መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ይድረስ ለሪፖርተር - ፕሬዚዳንትነት ተገቢ ክብርና ዋጋ ይሰጠው
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

ፕሬዚዳንትነት ተገቢ ክብርና ዋጋ ይሰጠው

ስለ መጭው የአገራችን ፕሬዚዳንት አመራረጥ ባወጣችሁ ጽሑፍ ከሚታሰቡት ሰዎች መካከል የተወሰኑት በእውነትም የሚያወዳድር ብቃት ያላቸው ይመስለኛል፡፡

ብቃት ስል ደግም በእውቀትም፣ ከቤተሰብም እስከ ሥራው መስክ ባሳይዋቸው የማስተዳደር ችሎታ፣ በሕዝብ ዘንድ ባላቸው ከበሬታ፣ በሙሉ ጤንነት ተንቀሳቅሰው አገርና ሕዝብን እየወከሉ በማስተባበር ለዕድገትና ልማት ጥረቶች የሚያግዙ በመሆናቸው ማለት ነው፡፡

ከእነዚህ መሰል መለኪያዎች አንፃር፣ ስማቸው ከተነሱት መካከል አንዳንዶቹ   ሚዛን የሚደፋ ካለመሆኑም በላይ ቦታውን እንደ መጨረሻ ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ  የሚሹት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ አቶ ቡልቻ ደመቅሳን፣ አቶ ብርሃኑ ደሬሳን፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች በተለያየ መንገድ በሦስት መንግሥታት ዘመን ዘዴና አቅዋም እያቀያየሩ የተቀመጡ፣ ባመዛኙም ከግል ምቾት ባሻገር ይህ ነው የሚባል ማኅበራዊ ፋይዳ ያላበረከቱ ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ፍላጎታቸው ዝናና ምቾት እንጂ ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ ነገር ያስገኛሉ ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል፡፡

ለመሆኑ አቶ ቡልቻ ፕሬዚዳንት ቢሆኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳደረጉት፣ በኦሮሚኛ አስተርጓሚ ቅጠሩልኝ ሊሉን ነው ወይስ ለእሳቸው የምንልከውን አቤቱታ ሆነ ሌላ ጉዳይ ለማስተርጐም ልንሯሯጥ?

አቶ ብርሃነ ደሬሳ አድብተው እያለሳለሱ በመቅረብ ክፍተት ሲገኝ ራሳቸውን ለሚገኘው ሹመት ማቅረብ የለመዱ ናቸው፡፡ አሁንም በየመድረኩ አንዴ በኒው ዮርክ በተራ የኤምሳሲ ሠራተኛነት የቆዩበትን ጊዜ አምባሳደር እንደነበሩ በማስመሰል ራሳቸውን እየካቡ የድርጅቱም ኤክስፐርት ለመሆን ይሞክራሉ፡፡ በቅርቡ እንኳን ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ጉዳይ በተደረገ ስብሰባ ላይ ራሳቸውን “አምባሳደር” ብለው ሲያቀርቡና ሲያስብሉ ተስተውለዋል፡፡ አለ በሚባለው የቀድሞ አምባሳደሮች ማኅበርም  “አምባሳደር ነኝ” ብለው እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል፡፡ እውነተኛ አምባሳደሮች ደግሞ በይሉኝታ ዝም ብለው ማስተናገድ መርጠዋል፡፡ ጉዳዮቹን የሚያውቁት እንደሚነግሩ ግን አቶ ብርሃኑ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የሠሩት መጀመርያ ኦፊሰር “ሴክሬታሪ” በዓለም ባንክ ደግሞ በዴስክ ደረጃ እንደነበረ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ሁኔታቸውን የታዘቡ “ሰውዬው እኮ ጡረተኛ ናቸው፤ በዚህ ዕድሜ ደግሞ ምን ቢከጅሉ ነው እንዲህ የሚሆኑት?” ሲባሉ መልሰው፣ “አይ ከንቲባነቱ እንዴት እንደተገኘና ምንስ እንደፈየደ እናስታውሳለን፡፡ አሁን ደግሞ ዕድሜ የማይገባው ፕሬዚዳንትነት አለኮ፤” በማለት ጠቆም ያደረጉን ትዝ አለኝ፡፡ ለነገሩ አቶ ብርሃኑ ለፕሬዚዳንትነት ራሳቸውን ካጩና ደጅ መጥናት ከፈለጉ መብታቸው ነው፤ ውሳኔውንም ለሚመለከታቸውና ተሰሚነትቱ ላላቸው እንተው፡፡ በዚህ ዕድሜና ባጋጣሚ የተመቻቸላቸውን የጡረታ ዘመን ከማጣጣም ይልቅ አሁንም ያልበረደ የሹመት ጥማት (አምቢሽን) ካላቸው መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው፡፡ ግን ለዚህም ሆነ በሌላ ምክንያት መረጃና ታሪክ አያዛቡ፤ ሳያስፈልግ በሁሉም ቦታ አለሁ በሚል እየባከኑም ትዝብት አይጋብዙ! 

እንደ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ያሉት ደግሞ ሁኔታዎች ያመቻቹላቸውን ሀብትና የገፋው ዕድሜያቸው የሚፈቅድላቸውን የዕረፍት ጊዜ በሌላ መልክና ቦታ ይወጡ እንጂ ቤተ መንግሥቱን ለዚህ ባይመኙት ጥሩ ነው፡፡ ምናልባትም በለመዱት የንግዱ ዓለም ጡረታቸውን ቢቀጥሉ የተሻለ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ እገምታለሁ፡፡

በተረፈ ሰዎች ሲሸመግሉ ዋናዎቹን መድረኮች ለባለ ዕድሜና ጊዜ መልቀቅ መልመድ ይገባል፡፡ ካለዚያ ራስም ደክሞ ሥራዎችንም መበደል፣ ሰውንም ማሰልቸት ይሆናልና ሁሉም አዛውንት በጥሞና ያስቡበት፤ መራጮቻቸውም እንዲሁ፡፡

በሌላ በኩል እንደ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ዓይነቱን ደግሞ ባይቸኩልና በዕድሜም ሆነ በችሎታ በሚበስሉበት ጊዜ ቢታሰቡ ይሻላል፡፡ እስቲ የምክር ቤት አባልነቱ ሆኖለት በዚያ እንየውና ለፕሬዚዳንትነቱ ይደርሳል፡፡ በሩጫው ሜዳ ያሳየው በፖለቲካ መድረክም ከተስተዋለ ያኔ እሱ አስቡኝ ሳይል ሕዝቡና የሚመለከታቸው መራጮ ይፈልጉታል፡፡

እንግዲህ ሌሎችንም እንዲሁ በጥንቃቄ መመዘን እንጂ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ምንም እንኳን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ባይሆንም የብሔራዊ ክብር መገለጫና ብዙ ፋይዳም ያላቸው ሚናዎችን ሊይዝ ስለሚችል ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይም በበጐ ሥራቸው፣ በሥነ ምግባራቸውና በችሎታቸው ዓርአያ የሚሆኑትን በጥሞና መምረጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ያልጎለመሱ ሰዎች ማሠልጠኛ ወይም ያበቁ አዛውንት መጠገኛ (ሪሳይክል ማድረጊያ) እንዳይደረግ ይታሰብበት እላለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሌሎቹን መመዘኛዎች የሚያሟሉ ሴቶችና በብሔረሰብም ስብጥር እስካሁን ያልተወከሉ ወገኖች ቢሆኑ ሚዛናዊነቱ የተሟላ እንደሚያደርገው ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

(ዘውዴ መንገሻ፣ ከአዲስ አበባ)

