መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ይድረስ ለሪፖርተር - በሕግ አምላክ!
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
31 March 2013 ተጻፈ በ 

በሕግ አምላክ!

የካቲት 20 ቀን 2005 ዓ.ም.ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ በአንድ የግል ጉዳዬ ምክንያት በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ4ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ቀጠሮ ነበረኝ፡፡

የፍርድ ቤቱን ቀጠሮ አክብሬ ለመገኘት ከቢሮዬ 7፡00 ሰዓት ላይ ወጣሁኝ፡፡ ሰዓቱ እስኪደርስ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ ላይ ከሚገኝ ካፌ ቡና አዝዤ ጥቂት ደቂቃዎችን በቁዘማ አሳለፍኩኝ፡፡ የቀጠሮው ሰዓት ሲቃረብ ወደ ፍርድ ቤቱ ሕንፃ አመራሁ፡፡

እንደገባው ግን የ4ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት አዳራሽ ሞልቶ ነበር የጠበቀኝ፡፡ የሰዉ ብዛት እያስገረመኝ በኮሪደሩ አንድ ጥግ ላይ ከነበረ አግዳሚ ወንበር ላይ አረፍ እንዳልሁ የችሎቱ አስተናባሪ ከተጠቀሰው የችሎት ማስቻያ ሰዓት ጥቂት ዘግይቶ በየተራ የባለጉዳዮችን በመጥራት ወደ ችሎቱ ክፍል ያስገባ ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታ የጀመረው የችሎቱ ውሎ እስከ 10፡00 ሰዓት ድረስ ቀጠሏል፡፡ እስከዚህ ሰዓት ድረስ የመጠራት ዕድል አልገጠመኝም ነበርና ሞልቶ ከፈሰሰው የችሎቱ አዳራሽ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ተስተናግዶ የሄደውን ሰው ባዶ ወንበር ስቆጥረው እጅግ ጥቂት በመሆኑ በዕለቱ የመስተናገዴን ነገር ወዲያውኑ ጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገባሁት፡፡ ‹‹መጣሁ!›› ብዬ ለሥራ ባልደረቦቼ ነግሬ ከቢሮዬ የወጣሁት ሰውዬ፣ ወደ ሥራ ገበታዬ የምመለሰው ‹‹ነገ›› ጠዋት እንዳይሆን እየሰጋሁ መጨረሻዬን ለማየት ጥበቃዬን ቀጠልኩ፡፡

የችሎቱ አስተናባሪ ቀደም ሲል ባላደረገው አኳኋን ጥቂት የተደራረቡ ፋይሎችን ይዞ ወጣና የባለጉዳዮችን ስም መጥራት ጀመረ፡፡ ከተጠሩት ግለሰቦች መካከል ሦስቱ በአዳራሹ አልተገኙም፡፡ አስተናባሪው ወደ ችሎቱ ተመልሶ ገብቶ ሌሎች ፋይሎችን ይዞ ወዲያው ተመለሰና ተጣርቶ ባጣቸው ሰዎች ምትክ እንዳመጣቸው የጠረጠርኳቸው ፋይሎች ላይ ያሉትን ስሞች መጣራት ጀመረ፡፡

 አንዱ እኔ ነበርኩኝ፡፡ ሦስቱ ተተኪ ሰዎች መኖራችንን ካረጋገጠ በኋላ ቀደም ብሎ በጠራው ላይ ሦስታችንን አክሎ በድምሩ ከጠራን አሥር ሰዎች በስተቀር፣ ሌሎቹ ለቀጣዩ ሳምንት እንዲመጡ ዳኛዋ ቀጠሮ መስጠታቸውን ገለጸ፡፡ አዳራሹ ወዲያውኑ በጫጫታና በሁካታ ተሞላ፡፡ የችሎቱ አስተናባሪ ሰዉን ለማረጋጋት በአዳራሹ ውስጥ የገጠመው ፈተና ብርቱ ነበር፡፡ አስተናባሪው ስለእውነት ትሁት ሰው ነው፡፡ በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ችሎቱ በአንድ ዳኛ እየተካሄደ ያለ መሆኑንና ይህም በፍርድ ቤቱ በተከሰተ የዳኛ እጥረት የተነሳ መሆኑን በማስረዳት ሰውን ለማግባባት ይሞክር ጀመር፡፡

እርግጥ በጎደለ ሰው እግር ተተክቼ ዳኛዋ ዘንድ ቀርቤ ሌላ ቀጠሮ የተሰጠኝ ቢሆንም፣ ለተከበረው ፍርድ ቤት በትህትና ማቅረብ የምፈልጋቸው ጥያቄዎች ግን ነበሩኝ፡፡ እነዚህም ብዛት ያለውን ሰው በአንድ ዳኛ እንዲዳኝ ግማሽ ቀን ሙሉ ሰብስቦና አስቀምጦ ማዋል ሳያንስ፣ የማታ ማታ ‹‹ልናስተናግዳችሁ አልቻልንም እና ለሌላ ቀን ኑ!›› ብሎ መበተን ፍትሐዊ አሠራር ነው ሆኖ ይታሰብ ይሆን? በቀጣዩስ፣ በተለዋጭም ይሁን በመደበኛ ቀጠሮ ልንስተናገድ ስለመቻላችን ምን ዋስትና አለን? በአንድ ዳኛ፣ በግማሽ ቀን ሊሰተናገድ የሚችለውን ሰው ብዛት አስቀድሞ ለመገመት የሚከብድ ነገር ሆኖ ነው መሰል ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት በከንቱ ሙልጭ እያሉ ሲባክኑ የሚውሉት!? . . . ኧረ በሕግ አምላክ!
ጌታነህ አ. (ከጀሞ ሚካኤል)
**  **   **

