መነሻ ገጽ - ርዕሰ አንቀጽ - መንግሥት ሆይ! ተመካከር! ጠንክር! ተግብር!
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
12 May 2013 ተጻፈ በ 

መንግሥት ሆይ! ተመካከር! ጠንክር! ተግብር!

ጠንካራ መንግሥት እንፈልጋለን፡፡ ተጠናክሮ ሕጐችን የሚተገብር፣ ተጠናክሮ ፍትሕና ዴሞክራሲ የሚያሰፍን፣ ተጠናክሮ ልማትን እውን አድርጐ ድህነትን የሚያጠፋ መንግሥት አገሪቱ ትፈልጋለች፡፡ ሕዝብ ይፈልጋል፡፡

በተለይ በተለይ የዓለም ሁኔታ አስቸጋሪ እየሆነ እየሄደ ባለበትና የኢኮኖሚ ቀውሱ ዓለምን እያንገዳገደ በሚገኝበትና ፈታኝ አካባቢያዊ ችግር እየቆነጠጠን በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ ጠንካራ መንግሥት እውን የሚያደርገው ተግባር የህልውናና የቀጣይ ጉዞ ዋስትና ነው፡፡

መንግሥት ችግር የለም፣ ሁሉም ነገር ‹‹በሽበሽ›› ነው ብሎ ተኩራርቶ ከሚቀመጥ ይልቅ ራሱንና ውስጡን ይፈተሽ፡፡ ራሱን መርምሮና አጥርቶ መጠናከር አለበት፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ሲል፣ ለራስ ህልውናና ተዓማኒነት ሲል፡፡

ከሁሉም በፊት መንግሥት እርሱ በርሱም፣ ከሕዝብ ጋርም ይነጋገር ይመካከር፡፡ 

በገዥው ፓርቲ ውስጥም፣ በመንግሥት ውስጥም እርስ በርስ መነጋገርና መመካከር ይጠናከር፡፡ ሁሉም የኢሕአዴግ ፓርቲዎች በተመሳሳይ የአየር ሞገድ ናቸው? በግልጽ ይነጋገራሉ? ይገመግማሉ? ወይስ የእከክልኝ ልከክልህ ጉዞ እየተጓዙ ናቸው? ዘጠነኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ከተካሄደ በኋላ የየራሳቸውንና የጋራ ጠንካራ የአስፈጻሚ አካል ስብሰባ አካሂደው ያውቃሉ? ምክንያቱም ማስተካከያ የሚያስፈልገው ጉዳይ ምንድን ነው ብለው ለይተው ማስተካከያ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ 

ከሕዝብ ጋርም መመካከር ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ መድረኮች ሲገኙ ሕዝብ የሚሰማውን እየተናገረ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ጠፋ፣ አቤቱታ አድማጭ የለም፣ የችግር ፈቺ ያለህ፣ ኑሮ ተወደደ፣ ፍትሕ የለም፣ ወዘተ እያለ ነው፡፡ ሕዝብ እንደዚህ ዓይነቶቹን ችግሮች ከተናገረ መንግሥት ችግር አድምጦ የሚፈታ መሆኑን በተግባር ማየት ይፈልጋል፡፡ መልሱን በተግባር ካላየ መናገሩም ዋጋ የለውም ብሎ ያቆማል፡፡ ተግባር ነው ምላሹ ከማለት ይልቅ ‹‹ትዝብት ነው ትርፉ›› ይላል፡፡ 

በመሆኑም ከሕዝብ ጋርም እርስ በርስም መንግሥት ሊነጋገርና ሊመካከር ይገባዋል፡፡ ጊዜም መውሰድ የለበትም፡፡

መነጋገርና መመካከር ለተግባር ነው፡፡ መጮህን ለመለማመድ አይደለም፡፡ ወይም ስብሰባ ተካሄደ ሕዝብም ተጋበዘ ለማለት አይደለም፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ ወሬ በዛ፣ ተግባር ግን የለም፡፡ መንግሥት ራሱ ስለሙስና ያወራል፡፡ በተግባር ግን የለም፡፡ መንግሥት ራሱ ስለመልካም አስተዳደር ያወራል፡፡ በተግባር ግን የለም፡፡ 

ተግባር! ተግባር! አሁንም ተግባር ያስፈልጋል! 

