መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ታክሲ - አሠላፊና ተሠላፊ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

እነሆ ጉዞ ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ። ማልዶ የጀመረው ግርግር ጨለማ በዋጠው ጎዳና ሊጠናቀቅ የጥቂት ሰዓታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። ካፊያውና ብርዱ ከታክሲ አለመገኘት ጋር ሲደመር ሆድን ባር ባር ይላል።

ብሶት ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ስለታመነ ይመስላል በዚያ ግርግር የሚሰማው ጨዋታና ስላቅ ብሎም የትዕይንቱ መብዛት አንዳች አስደሳች ስሜት ያጭራል።

ጃንጥላ ዘርግተው ካፊያውን ያመለጡ የመሰላቸው ቆነጃጅት ንፋስን ከነመፈጠሩ በዘነጋ አለባበሳቸው በቅዝቃዜ እየተርገፈገፉ ይንቀጠቀጣሉ። ታክሲ እስኪመጣ የፍቅር አጋር ማደን የጀመሩ ጎረምሶች፣ ‹‹መጠለል ይቻላል? የሰው ልጅ መቼም ልብስ፣ ምግብና መጠለያ ግድ ይለዋል ብለሽ እንደምታምኝ አለጠራጠርም። ተሳሳትኩ?›› እያሉ ይጠጋጋሉ። ድፍረት ከልባቸው ሞልቶ በዓይናቸው የፈሰሰ ዓይናውጣዎችን እያየ ጎልማሳው ይስቃል፡፡ ሌላው ትምህርት ይወስዳል። ‹‹አልተሳሳትክም፤›› ትለዋለች አንዷ ስለሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች የተጠና ቃሉን እንዳነበነበ።

የክረምት ጎርፍ ያሻው ቆንጆ ልብ ላይ ይጣለኝ ብሎ አጋጣሚ ፍለጋ የሚባዝነው በርካታ ነው የሚል ሐሜት ከወዲያ ማዶ ይሰማል። የመንገድ ጨዋታና ሐሜት መቼ ያልቅና! ‹‹ይኼውልሽ እዚህ አገር የአርባ ቀን ዕድል ሆነና ሁሉም ነገር በቁጠባና በልመና ነው። ቁጠባውም ገንዘብ ሲኖር ልመናውም ሰው ከተገኘ ማለቴ ነው፤›› እያለ የጨዋታውን አድማስ ለማስፋት ይታገላል። ከሁለቱ ማዶ በጨቀየው አስፓልት መንገድ ላይ ወደ ሳር ቤት ለመሄድ ታክሲ ሰው ይሻማል። ተራ አስከባሪዎች፣ ‹‹ይኼን ሕዝብ ጥለን የት እንሄዳለን?›› እያሉ የቤት መኪና ጭምር እንዲተባበር ይለምናሉ። ዝናብና ግርግር ለፕሮፓጋንዳ የሚመች ይመስላል።

አጠገቤ አንድ ወጣት እጅግ በብርድ እየተንዘፈዘፈ፣ ‹‹እኔን የማይገባኝ እኮ ቆዳቸው ከምን የተሠራ ቢሆን ነው እንዲህ የሚለብሱት በዚህ ብርድ?›› እያለ ሲጠይቅ ይሰማኛል። ወደሚያይበት አቅጣጫ ስመለከት ሦስት ልጃገረዶች በጣም አጠረ በሚባል አጭር ቀሚስ ይታዩኛል። ትችትና ማጉረምረም፣ ሳቅና ነቆራ፣ ብሶትና ትዕግስት ማጣት ጥንድ ጥንድ ሆነው የገነኑበት ምሽት፡፡

ቅዝቃዜውና ካፊያው ያማረረው ታክሲ ጠባቂ ድንገት በተከሰተው ጃጉዋር ታክሲ ለመሳፈር የሚያመነታ ዓይነት አልነበረም። አንዱ ባንዱ ተነባብሮ፣ ግብግብ የዳኘው ተሳፋሪነታችን ሲፀና ከታየነው ውስጥ በአንድ ጃንጥላ ተጠልለው የነበሩት ወንድና ሴት፣ ሦስቱ ልጃገረዶችና ያ ብቻውን ሲያወራ የነበረው ወጣት ይገኙበታል። ጢም ብላ ሞልቶ በታጨቀው ታክሲያችን መስታውቶቹ ላይ የትንፋሻችን ጉም ይገነባል። ‹‹ኧረ መስኮት! ቢያንስ መስኮት ይከፈት!›› ይላል ከወደኋላ። ‹‹አቦ አትጩህብና! ገና ለገና ተቃዋሚ ይነሳብኛል ብለህ በጩኸት ታደነቁረናለህ እንዴ?›› ይመልሳል መሀል መቀመጫ ቡዝዝ ባሉ ዓይኖቹ በመጠጥ መዳከሙ የሚታወቅበት ጀብራሬ። መጠጥ የሚያኮላትፈው ልሳኑ ከራሱ ጋር እንዳልሆነ የተገነዘቡት ሁሉም ተሳፋሪዎች ስለነበሩ መልስ የሚያቀነባብርለት አልነበረም። እሱ ግን ቀጥሏል።

‹‹የኢሕአዴግ ጩኸት አይበቃም እንዴ? አገር ማልማት ውለታ አድርጎት የተቃዋሚ ነገር ባስበረገገው ቁጥር የሚጮህብን አይበቃንም ወይ? መስኮት አይከፈትም ብሎ የሚቃወመኝ ሰው ይኖራል ብለህ ፈርተህ ገና ለገና ምንድን ነው እንዲህ ሰው ማደንቆር?›› እያለ ሲናገር አባባሉ ከማበሰጫት ይልቅ ፈገግ ያሰኛል። ‹‹አዲስ ነገር ፈርተን፣ አዲስ መንግሥት ፈርተን፣ አዲስ ሐሳብ ፈርተን መጨረሻችን ምን እንደሚሆን የሚነግረን ቢገኝ?›› ቀጥሏል ጀብራሬው በሞቅታ። ‹‹ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል›› ሆነና በመስኮት ይከፈት ሰበብ ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን የፖለቲካ እንካሰላንቲያ ማዳመጥ ግድ አለን፡፡ ነገሮች ሄደው ሄደው ማሳረጊያቸው ፖለቲካ ቢሆን ምን ይገርማል? ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም የፖለቲካ ጠቢብ የሆነ ይመስል በመሰለው መንገድ ይሰልቀዋል፡፡ ‹‹ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር…›› እያለ የሚያላግጠውም ከዳር ይታዘባል፡፡ ዓለም እንዲህ ነው እንግዲህ፡፡

ከኋላ እንደሰው ሳይሆን እንደ ዕቃ  ተጨናንቀው የተቀመጡ ተሳፋሪዎች፣ ከጀብራሬው  ፍሬ ሐሳብ ይልቅ አነጋገሩ እያዝናናቸው ታክሲያችን ጉዟውን ከጀመረ ቆይቷል። ስለመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ የሚያዝናና ጭውውት እየኮመኮምን ነው። ‹‹እኔ እኮ አንደኛውን አደስ አበባ ተሠርታ እስክታልቅ ወደ ክልል ከተሞች ‘ዕድገት በኅብረት’ ታውጆ ብንዘምት ይሻል ነበር ይላል አንደኛው። (ታክሲዋ የውስጥ መብራቷ ስላልበራ ተናጋሪው ማን እንደሆነ ለመለየት ያስቸግራል) ‹‹ዕድገት በኅብረት? የመቼውን አመጣህብን ደግሞ?›› ይላል የጎልማሳ ሰው ድምፅ። ‹‹ምነው? ምንችግር አለው? ዲሞክራሲያችን እንደሆነ አብዮታዊ ነው።

መንግሥታችንም ዋጋ ትመና ላይ ብቻ ጣልቃ ከመግባት በሰው አስተሳሰብ መቃናት ላይም ጣልቃ እየገባ ቢሠራ ነውር አለው?›› ይላል የፊተኛው። ‹‹ጉድ ነው! በስመ አብዮት የማንሆነው የለ፤ የምንሰማው አያልቅ! ሆሆ…›› ትላለች በወይዘሮ ድምፅ አንዷ ከኋላ መቀመጫ። ‹‹በእውነት ለመናገር በትራንስፖርት፣ በኔትወርክ፣ በውኃ፣ በመብራት እጥረት ምን ቅጡ ኑሯችን እየተመሰቃቀለ ሥራው ሊሠራልን ካልቻለ ወዳጃችን እንዳለው መንግሥት መሬትና ሕንፃ ሲያለማ እኛ ሰው ብናለማ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፤›› ይላል ከጋቢና ሌላው።

‹‹ማን ከማን ተሽሎ? እንዲያው ግን አንደኛውን ወደ ገጠሪቷ ኢትዮጵያ ‘ቫኬሽን’ ደረስ ብሎ መምጣቱ ሳይሻል አልቀረም ብትሉን እንስማማለን፤›› ይላል ጎልማሳው። ሰውን እያዋዛ ሲያጨውተው የቆየው ይኼው ርዕስ ሊቋጭ አካባቢ አንደኛው፣ ‹‹ኧረ ተው እባካችሁ! አሁን የአዲስ አበባ መልሶ መገንባት እስኪያልቅ ዞር አልን ብንል ማን ያምናል? የዘንድሮ ነገር ከፍቷል! የተፈናቃይና የአፈናቃይ ውዝግብ ባልተፈታበት አገር ደግሞ እኛም እንጨመርና ለጠላት በር እንክፈት? ቡድንተኝነት ከበጎ ዕሳቤ በላይ ነግሶ ወገኖቼ!›› ብሎ ከጋቢና ተናገረ። ወዲያው አንድነት ጎልቶበት ሞቃ የነበረው ታክሲያች ከደጁ ብርድ የባሰ ቀዝቃዛ መንፈስ ከበበው። ደስ የማይል የልዩነት ንፋስ ጭምር፡፡

ወያላው፣ ‹‹እባካችሁ ሒሳብ እየሰጣችሁኝ፤›› ይላል። ‹‹እስኪ መጀመሪያ መብራቱን አብራልን እንዴት እንስጥህ?›› ትለዋለች የመልኳ ነገር ያልተረጋገጠ ድምፀ መረዋ። (ለነገሩ የዘንድሮ ቁንጅና እንደሆን ለውርርድ አይቀርብም)  ‹‹መብራቱ ስለተቃጠለ  ነው። በደንብ የሚያበራ ሞባይል ያለው የለም?›› ይጠይቃል ወያላው በተባበሩኝ መንፈስ። ‹‹ከኃይል መቆራረጥ ነው ወይስ ከትራንስፎርመር ችግር ነው የተቃጠለው?›› ይላል አንድ ጎልማሳ እየሳቀ። ‹‹ኧረ እናንተ ለመሆኑ ኤርትራ 250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከባላንጣዬ ኢትዮጵያ በነፃ ቀርቦልኛል ያለችው ነገር እንዴት ነው?›› ትጠይቃለች ከመጨረሻ ወንበር የማናያት። ጨለማው ፍርኃትና መሸማቀቅ ለሌለበት ውይይት ያደፋፈረን ይመስላል። ምናልባትም ውስጥ ውስጡን የትንኮሳው ነገርም ደርቶ ይሆናል። (ነገራችን ሁሉ በጨለማ የጨለማም አይደል?) ‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ መንግሥት አልኩት ያለው ነገር ሳይኖር የፈጠራ ዜና በበዛበት በዚህ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ዘመን እስኪጣራ ጠብቀን ብናወራ ምን እንዳንሆን ነው?›› ከማለቱ አጠገቧ ተቀምጦ የነበረ ወጣት፣ ‹‹እሱን ሂድና ለሚዲያዎች ንገራቸው። በእነሱ አይብስም እንዴ ሳያጣሩ ወሬ ሳይገሉ ጎፈሬ…›› ብላ የምትመሰው ከመሀል ወንበር ከሰካራሙ አጠገብ ያለች ልጅ ናት።