**********************

‹‹አንድ ሰው ያሠለጠናቸው የአዳማ ባጃጅ ሹፌሮች››

አዳማ ከተማ ከዓመታት በፊት በቁጥር ጥቂት የነበሩና ከተማዋን ያደመቋት ባጃጅ ተሽከርካሪዎች፣ ዛሬ ላይ እንደበረሮ ተባዝተው ቁጥራቸው ከ3,500 በላይ ደርሰው  የከተማዋን መንገዶች ወረውት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ባጃጆች ጥቅም የጐላ ለመሆኑ ባጠየያይቅም፣ ጉዳታቸውም የዛኑ ያህል ነው፡፡ ማንኛውም ተሽከርካሪ ለእግረኞች ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት የሚታወቅና ግዴታም ጭምር ቢሆንም፣ እነሱ ቆመው ሕፃናትንና አረጋውያንን በትዕግሥት መንገድ እንዲያቋርጡ እንደማድረግ የተገላቢጦሽ መንገድ ለማቋረጥ የሚንቀሳቀሰው ሰው ቆሞ ባጃጆቹን ሲያሰልፍ መታየት ከጀመረ ውሎ ሰንብቷል፡፡ ይህ አዳማ ላይ ግዴታ ሆኗል፡፡ ይህን ጥሶ መንገዱን በድፍረት ለማቋረጥ የደፈረ ሰው ቀጣይ ዕጣ ፈንታው መገጨት ነው፡፡ ይህ በተደጋጋሚ በአዳማ ነዋሪዎች ላይ የተከሰተ በመሆኑ፣ ቅድሚያ ለሰው የተባለው ሕግ ቅድሚያ ለባጃጅ ከሆነ ውሎ ሰንብቷል፡፡ 

እንደውም አሁን አሁን መንጃ ፈቃድ ሲሰጣቸው መንገድ የሚሻገር ሰው ሲያጋጥማችሁ ቆማችሁ እንዳታሳልፉ፣ ቢቻል እንደውም መንገድ ወደሚያቋርጠው ሰው ስትጠጉ ፍጥነት ጨምሩ የሚል አደራና ቃለ መሐላ የፈጸሙ ይመስላል፡፡ በተለይ ዜብራ ማቋረጫ ላይ ሲደርሱ ዙሩን አክርሩ ተብለው እንደታዘዙ አትሌቶች ፍጥነታቸው አስገራሚ እየሆነ መጥቷል፡፡ ድንገት ያቋረጣቸው እግረኛም ካጋጠማቸው የስድብ ናዳ ይወርድበታል፡፡

 ሌላው በጣም የሚገርመው ግን የሁሉም ባጃጆች አሠልጣኝ አንድ ሰው ይሆን ማስባሉ ነው፡፡ ንቀታቸው፣ ዓመላቸው፣ ስድባቸው፣ ግልምጫቸው፣ ፍጥነታቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን በሥነ ምግባራቸውና በችሎታቸው የማመሰግናቸው መልካም የባጃጅ ሹፌሮች መኖራቸውን ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡ በተለይም ከመናኸሪያ በሥላሴ ገንደሃራ የሚሄዱት የባጃጅ ሹፌሮች ይጠቀሳሉ፡፡ 

 እነዚህን ሁሉ ዓመል ማስጣል ባይቻልም፣ መጪው ጊዜ ትምህርት ቤት የሚከፈትበት ወቅት በመሆኑ ሕፃናትና አረጋውያን ያለሥጋት መንገድ ማቋረጥ እንዲችሉ እባካችሁ የሚመለከታችሁና እናንተም የባጃጅ ሾፌሮች ሥርዓት ባለው መንገድ ቅድሚያ ለሰው ሕይወት በመጨነቅ ቁሙና፣ እናቋርጣችሁ እላለሁ፡፡ 

(ሰለሞን ማሞ፣ ከአዳማ)

************

የተከራይ አከራይ መመርያ አልታገደም

የሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 18 ቁጥር 1931 ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. በረቡዕ ዕትሙ #ከኃፊነት የተነሱ የቤቶች ኤጀንሲ ባለሥልጣናት ያወጧቸው መመርያዎች ታገዱ$ በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃውን ተመልክተነዋል፡፡

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ቀደም ሲል ሲሠራባቸው የነበሩ አንዳንድ መመርያዎች የተለያዩ የአሠራር ችግሮች ያሉባቸውና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ ስለነበሩ፣ እነዚህ መመርያዎች በአዲስ መልክ ተዘጋጅተውና ፀድቀው እስኪወጡ ድረስ ለጊዜው መታገዳቸው እርግጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የተከራይ አከራይ መመርያ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ዕውቅና ያገኘና ትክክለኛ ተቀባይነት ያለው ስለነበር አልታገደም፡፡ ሆኖም በጋዜጣው ላይ የተከራይ አከራይ መመርያ ታገደ በሚል የቀረበው ሐሳብ ስህተት ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል፡፡ የተከራይ አከራይ መመርያ ፈሩን የለቀቀ ሳይሆን በርካታ ሕገወጥ ነጋዴዎች በመንግሥት ሀብት ያለአግባብ እየከበሩ ያሉበትን የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ በተቻለ መጠን በማድረቅ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ፈር በማስያዝ በብዙኃኑ ዜጋ ተጠቃሚ ያደረገና ዕውቅና ያገኘ መመርያ ስለሆነ አልታገደም፡፡

