መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ሸማች - የኤሌክትሪክ ኃይል ጠኔ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
07 April 2013 ተጻፈ በ 

የኤሌክትሪክ ኃይል ጠኔ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ለተደጋጋሚ ትችት የተጋለጠ ነው፡፡ በኃይል አቅርቦት ዙርያ የሚታየው ክፍተት ተጠቃሚው እንዲማረር ማድረጉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገልጿል፡፡

በአንፃሩ የአገሪቱ የኃይል ፍላጎት በየጊዜው ከማደጉ ጋር ተያይዞ መንግሥት የኃይል አቅርቦትን ለመጨመር ያደረጋቸው እንቅቃሴዎች ለውጥ ማምጣታቸው የሚካድ አይደለም፡፡

ለዚህ ጥረቱ አንዱ ማሳያ የህዳሴው ግድብና ሌሎች ከፍተኛ የኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ላይ መሆኑና ለመገንባት መዘጋጀቱ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ጥረቱ እንዳለ ሆኖ፣ አሁንም ቢሆን ግን የኃይል አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር የተጣጣመ ሊሆን አልቻለም፡፡ በአጭር ጊዜ የኃይል አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ልክ ይሆናል ተብሎም አይጠበቅም፡፡

በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የኃይል መቆራረጦች መነሻ የኃይል እጥረት ሳይሆን ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር የተፈጠሩ ቴክኒካል ጉዳይ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ለማንኛውም የኃይል መቆራረጡ መንስኤ የኃይል እጥረም ይህን የቴክኒክ ጉዳይ፣ ደንበኞች አገልግሎቱ ተስተጓጉሎባቸዋል፡፡ አምራቾች ተቸግረዋል፡፡ እንደተባለው ከቴክኒክ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ችግር ከሆነም በዚህን ያህል ደረጃ የኃይል መቆራረጡ በተደጋጋሚ ሲከሰት ኮርፖሬሽኑ ምን እየሠራ ነበር? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

አንድ ደንበኛ በሳምንት ውስጥ ሁለትና ሦስት ጊዜ ለሰዓታት አገልግሎት ሲቋረጥበት፣ ይህ ግድፈት የቴክኒክ ይዘት ከሆነ፣ ለማስተካከል በወራት የሚቆጠር ዕድሜ የሚወስደው ለምንድነው?

ከኮርፖሬሽኑ ተሰጠ የተባለውን ምክንያት እንድጠራጠር የሚያደርገኝ፣ የኃይል መቆራረጡ የሚከሰተው በተወሰነ ቀናት ልዩነት፣ በተመሳሳይ ሰዓትና በተደጋጋሚ መሆኑ ቴክኒካዊ ችግር የፈጠረው ነው ለማለት ስለሚያስቸግረኝ ነው፡፡

ከአንዳንድ የክልል ከተሞች የሚሰማው ሮሮ፣ ከአዲስ አበባ የባሰ የኃይል መቆራረጥ መኖሩን ነው፡፡ ቢያንስ በሳምንት አንድ ሙሉ ቀን ኃይል የሚቋረጥባቸው ከተሞች አሉ፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ኃይል ይቋረጥብናል ያሉም አሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉት አጋጣሚዎች ከጥቂት ወራት ወዲህ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ችግሩ የቴክኒክ ብቻ ነው ብሎ ለመውሰድ ይከብዳል፡፡

በእኔ እምነት የቱንም ያህል የቴክኒክ ችግር ቢኖር በነጋ ጠባው ደንበኞችን የማያማርር ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ ከኃይል እጥረት ጋር ስለመያያዙ ግምት አለኝ፡፡

የኃይል መቆራረጡ ከዚህም ቀደም የተከሰተና አሁንም ሊከሰት የሚችል ስለመሆኑ ደንበኞች እምነት አላቸው፡፡ ችግሩ ካለ ደግሞ የኃይል አቅርቦቱን እንደተለመደው ፕሮግራም አውጥቶ፣ ደንበኞች በዚሁ ፕሮግራም መሠረት እንዲጠቀሙ ማድረጉ ክፋት አልነበረውም፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግን ይህንን አላደረገም፡፡ አለማድረጉም ደንበኞቹን አስከፍቷል፡፡ አሳዝኗል፡፡ በአንዳንድ ሥልጡን የዓረብ አገሮች እንኳ፣ ለደቂቃ ኃይል ከተቋረጠ ከግማሽ ቀን በላይ ይቅርታ እየተጠየቀ ለደንበኛው ተማፅኖ ሲቀርብ እንሰማለን፡፡ ይህ ቀርቶብን ቀድሞ ቢነገረን ባልከፋን ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መሳት የማይገባው ነጥብ አለ፡፡ ከአገራችን የኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ክፍተት ኮርፖሬሽኑን ብቻ የምናማረርበት ደረጃ ላይ እንደማንገኝ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ያለምንም ጥርጥር የአገሪቱ የኃይል ፍላጎት አድጓል፡፡ መንግሥትም የኃይል ቅርቦቱን ለማሳደግ እየለፋ ስለመሆኑም ልንስማማ እንችላለን፡፡ ሆኖም የፍላጎቱን ያህል አቅርቦቱ ስለሌለ፣ በአሁኑ ወቅት የምናየውን የኃይል መቋረጥ ሊያስከትል ችሏል፡፡

የኃይል ፍላጎቱ ለመጨመሩ መገለጫ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች መረጃዎችንም ማቅረብ ይቻላል፡፡ እየተገነቡ ያሉት ትልልቅ ፋብሪካዎች ብዙ ኃይል መፈለጋቸው አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ ወደ ሥራ የገባ አንድ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ከ40 ሜጋ ዋት በላይ ይበላል፡፡ የዚህን ፋብሪካ ያህል አይሁን እንጂ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ሥራ የጀመሩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በመቶዎች የሚገመት ሜጋ ዋት ኃይል እየተጠቀሙ ነው፡፡ በቅርቡም በአንድ የውጭ ባለሀብት ይገነባል የተባለው የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የኃይል ፍላጎቱ ሲሰላ ሙሉ የሐዋሳ ከተማ ፍጆታን ይሸፍናል መባሉን ስንሰማ፣ የኃይል ፍላጎቶችን በምን ያህል ደረጃ እየጨመረ መሄዱን የሚጠቁመን ነው፡፡ ወደፊት ሥራ የሚጀምሩ የተለያዩ ተቋማት የኃይል ፍጆታቸው እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡

ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉት የኃይል አቅርቦት እየጨመረ የመምጣቱን ያህል፣ ለቤት ውስጥ ፍጆታ፣ የተጠቃሚዎች ፍላጎትም በዚያው ልክ ማደጉን እንረዳለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በየዓመቱ የሚገነቡ የመኖሪያ ቤቶች፣ ሕንፃዎች ኮንደሚኒየም ቤቶችና የመሳሰሉት ያለ መብራት ኃይል ዋጋ ስለማይኖራቸው፣ የኃይል ፍላጎቱ ከምንገምተው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሚገነቡትና እየተገነቡ ያሉት የኃይል ማመንጫዎች በቂ ላይሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት ያጭራል፡፡ ስለዚህ ነገም የፍላጎቱን ያህል በቂ ኃይል ለማቅረብ የሚቸግር ሊሆን ስለሚችል መንግሥት በሚገነባቸው የኃይል ማመንጫዎች ብቻ ፍላጎቱን ለማሟላት የሚችል አይሆንም፡፡

ከፍላጎቱ መጨመር ጋር ተያይዞ የተባባሰ እጥረትና መቋረጥ ወደፊትም ሊፈጠር ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላ ለደቂቃዎችም ቢሆን የኃይል መቋራረጥ የሚያስከትለው ጉዳት እንዲሁ በቀላል የሚታይ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ኢንዱስትሪዎች በኃይል መቋረጥ ሳቢያ የሚፈጠርባቸው ጉዳትና አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው ለውጥ እየተስፋፋ ሲመጣና ተገልጋዩም ሲበረክት፣ በኃይል መቋረጥ ብዙ ሥራዎች ሊስተጓጎሉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በባንኮች አካባቢ፣ የኮርካንኪንግንና ሌሎች ተመሳሳይ ቴክኖሎጂዎች በግድም ጭምር እየተተገበሩ ነው፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች ያለ ኃይል አቅርቦት ርቀው የማይጓዙ በመሆኑ የደቂቃዎች የኃይል መጥፋት የሚፈጠርባቸው እክል ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡

ከዚህ አንፃር ዘርፉን ለማሳደግ፣ ሌሎች አማራጮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለጸውም የግሉ ዘርፍ መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ትልልቅ ተቋማት የራሳቸውን ኃይል ማመንጨት የሚችሉት ዕድል እስካልተሰማቸው ድረስ ፍላጎትና አቅርቦት የመሳሳባቸው ነገር መቼም ሳላይደርስበት ይችላል፡፡ በለውጥ ላይ ያለ አገር ሊያጋጥመው የሚችል ክፍተት መሆኑን በመገንዘብ ከደንበኞች ጋር በመመካከር ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ከዚህም ሌላ የአገልግሎት አሰጣጡን ወይም የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ በቂ መረጃ መስጠትም ከኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅ ነው፡፡