መነሻ ገጽ - ዜና - የኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አዲስ መጽሐፍ ታተመ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

የኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አዲስ መጽሐፍ ታተመ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበርነታቸውን በቅርቡ ያስረከቡት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ‹‹ሕይወቴና የፖለቲካ ዕርምጃዬ›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2005 ዓ.ም ገበያ ላይ ይውላል፡፡

የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ በመጽሐፋቸው ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የታሰሩ የቅንጅት አመራሮች በይቅርታ እንዲፈቱ የጠየቁት የአገር ሽማግሌዎች ሳይሆኑ፣ አንዳንድ የቅንጅት አመራሮች መሆናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ መረጃ ይፋ አድርገዋል፡፡

መጽሐፉ በስድስት ክፍሎችና በ175 ገጾች የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአመዛኙ በእሳቸው የሕይወት ውጣ ውረድና የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ያተኩራል፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ክስተቶችና ለቅንጅት መፍረስ ምክንያቶችን ያሉዋቸውን ምክንያቶች በመጽሐፉ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከምርጫው ጋር በተያያዘ የቅንጅት አመራሮች መታሰር፣ በእርቅ መንፈስ የተጀመረው ሽምግልና መጨረሻ ላይ እንዴት ወደ ይቅርታ መጠየቅ እንደተቀየረ፣ በዚህ ሒደት በእስር ላይ ይገኝ የነበረው የቅንጅት አመራር መከፋፈል ምን ዓይነት ገጽታ እንደነበረው የሚተነትኑ መረጃዎች በመጽሐፉ ተካቷል፡፡ 

በተለይ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ ወደ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ብቻ ሳይወረውሩ፣ በራሱ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ችግሮች አንድ በአንድ ነቅሰው በመጽሐፋቸው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ኢንጂነር ኃይሉ በዚሁ መጽሐፋቸው የቅንጅት እስረኞችን ለማስፈታት በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ስለሚመራው የሽማግሌዎች ቡድን እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹ፕሮፌሰር ኤፍሬም የቤት ሥራ ተሰጥቶት እሺ መልሱን ይዤ እመጣለሁ ብሎ ምንም ሳይሠራ እንደሚመጣ ለእኔ ግልጽ ነበር፡፡ ለጠየቅነው አንድም የይሁንታ መልስ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ባለሥልጣናት ዝም በል ሲሉት ነው መሰለኝ ለጥቂት ሳምንታት ይጠፋል፡፡ በኋላ ደግሞ ተስፋ አይቆርጥም ምንም ሳይዝ ይመጣል፡፡ አካሄዱ ሁሉ የእኛን ጥንካሬ ለማዳከም ይመስላል፡፡ በወቅቱ እኔ ፕሮፌሰሩ በራሱ ፈቃድ እርቅ ለማውረድ ብሎ ይመጣል ብዬ እገምት ነበር፡፡ በኋላ ግን የደረስኩበት እነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንዲመጡና እርቅ እንዲካሄድ ያደረጉት የእኛ ሰዎች ናቸው፡፡ የእኛ ሰዎች ምንም ዋጋ ተከፍሎ መውጣት መፈለጋቸው ስለታወቀ መንግሥት አቋሙን እያጠነከረ መጣ፡፡ ከእኛ የሚፈለገው ነገር በየቀኑ መልሶ እኛኑ የሚያዋርድ ሆነ፤›› ይላሉ፡፡

ፓርላማ የመግባትና ያለመግባት ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ወደኋላ መለስ ብለው ሲያስቡት ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር አስታውሰው፣ ፓርላማ የገቡትስ ምን አገኙ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ 

ከምርጫ 97 በኋላ የቅንጅት አመራሮች በጅምላ ሲታሰሩ ከሌሎች ጓደኞቻቸው እንዲነጠሉ ተደርገው ለ28 ቀናት በጨለማ ቤት ውስጥ በቀድሞው ማዕከላዊ እንዲታሰሩ መደረጉን በመጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡

የኢንጂነር ኃይሉ ይህ መጽሐፍ ክፍል አንድ ሲሆን፣ ክፍል ሁለት በ2006 ዓ.ም ለንባብ እንደሚበቃ የመጽሐፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ አስታውቋል፡፡ የመጽሐፉ የመሸጫ ብር 55 ሆኖ በነገው ዕለት ለገበያ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