መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ታክሲ - ብሶት ሲቀሰቀስ ብዙ ያናግራል
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
14 August 2013 ተጻፈ በ 

ብሶት ሲቀሰቀስ ብዙ ያናግራል

እነሆ ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ የሚጓዝ ታክሲ ውስጥ ተሳፍረናል። ታክሲያችን ጭኖ ከመንቀሳቀሱ በትራፊክ ፖሊስ ፊሽካ እንዲቆም ታዘዘ። ‹‹አቤት?›› ይጠይቃል ሾፌር።

‹‹መንጃ ፈቃድህን አምጣ፤›› ይመናጨቃል ትራፊክ ፖሊሱ። ‹‹ምን በደልኩ? ንገረኛ?›› ይላል ሾፌሩ ተማሮ። ‹‹ሰውዬ እኔን አይደለም አገር ነው እየበደልክ ያለኸው፤›› ይለዋል ምን ያነካካኛል በሚመስል በቁጣ እያየው። ወያላው ድምፁን እኛ እንድንሰማው መጥኖ፣ ‹‹አገሩንስ ቢሆን የሞላችሁት እናንተ አይደላችሁ?›› ይላል የሚይዝ የሚጨብጠው እየጠፋው። ‹‹እሺ ለምን ጥፋቴ አይነገረኝም?›› ሾፌሩ መንጃ ፈቃዱን ከኋላ ኪሱ ቦርሳ አውጥቶ ለትራፊክ ፖሊሱ እያቀበለው። ትራፊክ ፖሊሱ ደስ በማይል አስተያየት ሾፌሩን ገላምጦ በመስታወቱ ውስጥ አንድ በአንድ ያየን ጀመር። ‹‹ወደ እኛ ሊዞር ነው እንዴ?›› ሲል አንዱ ከኋላ ሌላ፣ ‹‹ምን ይታወቃል ወንድሜ ዘንድሮ ፍረጃው አይጣል ነው። ፀረ ልማት፣ አክራሪ፣ አሸባሪ፣ የአገር ጠላት ኧረ ስንቱ…›› ትለዋለች የፌዝ ሳቅ እየሳቀች። ትራፊክ ፖሊሱ መንጃ ፈቃዱን እየተመለከተ ቅጣቱን ሊጽፍ ሲል ሾፌራችን አላስችል ብሎት ወረደ። ወያላው ተከተለው። ተሳፋሪዎች ያሰኛቸውን ማውራታቸውን ቀጠሉ። 

‹‹ወይ ጉድ ይኼ አገር ሁሉ ጉልበተኛ ሆኖ አረፈው በቃ? በሕግ ማስከበርና በልማት ስም ዘንድሮ የሚሠራውን ነገር ተውት፡፡ እስኪ ውስጡ ለቄስ ይሁን፤›› ሲል ከጋቢና አንዱ ይናገራል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ተሳፋሪ መስኮቱን ከፍታ፣ ‹‹ኧረ ተወው በፈጠረህ የዛሬን ብትምረውስ?›› እያለች ቢራራ ብላ ትራፊክ ፖሊሱን ትለምነዋለች። ከእርሷ ኋላ የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹እንዴ ምን አጥፍቶ ነው ቆይ ልመናው? ጥፋቱ አይነገረም እንዴ መጀመሪያ? እንዴ ጎበዝ ኧረ መብትና ግዴታችን እንወቅ እባካችሁ?›› እያለ ማሳሰቢያ ሰጠ። በዚህ ወጣት አባባል  ልቡ የተነካ አንዱ ጎልማሳ፣ ‹‹ጠፍቶን መሰለህ ዝምታ የለመደብን? በመብት ጥያቄ ያየነውን ዓይተን እንጂ ለነገሩ በደህናው ጊዜ ተወልደህ ምኑን ታውቀዋለህ?›› ብሎት ተከዘ። እኛም በየራሳችን ሐሳብ ተውጠን ዝም አልን፡፡