ይኼኔ ደህና ዝም ብሎ ይጓዝ የነበረው ባለሞቅታ፣ ‹‹በእውነቱ የሴቶች ተሳትፎ ከምጠብቀውና ከማስበው በላይ እየጨመረ መጥቷል። ግን ታክሲና ካፌ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ፓርላማም ውስጥ ይሁን። ለነገሩ የአንድ ፓርቲ ቤተሰብ መሀል አየናችሁ አላየናችሁ ምን ለውጥ ይኖረዋል? ንገሪኝ ምን ለውጥ ይኖረዋል?›› ብሎ ብሎ ሊመታት ቃጣ። ልጅቷ ስትጮህ የታክሲው ግስጋሴ ወዲያው በረደ። ተሳፋሪዎች በሙላ በቁጣ ወያላውን መጠጥ ያጠወለገውን ሰው እንዲያስወርደው ጮኹበት። ወያላው አምርሮ አርፎ እንዲቀመጥ ሲገስፀው ሰውየው የመለሰው መልስ የተሳፋሪዎችን ሐሳብ ለሁለት የከፈለ ነበር። ‹‹እሺ የተከበሩ አፈ ጉባዔ!›› ካለ በኋላ ወያላውን፣ ‹‹በእውነቱ ታክሲዋ የጫነችው 99.9 የኢሕአዴግ አባላት መሆኗን አላወቅኩም ነበር፤›› ነበር ያለው። የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ደብዛው መጥፋት የሚቆረቁረው ሁላ በዚህ አባባል ሕመሙ ሲያገረሽበት በግልጽ ይስተዋላል፡፡

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። የቸርችል ጎዳናን እንደ ሮኬት እየተምዘገዘገ ታክሲያችን እየወጣው ነው። ‹‹መንገዱ ዳገት! ኑሮ ዳገት! ፖለቲካው ዳገት፤›› ይላል አንድ ጎልማሳ። ‹‹በጣም እንጂ በተለይ የፖለቲካው ሜዳ የጥቂቶች ብቻ መሆኑ ‘ሂድ! ወዴት?’  ‘ቁም! እንዴት?’ እንዳንል ሽባ አረገን፤›› ትለዋለች ከአጠገቡ የተቀመጠች። ኑሮ በፖለቲካ እየታገዘ ሲብራራ የሁሉም ተሳፋሪዎች ጆሮ ይቆማል። ‹‹እንዲያው እዚህ አገር ግን. . . ›› ትላለች አጭር ቀሚስ ከለበሱት ኮረዳዎች አንደኛዋ። ‹‹ምናለበት ሰው ሰጥ ለጥ ብሎ ቢኖር? በቃ አርፎ መቀመጥ ማንን ገደለ? ደግሞስ አሁን ያለው ነፃነትና ሰላም አልበቃን ብሎ ነው?›› እያለች ወደ ጓደኞቿ ዞራ ትናገራለች።

‹‹እውነት ነው! ምናልባት ለአለባበስና ሰዓት እላፊ ለሌለበት የምሽት ሕይወት በቂ ሊሆን ይችላል።  ለአገራቸው የበኩላቸውን ሠርተው የመሰላቸውን ሐሳብ አዋጥተው ማለፍ ለሚፈልጉ ባለራዕይዎችን ግን የሚበቃ አይመስለኝም። እናም ሁላችንንም ወክለሽ ባትናገሪ ደስ ይለኛል፤›› ይላታል ከወዲያ ማዶ ለዘብ ባለ ቃና። ልጅቷ አፍራና ተሸማቃ ዝም ስትል ጎልማሳው፣ ‹‹ጎበዝ ምንም እንኳ ፖለቲካዊ ተሳትፏችን ለዚህች ታዳጊ አገር ቢያስፈልጋትም ከመሰሪዎችና ከሴረኞች አደጋ ራሳችንን እየጠበቅን ይሁን፤›› ሲል ይደመጣል። ከወዲያ ‹‹አዎ! ሠልፍና ሠልፈኛው በዝቷል። የተሠለፈና ያሠለፈ ሁሉ ሰላማዊ ነው እንዳንል እንደዚህ ዘመን ጥሩ ምስክር የለንም፤›› ይላል።

 ታክሲው ቆሞ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ሲል ያ ብቸኛ ወጣት ‹‹ሰላማዊ ሠልፍ እንዲህ ከተፈራና በሩቁ ከተባለ ዲሞክራሲ ምኑን ዲሞክራሲ ተባለ ታዲያ?›› ሲል ይሰማኛል። አሠላፊና ተሠላፊ በበዛበት በዚህ ጊዜ ብዙ መባል ተጀምሯል፡፡ ቀና ብዬ ዙሪያዬን ሳይ ሁሉም ተሳፋሪዎች ቀስ በቀስ ወርደው መበተን ጀምረዋል። መልካም ጉዞ!