ተግባራዊ ዕርምጃ እንሻለን
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚንያ ለመዋጋት ባደረገው ዘመቻ አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገቡን በመጠቆም ለበለጠ ውጤት ጠንክሮ እንደሚሠራ እየገለጸ ይገኛል፡፡ ሆኖም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ግን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባሮች እውን ለማድረግ ዝግጁ ያለሆነና መተግበር የማይችል መሆኑን ለማሳየት መረጃዎችን እነሆ ለማለት ፈለግን፡፡ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማም ሆነ በሥሩ የሚገኙ ወረዳዎች ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› የሚለውን መፈክር ከመለጠፍ ውጪ ትግበራው ላይ ዜሮ ናቸው፡፡

ይኸውም 1. መንግሥት ያስቀመጠውን የሥራ ሰዓት አያከብሩም፤
2. ለጉዳዮች በአግባቡ ምላሽ አይሰጡም፤
3. ባለጉዳዮችን በነገ ዛሬ ቀጠሮ የሚያንገላቱ ናቸው፤
4. አስተያየት የሚሰጠውንና ጥያቄ የሚጠይቀውን ሁሉ በተቃዋሚነት በመፈረጅ ማሸማቀቅ ዋነኛ ተግባራቸው ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በየወረዳው የተመደቡ የፍትሕ አካላትም እንዲሁ፤ ብቃት የሌላቸው፣ ሰዓት አክብረው በሥራ ገበታቸው ላይ የማይገኙ፣ ራሳቸው የሰጡትን ቀጠሮ ዕለቱንና ሰዓቱን በአግባቡ የማያስተውሉ፤ ባለጉዳዩን በቀጠሩበት ሰዓት ባለመገኘት፣ ሰበብ እያበዙ ቀጠሮ ማራዘምን ሥራዬ ብለው የያዙ ናቸው፡፡ ለይስሙላ ባስቀመጡት የአስተያየት መስጫ፣ አስተያየት ሲሰጣቸው መቀበልም፣ መተግባርም የማይችሉ ናቸው፡፡

እኛ እናውቃለን የሚሉ መሆናቸውን ስንመለከት፣ የአስተዳድሩን የእርምት ዕርምጃ አሰናካይ በመሆናቸው ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ያድርግ እያልን፣ እንደተቀረው የመዲናችን ነዋሪ፣እኛ የመልካም አስተዳደር ትሩፋቶችን ለማግኘት ይቻለን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች
**  **   **

‹‹በዘመነ ግልፀት ይቅር ድብቅነት!››
አንድ ወዳጄ ‹‹ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ጊዜ ‘ዓመተ ዓለም’፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ደግሞ ‘ዓመተ ምሕረት’ ተብሎ በሁለት ዘመን ብቻ መከፈሉ አይመቸኝም፡፡ አሁን ሦስተኛው ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ‘ዓመተ ግልፀት’ መባል አለበት፤›› ብሎ ያጫወተኝ ሁልጊዜ ከአዕምሮዬ አይጠፋም፡፡ የመረጃ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት፣ በግሎባላይዜሽን አስተሳሰብ ዓለም ወደ አንድ መንገድ እየመጣች ያለችበት ጊዜ ላይ በመድረሳችን ዓመተ ግልፀት የሚለው ቃል እንደተጠበቀ ሆኖ ለጽሑፌ እንዲያመቸኝ እኔ ደግሞ ‹‹ዘመነ ግልፀት›› ብዬዋለሁ፡፡

ወደዋናው ጉዳዬ ስገባ፣ በአገራችን ጤና፣ ስፖርት፣ ትምህርት ወዘተ ለማስፋፋት፣ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ሰላም ለማስከበር፣ እንዲሁም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መንግሥት ከሚያደርገው ርብርብ በተጨማሪ ኅብረተሰቡን በማስተባበር በተለያዩ ጊዜያት ገቢ የማሰባሰብ ፕሮግራሞች ሲካሄዱ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ወዳድ በመሆኑ ለተለያዩ ጉዳዮች ዕርዳታ ሲጠየቅ በፈቃደኝነት አቅሙ የቻለውን ያህል በመለገስ ሕዝባዊነቱንና ወገናዊነቱን ከማሳየት ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፣ በሁለተኛው ምዕተ ዓመት (ሚሌኒየም) ክብረ በዓል፣ ልመና ይብቃ ለተባለው ፕሮግራም፣ ለአትሌቲክስ መንደር ምሥረታ፣ ለሕፃናት የልብ ሕሙማን ሆስፒታል፣ ለህዳሴ ግድብ፣ ለለንደን ኦሊምፒክ ወድድር፣ ለአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ጊዜ (ለብሔራዊ ቡድኑ) የተዋጣውን ገንዘብ ማንሳት ይቻላል፡፡

