መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ሸማች - የማያዋጣ ጉዞ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

‹‹አዲስ ንግድ ለዕድገት›› የሚል መጠርያ የተሰጠው የ2006 አዲስ ዓመት ዋዜማ ንግድ ባለፈው ሳምንት ተከፍቷል፡፡

በየዕለቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጐብኝዎች ያስተናግዳል በሚባለው በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ ከ350 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዓውደ ዓመቱን ተንተርሰው የሚዘጋጁ እንዲህ ዓይነት የንግድ ትዕይንቶች ከሌሎች የንግድ ትርዒቶች የሚለዩት በአመዛኙ ሽያጭ ተኮር በመሆናቸው ነው፡፡ የሆነ ሆኖ በዓውደ ርዕዩ ላይ ከተሳተፉት ኩባንያዎች መካከል አንዳንዶቹ ለተሳትፎም ሆነ ለሽያጭ ይዘው የቀረቡትን ምርቶች እንዳነጣጠረባቸውና አሻግሬ እንድመለከት ገፍተውኛልና፡፡

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በአንዱ አዳራሽ ውስጥ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ከታደሙ ኩባንያዎች መካከል አንዱን ብቻ በምሳሌነት ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ኩባንያው ዲቬያጆት ኢንተርፕራይዝ ይባላል፡፡ ይህ ኩባንያ በዕለቱ ለማስተዋወቅና ለሽያጭ ያቀረበው በተለያዩ ዲዛይኖች የተሠሩ እስክርቢቶዎችን ነው፡፡ 

የኩባንያው ባለቤቶች ህንዳውያን ናቸው፡፡ የዚህን ኩባንያ ምርት በተለየ እንድመለከት ያደረገኝ ደግሞ ለሽያጭ ያቀረባቸው እስክርቢቶዎች እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መመረታቸውን በመረዳቴ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ተመረቱ የተባሉትን እስክርቢቶዎች ለሙከራ ጽፌባቸዋለሁ፡፡  ዕድሜያቸውን እንጃ እንጂ በሙከራዬ ለጽሑፍ የሚመቹ እንደሆኑ አምኛለሁ፡፡ ዋናው ጉዳዬ የእስክርቢቶው የጥራት ደረጃ ወይም ይዘት ስላልሆነ በዚህ ላይ ብዙ ማለት አልፈልግም፡፡ 

ህንዳውያኑ መቼም ቢሆን የገበያው ፍላጐቱ የማይነጥፈውን እስክርቢቶ እዚሁ በማምረት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መግባታቸው ዋናው ነገር ነው፡፡ 

ከልጅነት እስከ ጉርምስና ድረስ በትምህርት ቤትና ከዚያም በሥራ መስክ ያሟጠጣቸውን የእስክርቢቶዎች ብዛት አሰላለሁ፡፡ ያለ እስክርቢቶ የማይንቀሳቀሱ ሚሊዮኖችንም አሰብኩና ለገበያና ለትርፍም የሚያዋጣ ምርት ቢሆንም፣ ለዓመታት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ እየፈሰሰበት ከውጭ ሲጋዝ  የቆየ ምርት ነው፡፡ ከኬንያ የሚገባውን ቢክ ብዙዎቻችን ስንጽፍ አርጅተንበታል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት የሆነ እስክርቢቶ በአንድ ወቅት ተሞክሮ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ሙከራ ብቻ ሳይሆን ‹‹ኢትዮ ቢክ›› በሚል ስያሜ ለገበያ ቀርቦ እንጠቀምበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ዛሬ ግን ‹‹ኢትዮ ቢክ›› የት እንደደረሰ፣ ምርቱ ለምንስ እንደቆመ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ካልተሳሳትኩ ኢትዮ ቢክ የሚለውን እስክርቢቶ ሲያመርት የነበረው መንግሥታዊ ድርጅት ነው፡፡ የግል ድርጅቶች ነገሩን አስበውትም የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ 

ሌላው ቀርቶ ለዘመናት የእስክርቢቶ ምርቶችን ከውጭ ሲያስገቡ የነበሩ ኩባንያዎችም ከማስመጣት ወደማምረት የመዞር ወኔው አልነበራቸውም፡፡ ዛሬ ህንዳውያኑ እንደከፈቱት ዓይነት የእስክርቢቶ ማምረቻ ለመክፈት ግን ዕድሉ ነበራቸው፡፡ የዘለቄታው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ዕድል የነበራቸው የአገር ልጆችን ቀድሞ የህንዱ ኩባንያ እስክርቢቶ ለማምረት ገብቷል፡፡ ምርቱንም አቅርቧል፡፡ 

የእስክርቢቶውን ጉዳይ በዚህ ደረጃ ማንሳቴ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የአገሬ ሰዎች በተለይ ፍራንካ አላቸው የምንላቸው ነጋዴዎች፣ በቀላሉ እዚህ ሊያመርቱት የሚችሉትን ነገር ከውጭ በማስመጣት ብቻ ለትርፍ ወዲህ ወዲያ ሲሉ፣ የውጮቹ ኩባንያዎች እንዲህ ባለው መንገድ እየገቡ መሆኑን ለማስታወስ ጭምር ነው፡፡

በተለይ የእስክርቢቶ አመራረትን የሚያውቁ ሰዎች የሚናገሩት ማምረቻውን ለመትከል የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት እጅግ አነስተኛ መሆኑንና ለምርቱ የሚያስፈልገውም ግብዓት በቀላሉ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡ 

እስክርቢቶ ለማምረት ምን ያህል ይፈጃል በማለት ከወዳጆቼ ጋር ስንወያይ፣ ኢንቨስትመንቱ ጥቂት ገንዘብ የሚጠይቅ አናሳነት ለመግለጽ፣ እንደሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀብታም ለመንሸራሸሪያ የሚጠቀምበትን ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል ለመግዛት እንኳ ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ 

እንዲህ በቀላል ወጪ ሊገነባ የሚችል ማምረቻ ማቋቋም እየተቻለ፣ እስክርቢቶ ከውጭ በገፍ መግባቱ ከንክኖኛል፡፡ ምናልባት የህንዱ ኩባንያ ምርት በገበያ ተወዳዳሪ፣  በጥራቱም ተመራጭ ቢሆን እስክርቢቶ በማስመጣት ብቻ ለዘመናት ሲያተርፉ የነበሩ ኩባንያዎችን ከአገር ውስጡ የውጭ ኩባንያ (ከህንዱ) እስክርቢቶ ገዝተው ለማከፋፈል ይገደዱ ይሆን? የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ ለማንኛውም የአገራችን የቢዝነስና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሲታሰብ እንዲህ በቀላሉ የሚመረቱትን ለማምረት ያለው ተነሳሽነት እጅግ ቀዝቃዛ መሆኑ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡  እርግጥ ለኢቨስትመንቱ ደንቀራ አሠራሮች ተብታቢ መሆናቸው አይካድም፡፡

እስክርቢቶ  እንደምሳሌ ተነሳ እንጂ እዚህ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉና በየዓመቱ ያልተገባ የውጭ ምንዛሪ የሚወጣባቸው ምርቶች በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ሳያንስ  የአገራችን ነጋዴዎች በቀላሉ ሊያመርቱት የሚችሉትን ሸቀጥ የውጭ ኩባንያዎች አጥንተው ዘው ብለው ሲገቡበት የሚያስቆጨው፣ “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” የሚለው ብሒል ሲሠራብን በመታየቱ ጭምር ነው፡፡  

የውጭ ካልሆነ በቀርና ሸቀጡ ሁሉ ምርት ከማዶ ሔደው ካላስመጡና ካላከፋፈሉ ትርፍማነት የማይመስላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሄ ነገር በዚህ ረገድ ያለው ችግር ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት አንድ ሁለት ምሳሌ ላንሳ፡፡ ኢትዮጵያ በቀርከሃ ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን ደረጃ ትይዛለች፡፡ ከቀርከሃ እጅግ ብዙ ቁሳቁሶች ይመረታሉ፡፡ ከብዙዎቹ ምርቶቹ መካከል አንዱ የጥርስ መጐርጐርያው ስቴክኒ ወይም የ‹‹ጥርስ እንጨት›› የምንለው ነው፡፡ 

አሁንም ድረስ ስቴክኒ ከውጭ ይመጣል፡፡ በእርግጥ አንድ አገር በቀል ኩባንያ ስቴክኒ በማምረት ላይ ቢሆንም ከውጭ የሚገባውን አላስቀረውም፡፡ አሁንም ለጥርስ እንጨት  ዶላር እየወጣበት ከቻይና ይመጣል፡፡ 

አዮዳይዝድ ጨውንም እንውሰድ፣  ጨው በገፍ በሚገኝበትና በሚመረትበት ኢትዮጵያ አገር አዮዳይዝ የገባበት ጨው ከውጭ ይገባል፡፡ ከውጭ የሚገባውን አዮዳይዝድ ጨው ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ዕምቅ ሀብት እያለ ከውጭ ማስመጣቱ ሞኝነት ነው፡፡ አስመጪው ግፋ ቢል  ሁለት ሚሊዮን ብር አውጥቶ ጥሩ የአዮዲን ጨው ማምረት ይችል እንደነበር ስታስቡ፣ ምን እየተሠራ ነው አትሉም? እርግጥ አምራቾቹ የአዮኦዲንና ሌሎች ኬሚካሎች የአቅርቦት እግር እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ በአገር ውስጥ በጥራትና በይዘትም ተወዳዳሪ ቢሆኑም፣ ከውጭ የሚገባውን ምርት አለማስቀረታቸው ይገርመኛል፡፡ አዮዳይዝድ ጨው እዚህ እያመረቱ ያሉትን ማበረታታት ሲገባ፣ ለአስመጪው ዶላር መፍቀድስ ተገቢ ነው? ለዚያውም በስንት እዬዬ የሚገኘውን ዶላር?

አንድ ጊዜ ደግሞ ለትምህርት አገልግሎት የሚውል መስመሮችን መሥርያ የሆነው ማስመሪያ እንዴት እንደሚመረት አይቼ ጉድ ብያለሁ፡፡ በእጅጉ አነስተኛ በሆነ ቦታ ላይ የተተከለ ማሽን፣ በጥቂት ጊዜ ብቻ በርካታ ማስመሪያዎችን እየሠራ ሲያወጣ አይቻለሁ፡፡ በበርካታ ሰበቦች ግን ከውጭ ማስመጣቱ ቀጥሏል፡፡ የእርሳስ ፋብሪካ ቢከፈትም ምርቱ በቂ ባለመሆኑ ከውጭ በገፍ ይገባል፡፡ ለትዝብት እየመረጥኩ ለአስረጅነት ተጠቀምኩባቸው እንጂ በቀላሉ እዚሁ የምናመርታቸው ሸቀጦች ቁጥር የትየለሌ ነውና፣ አቅሙና ዕድሉ ያላቸው የአገሬ ሰዎች ይገድደናል ብለው የበለጠ ሊጠቅምና ሊያስመሰግን ወደሚችለው ሥራ ቢገቡስ?

በአጠቃላይ  በአገር ውስጥ በቀላሉ የሚመረቱ እጅግ በርካታ ሸቀጦች ቢኖሩም ጥቃቅኖቹንና ጥቂት ገንዘብ የሚጠይቁትን ግን ደግም ለፍጆታ የሚውሉትን፣ ምርቶች ለማምረት የማይደፍረው ለምን እንደሆነ ብዙ ሳያነገግር አይቀርም፡፡

መንግሥት  እንዲህ ላሉ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ በመላ አገሪቱ ውስጥ ያሉና በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየፈሰሰባቸው ያሉ የአነስተኛና ጥቃቅን ማኅበራት ከተለመደ ሥራ ወጣ ብለው አዋጭ የሆኑ፣ በቀላሉ ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡና የውጭ ምንዛሪ የሚያድኑ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ቢሳተፉ ውጤት ሊገኝ ይችላል፡፡ ለፈጠራ መበረታታትም መንገድ ይከፍታል፡፡ 

ለአንድ አነስተኛ ማኅበር በዓመት የሚሰጠውን ያህል ብድር የማይፈጁ ግን የውጭ ምንዛሪን የሚያድኑ እንደህንዳውያኑ የእስክርቢቶ ፋብሪካ ዓይነቶቹ እንዲከፈቱ ቢደረግ፣ ክፍተቱን በተወሰነ ደረጃ ማጥበብ ይቻላል፡፡ ምኑንም ምናምኑንም እያግበሰበሱ ማስመጣቱ ልጓም ቢበጅለትስ?