መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ይድረስ ለሪፖርተር - በእጅ የያዙት ወርቅ…
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
25 August 2013 ተጻፈ በ 

በእጅ የያዙት ወርቅ…

ይህ ጽሑፍ የሚያትተው ማዘጋጃ ቤት አካባቢ ስለሚገኘው የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልትና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሐውልቱ ዙሪያ ሰማዕቱን ለማሰብ እየታተሩ ስለነበሩ ወጣቶችና የአካባቢውን ድባብ ለማሳየት ነው፡፡

ይህን ከማተቴ በፊት ግን ልገልጸው የፈለኩትን ነገር አጉልቶ ለማሳየት በሌላ መንገድ ለመግለጽ ብሞክር የተሻለ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ 

በኢትዮጵያ ሰዎች ሠርግ ወይም ፓርቲ ላይ እንዲታደሙ ሲጠሩ በጥሪው ሰዓት ያለመገኘታቸው እንዳለ ሆኖ፣ ከሠርግ ይልቅ የቀብር ሥርዓት ላይ በዛ ብሎና ሰዓት አክብሮ መገኘት የተለመደ ነው፡፡ አሳጥሬ ለመግለጽ የፈለኩት ነገር ከላይ በመግቢያው እንዳስታወቅኩት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ጉዳይ ለማውሳት ሆኖ፤ በይበልጥ ግን የሐውልቱ ለጊዜው ከቦታው መነሳት ጋር በተያያዘ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ላይ ‹‹እኔ ጦማረኛ ነኝ›› ያለ ሁሉ ሲረባረብ ማየቴ በእጅጉ አስገርሞኝ ነው፡፡ 

ይህ ሁሉ ታዳሚ ስሜቱ ተቆርቋሪነትና አክብሮት ከሆነ እሰየው፡፡ ግን እስከዛሬ የት ነበር? ያው እንግዲህ አንድ ሰው በሕመም ወይም በችግር ላይ ሳለ ሳይሆን ከሞተ በኋላ ከንፈር መምጠጥ ልማዳችን ሆኖ ካልሆነ በስተቀር፣ ሐውልቱ ከቦታው ለጊዜው በሚነሳበት ጊዜ በስፍራው የነበረው የሕዝብ ብዛት ከላይ የገለጽኩትን መልካችንን ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ አይመስላችሁም? ሐውልቱ በመንገድ ልማት ምክንያት ለጊዜው ሲነሳ በሆነው ባልሆነው ምክንያት መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ልማዳችን ብዙ ነገር ብለናል፡፡ ግን እኛ ምን አድርገን እናውቃለን?

ቀደም ብሎ የሰማዕቱን ሐውልት ለመንከባከብ ልባችን ከልብ ቢያስብ ኖሮ ኪሳችንን ምንም ሳንጎዳ ልንሠራው የምንችለው ነገር ነበር፡፡ ግን እኛ ነቢያቶቻችንን ብዙ የምናከብር አይደለንምና ልንሠራቸው ስንችል ሳንሠራቸው ቀርተን የተውናቸው ብዙ የቤት ሥራ ዕዳ ያሉብን ሰዎች ነን፡፡ 

ይህን ሁሉ ስል በዋናነት ለመጻፍ ስለፈለኩት በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዙሪያ ተገኝተው እንዳቅማቸው ሰማዕቱን ለመዘከር ስለሚሞክሩት ወጣቶች ለመናገር ነውና ወደዚያው ላቅና፡፡ 

ለምሳሌ አምና ሐምሌ 22 ቀን 2004 ዓ.ም. ታላቁ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ እጅግ ንጹሕ ደማቸው በግፍ የፈሰሰበት 76ኛ ዓመታቸውና መታሰቢያ ሐውልታቸው የቆመበት 71ኛ ዓመት ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ እንዳቅማችን ሰማዕቱን ለመዘከር በቁጥር ጥቂት የምንሆን ሰዎች ከያለንበት ተደዋውለን ሐውልቱ ካለበት ሥፍራ እንገናኛለን፡፡ ብዙዎቻችን አጋጣሚው ያሰባሰበን እንጂ በቅርበት የምንተዋወቅ አይደለንም፡፡ 

