መነሻ ገጽ - ርዕሰ አንቀጽ - ለአዲስ ዓመት አዲስ አመለካከት!
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

ለአዲስ ዓመት አዲስ አመለካከት!

መልካም አዲስ ዓመት፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ወደ 2006 ዓ.ም. እየተሸጋገርን ነን፡፡ በዓሎች ከዕምነታችንና ከባህላችን ጋር ተያይዘው የሚፈጥሩት የተለያየ መንፈስ አለ፣ ደስታ አለ፡፡ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይለበሳል፣ ይጨፈራል፣ ይጸለያል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ የበዓል አከባበር አሁንም በደስታ እንዲጠናቀቅ እየተመኘን በአዲሱ ዓመት ግን ሀብት፣ ሃይማኖት፣ ባህልና አመለካከት ሳይለየን እንደ ሕዝብና እንደ አገር በጋራ የምናከብርበት መንፈስ እንፍጠር እንላለን፡፡

‹‹ለአዲስ ዓመት አዲስ አመለካከት!›› የሚል መፈክር ይዘን ‹‹ለአዲሱ ዓመት ከቅልጥምና ከዱለት በላይ የላቀ አቀባበል እናድርግለት፤›› እንላለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ማስተካከል፣ መለወጥ፣ ማስወገድና መፍጠር የሚገባን አመለካከቶች አሉ፡፡ በ2006 ዓ.ም እነዚህን እውን እናድርግ፡፡

ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ 2005 ዓ.ም. በታሪካችንም ሆነ በዕለታዊ ኑሯችን አጋጥሞንና አይተነው የማናውቅ አላስፈላጊ የሃይማኖት መለያየት፣ መራራቅ፣ ጥላቻ፣ ጥርጣሬ፣ ረብሻ፣ እስርና ግድያ ያየንበት ዓመት ነበር፡፡ ይህ በ2006 ዓ.ም በጭራሽ መወገድና መቀየር ያለበት ነው፡፡ የመብት ጥያቄ ካለ ሕገ መንግሥቱም ይፈቅዳል፡፡ ነገር ግን ሕገወጥነትን በማስወገድ፣ ጥላቻን ባለመስበክ፣ የሌላውን መብት ባለመንካትና ፍፁም ሰላማዊና ኢትዮጵያዊ በሆነ መንገድ መብት መጠየቅ አለበት፡፡ ይህ አመለካከት በ2006 ዓ.ም. ተጠናክሮ፣ ዳብሮ፣ በፍቅርና በሰላም ታጅቦ መታየት ይገባዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት አዲስ አመለካከት እንጠብቃለን፡፡ 

በ2005 ዓ.ም. ሙስናን ለመዋጋት ዕርምጃ የተወሰደበት ዓመት ነው፡፡ ሙስናን መዋጋት ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነውና ሕጋዊነትን በማጠናከርና ሕዝብን መሠረት በማድረግ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን፡፡ ነገር ግን የፀረ ሙስና ትግሉ ከዚህም በላይ መሆን አለበት እንላለን፡፡ በ2006 ዓ.ም. አዲስ የፀረ ሙስና ትግል በማጠናከር መካሄድ አለበት እንላለን፡፡

አደጋ ከደረሰ በኋላ አምቡላንስና ግሉኮስ ይዞ ከመረባረብ ይልቅ ከመጀመሪያው አደጋው እንዳይደርስ የሚያደርጉ አሠራሮች፣ ሕጎች፣ አወቃቀሮች፣ አመዳደቦችና አሿሿሞች ይኑሩ እንላለን፡፡ ለባለሥልጣናትም ከመጀመሪያው ከሙስና የፀዱ የሚያደርግ የሥነ ምግባር ደንብ ይውጣላቸው፡፡ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ኅብረተሰቡን ለማስተናገድ መከተል ያለበት አሠራርና ደንብ በግልጽ ይቀመጥለት፡፡ ተከታታይና አስፈጻሚ አካል ማከናወን ስላለበት ኃላፊነት በግልጽ ይቀመጥ፡፡ ወደ ጉቦና አላስፈላጊ ግንኙነት የሚያመሩ ጉዳዮች በሕግ ይወገዙ፣ ይታረሙ፡፡ 

ሁሉንም ችግር በእስርና በችሎት ልንፈታው አንችልም፡፡ ባህል ሆኖ፣ ሕግ ሆኖ፣ ልምድ ሆኖ፣ አሠራር ሆኖ በየዕለቱ ሙስናን የምናወግዝበትንና የምንታገልበትን አመለካከት እንፍጠር፡፡ በየትምህርት ቤቱ፣ በየመሥርያ ቤቱ፣ በሙያ ማኅበራትና በመኖሪያ አካባቢዎች ሳይቀር ይህንን አመለካከት እናስርፅ፡፡ ባህል ሆኖ ይደግ፡፡ አዲስ አመለካከት ለአዲስ ዓመት፡፡

