መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ሸማች - ብርሃን አልባ ጎዳናዎች
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
04 August 2013 ተጻፈ በ 

ብርሃን አልባ ጎዳናዎች

በአራቱም አቅጣጫ አዲስ አበባ እየሰፋች ነው፡፡ አዳዲስ መንደሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ግድ ነውና ከከተማዋ መስፋፋት ጋር ተያይዞም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተዘረጉ ነው፡፡ 

ይብዛም ይነስም አዳዲስ በምንላቸው ሰፈሮች ውስጥ የሚሠሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ከቀድሞ የከተማው መንገዶች ጋር እንዲገናኙ ሆነው ተሠርተዋል፡፡ እየተሠሩም ነው፡፡ በተለይ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የተሠሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን መጥቀስ እንችላለን፡፡

ብዙዎቹ በኮብልስቶን የተሠሩ ናቸው፡፡ በአስፓልት ደረጃ አገናኝ መንገዶች የተገነቡላቸው የኮንዶሚኒየም መንደሮች የመኖራቸውን ያህል ገና በጅምር ላይ ያሉም አሉ፡፡

ይሁን እንጂ በአዳዲስ መንደሮችም ይሁን በከተማው ዋና ዋና መንገዶች ግንባታ ጐን ለጐን በፍጹም መቅረት የሌለባቸው የመንገድ ዳር መብራቶች ጉዳይ ግን የታሰበበት አይመስልም፡፡ እንዲህ ካሉ የመንገድ ግንባታዎች ጋር ተያይዞ ሊኖሩ የሚገባቸው የመንገድ ዳር መብራቶች የግድ አስፈላጊ መሆናቸውን በማመን በመንገድ ዲዛይኑ ሥራ የተካተቱ ስለመሆናቸው ግን አይጠረጠርም፡፡ ይህ ችግር በአብዛኛው የሚታየው በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ቢሆንም፣ በዋና ጎዳናዎች ላይም የመንገድ ዳር መብራት ያለመተከሉ ወይም ብርሃን አልባ መሆን አዲስ አባን የምሽት ዱካክ እንዲጫናት አድርጓል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሰፈሩባቸው አንዳንድ የኮንዶሚኒየም መንደሮች የውስጥ ለውስጥ መንገዶቻቸው መብራት አልባ በመሆናቸው ነዋሪው ሲማረር መታየቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

የመንገድ ዳር መብራቶች ለውበትም ጭምር የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ዋናው አገልግሎት ግን የከተማው ነዋሪዎች ያለችግር እንዲጓዙ ማስቻል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የመንገድ ዳር መንገዶቹ ቢያንስ ቢያንስ በተወሰነ ርቀት እንኳ ተተክለው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ አይደለም፡፡ እንደውም አሁን አሁን የመንገድ ዳር መብራቶችን የማኖር አስፈላጊነት የታሰበባቸው የማይመስልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡

ይህ ደግሞ ጭለማን ተገን በማድረግ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ የመንገድ መብራት በሌለባቸው የከተማው ጎዳናዎች ለትራፊክ አደጋ መጨመር ዓይነተኛ ምክንያት መሆናቸውም ይታመናል፡፡

ችግሩ ለአገልግሎቱ የሚውሉ ፖሎችን ካለመትከል ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን የተተከሉትም ቢሆኑ በአግባቡ አገልግሎት ሲሰጡ አለመታየታቸው ጭምር ነው፡፡ በአግባቡ አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉ የከተማው የመንገድ ዳር መብራቶች በአንድ አጋጣሚ ቢበላሹ እንኳ ፈጥኖ የመጠገንና ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ የማድረጉ እንቅስቃሴ ከተቀዛቀዘ ቆይቷል፡፡

በአጠቃላይ ከእያንዳንዱ መንገድ ግንባታ ጐን ለጐን ሊሠሩ የሚገባቸው የመንገድ ዳር መብራቶች ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ አገልግሎት ላይ ያሉትንም ቢሆኑ በአግባቡ እያገለገሉን ባለመሆኑ ለወንጀልና ለአደጋ መንስዔ እየሆኑ በመምጣታቸው ጉዳዩ የሚመለከተው አካላት በእጅጉ ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ሆኗል፡፡

የመንገድ ዝርጋታና አዳዲስ መንገዶች መፈጠርን ተከትሎ እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅን ለመግታት የግድ ሊኖሩ የሚገባቸው የትራፊክ መብራቶችና ምልክቶች ጉዳይ እንዲሁ ብርቅ እየሆኑብን መምጣታቸው ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ዕድል ኖሮት በከተማችን ዋና ዋና ጎዳናዎችን ዞሮ መመልከት የቻለ ሰው በቂ የትራፊክ ምልክትና የትራፊክ መብራቶችን ማየት ይቸገራል፡፡ በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ሊተከሉ ይገባቸው የነበሩ የትራፊክ መብራቶችን ለማግኘት ብዙ መድከም ይጠይቃል፡፡

እንደ ኮንዶሚኒየም ባሉ መንደሮች ውስጥ የትራፊክ መብራት በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት፣ በነባሮቹ መንገዶች ላይ እንኳን በአግባቡ መብራትና ምልክት ማስቀመጥ አልተቻለም፡፡ የትራፊክ መብራት ሳይቋረጥ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ መንገዶች ላይ ሳይቀሩ የትራፊክ መብራት አልባ ሆነዋል፡፡ አሊያም መብራቶቹ ተበላሽተዋል፡፡ ወይም ደግሞ በግጭት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡ እነዚህን ወሳኝ የሆኑ መገልገያዎች ችግር ሲገጥማቸው የሚያስተካክልና አገልግሎቱ በሚፈለግባቸው ቦታዎች ላይ አገልግሎት ሊሰጥ የሚገባው አካል ምን እየሠራ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉ የተወሰኑ የትራፊክ መብራቶች ካሉም በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ አገልግሎት የሚሰጡት ከስንት አንዴ እንደሆነም እንታዘባለን፡፡

የትራፊክ መብራት ያለመኖር በከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ላይ ሊፈጥር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መገመት አያዳግትም፡፡ በተለይ በክረምት ወቅት የትራፊክ መብራቶችን ተክተው ለማስተናበር ወዲያ ወዲህ የሚሉ የትራፊክ ፖሊሶች በማይኖሩበት ወቅት የከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ተገልጋዮች ሲቸገሩ እያየን ነው፡፡ ለአደጋዎች መባባስም ምክንያት ይሆናል፡፡

በጥቅሉ የመንገድ ግንባታዎች ሲታሰቡ አብረው ሊተከሉ የሚገባቸው የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የትራፊክ ምልክቶችና የተሽከርካሪ ማስተናበሪያ መብራቶች ታሳቢ መደረጋቸው አይቀርም፡፡

የመንገድ ዲዛይኑ እነዚህን አስፈላጊ አገልግሎቶች ሳያካትት አይሠራም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ችግሩ ያለው አስፈጻሚው አካል ላይ ነውና አዲስ አበባችን በምሽት ብርሃን አልባ እየሆነች መንገዶቿም የትራፊክ ማሳለጫ መብራቶችና ምልክቶች የማይታዩባት በመባል እንዳትጠቀስ መፍትሔ ይፈለግ፡፡