አምና እኔም በዚሁ ቀን ከቀኑ አሥር ሰዓት ላይ በቦታው ስገኝ ቀድመው የተገኙት አንድ ወጣት ልጅ፣ አንዲት እህት ከካህን ባለቤቷ ጋርና በየዓመቱ ከእኛ ጋር ሻማ በማብራት የሚያከብረው ትንሹ ልጃቸው ነው፡፡ ይህን ቀን በየዓመቱ ስናከብር ይቺ እህት ድፎ ዳቦ ጋግራ ማምጣቷ የተለመደ ነው፡፡ የአበባ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱም ተስተጓጉሎ አያውቅም፡፡ ሻማ ማብራቱና መታሰቢያ ፎቶ መነሳቱም እንዲሁ፡፡ 

እናም በዕለቱ ሐውልቱ ወዳለበት ጊቢ ስንዘልቅ ግርምት ፈጣሪ ስለነበረው ነገር ልግለጽ፤ ታዋቂው የአገራችን ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ስለ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ መዘከር የሚናገረውን ታዋቂ ግጥሙን የጻፈበትን ምክንያት ሲናገር፣ ‹‹አንድ ሰካራም በእሱ አገላለጽ (ጀብራሬ) ሐውልቱ ላይ ሲሸና በማየቴና በመቆጨቴ ነው፤›› ብሎ ነበር፡፡ 

እኛም ወደ ጊቢው ዘልቀን ሁኔታዎችን ለመቃኘት ስንሞክር፣ ይግረማችሁ ብሎ ሐውልቱ ሥር ዓይነ ምድር ተከምሮ አየን፡፡ በጣም አዘንን፤ በሕሊናችን የኋሊት ተጉዘን አባቶችና እናቶቻችን ስለ አገር ክብር ብለው የሆኑትን አሰብን፡፡ ወደፊት ደግሞ በምናብ ተጉዘን መፃኢው ዘመን ምን ያመጣ ይሆን? ብለን አሰብን፡፡ እናም ፀጋዬ በዚህ ዘመን ኖረህ ይህን ጉድ አይተህ ቢሆን ኖሮ ምን ትል ይሆን? ምን ትጽፍ ይሆን? ብለን አሰብን፡፡

ይበልጥ ያስገረመን ደግሞ ይህ ቆሻሻ ነገር እዚያ የተከበረ ሐውልት እግር ሥር መገኘቱ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ሐውልቱ ሥር ለመጸዳዳት የሚችለው ወደኋላ ተንደርድሮ በከፍታ ዝላይ ቦታው ላይ መቆም ሲችል ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሐውልቱን ዘመናዊ አድርጎ ለማሳመር ሐውልቱ ዙሪያውን ከቦ ያለ ጐድጓዳ ቦታና በጣም በቆሻሻ ውኃ የተሞላ ስለሆነ ነው፡፡ ወቅቱም ክረምት መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡ 

አካባቢው ላይ ያለውን ቆሻሻ መጥረጊያ ገዝተን የቻልነውን ያህል እዚያው ባለው ቆሻሻ ውኃ አፀዳነው፡፡ የአበባ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱን ያካሄድነው በአካባቢው ላይ አትክልት ከሚሸጡ ሰዎች ሦስት ሳጥኖች ተውሰን፣ በቆሻሻው ውኃ ላይ በማኖርና በሳጥኑ ላይ በጥንቃቄ በመራመድ ነበር፡፡ 

ከዚህ በኋላ ከላይ በገለጽኳቸው ካህን ሰማዕቱን እንድናስብና እዚያ እንድንገኝ የፈቀደልንን ፈጣሪ እንድናመሰግን ቡራኬ ተደርጎ፣ ዳቦ ተቆርሶ እየበላን ትንሽም ቢሆን የሚያምር ድባብ ለመፍጠር ሞከርን፡፡ 

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ስለ ሰማዕቱ የጻፈው ታዋቂ ግጥሙ በመነባንብ መልክ ከቀረበ በኋላ ፕሮግራሙ አበቃ፡፡ በዕለቱ የነበሩ ሰዎች ቁጥር 15 ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ 

በዚህ ዓመት ደግሞ ሐምሌ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ሐውልቱ በባቡር መንገድ ግንባታ ምክንያት ከቦታው ላይ በክብር ተነስቶ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም ስለተወሰደ፣ የዘንድሮውን በዓል ያደረግነው በገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሚገኘው የሙዚየሙ ጊቢ ውስጥ ነበር፡፡ የመጀመርያው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እንደሆነ የሚነገርለት ሐውልት እዚያ ስለሚገኝ፣ በሐውልት ዙሪያ በቁጥር ሦስት ወንዶችና አንድ እህት በየዓመቱ ሻማ በማብራት ከሚያከብረው ትንሹ ልጇ በተጨማሪ እዚያው ካገኘናቸው ሁለት የቤተ ክርስቲያኑ ሰዎች ጋር አበባ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱን ፈጸምን፡፡ 

ታዲያ እውነት ለሰማዕቱ እውነተኛ አክብሮት ከነበራቸው ሐውልቱ የተነሳ ዕለት የነበሩት ግለሰቦች ወዴት ሄዱ? በየጋዜጣውና በየመጽሔቱስ ብዕራቸውን ያሾሉት ጦማረኛዎችስ ምነው ሐውልቱን በንፅሕና እንዲጠበቅ ቢያደርጉት? ለማንኛውም እኔ ትዝብቴን እንካቹህ ብያለሁ፡፡ 

(ተክለ ወልድ ደበሌ፣ ከአዲስ አበባ)

*****************

ከራስ በላይ ነፋስ ቢነፍስስ?

ትልልቅ የንግድ ተቋማትና ማንኛውም ነጋዴ እስካዋጣው ድረስ የፈለገው ዘርፍ ላይ የመሰማራት መብት አለው፡፡ የእኔ አስተያየት ግን አንዳንድ ባለሀብቶች ትልልቅ ካፒታል ይዘው ባለማወቅ ይሁን በግድ የለሽነት ብቻ በአነስተኛ ሥራዎች ላይ ከትናንሽ ነጋዴዎች ጋር አላግባብ ሲወዳደሩ ይታያል፡፡ 

ይህ ከንግድ ሕጉ አንፃር እንዴት ይታያል? ለአገሪቱም አስተዋጽኦ በሚያበረክቱበት ደረጃ ቢሠሩ ምን አለ? በትልልቅ ድርጅቶች ዘንድ ሁሉንም ሥራ በድርጅት መዋቅር ጠቅልሎ መያዝ ቢቀርስ፡፡ በተለይም ከኮንስትራክሽንና ከነዳጅ ማደያዎች ትምህርት ቢወሰድስ መልካም ነው እላለሁ፡፡ 

አንድ ትልቅ ኮንትራክተር ሥራውን ከሠራ በኋላ ወደ ሌላ ግንባታ የሰው ኃይሉን በማዘዋወር የቀሩትን ትንንሽ ሥራዎች ለምሳሌ፣ ግንብ፣ ልስን፣ ሴራሚክ፣ ቀለም ወዘተ. ሥራዎችን ለትናንሽ ኮንትራክተሮች ይሰጣል፡፡ ሥራውን እየተቆጣጠረም የአሠሪውን ጊዜ ይቆጥባል፡፡ በዚህም ሥራ ከመፍጠሩ ባሻገር ለትንሹ ነጋዴ የሀብት ክፍፍል እንዲደርሰው ያደርጋል፡፡ 

አንድ የነዳጅ ኩባንያም ሥራውን በጨረታ ያስተላልፋል እንጂ ራሱ አይቸረችርም፡፡ ከዚህ ተምረን ውስኑን ሀብታችንን በሚገባው ቦታ እየተጠቀምን፣ አገራችንን ራሳችንንና ሌሎችንም እንጥቀም፡፡ ከሁለቱ ዘርፎች ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ተሞክሮ ተወስዶ ሌሎችም ዘርፎች ላይ ቢንፀባረቅ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ 

(አቤል ሰይፉ፣ ከአዲስ አበባ)