መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ሸማች - ምክንያት አልባ ዋጋዎች
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
31 March 2013 ተጻፈ በ 

ምክንያት አልባ ዋጋዎች

በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ግልጽ ያልሆኑ፣ አደናጋሪ ክስተቶች ተበራክተው ይታያሉ፡፡ የተለመዱ ናቸው ማለትም ይቻላል፡፡

በተለይ ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ወቅታዊ የሸማቾችን ፍላጎት በመንተራስ የሚፈጸም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በተደጋጋሚ እንመለከታለን፡፡ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለሁለት ወራት በሚቆየው የዓብይ ጾም ወቅትም የተወሰኑ አቅርቦቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ በተጠቃሚዎች ይፈለጋሉ፡፡ የዚያኑ ያህል ዋጋቸው ይጨምራል፡፡

በዓብይ ጾም ገበያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ፍላጎታቸው ከጨመሩ ምርቶች መካከል የአትክልት፣ የፍራፍሬ ምርቶችና ዓሳ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ምርቶች የተጠቃሚው ፍላጎት ስለሚጨምር ብቻ ዋጋቸውን ከፍ በማድረግ መሸጥ እንደ ትክክለኛ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

እነዚህን ምርቶች ወደ ለገበያ የማቅረቡ ሒደት ጾሙ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ከነበረው አካሄድ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይኖርና ምንም ዋጋ የሚያስጨምር ምክንያት ሳይከሰት በእጥፍ ዋጋ የተጨመረባቸው ሆነው የታዩም አሉ፡፡ እርግጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የፍላገት መጨመር የዋጋ መጨመርን እንደሚያስከትል ያብራራሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው ትንታኔ ግን ገበያው በአቅርቦትና ፍላጎት ኃይሎች ላይ ተመሥርቶ የሚመራ በሚሆን ጊዜ እውነተኛውን የገበያ ዋጋ ሊያመላክቱ የሚችሉ ናቸው እንጂ የማይታዩ እጆች፣ ለመተንበይ የሚያስቸግሩ ክስተቶችና ጣልቃ ገብነቶች በበዛበት ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንተና ሚዛናዊነቱን ይስታል ብዬ አስባለሁ፡፡

ለምሳሌ በጾሙ የመጀመርያ ሳምንት፣ በሰባት ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቲማቲም ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ግን በአትክልትና ፍራፍሬ መደብሮች የመሸጫ ዋጋው አሥራ አራት ብር ደርሷል፡፡ ለወቅቱ ተፈላጊ የሆኑ ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችም እንደ ቲማቲሙ በአንዴ በእጥፍ አይቀጠልባቸው እንጂ ዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡

በእርግጥ የፍላጎት እየጨመረ መምጣት በዋጋ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ተፅዕኖ የማይካድ ባይሆንም፣ እነዚህን ምርቶች ወደገበያ ለማምጣትና ወደ ሸማቹ ለማድረስ ከሦስትና አራት ሳምንታት በፊት ከነበረው ወጪ በላይ የሚጠይቁ አለመሆናቸውን ስናስብ ጭማሪው የተጋነነ መሆኑን እንረዳለን፡፡

የትራንስፖርት ዋጋ አልጨመረም፡፡ አምራቾች ወቅቱን ስለገመቱና ስላገናዘቡ የምርት እጥረትም የለም፡፡ እጥረት ከሌለና ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ተጨማሪ ወጪ ካልጠየቀ ዋጋው ለምን በዚህን ያህል ደረጃ ተወደደ የሚለው ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል፡፡ የምርት ቅብብሉን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች እንደሚሉት፣ በቀናት ልዩነት አንዳንድ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ባልታሰበ መጠን ዋጋቸው ለመናሩ ዋነኛው ምክንያት በቅብብሎሹ መሀል ያለው የጥቂት ደላሎች እጅ መርዘም ነው፡፡

ምርቶቹ በቂ ተቀባይ ያላቸውና የሚፈለጉ በመሆኑ፣ ዋጋ እስኪጨምር በመጋዘን ሳይሸጡ ይቆዩ የማይባሉ ወይም በቶሎ የሚበላሹ ምርቶች ሆነው ሳለ፣ ደላሎቹ ለአምራቾቹ የተወሰነ ጭማሪ ሰጥተው እነሱ ደግሞ ከፍተኛ የትርፍ መጠን ይዘው ወደ ገበያ እንዲገባ ማድረግ መቻላቸው የዋጋ ለውጡን አስከትሏል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ዘወትር ወቅት እየተጠበቀ የሚከሰት ሆነ እንጂ ባለው እውነታ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ የደረሰበትን ያህል መሆን እንዳልነበረበት ይታመናል፡፡ ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ሌላ በሰሞኑ ገበያ በተጠቃሚዎች የሚፈለገው ዓሳም ዋጋው እንደተለመደው ተጋንኖ ለገበያ እየቀረበ ነው፡፡ ከአገሪቱ ዓመታዊ የዓሳ ሽያጭ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው በዚህ ጾም ወቅት የሚሸጥ መሆኑን በመረዳትና ፍላጎቱን በመገንዘብ ከፍተኛ የትርፍ መጠን ተይዞለት እየተሸጠ ነው፡፡

