መነሻ ገጽ - ዜና - የሪል ስቴት ግብይት ረቂቅ አዋጅ መነጋገሪያ ሆኗል
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

የሪል ስቴት ግብይት ረቂቅ አዋጅ መነጋገሪያ ሆኗል

•    የአክሰስ ሪል ስቴት ችግር የገበያ መቀዛቀዝ ፈጥሯል

በአክሰስ ሪል ስቴትና በደንበኞቹ መካከል የተነሳውን አለመግባባት ተከትሎ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያረቀቀው የሪል ስቴት ልማትና ግብይት አዋጅ ሰሞኑን መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡

ረቂቅ አዋጁን የተመለከቱ የሪል ስቴት ደንበኞች መንግሥት ዘይቶም ቢሆን ያዘጋጀው ጥሩ ረቂቅ አዋጅ ሲሉ፣ የሪል ስቴት አልሚዎች በበኩላቸው የተደበላለቀ ስሜት እያንፀባረቁ ነው፡፡

ሪፖርተር ካነጋገራቸው የሪል ስቴት አልሚዎች መካከል የተወሰኑ ‹‹ረቂቅ አዋጁ ለቤት ገዥዎች ያደላ ነው›› ሲሉ፣ የተወሰኑት አልሚዎች ደግሞ ‹‹ቤት ገዥዎች ጉዳት የሚያመጡ ስላልሆኑ፣ አልሚውን በሚመለከት ጠበቅ ያለ ሕግ መውጣቱ ችግር አይፈጥርም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው የሪል ስቴት ልማትና ግብይት ረቂቅ አዋጅ በ31 አንቀጾችና በሰባት ክፍሎች ተከፋፍሏል፡፡

ሁሉም የሪል ስቴት አልሚዎች ረቂቅ አዋጁ የሪል ስቴት ገዥዎችን የሚጠቅም ሆኖ፣ በእነሱ ላይ ግን ጠበቅ ያለ መሆኑን ያምናሉ፡፡ በአዋጁ ክፍል አራት አንቀጽ አሥር እንደተጠቀሰው የሪል ስቴት አልሚው ቤቶቹን ለመገንባት ለሚያስችለው መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ከሚመለከተው አካል ከመረከቡ በፊት፣ በመገናኛ ብዙኅን ማስታወቂያ ማስነገርም ሆነ ሥራውን ማስተዋወቅና ደንበኞችን መመዝገብ አይችልም ይላል፡፡

በመቀጠልም አልሚው በሕጋዊ መንገድ የተረከበውን መሬት ሊያስተናግድ ከሚችለው ደንበኛ በላይ መመዝገብ እንደማይችል፣ የሪል ስቴት አልሚው እንዲያለማ በተሰጠው ቦታ ላይ የተመዘገቡና ውል የፈጸሙ ደንበኞችን ስም ዝርዝር፣ የሚገዙትን ቤት ዓይነትና ይዞታ መጠን በዝርዝር ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ማሳወቅ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ስለ ሪል ስቴት አልሚው የውል ግዴታ ባስቀጠበት አንቀጽ 11 ደግሞ የሪል ስቴት በአልሚውና በደንበኛው መካከል ቤት ገንብቶ ለማስረከብ የተደረገ የሽያጭ ውል ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቦ የተረጋገጠ መሆን አለበት ይላል፡፡ በመቀጠልም የሪል ስቴት አልሚውና ደንበኛው የሚያደርጉት ውል ደንበኛው የከፈለውን ቅድመ ክፍያ፣ ቀሪውን ክፍያ ከፍሎ የሚያጠናቅቅበት ጊዜ፣ የአልሚውንና የደንበኛውን ግዴታና ኃላፊነት፣ የሚገነባው ቤት የሚገኝበትን ቦታ፣ ግንባታው ተጠናቆ የሚረከብበትን ጊዜና ውሉ ሊቋረጥ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች የሚያሳይ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

እነዚህን ጨምሮ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈሩት አብዛኛዎቹ ነጥቦች ለቤት ገዥው የሚያደሉ ናቸው ቢባልም፣ የአዋጁን ጥሩነት አምነው የተቀበሉ እንዳሉ ሁሉ ትናንሽ ሪል ስቴቶችን ይጎዳል፤ በአልሚዎች ላይ የከተማ አስተዳደሮች ቢሮክራሲ እንዲበረክት ያደርጋል የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦች በዘርፉ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በየደረጃው ካሉ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ባለፈው ሐሙስ ተዋናዮቹ እንዲካተት የሚፈልጉትን ሐሳብ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የሚፈልገው ግብዓት ከተደረገለት በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡

ይህ የሕግ ረቂቅ አክሰስ ሪል ስቴት ከፈጠረው መጠነ ሰፊ ጉድለት ጋር ተያይዞ የተረቀቀ መሆኑን የሚኒስቴሩ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አክሰስ ሁለት ሺሕ ደንበኞቹን ችግር ላይ ከጣለ በኋላ የሰሞኑ የሪል ስቴት ገበያ ከመቀዝቀዙም በተጨማሪ፣ ደንበኞች ወደ አልሚዎች በመሄድ በርካታ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ሰንብተዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የሪል ስቴት አልሚ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደንበኞች አሁን በመጠየቅ ላይ ያሉትን ዝርዝር ጥያቄዎች ቀደም ብለው መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ ገበያው የሚመጡ ደንበኞች የተጠኑ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ግዥ እንዲፈጽሙ መክረዋል፡፡
 
ከዚህ በተጨማሪም ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ዋነኛ ተዋናዮች ለአክሰስ ሪል ስቴት ደንበኞች ምክር ለግሰዋል፡፡ ተዋናዮቹ እንደሚሉት የአክሰስ ደንበኞች የአክሰስ አክሲዮን ባለቤት ሆነው፣ በቀረው ሀብት ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማድረግ ካለባቸው ጉድለት የታየበትን 400 ሚሊዮን ብር ለሁለት ሺሕ አካፍለው የሚደርስባቸውን 200 ሺሕ ብር ኢንቨስት ቢያደርጉ፣ ግዙፍ የሪል ስቴት ተቋም ባለቤት መሆን ይችላሉ ይላሉ፡፡ የራሳቸውን መኖርያ ቤትም በአጭር ጊዜ መገንባት የሚችሉበት አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው፣ ለዚህ ስኬት ግን ጠንካራ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊመሠርቱ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