሠራ ማድረግ ነበር፡፡ 

በዚሁ መሠረት ከ1350 ሔክታር መሬት ይዞታ ያለው ቲቢላ እርሻ ልማት 84 በመቶ የሚሆነውን የባለቤትነት ድርሻ አፍሪካ ጁስ የተባለ የሆላንድ ኩባንያ፣ ቀሪውን 16 በመቶ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርሻ ይዘው አፍሪካ ጁስ በሚል መጠሪያ 10 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ያለው አዲስ ኩባንያ ፈጠሩ፡፡

በሆላንዱ ኩባንያና በኢትዮጵያ መንግሥት በጥምረት የተመሠረተው አዲሱ ኩባንያም የቲቢላ እርሻ ልማትን ተረከበ፡፡ የኩባንያው ዋና ዓላማ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶችን በማምረትና ለጭማቂ ፋብሪካዎች ዋነኛ ጥሬ የሆነውን ጭማቂ በማዘጋጀት ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርብ ማድረግ ነው፡፡ 

የአፍሪካ ጁስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባይነህ ኢሳያስ እንደገለጹት፣ አፍሪካ ጁስ ሲመሠረትና እ.ኤ.አ ወደ 2009 ሥራ ሲገባ ሦስት ዋና ዋና አላማዎችንም ይዞ ነው፡፡ ይህም ዘመናዊ ትሮፒካል ፍራፍሬዎችን ማልማት፣ ከሚያመርተው ፍራፍሬዎች ጭማቂዎችን ማቀነባበርና ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሥራት አርሶ አደሮቹ የሚያመርቱትን ፓሽን ፍሩትና ሌሎች ፍራፍሬዎች ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ በማድረግ የውጪ ንግድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ 

ወደ ሥራ ሲገባም የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ዘመናዊ የጭማቂ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙበትን ጭማቂ ማምረቻ ፋብሪካ መትከል ነበር፡፡ ጣልያን ሠራሽ የፍራፍሬ መጭመቂያና ማቀነባበሪያ ማሽኑን ከ2.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የጠየቀ ሲሆን፣ የፋብሪካው ተከላ አንድ ዓመት ሳይፈጅ በመጠናቀቁ በዓመቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ዶ/ር አባይነህ ገልጸዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ለአውሮፓ ገበያ የቀረበው ምርት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የማይታወቀውን ፓሽን ፍሩት የተባለውን ፍራፍሬ ምርት በመጭመቅ ነው፡፡ የዚህ ጭማቂ ዓይነት በቀጥታ ለተጠቃሚው የሚቀርብ ሳይሆን የፍራፍሬ ጭማቂ ኩባንያዎች እንደ ዋነኛ የጥሬ ዕቃ የሚጠቀሙበት ወይም አሽገው ለገበያ የሚያቀርቡት ነው፡፡ 

የፓሽን ፍሩቱን ዝርያ ከውጭ በማምጣትና በመትከል ከፋብሪካው ተከላ ጋር ጐን ለጐን ማልማት በመቻሉ ፋብሪካው በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባ አስችሎታል፡፡ ፓሽን ፍሩት ደግሞ በአውሮፓ የሚፈለግ ጭማቂ በመሆኑ የውጭ ንግዱን በቶሎ ማስኬድ መቻሉን ከዶ/ር አባይነህ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ኩባንያው ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ምርት እየጨመረ ለመምጣቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ዋናው ግን ኩባንያው በፍትሐዊ ንግድ መርህ የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የፓሽን ፍሩት ወይም የትሮፒካል ጁስ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ በፍትሐዊ ንግድ ሰርቲፋይድ የሆነው አፍሪካ ጁስ ብቻ በመሆኑ ጥሩ ገበያና ዋጋ እንዲያገኝ አስችሎታል ይላል፡፡ በፍትሐዊ ንግድ ሰርቲፋይድ መሆን በጥሩ ዋጋ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ጠቀሜታዎች አሉት የሚሉት ዶ/ር አባይነህ፣ የአውሮፓ ገዥዎች በዚህ ደረጃ ከሚሠራ ኩባንያ የመግዛት ፍላጐታቸው ከፍተኛ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት 250 ሔክታር የሚሆነው የድርጅቱ መሬት በዚሁ ፓሽን ፍሩት የተሸፈነ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ጭማቂ ምርቱን የበለጠ ለማሳደግ የፓሽን ፍሩት የሚሸፍነው እርሻ ወደ 600 ሔክታር ለማድረስ ታቅዷል፡፡ በተከታታይ ዓመታት የላከው የፓሽን ፍሩት ጭማቂ መጠን ከዓመት ዓመት እየጨመረ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ አንድ ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉም ተጠቅሷል፡፡ 

ጭማቂውን በማቀነባበርና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኩባንያ ለመሆን የበቃው አፍሪካ ጁስ፣ የፓሽን ፍሩቱን እርሻ እያስፋፋ በመሆኑ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የጭማቂ መጠን እያደገ መምጣት ችሏል፡፡ እንደ ዶ/ር አባይነህ ገለጻ በሚቀጥለው ዓመት ከፓሽን ፍሩት ጭማቂ የሚገኘው ገቢ በእጥፍ በማደግ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ 

የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ የሚመረትባት ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ጭማቂ የሚያቀነባብር ፋብሪካ የሌላት በመሆኑ የታሸጉ ጭማቂ ምርቶችና የጭማቂ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ፋብሪካዎች የጭማቂ ጥሬ ዕቃ የሚያስገቡት ከውጭ ነው፡፡ የአፍሪካ ጁስ ግን ይህ ታሪክ መለወጥ እንዳለበት ያምናል፡፡ ከፓሽን ፍሩት የጀመረውን የጭማቂ ምርት በሌሎች ምርቶችም የሚቀጥል መሆኑንና ፓፓዬ፣ ብርቱካን፣ ቲማቲምና የመሳሰሉ ምርቶችን የሚያመርት በመሆኑ ከራሱ እርሻና ከሌሎችም አካባቢዎች በመሰብሰብ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተለይ ለአዲስ አበባ ገበያ የሚቀርበው የውጭ የፓፓዬ ምርት ለገበያ በማቅረብ የሚታወቅ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከውጭ ከሚገቡ ጭማቂዎች ውስጥ የማንጐ ጭማቂ ቀዳሚ እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ር አባይነህ፣ በአገር ውስጥ ያሉ የጭማቂ ማቀነባበሪያዎች አሽገው ለሚያቀርቡት ጁስ ጥሬ ዕቃውን ከውጭ ሲያመጡ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለአገር ውስጥ የጭማቂ አሻጊዎች ወይም አምራቾች  ለማንጐ ጁስ የሚጠቀሙበትን ጥሬ ዕቃ ከአፍሪካ ጁስ መግዛት ጀምረዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በማንጐ ምርት የምትታወቅ መሆንዋን ያስታወሱት ዶ/ር አባይነህ፣ ምርቱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኝና ጥሬ ዕቃውን ያለማቋረጥ ማምረት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ምርቱ የሚደርስበትም ጊዜ እንደየአካባቢው የሚለያይ በመሆኑ፣ አፍሪካ ጁስ ከእነዚህ አካባቢዎች ያለውን ማንጐ በመሰብሰብ ለፋብሪካዎች የሚሆን የማንጐ ጁስ እያመረተ ነው፡፡ ዶ/ር አባይነህ ኢትዮጵያ የማንጐ ጁስም ሆነ ጥሬ ዕቃውን ከውጭ ማስገባት የለባትም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ማንጐ በደረሰ ጊዜ ብቻ ጭማቂው እንደማይመረት የገለጹት ዶ/ር አባይነህ፣ የፋብሪካው ቴክኖሎጂ የማንጐ ምርት ሳይበላሽ ለ18 ወራት እንዲቆይ ስለሚያስችል ዓመቱን ሙሉ ማምረት ይችላል ብለዋል፡፡

ኩባንያው የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ጨምቆ ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባሻገር «ኮንሰንትሬት» የተባለ ምርት ያመርታል፡፡ የዚህን ምርት ጭማቂ የሚያሽጉ ኩባንያዎች ውኃ በመጨመርና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው የታሸጉ ጁሶችን እንዲያመርቱ የሚያስችል ነው፡፡ ይህን ምርት ለማምረት አንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የጠየቀ ማስፋፊያ ተሠርቷል፡፡ 

ፋብሪካው የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በተፈጥሮ ውኃ የሚጨምቅ ሲሆን፣ ማስፋፊያ ግንባታው የተተከለው ማሽን ደግሞ የፍራፍሬ ጭማቂውን ውኃ በማትነን የታሸገ ጭማቂ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ማምረት የሚያስችል ነው፡፡ 

«ኮንሰንትሬት» ምርት ከጭማቂው የበለጠ ጠቃሚ የሚሆነው ምርቱን ለመላክ ቀላልና ወጪው ዝቅ የሚል መሆኑ ነው፡፡ በተለይ በአምስት ኮንቴይነር የሚላከው የፍራፍሬ ጭማቂ በኮንሰንትሬት መልክ ቢሠራ በአንድ ኮንቴይነር ሊጫን የሚችል በመሆኑ ወጪዎችን ይቀንሳል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ኩባንያው በሚያስተዳድራቸው በሦስቱ ንዑስ እርሻ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኘው 1,350 ሔክታር መሬት 550 ሔክታሩ በፍራፍሬ የተሸፈነ ሲሆን፣ ቀሪው በምግብ ሰብል ምርት የተሸፈነ ነው፡፡ 

ከፍራፍሬ ውጪ የምግብ ሰብል ምርቶችን የሚያመርተው ኩባንያው ከ1,700 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ቀለብ ለማቅረብ እንዲያስችለው ነው፡፡ በጅምላ ዋጋ ለሠራተኞቹ የሚቀርቡ እንደ በቆሎ ያሉ ምርቶችን የሚያመርት ሲሆን፣ ብዙም ውኃ ገብ ያልሆኑና ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የሚጠይቀው መሬት ላይ ደግሞ ጤፍ እያመረተበት እንደሆነም ዶ/ር አባይነህ ይገልጻሉ፡፡ 

በዘርፉ ያለው ገበያ ጥሩ በመሆኑ እንደ ፓሽን ፍሩቱ ሁሉ የማንጐ ጭማቂውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ኩባንያው የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዋናው ዓላማ ግን ወደ አገር ውስጥ ለሚገባው ጭማቂም ሆነ የጭማቂ ማቀነባበሪያዎች ለሚጠቀሙት የጭማቂ ጥሬ ዕቃ መግዣ እየወጣ ያለው የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት በአገር ምርት እንዲተካ ማድረግ ነው፡፡ ዶ/ር አባይነህ እንዳሉትም ይህንን ለማድረግ በቂ የሆነ አቅም አለ፡፡ አስመጪዎቹም አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት እየተጠቀሙ በመሆኑ፣ በገፍ የሚገባው የታሸገ ጭማቂ በአገር ውስጥ ምርት ይተካል የሚል እምነት አላቸው፡፡