ሸማቹ ጥሬ ዓሳውን በቀጥታ ከዓሳ መሸጫ ሱቆች የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ አሁን አሁን እንደውም በአዲስ አበባ ከተማ ጥሬ ዓሳ የሚሸጡ መደብሮች የሉም ወደሚባልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ወደ ከተማዋ የሚገባውን አብዛኛውን ጥሬ ዓሳ የሚረከቡት ሆቴሎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ሸማቹም ምርቱን ቤቱ ወስዶና አዘጋጅቶ ለመጠቀም ያለው ዕድል አናሳ በመሆኑ የዓሳና ከዓሳ የሚዘጋጁ ምግቦችን የሚያገኘው በሆቴሎች ብቻ የተገደበ እንዲሆን  አድርጓል፡፡

ይህ ሒደት በዓሳ የሚሠሩ የምግብ ዓይነቶች ዋጋ ከአብዛኛው ተጠቃሚ አቅም በላይ እንዲሆን ማድረግ ከጀመረም ውሎ አድሯል፡፡ በአዲስ አበባ አንድ መካከለኛ የሚባል የዓሳ ጥብስ አማካይ ዋጋው ከ75 ብር በላይ ነው፡፡

በአንጻሩ ዓሳ ለመመገብ የፈለገ አንድ ደንበኛ ለአንዲት ዓሳ በሚጠየቀው ዋጋና ሆቴሎቹ ጥሬ ዓሳን በሚረከቡበት ዋጋ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የአገሪቱ የዓሳ መሸጫ ዋጋ በተለይ በጾም ጊዜ፤ የሚቆረጥለት ዋጋ እጅግ የተጋነነ ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ በአሁን ወቅት በከተማችን ካሉ አብዛኛው ሆቴሎች ውስጥ ከመጠነኛ ክትትል ጋር የሚቀርብ አንድ ጥሬ ዓሳ፣ አዲስ አበባ ሲደርስ የሚያስወጣውን ወጪና ከደረሰ በኋላም ተጠብሶ በሚሸጥበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት መመልከቱ ብቻ ይበቃል፡፡

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው የዝዋይ ሐይቅ፣ አምራቾች አንድ መካከለኛ፣ ጥሬ ዓሳ ዋጋው ተወደደ ከተባለ፣ የሚያስረክቡት ከአምስት ብር የዘለለ አይደለም፡፡

በአብዛኛው ግን አንድ ጥሬ ዓሳ በአራት ብር ነው የሚሸጠው፡፡ ይህ የወቅቱ ዋጋ ነው፡፡ በዚህ ያህል ዋጋ የተገዛው ዓሳ ነው እንግዲህ እዚህ ደርሶና ተጠብሶ ለበላተኛ ሲቀርብ 75 ብርና ከዚያም በላይ እስከ መቶ ብር የሚጠየቅበት፡፡

የቱንም ያህል ቢሆን ከምርት ቦታው አዲስ አበባ ለመድረስ የሚጠይቀው የማጓጓዣ ወጪና ለምግብ ዝግጅቱ የሚፈለገው ግብዓት ከፍተኛ ቢሆን እንኳ፣ የተጠበሰ ዓሳ ይህን ያህል ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡

የዓሳ ዋጋ ግዝፈት እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ ምርት የገበያ ሥርዓት ጉዳይም ሊተች ይገባዋል፡፡ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የዓሳ ተመጋቢ ቁጥር ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በቂ የሆነ የዓሳ አቅርቦት እያለ በጥራት አለመመረቱ፣ ሳኒቴሽንና ኃይጂኑ ያሳስባል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩና ሥራዬ ብለው የሚተዳደሩበት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡

በእርግጥ ዓሳ በማጥመድ ኑሮ የሚገፋ አጥማጆች በሺዎች ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡ ይህም ቢሆን በዘመናዊ መንገድ የሚመረት አይደለም፡፡ ይህም በመሆኑ በአነስተኛ ዋጋ ከአምራቹ እጅ የሚወጣው ዓሳ፣ ተጠቃሚው ዘንድ ሲደርስ ዋጋው እንዲዋጋ አድርጐታል፡፡

ተጠቃሚው ጥሬ ዓሳ በቀላሉ እንዳያገኝና ሆቴሎች ሰፊ የትርፍ መጠን እንዲይዙበት መንገድ የከፈተላቸው ሌላ ምክንያት ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ ዘመናዊ ኩባንያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው ነው፡፡

ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ከተፈለገ፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ኩባንያዎች መበርከታቸው ግድ ነው፡፡ በጾም ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም ይህ ምርት በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበት መንገድ እስካልተፈጠረ ድረስ ነገም የዓሳ ጉዳይ እንዲሁ መቀጠሉ አይቀሬ ነውና ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