መነሻ ገጽ - ዜና - መርከበኞች የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አነሱ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

መርከበኞች የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አነሱ

•    አዲሶቹ መርከቦች ያለሥራ መቆማቸውን ወቀሱ

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ባህረተኞች ተመጣጣኝ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው፣ የቀረጥ ነፃ መብት እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከበርላቸው ጠየቁ፡፡

ኢንተርፕራይዙ በዕረፍት ላይ ከሚገኙ የመርከብ ላይ ሠራተኞች ጋር በሥራ እንቅስቃሴያቸውና በድርጅቱ አጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ ባለፈው ዓርብ የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዷል፡፡ ካፒቴኖች፣ ቺፍ ኢንጂነሮችና በመርከብ ትራንስፖርት ላይ የተለያየ ሥራ ደርሻ ካላቸው ቁጥራቸው አንድ መቶ ከሚሆኑ ሠራተኞቹ ጋር የኢንተርፕራይዙ ዋና ዋና ባለሥልጣናት ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ የደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዲሁም የመርከብ ላይ የሕክምና አገልግሎትና ኢንሹራንስ እንዲሻሻሉላቸው ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተከፈላቸው ያለው ደመወዝ ከዘርፉ ዝቅተኛ ክፍያ ጋር በእጅጉ ልዩነት ያለው መሆኑን፣ ጥያቄያቸው የቅንጦት ሳይሆን የአገሪቱን የአቅም ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአንድ ዶላር ዋጋ ከ18 ብር በላይ መሆኑ ገሃድ ቢሆንም፣ በጉዞ ወቅት የሚከፈላቸው አበል ግን ከዓመታት በፊት በነበረ የምንዛሪ ስሌት እየተሰላ በመሆኑ አግባብ አይደለም ሊስተካከል ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በጉዞ ወቅት ቆይታቸው ምንም ዓይነት ሕመም ቢገጥማቸው ሕክምና የሚያገኙት በየብስ ከሚገኙ አለቆቻቸው ጋር በሚደረግ የሬዲዮ ግንኙነት ፈቃድ ከተገኘ ብቻ መሆኑ፣ እንዲሁም በዕረፍት ጊዜ (በየብስ ቆይታቸው) ሕክምና ለማግኘት የኢንተርፕራይዙ ኃላፊዎች ጥያቄያቸውን ከማድመጥ ይልቅ ዕረፍት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው በሚል ጥርጣሬ ምላሽ አለመስጠት በባህረኞች ጤንነት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በጉዞ ወቅት በሕመም ላይ የነበረ አንድ ሠራተኛ በአግባቡ ሕክምና ሊያገኝ ባለመቻሉ ከሥራ መልስ በየብስ ላይ በሕይወት የቆየው ለሁለት ወራት ብቻ ነው፤›› በማለት የችግሩን አሳሳቢነት በገጠማቸው ታሪክ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቀረጥ ነፃ መብት የነበራቸው በመሆኑ በዝቅተኛ ዋጋ ከሚጓዙባቸው አገሮች መኪና በማስገባት ተጠቃሚ እንደነበሩ፣ ይህም የሚከፈላቸው ደመወዝ ዝቅተኛ ቢሆንም ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩ ስላስቻላቸው በሥራቸውና በድርጅታቸው ደስተኛ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለመኖር ሲሉ በርካታ የረጅም ዓመታት ልምድ የነበራቸው በድርጅቱ ወጪ የተማሩ ሠራተኞች መልቀቅን መርጠዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ነባርና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች 10 በመቶ ብቻ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ያሳሰቡት አንድ ካፒቴን አንድ ኢትዮጵያዊ የመርከብ ማኔጀር እያለ አንድ የውጭ ዜጋን በማኔጀርነት መቅጠር ግድ ሲሆን፣ በሁለቱ መካከል በሚፈጠረው ልዩነት ኢትዮጵያዊውን ማኔጀር ማጣት ምን ያህል ጉዳት መሆኑን ወደፊት መገንዘብ ይቻላል በማለት ስለወደፊቱ ሁኔታ ጭምር እንዲታሰብ መክረዋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊን በመርከብ ኢንጂነሪንግ ማሠልጠን ለዚህ ድርጅት የወደፊት ሀብት ነው፡፡ አሁን ግን የተያዘው ሜካኒካል ኢንጂነሮችን መቅጠር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በከፍተኛ ወጪና በብድር በቻይና ተገንብተው ኢንተርፕራይዙ ከተረከባቸው መርከቦች መካከል ለነዳጅ ማጓጓዣ የመጡት ሁለት መርከቦች ያለአገልግሎት ቆመው መገኘታቸውም እንዳሳዘናቸውና የሀብት ብክነት መሆኑንም ከወቀሳ ጋር ገልጸዋል፡፡ አዲሶቹ መርከቦች ሲታሰቡ ሌሎች ገበያዎችን ሰብሮ የመግባት የቢዝነስ ዕቅድ ሊወጣ ይገባ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎችን ከማመላለስ ባለፈ የሌሎች አገሮችን ወጪ ዕቃዎች በማመላለስ መርከቦች ባዶአቸውን ከመጓዝ ገቢ እንዲያመጡ ማድረግ ይታሰብበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ሦስት የመንግሥት ድርጅቶችን በማዋሀድ ከዓመት በፊት የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 1,480 ሠራተኞች በአጠቃላይ አወቃቀሩ ሥር የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 449 ያህሉ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ባህረኞች ናቸው፡፡ ድርጅቱ ካሉት መርከቦችና በአሁኑ ወቅት በቻይና በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አስገንብቶ እየተረከባቸው ከሚገኙ ተጨማሪ ዘጠኝ አዳዲስ መርከቦች ጋር ያሉት የባህር ሠራተኞች ቁጥር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ መርከብ ውሰጥ እስከ 15 ባህረኞች የሚያገለግሉ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን ከዚህ በላይ ባህረኞችን በአንደ መርከብ ታሰማራለች፡፡