በቴሌቶን፣ በመዋጮ፣ በቦንድ ግዥ፣ በልዩ ሎተሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በSMS ዘዴዎች ገቢ የማሰባሰብ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደተሰበሰበ፣ ስንቱ ሥራ ላይ እንደዋለ፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደቀረ፣ በቀጣይ ለምን ተግባር ሊውል እንደታቀደ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ሕዝቡ በተከታታይ እንዲያገኝና በግልጽ እንዲያውቀው ሲደረግ ግን አይስተዋልም፡፡
ሕዝቡ በመንግሥታዊ መሥርያ ቤቶች፣ በልማት ድርጅቶች፣ በብሔራዊ ኮሚቴዎች፣ በፌዴሬሽኖች፣ በሕዝባዊ ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙኅን በመሳሰሉት አካላት ላይ እምነት እንዲኖረው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እስካለ ድረስ ዜጐች ሕገ መንግሥቱ የፈቀደላቸውን መረጃ የማግኘት መብት ሊነፈጉ አይገባም የሚል እምነት አለኝ፡፡ የመረጃ ነፃነት ከዚህ ይጀምራልና፡፡
በዘመነ ግልፀት፣ የምን ድብቅነት ነው?አቦ!
ቸር እንሰንብት
ኬኩ ነኝ (ከመነን አካባቢ)
**  **   **


‹‹የሠራተኞች ድርጅት መቀያየር የጡረታ መብታቸውን አያሳጣም፣ የአቅድ አባልነት ካርድ ማግኘትም መብታቸው ነው››
ባለፈው እሑድ፣ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ ባወጣው እትም ላይ ‹‹ጡረታችን የት ነው የሚገባው?›› በሚል ርዕስ፣ በአንድ የግል ሪል ስቴት ድርጅት ውስጥ በግንበኛ ፎርማንነት ተቀጥረው የሚሠሩ ግለሰብን አስመልክቶ የወጣ ዘገባ ላይ ለመረዳት እንደቻልነው፣ በድርጅቱ አሠሪዎችና በአስተያየት ሰጪው ግለሰብ መካከል የግንዛቤ እጠረት አለ፡፡ የግል ድርጅቶችን ሠራተኞች የጡረታ መብት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 715/2003 ዓ.ም. እንደተቀመጠው፣ ከሰኔ 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ፕሮግራም ሽፋን እንዳላቸው አስፍሯል፡፡

በዚህ መሠረት በዕቅዱ የሚታቀፉ የግል ድርጅቶች በሙሉ ድርጅታቸውንና ሠራተኞቻቸውን የማስመዝገብና የምዝገባ መረጃዎችን አደራጅቶ የመያዝ እንዲሁም የሠራተኞችንና የድርጅቱን የጡረታ መዋጮ በአዋጁ ላይ በተቀመጠው መጠንና ጊዜ ኤጀንሲው ሕጋዊ ውክልና ለሰጠው ገቢ ሰብሳቢ አካል ገቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይሁንና ቅሬታ አቅራቢው ባለመብት እንደገለጹት፣ አንዳንድ አሠሪ ድርጅቶች ከአዋጁ ድንጋጌ በመውጣት ድርጅታቸውንና በድርጅታቸው ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ዜጎችን እንዳላስመዝገቡ እንዲሁም ከሠራተኞች የተሰበሰበውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ እንዳላደረጉ ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ጥቆማዎች እየደረሱት፣ ኤጀንሲው በሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በኩል እየተከታተለው ይገኛል፡፡
አሠሪ ድርጅቶች በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን የጡረታ መዋጮ መጠን ከሠራተኞተ የወር ደመወዝ ተቀናሽ በማድረግና የራሳቸውን ድርሻ በመጨመር ኤጀንሲው የጡረታ መዋጮ እንዲሰበሰብለት ሕጋዊ ውክልና ለሰጠው አካል ማስገባት፣ ድርጅቱንና ሠራተኛውን የማስመዝገብ ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ይህንአለማድረግም በሕግ እንደሚያስጠይቅ ይታወቃል፡፡ ሠራተኛውም በማኅበራዊ ዋስትና አቅድ ስለመታቀፉ ማረጋገጫ የዕቅድ አባልነት ካርድ እንደሚሰጥ በመረዳት ተገቢውን ቅጽ መሙላት ይጠበቅበታል፡፡ ሰለዚህ ጠቋሚው መብቱን ለማስከበር ቅሬታውን ለኤጀንሲው ቢያቀርብ ኤጀንሲው አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ማስተካከያ እንደሚያደርግ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ኤጀንሲ