መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ሸማች - የሦስቱ ተቋማት ጉዳይ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
24 March 2013 ተጻፈ በ 

የሦስቱ ተቋማት ጉዳይ

ከተማ ቀመስ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ነዋሪዎች ከመብራት፣ ከስልክና ከውኃ አገልግሎቶች ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው፡፡

በገጠራማው አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ቢሆኑ የመብራትና የስልክ አገልግሎቶችን እያገኙ ነው፡፡ በተለይ የሞባይል ተጠቃሚ የሆኑ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች ቁጥር እያደገ ለመምጣቱ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በአሁኑ ወቅት የሞባይል ደንበኞች ቁጥር ከ20 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ነው፡፡ 

ሦስቱም የአገልግሎት ዓይነቶች ከእያንዳንዱ ዜጋ ዕለታዊ እንቅስቃሴ ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው ዕለታዊ ሥራዎቻችን ሁሉ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥገኝነት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡ መሠረታዊ ፍላጐቶች ከሆኑት ውስጥም እንዲመደቡ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡

ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ተዘርግቶላቸው እየሠሩ ያሉት እነዚህ አገልግሎቶች ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ እንደምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው ደንበኞች ለእነዚህ አገልግሎቶች ክፍያ ለመፈጸም የሚያሳዩት ትጋት ነው፡፡ እልህ አስጨራሽ ወረፋዎችን ተቋቁመው በመክፈል አገልግሎቱ እንዳይቋረጥባቸው ይደክማሉ፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞችን የያዙትና ወደፊትም ሚሊዮን ደንበኞች የሚኖሯቸው እነዚህ መሠረታዊ አገልግሎቶች፣ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት አገልግሎታቸው ቢስተጓጐል የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚጠረጠር አይደለም፡፡ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ሳይተጓጐል ለወራት የዘለቁበት ጊዜ አለ ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር ግን ይከብዳል፡፡

ኃይል በተቋረጠ ቁጥር በግለሰብም ሆነ በተቋማት ደረጃ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ወደ አንድ ሆቴል ጐራ ብሎ ተመግቦ፣ የሚጠጣ ውኃ የሚጠብቅ ደንበኛ፣ የቧንቧ ውኃ ዛሬ የለም ሲባል፤ የታሸገ ውኃ ወይም ለስላሳ መጠጦችን ለመጠቀም ይገደድ ይሆናል፡፡ ያላሰበው ወጪ ቢሆንም፣ ያንን የሚያደርገው ግን አቅም ሲኖረው ነው ማለት ነው፡፡ ውኃ በተቋረጠ ቁጥር ምርት የሚስተጓጐልባቸውን ተቋማትም ቤት ይቁጠራቸው፡፡

ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆነው የሚንቀሳቀሱት የመብራት፣ የውኃና የስልክ አገልግሎቶች በተጓዳለ አገልግሎታቸው በተደጋጋሚ ትችት የሚቀርብባቸው፣ ሁሌም የልብ የማያደርሱ ናቸው፡፡

ያለችግር፣ ያለኔትዎርክ መንገጫገጭ፣ የሞባይል ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት እያገኘ ያለ ደንበኛ ለመኖሩ ከቴሌ በቀር ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ በየዕለቱ ቧንቧው የሚፈልገውን ያህል ውኃ የሚያፈስለት ደንበኛ አይኖርም፡፡ መብራትም ቢሆን እንዲሁ ሙሉ ሳምንቱን ሳይቆራረጥበት ዘልቄያለሁ የሚል ደንበኛ ማግኘትም ብርቅ ነው፡፡

በተለይ ሰሞኑን የኔትዎርክ መቆራረጥ ደንበኞችን እያማረረ ነው፡፡ ቴሌ ለኔትዎርኩ መቋረጥ የራሱን ምክንያት የሚያቀርብ ቢሆንም አገልግሎቱ እንዲቆራረጥበት የማይፈልገው ደንበኛ ምክንያቱ ሊጠቅመው አይችልም፡፡

ቴሌ የሚሰጠው ምክንያት አሳማኝ ቢሆን እንኳ ደንበኛው ሰበቦች እስከመቼ ምላሽ ይሆናሉ? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ መከራከርም ይችላል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ እንደቴሌ ደንበኛ ሆነን እያየነው ያለው ክስተት፣ የኃይል መቆራረጥ በተፈጠረ ቁጥር የሞባይል ኔትዎርክም ችግር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ የኃይል መቆራረጥ ሲከሰት የሞባይል ኔትዎርክ አብሮ እልም እያለ ነው፡፡

የኃይል መቋረጡ የቴሌ አገልግሎትን ከማስተጓጐል ባለፈ የመብራት ኃይል ደንበኞች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው የሚቋረጥባቸው በመሆኑ አሁን አሁን ያልተነገረ የፈረቃ አገልግሎት ተጀመረ እንዴ? እያስባለ ነው፡፡

አንድ ደንበኛ በሳምንት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ኃይል ይቆራረጥበታል፡፡ የኃይል ሥርጭቱ መቋረጡ ሆን ተብሎ የሚደረግና ተመሳሳይ በሆነ ሰዓት የሚከሰት መምሰሉም አጠያያቂ ነው፡፡

የኃይል አቅርቦት እጥረት ኖሮ ሁሉንም ደንበኛ ለማስተናገድ ሳይቻል ቀርቶ፣ ያለውን ኃይል በክፍፍል ለማቅረብ ታስቦም ከሆነ ይህንኑ እውነት ተናግሮ፣ ደንበኛው ለዚያ ፕሮግራም እንዲዘጋጅ ማድረግም ጥሩ መላ ነበር፡፡

ሆኖም ይህ ባለመደረጉ ደንበኞች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳረፉን እናያለን፡፡ የውኃ አቅርቦቱም ቢሆን እንዲሁ ነው፡፡ ቀን ቀን ምንም ዓይነት ውኃ የማያገኙ አካባቢዎች አሉ፡፡ ማታ፣ ሲበዛም ሌሊት ብቻ ውኃ የሚቀርብላቸው ሰፈሮች ጥቂት አይደለም፡፡  በሁለት፣ በሦስት ቀን አገልግሎቱን የሚያገኙ ደንበኞች ብዙ ናቸው፡፡

ውኃ ካገኘን ሳምንታችን አለፈ የሚሉ ቅሬታዎች፤ ውኃ ራቅ ካለ አካባቢ ለማመላለስ ተገደድን የሚሉ ደንበኞች ጥቂት ናቸው አይባልም፡፡

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ በሰፈሬ ውኃ ከጠፋ ሳምንታት እንደተቆጠረ ሲነግሩኝ እኔም ማታ ማታ ብቻ እንደማገኝ ገልጨላቸው ነበር፡፡ እርሳቸው የውኃ ችግራቸውን ለመቅረፍ መላ ያሉት ወደ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ሄደው ውኃ በቦቴ ገዝተው መጠቀምን ነበር፡፡ ለተከታታይ ቀናት አንድ ቦቴ ውኃ በመቶ ብሮች እየገዙ መጠቀም መቻላቸውንም ነግረውኛል፡፡

የውኃ መስመሩ አገልግሎት ባለመጀመሩ እንደተለመደው በቦቴ እየገዙ የውኃ ታንከራቸውን እየሞሉ የተጠቀሙት ግን ለተወሰኑ ቀናት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ በኋላ ለግለሰብ በቦቴ ውኃ አንሸጥም የሚል መልስ ከባሥልጣን መሥርያ ቤቱ ስለተሰጣቸው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንዴት እየተጠቀሙ እንደሆነ ባላውቅም የከተማችን የውኃ ችግር እንዲህ ባለው አጋጣሚም ጭምር የታጀበ ለመሆኑ ማሳያነቱ ግን ግልጽ ነው፡፡

በጥቅሉ እነዚህ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የአገልግሎት ዓይነቶች ያለምንም እንከን ደንበኞችጋር የሚደርሱበት ጊዜ መቼ እንደሆነ እንድንናፍቅ ተገደናል፡፡

ቢያንስ አንድ ዓመት እንኳ ያለእንከን የሚያገለግሉን መቼ ይሆን? እርግጥ ነው በከተሞች አካባቢ የነዋሪው ቁጥር መብዛቱና የውኃ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ፈላጊው ቁጥር መላቁ መሥርያ ቤቶቹ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የራሱ ተፅዕኖ ማሳደሩ ባይታበልም፤ ዘላቂ መፍትሔ ለምን እንደማይኖር ግን ሁሌም ግራ ይገባኛል፡፡

በጥቂት ወራት ልዩነት የሚታየው እንከን አንድ ቦታ ላይ እንዲቆም ካልተደረገ፣ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ካልተበጀ በቀር ወደፊትም እነዚህን መሥርያ ቤቶች ሳናማርር የሚጠባ መስከረም ላይኖር ነው፡፡

ክፍተቱን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻል እንኳ፣ ችግሩን ለመቀነስ፤ ለምሳሌ መብራት ሲቋረጥ እልም የሚለውን ኔትዎርክ ለማስተካከል አማራጭ የኃይል አቅርቦት የመጠቀም ልምድን ማዳበር ይገባል፡፡ ለኔትዎርክ መቆራረጡ ሕንፃዎች ምክንያት መሆናቸው ከታወቀ፣ ሕንፃዎቹ ላይ አንቴናዎችን ለመትከል ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡

የኃይል መቋረጡ ምክንያት የኃይል አቅርቦት እጥረት ከሆነ ደግሞ፣ እጥረቱን ለመድፈን ባይቻል እንኳ በዚህ ቀን፣ በዚህ ሰዓት ኃይል አቋርጥብሃለሁ ብሎ ለደንበኛው ቀድሞ መናገር ጥሩ መላ ብቻ ሳይሆን ከዘወትር ትችት ያድናል፡፡ በሰለጠነው ዓለም ይቅርታ የሚጠየቅበት፣ ጨዋነት የሞላበት አሠራር ነው፡፡ የውኃውንም ሥርጭት በዚህ መንገድ ማስኬድ ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ወደፊትም እያደገ የሚሄደውን የእነዚህን ተቋማት አገልግሎቶች በጥራት መስጠት ካስፈለገ ሥር ነቀል ለውጥ ከማድረግ ጐን ለጐን ተገልጋዮች ተመሳሳይ አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን የግል ተቋማት እንዲፈጠሩ ማድረግም መልካም ነው፡፡

የኃይል ፍላጐት እየናረ ስለሚሔድና የሚፈለገውን ኃይል ለማቅረብም ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ፣ አንዳንድ ተቋማት የራሳቸውን የኃይል ፍላጐት ራሳቸው እንዲያሟሉ የሚያደርግ አሠራር ሥራ ላይ ቢውል፣ ችግሩን በመቀነስ ጥቂትም ቢሆን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