ባለጉዳይ የተወሰኑ ባለሥልጣናትንና በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችን ለማግኘት እየተቸገረ ነው፡፡ ወይ ቢሮ አይገቡም፣ ወይ ማነጋገር አይፈልጉም፣ ወይ ጉቦ የማይሰጥ አይወዱም፣ ወይ መወሰን አይችሉም፡፡ ከዚህ አልፎ ባለጉዳይ አያነጋግሩም፡፡ ቅሬታ የማይሰሙ፣ ውሳኔ የማይሰጡና የማይፈርሙ ኃላፊዎች በእጅጉ እየተበራከቱ ናቸው፡፡ የሕዝቡን ሕገ መንግሥታዊ መብት እየረገጡ ናቸው፡፡ በርካታ ዜጎች ለአደጋ እየተዳረጉ ነው፡፡ ብዙዎቹ ኢንቨስተሮች ተስፋ እየቆረጡ ነው፡፡ በርካታ የዳያስፖራ ወገኖች ‹‹ፎር ጉድ›› ብለው መጥተው ‹‹ወቸ ጉድ›› ብለው እየተመለሱ ነው፡፡ 

በ2006 ዓ.ም. ሕዝብ ለመብቱ የሚሟገትበትና ኃላፊነት የያዙ ሹሞች ሕዝብን የሚያዳምጡበት አዲስ አመለካከት ይፈጠር፡፡ ዜጋ በአገሩ መኩራት አለበት፡፡ ፀረ ሕዝብ ሹም ማፈርና መሸማቀቅ አለበት፡፡ ለዚህም አዲስ አመለካከት፡፡

በ2006 ዓ.ም. መንግሥት አዲስ አመለካከት መፍጠርና ማጠናከር አለበት፡፡ የተቋምና የሲስተም ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይንቀሳቀስ፡፡ ተቋማት ይጠናከሩ፡፡ የሚሠሩት በሲስተም ይሁን፡፡ እስካሁን ያሉት የመንግሥት ተቋማት ትልቁ ድክመት ይህ ነው፡፡ ራሳቸውን የቻሉና በሕግ የሚመሩ ተቋማት አይደሉም፡፡ የአቶ እከሌ መሣርያዎች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ሥራና የሚያከናውኑት እንቅስቃሴ መርህና ሲስተም መሆኑ ቀርቶ ገጠመኝ እየሆነ ነው፡፡ የተገነባ ነገር አይነካም የሚል መመርያ ቢኖርም የአቶ እከሌ ከሆነ ግን ይነካል፣  ይነጠቃል፡፡ ታጥሮ የማይለማ መሬት ይነጠቃል ይባልና የአቶ እከሌ ከሆነ ግን አይነካም፣ አይነጠቅም ይባላል፡፡ ሥርዓት ሳይሆን ገጠመኝ ነው፡፡

በ2006 ዓ.ም. ለተቋማት ግንባታና ለሲስተም ዝርጋታ መንግሥት አዲስ አመለካከት ይዞ በአዲስ መንፈስ ይንቀሳቀስ፣ ይረባረብ፣ እንላለን፡፡ በወጣቱ ትውልድ ላይ ልዩ ኢንቨስትመንት የሚያደርግ አዲስ አመለካከት በ2006 ዓ.ም. ያስፈልገናል፡፡ ወጣቶች ለጫት እየተዳረጉ ነው ብለን እናማርራለን፡፡ የማሳጅ አገለግሎት የሴተኛ አዳሪነት መናኸሪያ ሆነ ብለን እንነጫነጫለን፡፡ ወጣቱ በአገሩ ሳይሠራ ውጭ አገር እሄዳለሁ እያለ  ለሞትና ለውርደት እየተዳረገ ነው ብለን እናለቅሳለን፡፡

ይህ ዓይነቱ ችግር በ2005 ዓ.ም. በእጅጉ ተባብሶ ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም. እንቀይረው፡፡ ወጣቱ ከእንደዚህ ዓይነት አደጋዎች እንዲርቅ መንግሥትና ሕዝብ በወጣቱ ላይ  ኢንቨስት ያድርጉ፡፡ ኢንቨስት ያልተደረገበት ወጣት ትኩስና አኩሪ ትውልድ ሊሆን አይችልም፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ ድጋፍና ማበረታቻ ያልተደረገለት ወጣት አኩሪ ሊሆን አይችልም ብለን እንመን፡፡ ስለዚህ አኩሪ የሆነ ወጣት ትውልድ ለማየት ሕዝብና መንግሥት ኢንቨስት ያድርጉ፡፡ ይህ ተጠናክሮ ሊያዝ የሚገባው አመለካከት ነው፡፡ 

ኧረ ስንቱ!

ልዩነት ቢኖረንና አለመግባባት ቢፈጠርም፣ ጥላቻንና መራራቅን ከማባባስ ይልቅ በውይይት፣ በመመካከርና በመገናኘት ችግሮችን ልንፈታ የምንችል መሆናችንን አምነን፣ በ2006 ዓ.ም. ለምክክርና ለውይይት ልዩ ክብርና ቦታ የሚሰጥ አመለካከት ይዘን እንጓዝ፡፡

ካለፈው ዓመት አዎንታዊ አመለካከቶችን ወስደን ተጨማሪ መልካም አመለካከቶች በማምጣት በአዲስ ዓመት አዲስ ድል እናስመዝግብ!

መልካም አዲስ ዓመት!

ለአዲስ ዓመት አዲስ አመለካከት!