ወያላው ተመልሶ መጣ። ‹‹ምንድን ነው የሚለው?›› ይጠይቀዋል ከኋላ። ወያላው፣ ‹‹የ2005 ቦሎ አለጠፋችሁም ተብለን ነው፤›› ብሎ ሲመልስ፣ ‹‹ለዚህ ነው ታዲያ እንዲህ የምትዳረቁት? በ20 እና 30 ብር አትሸኙትም ነበር?›› አለች ነቃ ያለች ሳቂታ ከጎልማሳው አጠገብ እንደተቀመጠች። ጎልማሳው፣ ‹‹ሆሆ ጭራሽ አሁን ዙሩ በከረረበት ሰዓት ያውም ሕዝብ ፊት ማን ይለቅሽና?›› ይላታል። ‹‹ውይ! እንዲያው መቼ ይሆን እንዲህ በእጅ መንሻ ለመገላገል ማሰብ ነውር የሚሆነው? ስማ እንዳትሰጥ ሙስና አሳፋሪ ነገር ነው፤›› ብሎ ወያላውን እያየ ተናገረ አንዱ ከወጣቱ ጎራ።

ጎልማሳውና ሳቂታዋ ተሳፋሪ ወያላውን ለጉቦ ማደፋፈራቸው መጨረሻ ወንበር ላይ በተቀመጠ ወጣት ተሳፋሪ መወቀሳቸው አናደዳቸው መሰል፣ ‹‹ኧረ የዘንድሮ ሰው ድፍረት ምን ነው እንዲህ ሠፈር ውስጥና ታክሲ ውስጥ ብቻ ሆነ? በሚሊዮን በሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብና ንብረት የሚጫወቱ እያሉ እኛ በ20 እና 30 ብር እንዲህ መዓት ይውረደብን?›› እያሉ እርስ በእርሳቸው ያወጋሉ። ‹‹ከመንግሥት ደግሞ የባለሀብቱ ይብሳል እኮ! መቼስ ክርስቶስ ‘ባለፀጋ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል’ ያለው በትክክል ለዚህ ዘመን አግበስባሽና ነቀዝ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፤›› ትላለች አንዲት ወይዘሮ። ‹‹እህሳ! ደሃማ እንዲህ ያለው ‘ኔትወርክ’ ውስጥ ምን ሊያደርግ ይገባል?›› ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ቆንጆ። ያለችውን ሰምቼ ዞር ብዬ ባያት ውበቷ አስደንብሮኝ የምናገረው ጠፍቶኝ ዝም አልኩ። ውበትና ንቅዘት እንዲህ በአንድ ዘመን እኩል ይናሩ? ወይ ግጥምጥሞሽ።  

ሾፌራችን መንጃ ፈቃዱ ተመልሶለት በማስጠንቀቂያ ተለቋል። ያመለጠውን ሥራና የሥራ ዕድል ለመመለስ ይመስላል ሾፌራችን በአንዴ ቀበና ደርሶ ወራጅ እየሸኘ ነው። አንዲት ዘምቢል ያንጠለጠሉ እናት ከውስጥ ባሉ ተሳፋሪዎች ዕርዳታ ታግዘው እያጉረመረሙ ገብተው ተቀምጡ። ‹‹አሄሄ! አዬ! ወይ ጉድ!›› ይላሉ አሥር ጊዜ። ጉዟችን ቀጠለ። ሒሳብ ያልከፈለ ሳንቲምና ዝርዝር ፍለጋ ኪሱን ያስሳል። ከአዛውንቷ እናት አጠገብ ያለች ወጣት፣ ‹‹ምነው እማማ አመመዎ?›› ብላ ስትጠይቃቸው እንሰማታለን። ‹‹ኧረ ዞር በይልኝ! ምን አደረግኩሽ አንቺዬ? ደግሞ በዚህ ኑሮ ላይ ልታመም? እንዲያው ሰው ግን ዘንድሮ ምን ነካው እባካችሁ?›› ይላሉ አዛውንቷ ፍፁም ተበሳጭተው። ‹‹ኧረ እኔ እንደዚያ ለማለት ፈልጌ አይደለም እማማ፤›› ትላለች ደንግጣ ልጅቷ።

አዛውንቷ፣ ‹‹የሰው ነገር እየገረመኝ እኮ ነው ልጄ። የሁሉንም ሆድ አንድ እንጀራ ነበር የሚያጠግበው አንዱ በጣም ሀብታም አንዱ የነጣ ደሃ ሆኖ እያየሁ ነገር ዓለሙ አልገባሽ ይለኛል፤›› ብለው በረጅሙ ተነፈሱ። ‹‹እውነታቸውን እኮ ነው ዓለም ያላት ሀብት ድህነትን ታሪክ ማድረግ አይደለም ተረት እስኪሆን ድረስ የማስረሳት አቅም ነበረው። ምን ዋጋ አለው ሰዎች ስንባል ከአመፅና ተንኮል ጋር ተወሳስበን ተፈጥረን አንዱ ሲበላ አንዱ ሆዱ ይጮሃል። በጦርነትና በግጭት ስንታመስ ዘመናችን ያልቃል። ጥቂቶች ብዙኃኑ ላይ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ቀን ከሌት ሲባጁ ኑሮ ምስቅልቅሉ ይወጣል፤›› እያለ ጎልማሳው አዛውንቷን ደግፎ ይናገራል። መናገር ሲታክተው በየመሀሉ ዝም ይላል። ሁሉም ጆሮውን ሰጥቶ እያዳመጠው፣ ‹‹መጥኔ ለዚህች ዓለም፤›› ሲል ይሰማል። መጥኔ!  አዛውንቷ፣ ‹‹ለመሆኑ የዚህ አገር ነጋዴ ምን ሊሆን ነው የሚፈልገው? መንግሥትስ አለ ወይ? የዋጋ ንረቱ ያላግባብ ተቆልሎብን ጀርባችንን እያጎበጠው ነጋዴው በሚዛን ይሰርቀናል፡፡ እብቅና ገለባ ይሸጥልናል፡፡ ነጋዴ ለመሆኑ አገርና ወገን የለውም? ወይስ ሆዱ ነው አገሩ?›› ሲሉን ምሬታቸው ገባን፡፡ የሚያስመርር ዘመን ይሏችኋል ይኼ ነው፡፡  

ቀስ በቀስ ጨዋታው ወደ ሙስና ሲያመራ፣ ‹‹ኤድያ ሙስና አልነው ሌላ ስም ሰጠነው ያው ምንጩ እኮ አንድ ነው እናንተ፤ መሃይምነት፤›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹አሁንማ በዋናነት እያስቸገረን ያለው ነገር መሃይምነት ነው፤›› ጎልማሳው ያቋርጣታል፡፡ ‹‹እንዴ! ኧረ እባክሽ መንግሥት እንዳይሰማሽ እንዲህ ስትይ። በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በየዓመቱ ከየዩኒቨርሲቲው እየወጡ በየት በኩል ነው መሃይምነት ያጠቃን?›› ብሎ ይጠይቃታል። ‹‹እሱን እኮ ነው የምለው። ሁለተኛ ደረጃ መሃይምነት ለማለት ፈልጌ ነው። ‹እያዩ አያዩም እየሰሙ አይሰሙም› ዓይነት የሆነውን። እስኪ ይታያችሁ ሶሪያንና ግብፅን ያየ ትርምስ ውስጥ ካልገባን ይላል?›› ብላ ጥያቄ ከመሰንዘሯ፣ ‹‹እንዴ! ታደያ ይኼ ዲሞክራሲያዊ መብትን መጠቀም እንጂ ከመሃይምነት ጋር የሚያያይዘው ምን ነገር ተገኘበት?›› ብላ አጠገቤ ያለችው ሸጋ ልጅ ጠየቀቻት።

(አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ ይላል ልቤ) ‹‹በመብት ስም ከምንተናነቅ ሰላም አይሻልም? አጋንኘው ከሆነ ይቅርታ አድርጉልኝ፤ ግን ገና ሳንጠግብ፣ ገና ዳዴ ማለታችንን ትተን ቆመን መራመድ ሳንጀምር፣ ዲሞክራሲ ሲሉ ሰማንና እኛም የሌሎችን ውድቀት መድገም አለብን? ‘ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት፣ አርዝመው ቢያስሯት የፈቷት መሰላት’ አሉ አበው፤›› ብላ የስላቅ ተረቷን ከመጨረሷ ከኋላ ከተቀመጡ ወጣት ተሳፋሪዎች ያዟት፡፡ በተለይ አንደኛው፣ ‹‹ተረቱ ‘ዶሮን ሲያታልሏት ውኃው የሚሞቀው ለገላሽ ነው አሏት’ በሚለው ይስተካከል። ምንድን ነው ዘመኑ እኮ የለውጥ ነው፤›› ሲል ሌላኛው፣ ‹‹አርቆ የማያስብ ማለት እንዳንቺ ያለውን ነው፤›› ሲል ይሰማል። ድህነት ወደኋላ ሲጎትተን፣ ሥልጣኔ ከፊታችን ሲጠራን፣ በጎንና በጎን አለማወቅ፣ ኢ ምክንያታዊነት ተምሮ እንዳልተማረ፣ ፊደል ቆጥሮ እንደረሳ ሲያሳማን ‘አወይ ፍርጃ’ ማለት ብቻ ሆነ ሥራችን። 