ይህንን ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያውያን ባህረኞች ኑሮ በአብዛኛው ዕረፍት የሌለውና ውጥረት የተሞላበት መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም እ.ኤ.አ ከ2007 ወዲህ የባህር ላይ ሕይወት በተለያዩ ምክንያቶች አስጨናቂ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥና የባሀር ወንበዴዎች መበራከት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መርከቦችም በቅርብ ጊዜ ከሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች የጠለፋ መኩራ ማምለጣቸው ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በዚህ አስቸጋሪ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች የክፍያና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ጥያቄ ተገቢነት አለው በማለት የሚያስረዱ አሉ፡፡

በውይይቱ ያነሷቸው ጥያቄዎች የቅንጦት ካለመሆናቸው በተጨማሪ ለድርጅቱና ለአገሪቱ ያላቸውን መቆርቆር ሲያስገነዝቡ፣ የመርከቦች ከጂቡቲ ወደብ ያለ ጭነት መንቀሳቀስን በከፍተኛ ቁጭትና ስሜት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የድርጅቱ መርከቦች ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ አንድ ሚሊዮን 379 ሺሕ 301 ቶን ዕቃ ወደ አገር ያጓጓዙ ሲሆን፣ ከጂቡቲ ወደብ ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች ያጓጓዙት የወጪ ዕቃዎች መጠን ግን 107 ቶን ብቻ ነው፡፡

ከባህረኞቹ ጋር የተወያዩት የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎችም ያነሷቸውን ጥያቄዎች እንዲሁም በተቆርቋሪነት የጠቀሷቸውን ችግሮች እንደግብዓት እንደሚወስዱት ተናግረዋል፡፡ የባህር ትራንስፖርት ዘርፉን የሚመሩት ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ በአብዛኞቹ ጥያቄዎች ላይ መልስ መሰጠት ሲጀምሩ የተናገሩት ይህንን የሚገልጽ ነው፡፡
‹‹ያነሳችኋቸውን አብዛኞቹን ጉዳዮች እንደ ግብዓት እንወስዳቸዋለን፡፡ በተቆርቋሪነትና አርቆ አሳቢነት የተሞሉ ናቸው፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ከሕክምና አገልግሎትና ከኢንሹራንስ ጥቅሞች ጋር ተያይዞ በተነሳ ጥያቄ ዙሪያ ግን ምናልባትም በግንዛቤ አለመኖር የተፈጠረ ካልሆነ በስተቀር ድርጅቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አንድ የባህር ሠራተኛ የቤተሰብ ሐኪም ሊኖረው ይገባል በሚል አመለካከት ድርጅቱ እንደሚሠራ፣ የአንድን ባህረኛ አጠቃላይ የጤናና የሕክምና ሁኔታ የሚከታተል መሆኑን፣ በባህር ጉዞ የጤና መታወክ በሚገጥመው ጊዜም ካፒቴኑ ከዚህ ሐኪም ጋር ስለጤና መታወክ ምልክቶቹ በመነጋገር ሐኪሙም ከቀድሞ የግለሰቡ የሕክምና መረጃ ጋር በማገናዘብ በመርከብ ላይ ከሚገኝ መድኃኒት የሚታዘዝለት አሠራር መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ከፍተኛ የጤና መታወክ በሚከሰትበት ጊዜም ካፒቴኑ ሕይወት የማትረፍ መሉ ሥልጣን እንዳለው፣ ይህም በአቅራቢያው ከሚገኝ አገር ሔሌኮፕተር በማዘዝ ወደ ሆስፒታል እንዲሄድ ማድረግን ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ይህንን መብት ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

ከወራት በፊት ድርጅቱ የተረከባቸው ሁለት የነዳጅ መርከቦች (ታንከሮች) ያለ ሥራ መቆም ድርጅቱንም በእጅጉ ያሳዘነ ነው የሚሉት ቺፍ ኢንጂነሩ፣ ችግሩ የተፈጠረው የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት እነዚህ መርከቦች በገቡበት ወቅት ለነዳጅ ማጓጓዣ ከሌላ ድርጅት ጋር ውል በመግባቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ችግሩን በመቅረፍ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን፣ ሌሎቹ አዳዲስ መርከቦች እንዲሁም ያለጭነት ከጂቡቲ ወደብ የሚመለሱ መርከቦች ጉዳይም ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት የገበያ ማፈላለግ ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ቱሳ ከባህረኞቹ የቀረቡ ጥያቄዎችን በገንቢነት በመቀበል መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ የቀረጥ መብትና የመኖርያ ቤት ጥየቄያቸውንም ለመመለስ ከመንግሥት ጋር እንደሚደራደሩ ገልጸዋል፡፡