መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ሸማች - ድር ያደራባቸው ድረገጾች?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

ድር ያደራባቸው ድረገጾች?

ይብዛም ይነስ ዓለም የደረሰበትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኮሙዩኒኬሽን ውጤቶችን እየተጠቅምን ነው፡፡

በተለይ ዘመናዊ መረጃዎችን ሊያቀብሉን በሚችሉ መሳሪዎች እየተገለገልን ነው፡፡ በኢንተርኔት የተሳሰሩት ኮምፒውተርና ሞባይል ስልኮቻችን ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናዊ መሳሪያዎች ከየትኛውም የዓለም ጥግ የሚለቀቀውን መረጃ በቀላሉ የማግኘት ዕድልም ተጎናጽፈናል፡፡

የቴሌ ኔትወርክ ካልበጠበጠን በቀር በሞባይልና በኮምፒውተራችን ከሌላው ዓለም ጋር የመገናኘት ዕድል አለን፤ ያውም በቅጽበት፡፡ ወቅታዊ የገበያ መረጃዎችን መቀባበልም ተችሏል፡፡ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመስፋፋታቸውም መረጃዎችን በቅጽበት የምንቀበልባቸው መንገዶች እየተዘረጉ ነው፡፡ በግልም ሆነ በኩባንያ ደረጃ መረጃዎችን የምናቀብልበትና የምንቀበልበት ድረገጽ  እየተስፋፋ ነው፡፡ 

የአገራችንን የድረገጽ አገልግሎት በተመለከተ ግን ያለው ክፍተት የሚያስተዛዝብ እየሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ በመንግሥት፣ በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በሙያ ማኅበራት፣ በቢዝነስ ተቋማት፣ በአገልግሎት ሰጪዎች ወዘተ… ድረገጾች እየተስፋፉና እየበረከቱ ነው፡፡ የጎብኞቻቸውን ቁጥር ሳይቀር ይነግሩናል፡፡

የሚያሳዝነው ግን አብዛናዎቹ ድረገጾች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ለዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ተወስኖ ድረገጾች መታነጻቸው አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ አገልግሎታቸውን  ማግኘት ከማይቻልበት ደረጃ መደረሱ ግን ከንቱ ልፋት ሊያሰኘን ይችላል፡፡ 

የድረገጹ መከፈት በዋናነት መረጃ ለመስጠት ነው፡፡ ተገልጋዮች ወይም የድረገጽ ጎብኝዎች የድረገጹ ባለቤት የሆነው ተቋም ያለበትን ደረጃ ለማወቅ፣ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለመገንዘብ ወይም ለሌላ የመረጃ ፍላጎታቸው ጭምር ሊጎበኙት ይችላሉ፡፡  የድረገጹ አንዱ መገለጫም ይኼው ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ድረገጾችን ስንመለከት፣ አብዛኛዎቹ ከሚጠበቅባቸው አገልግሎት ጋር የተጣጣሙ አይደሉም፡፡ ሊሰጡን የሚገባውን መረጃ ባለመስጠት ይታወቃሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ሳስብ ትላልቅ የምንላቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት ሳይቀሩ ድረገጾቻቸው በቂ ወይም ወቅታዊ መረጃ የሌላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዱማ ከታነጸበት ቀን ጀምሮ መረጃው ያልተቀየረለት ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የተጫነ መረጃን ይዞ የሚገኘው በርካታ ነው፡፡ አንዳንዱ ድረገጽ ከፍቻለሁ ለማስባል ያነጸው ይመስላል፡፡ 

አብዛኞቹ ተቋማት ድረገጾቻቸውን እየተከታተሉ አዳዲስ መረጃዎችን የሚጨምሩ ባለሙያዎች እንደሌላቸው ይሰማኛል፡፡ ድረገጽ ይኑር ከተባለ ግን ለዚሁ ሥራ የሚመደብ  ባለሙያ መኖር እንዳለበት አለመታሰቡ፣ አሁን ለምናየው ክፍተት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን እገምታለሁ፡፡

በቅርቡ አንድ ወዳጄ ስለአንድ ትልቅ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ለማወቅ ፈልጎ ድረገጹን ሲጎበኝ ያገኘው መረጃ የቆየ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ በድረገጹ ላይ ያለውን አድራሻ ይዞ ወደተባለው መሥርያ ቤት ሲሄድ ሊያገኘው ባለመቻሉ፣ ያውቃሉ የተባሉ ሰዎችን አጠያይቆ ሊያገኘው መቻሉን ገልጾልኛል፡፡ ድረገጹ ቢያንስ መሥሪያ ቤቱ ቀድሞ ከነበረበት ሥፍራ ወደሌላ ሥፍራ መቀየሩን እንኳ የማይነግረን ከሆነ መኖሩ ለምን ይጠቅማል?

አንዳንድ ድረገጾች የተቋሞቻቸውን አጠቃላይ ማንነትና ስለሚሰጡት አገልግሎት ከመዘርዘር አልፈው፣ የድርጅቶቹን ቦርድ ሰብሳቢ፣ ሥራ አስኪያጅና የሌሎች ሥራ ኃላፊዎችን የስም ዝርዝር ያሰፍራሉ፡፡ ከመሥሪያ ቤቱ ስለሚፈለገው መረጃ ለመስጠት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ጭምር በምስል አስደግፈው ይጭናሉ፡፡ የስልክ ቁጥሮችና የኢሜል አድራሻዎችም ይኖራሉ፡፡ የድረገጹን መረጃዎች ተከታትሎ የመቀየር፣ በአዲስ መረጃ የመተካት ችግር ስላለ ግን ከኃላፊነታቸው የለቀቁ እንደውም የሞቱ የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ በሕይወት እንዳሉ በድረገጹ ላይ ተለጥፈው ሊታዩ ይቻላሉ፡፡ 

የአንድ ድርጅት ድረገጽ ላይ ሁሌም የምመለከተው አንድ መልዕክት አለ፡፡ የሥራ አስኪያጁ መልዕክት ተብሎ የተለጠፈው ጽሑፍ ሦስት ዓመት አልፏታል፡፡ መልዕክቱ የዕድሜ ልክ መሆኑ ባይታወቅም፣ በሦስት ዓመት ውስጥ አለመለወጡ፣ ሌላ ነገር መናገር አይችሉም እንዴ? አሰኝቶኛል፡፡

የድረገጽ አገልግሎት ሁሉንም ወገን በቀላሉ ለማግኘትና መረጃ ለመስጠት የሚጠቅም መሆኑ ባይካድም፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና የግል ድርጅቶች ግን በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገባቸው ስለመሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ድረገጹ በመላው ዓለም ሊጎበኝ፣ ከአገር ገጽታም ጋር ሊያያዝ ይችል ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ አንድ ነገር ማወቅ የሚፈልግ የሰው አገር ሰው፣ ከእነዚህ ድረገጾች መረጃ ወስዶ ሲጠቀም፣ ወቅታዊ ያልሆኑና ያፈጁ መረጃዎች በድረገጽ መለጠፋቸው አሳሳች እንደሚሆኑ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የአገርን ስም ጠቅሰው የሚሠሩ ድረገጾች የራሳቸው ደረጃ ሊኖራቸውም ይገባል፡፡ ዓለም በሚያየው ድረገጽ ላይ የተንሻፈፈ መረጃን በፎቶ አስደግፎ መለጠፍ ለትዝብት ይጋብዛል፡፡ በዚያ ላይ በአስቀያሚ ዲዛይን የታነጹ ድረገጾች ሲሆኑ ደግሞ እንዴት እንደሚያሰለቹ ይታያችሁ? 

የሚለጠፈው መረጃ በባለሙያ የሚዘጋጅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የበቃና የነጠረ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሌላ አገር ሰዎች የሚፈልጓቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ተቋማት ለዲዛይን ብቻም ሳይሆን፣ ለቋንቋቸውም ጭምር መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀም አስቂኝና አስፈሪ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት፣ ድረገጾች ይበልጡን ለትችት ይመቻሉና፣ የቋንቋ ባለሙያ ቢቃኛቸው አይከፋም፡፡ 

 አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ የአስጎብኝ ድርጅቶች ፈቃድ ለማሳደስ ድረገጾቻቸው በአግባቡ ስለመሥራታቸው ይታያል፡፡ ይህ ግዴታ ከሆነ፣ የድረገጾቹ መረጃ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግም ተገቢ ይሆናል፡፡ ወቅታዊ መረጃዎችን የያዙ፣ በየጊዜው የሚታደሱና የተገልጋዩን የመረጃ ፍላጎት በሚመጥን ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

በ2006 ዓ.ም. የአገሪቱ የተለያዩ ድረገጾች የምንጠብቅባቸውን አገልግሎቶች እንዲሰጡን በመመኘት፣ መልካም አዲስ ዓመት!!