በአሁኑ ጊዜ ዜጐች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮችም የት ነው አቤት የሚባለው አያሉ ማማረር ጀምረዋል፡፡ ዳያስፖራውም አገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ መጣሁ፣ ሥራ ለመክፈት ተመለስኩ፣ ነገር ግን ችግር ሲያጋጥም የሚፈታ አካል የለም እያለ ሲያማርር ይሰማል፡፡ መፍትሔ የሚሰጥ ጠፍቶ በርካታ ሰዎች ቆመዋል፡፡ 

እያጋጠመ ያለው ችግር በሥራ ዕድል ሲገመትና በካፒታል ሲተመን እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ ኢንቨስትመንቶች አስቸኳይ ምላሽ ካላገኙ ኪሳራው የአገርም፣ የሕዝብም፣ የድርጅትም፣ የግለሰብም ነው፡፡ አንዱ ችግር ሲያጋጥመው ሌላውም እየታዘበ ነግ በእኔ ብሎ መሸማቀቅ እንደሚጀምር ሊታወቅ ይገባል፡፡ 

በተለይ በአንድ ትልቅ ችግር ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብ እየተነጋገረበት ነው፡፡ ግልጽ ጥያቄ እየቀረበበት ነው፡፡ መንግሥት ሙስና እንዳለ እያመነነና እያወቀ ለምን ዕርምጃ አይወሰድም የሚል ነው፡፡ መንግሥት መልካም አስተዳደር እንደሌለ እየተናገረና እያመነ ለምን ዕርምጃ አይወሰድም የሚል ነው፤ እውነትም ነው፡፡ መንግሥት ለምን ዕርምጃ አይወሰድም?       

ዕርምጃ መወሰድ ስላለበትና በተግባር መታየት ስላለበትም ተመካከሩ ተነጋገሩ እያልን ነው፡፡ ችግሩ እንዳለን ለማመን መነጋገር መቅደም አለበት፡፡ ችግሩ መኖሩን ካመናችሁ ዕርምጃ እንዳትወሰዱ የሚያደናቅፋችሁ ምን እንደሆነ ተነጋገሩበት፡፡ 

ሕዝብ ከመንግሥት ትክክለኛ ምላሽ ካላገኘ ‹‹ሐሜት›› ቢመስልም የራሱን ድምዳሜ እየወሰደና እየተናገረ ነው፡፡ ዕርምጃ የማይወስደው ሁሉም ‹‹ሙሰኞች›› ስለሆኑ መድፈር አቅቷቸው ነው እያለ ነው ሕዝቡ፡፡ ለመልካም አስተዳደር በተግባር የቆመ ስለሌለ ለመልካም አስተዳደር ጠንቅ በሚሆነው ላይ ዕርምጃ መውሰድ አይችሉም እያለ ነው ሕዝቡ፡፡

ለዚህም ነው መንግሥት መግለጫ ከመስጠት አልፎ በተግባር ይኼው ፀረ ሙስና ዕርምጃዬ፣ ይኼው የመልካም አስተዳደር ዕርምጃዬ ብሎ ማሳየት አለበት፡፡ በተግባር!

እንደዚህ ዓይነት ቆራጥ ዕርምጃ በወቅቱ ካልተወሰደ ሙሰኞችና ምግባረ ብልሹዎቹ የበላይነት እየያዙ ይመጣሉ፡፡ እነሱ የበላይነት ከያዙም ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሳይሆን የማፍያ መንግሥት በይፋ ይመሠረታል፡፡ የማፍያ መንግሥት የሚገነባው ደግሞ የማፍያ ሥርዓት ነው፡፡ ወንጀል፣ ምግባረ ብልሹነት፣ መከፋፈል፣ መጋጨት፣ ፍርኀትና ሥጋት የነገሠበት ሥርዓት ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው ሁሌም በተደጋጋሚ እባክህ መንግሥት ሆይ

-ተነጋገር!

-ተመካከር!

-መርምር!

-ተግብር!

-ተ ጠ ና ከ ር!

እያልን ያለነው፡፡