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ጎልማሳው ምን ሰምቶ ማንን አይቶ እንደሆነ አናውቅም፣ ‹‹ኧረ የዘንድሮ ወጣትስ እንጃለት። ባለለፈው አንዱ (ይታያችሁ እንግዲህ በቴሌቪዥን መሆኑ ነው) ጋዜጠኛው ‘ክረምት እንዴት ይዞኋል?’ ብሎ ቢጠይቀው ‘ተወኝ እስኪ! ሩኒን ሳላየው ነግቶ እየመሸ’ ብሎ መለሰለት። እንዲያው መጨረሻውን ያሳምረው ነው የሚባለው፤›› እያለ ሲናገር ወጣቶችና ሕፃናት ስፖርት ማዕከል ጋር ደረስን። መንገዱ ከተራቸው በሚነሱ ታክሲዎችና አውቶሞቢል መኪኖች ስለተዘጋጋ ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ማራገፍ ተስኗት ቆማለች። ‹‹የዘንድሮ ልጆች ዓላማ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ አይመስሉም። ዝም ብለው ብቻ የበይ ተመልካች ሆኖ መኖር ‘ሆቢያቸው’ አድርገውታል። እንደ ሩኒና ከእናትና ከአባታቸው በላይ አስበልጠው እንደሚወዷቸው የሆሊውድ ፈርጦች መሆን እየቻሉ፣ ተቀምጠው ማውራትና ማጨብጨብ ብቻ ነው የሚፈልጉት፤›› ከማለቷ አዛውንቷ ቀበል አድርገው፣ ‹‹እናንተ አርዓያ ያልታየበትን ዘርፍ ነው የጠራችሁት።

ይኼው በአትሌቲክሱ ተተኪ አጥተን አይደለም እንዴ አንገታችንን የምንደፋው? ገዛኸኝ አበራ በሕይወት ባለበት አገር፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በሕይወት ባለበት አገር፣ እነ አበበ በቂላ ስማቸው ከመቃብር በላይ እንደ ባንዲራ በሚውለበለብበት አገር ቢያንስ እነሱን ማስታወስ ሲገባው ወኔ የከዳው ትውልድ እኮ ነው የመጣብን፤› ብለው በቁጭት እጃቸውን ጨበጡ። ‹‹ጥሩነሽ ዲባባን የመሰለች ጀግና ለዚህ ትውልድ የቅርብ ጊዜ አርዓያ ካልሆነች ማን ይምጣላችሁ ታዲያ?›› እያሉ ተብሰለሰሉ፡፡

‹‹ኧረ ወረዱብን እኮ፤›› ይላል ወጣቱ ከዚህም ከዚያም። ‹‹ምን ዋጋ አለው ወኔ ብቻውን የቡድን ሥራ ከሌለ? በአሥር ሺሕና በማራቶን የተበላነው እኮ ወኔ ጠፍቶ ሳይሆን የቡድን ሥራ ዜሮ ስለነበር ነው፤› ከማለቷ ቆንጅት፣ ‹‹እውነትሽን ነው። ምን ዋጋ አለው ልማት ልማት ቢሉ፣ ዕድገት ዕድገት ቢሉ፣ በቡድን ሥራ ያልታገዘ ዕድገትና ለውጥ፣ በቡድን ሥራ ያልታገዘ ዲሞክራሲ፣ በቡድን ሥራ ያልታገዘ ሩጫ መጨረሻው መሀል መንገድ ላይ መቅረት ነው!›› እያለ ጎልማሳው ሲናገር ታክሲያችን ቦታ አግኝቶ ቆሞ ነበር። አዛውንቷ ዘንቢላቸውን ይዘው ሲወርዱ፣ ‹‹አብሮ ከመብላት በላይ አብሮ መሥራት ቢለምድብን የት በደረስን? ለቡድን ሥራ እኮ በሥነ ልቦናም መግባባት ያስፈልጋል…›› ሲሉ የሰሞኑን ብሶት ያስተጋቡ መሰለን፡፡ ብሶት ሲቀሰቀስ ብዙ ያናግር የለ? ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ሲሸኘን እየተብሰለሰልን ወርደን በአራቱም አቅጣጫ ተበታተንን። መልካም ጉዞ!