ነገር ግን መመርያው ወጥቶ ተግባራዊ በሆነበት ወቅት አንዳንድ ሕገወጥ የተከራይ አከራዮች ያልተገባ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ በርካታ የመንግሥት ተቋማት በር አንኳኩተዋል፡፡ ወጥተው፤ ወርደዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሚመለከታቸውና በመመርያው ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው ሰዎች ተገቢውን ብይን አግኝተዋል፡፡

የመመርያው ዋና ዓላማ በአዋጅ 555/2000 አንቀጽ 6/3 ማስፈጸሚያ በቤቶች አስተዳደር መመርያዎች የማይሸነፉ ጉዳዮች ሕጋዊ በሆነ አሠራር ማስተካከል፣ ኤጀንሲው በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ በተፈጸሙ ውስብስብና ሕገወጥ ተግባራት ላይ መፍትሔ መስጠት፣ ኤጀንሲው ከሚያስተዳድራቸው ንግድ ቤቶች መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ ማድረግና በንግድ ሥራ የተሰማራውን ብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ነውና፡፡ 

(የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ)

**************************

ሥልጣን አላገኘሁም ብዬ ተቃዋሚ አልሆንም 

ባለፈው ረቡዕ በነሐሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ዕትም ሪፖርተር ላይ በወጣው ‹‹የቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሉታዊ ገጽታዎች›› በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሑፍ አንብቤዋለሁ፡፡ የጸሐፊውንም ሐሳብ አከብራለሁ፡፡ የአንድ አገር የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑት ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ባህሪዎች አንዱ እንደሆነም እረዳለሁ፡፡

ይሁንና እኔን አስመልክቶ የተሰጠው ማብራሪያ እኔን ገላጭ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እኔ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሰጠኝም አልሰጠኝም ተቃዋሚ መሆን አልችልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ለመቀላቀል ምንም ፍላጎት የለኝም፡፡ እስካሁን እንደኖርኩት ሁሉ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሳልሆን መኖር ነው የምፈልገው፡፡

ጸሐፊው በገዥው ፓርቲ ላይ ያላቸው አመለካከት ከእኔ ለየት ያለ ነው፡፡ እርሳቸው በራሳቸው ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን በግል እምነቴ ደግሞ ኢሕአዴግ ማለት የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለሥልጣንና ለዲሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደርና ለነፃነት፣ ለዕድገትና ለብልፅግና ያበቃ የአገራችን ትልቅ ተምሳሌት የሆነ ፓርቲ ነው፡፡

እኔም ሆንኩኝ ሌሎች ዛሬ ከፍተኛውን የመንግሥት ሥልጣን መሾም እንችላለን የምንለው ሰዎች ኢሕአዴጎች በታገሉበት፣ በደሙበትና በተሰውበት ነው፡፡ ይህንን ገድል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያከብረው ይኖራል፡፡ በእኔ እምነት ኢሕአዴግ ሹመት የሚሰጠው መነሻው ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ የእኔና የጸሐፊው አመለካከት በእጅጉ ይለያያል፡፡ 

በመሆኑም ሥልጣን ባገኝም ባላገኝም ከሕገ መንግሥቱ አኳያ ነው እንጂ የማየው ጉዳት ወይም ጥቃት እንደደረሰብኝ ወይም ድጋፍ እንደተደረገልኝ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሥልጣን ባላገኝ ወደ ተቃዋሚነት አልሸጋገርም፡፡ መነሻዬም ሥልጣን የማግኘት ጥያቄ አይደለምና፡፡ ሥርዓቱን የምወድበት የእኔ መነሻ ገና በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴጎች አገሪቱን እንደተቆጣጠሩ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሥልጣን ባስረከቡበት ወቅት፣ የእኔንም ብሔረሰብ (ካፋ) ጠርተው የውክልና ሥልጣን እንዲያገኝ ያደረጉበትን መንገድ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብም እንደ ራሴ ብሔረሰብም ሁሌም ስዘክረው የምኖረው ነው፡፡ 

(ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ)