መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ታክሲ - ውጥረትን አርግቡ!
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

እነሆ ጉዞ ከሳሪስ አቦ ወደ ስቴዲየም። ‹‹የኢትዮጵያ ምድር አንቺ የደም ጎዳና መስክሪ አፍ አውጭና፤›› ይላል በመረዋ ድምፁ አንጋፋው ድምፃዊ ምንሊክ ወስናቸው።

በቅፅበታት ልዩነት ታክሲዋ ላይ እየወጣ የሚሳፈረው ተሳፋሪ ጭልጥ ብሎ በሐሳብ ይነጉዳል ግጥሙን እየሰማ። ሾፌሩ ሆን ብሎ ይመስላል እየቆየ ድምፅ ጨመር ያደርግበታል። ሀቅ ነውና ታሪክ ነውና ያለተቀናቃኝና ያለተሟጋች ሙዚቃው ከታክሲው አልፎ ጎዳና ድረስ ይሰማል። መጭ ሂያጁ የሚያልፍ የሚያገድምበት ጎዳና ጨቅይቶ ደርቆ ቀይ ቀለም የተቀባ ይመስላል። ‹‹ከዚያ እስከዚህ ድረስ የጦርነትንና ያለመግባባት ታሪክ ያየለብን እንዲያው ለምን ይሆን?›› አንዱ ይጠይቃል መልስ ግን የለም። እንኳን በታክሲ ውስጥ በምሁራን መድረክ መልስ ጠፍቷል። ‹‹ቅዠትና ሕልም ተደበላልቆባት ዘመኗ እዚህ የደረሰ አገር ወይኔ!›› ትላለች አጠገቤ የተቀመጠች ወጣት። የማይታወቅባት መስሏት እንጂ እንባ ያቀረረ ዓይኗ እንኳን ቅርቧ ላለ ወዲያ ማዶ ሆኖ የሚያየውም የሚታዘበው ነው። 

‹‹ሕዝብ ቅድሚያ ያልተሰጠባት፣ ኋላ ቀርነትና ሥልጣኔ በፊትና በኋላ ሲጎትቷት የሚደርስላት ያጣች፣ ድህነት ከሐሳብ እስከ ቁስ ሁሉን አሳጥቶ ላሰቃያት ምድር በእንባ መራጨት ሲያንስ ነው?›› ይላል የማናየው። ይኼኔ ታዲያ አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹እባክህ ሾፌር ወዲያ አሳልፈው፤›› ብሎ ተነጫነጨ። ‹‹ምነው?›› ይጠይቀዋል እንደሱ በጉልምስና የዕድሜ ክልል የሚገኘው ሸፌራችን። ‹‹የኖርነው አልበቃ ብሎ ደግሞ በትዝታ የምንለበለበው ምን በወጣን?›› ይመልሳል። ‹‹የለም ወጣቱ አዲሱ ትውልድ ይስማ ። የገደልንም እኛ የሞትንም እኛ። ወዴት ወዴት ነው ሽሽቱ?!›› ይመልሳሉ ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጡ አዛውንት። ‹‹በቀበሌ እስር ቤት ታፍኖ የቆየ፣ በቀይ ሽብር ወድቆ ሜዳ ላይ የታየ፣ እስኪ ተናገሪ ታሪክሽን በሙሉ የሞቱልሽ ሞተው የገደሉሽ ካሉ!›› ማለቱን ሲቀጥል አንጋፋው አቀንቃኝ  የሆዱን በሆዱ እንደያዘ ጆሮውን ያልቀሰረ ተሳፋሪ አልነበረም፡፡

ታክሲያችን ሞልቶ ተንቀሳቅሰናል። ወያላችን ጫቱን ከሸጎጠበት ሥፍራ መሰስ አድርጎ አውጥቶ ሾፌሩን ‹‹አቦ ራፕ ምናምን ክፈት ስለባቡር፣ ስለግድብ፣ ስለቁጠባ ቤት በምናስብበት በዚህ የልማት ዘመን ሰቆቃ ታሰማናለህ?›› እያለ ይነጫነጫል። ‹‹በጣም!›› ይላል ከሸፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ወጣት። ሾፌሩ ሌላ ካሴት እስኪያስገባ ታክሲው ውስጥ ፀጥታ ሰፍኗል። ‹‹እንዲያው ይህንን የትዝታ ቅኝት መርጦ ለዚህ አገር የሰጠውን ባውቀው?›› ስትል ከኋላ መቀመጫ የተሳፈረች ቆንጆ እንሰማታለን። ‹‹ምን ትይው ነበር?›› ይጠይቃታል አጠገቧ የተቀመጠው። ‹‹ወዲያ ውሰድልን የምለው መስሎህ ነው? አድናቂው እንደሆንኩ ነው እንጂ የምተነትንለት! ከዓለም ባንክ የተበደርነው ዕዳ እስከ ልጅ ልጅ ልጆቻችን ኪስ የደረሰብን ሰዎች ቁርጣችን ሳይታወቅ ትዝታን ወዲያ ማለት ተገቢ አይመስለኝም፤›› ትለዋለች። ‹‹እውነትሽን ነው። በዚያ ላይ ተካፍሎ መብላትና ተባብሮ መሥራት ሲረሱ በደህና ቀን ያሳለፍነውን ጊዜ ‘የአብሮ መብላት ተሳስቦ ኑሮ ገዳም ሠፈር ቀረ ድሮ’ እያልን በትውስታ ካልኖርነው ዋጋም የለን፤›› እያላት ወደ ስቆ ማሳሳቁ ጨዋታ ከተታት። 

ወያላው ‹‹እንዴት ነው ዘንድሮ አረንጓዴ መብራት እባክህ?›› ሲል እንሰማዋለን። ሾፌራችን፣ ‹‹ላለውና ሌለው እኩል መቼ ይበራል?›› ብሎ ይመልሳል። የንግግራቸውን ሚስጥር የተረዳው ፈገግ ሲል በቀጥታ የተረጎሙት አዳዲስ ስለተተከሉትና እየተተከሉ ስላሉት የትራፊክ መብራቶች መጨዋወት ጀምረዋል። አንዱ፣ ‹‹ለምን እንደሆነ አላውቅም የእነዚህን መብራቶች ደቂቃ ቆጣሪ ሳይ አልቅስ አልቅስ ይለኛል፤›› ሲል ‹‹ለምን?›› በማለት ሌላው ይጠይቀዋል። ምን ነካህ እንዲህ በቀላሉና ቶሎ መተላለፍ ስንችል እኔ ልቅደም እኔ ስንባባል የባከነው ዕድሜና ጊዜ ትዝ እያለኝ ነዋ፤›› ይለዋል ቆፍጠን ብሎ። ‹‹አላስኖር ባዩ በርክቶ ሳይኖር ያለፈው የአገርና የሕዝብ ዕድሜ በደንብ የገባው ይመሳለል። ቢዘገይም የጊዜ ጥቅም ገብቶሃል ማለት ነው፤›› እያለ ያኛው ያሾፍበታል። ይኼ ሲደማመር ይሆን ያልተኖረ ዕድሜ መጽሐፍ የሚወጣው? መጥኔ!

‹‹ወራጅ›› ብለው ሦስተኛ ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ወንድና ሴት ወረዱ። እነሱን ተክተው ሁለት ወጣቶች በጋለ ስሜት እየተጨዋወቱ ገብተው ተቀመጡ። ‹‹አቤት! ይኼ ቤት ደርሶኝ ብቻ እኔ ነኝ የማውቀው፤›› ይላል አንደኛው። ልቡ በጉጉት እየደለቀ የተስፋና የሕልሙን ረቂቅነት እያነጣጠረ ያወራል። ‹‹የትኛው ቤት?›› ጓደኛው በማሾፍ ይጠቀዋል። ‹‹የቁጠባው ነዋ! ከኪራይ ቤት ወጥቼ። ሳልሳቀቅ ቀልቤ ካረፈባት ቆንጆ ግምገማ  ተቀምጩ?›› ብሎ ከመጨረሱ፣ ‹‹ጉድ ነው! ምን ነው ይኼን ያህል አከራዮችህ ማዕቀብ ጥለውብሃል እንዴ?›› ብሎት ጓደኛው ሳቀ። ‹‹አንተ ደግሞ ነገር ማስፋት ስትወድ። እኔ ያልኩት ልቤ ያረፈባትን ልጅ የገዛ ራሴ ቤት ውስጥ ጊዜ ሰጥቼ መገምገም መቻሌን ነው። አንተ ደግሞ ምን ይሻልሃል?›› ይለዋል ልቡ ውልቅ ብሎ። 

‹‹ይኼ ግምገማ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት እስከ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ድረስ ያልገባበት የለም ማለት ነው?›› ይላሉ አዛውንቱ ብቻቸውን እየሳቁ። ‹‹የምን ግምገማ ነው የምታወራው?›› ግራ የተጋባው ጓደኛው ይጠይቃል። ‹‹የትዳር ነዋ! የዘንድሮ ትዳር ለምን ይመክናል አትልም? ሰው የራሱ ቤት ስለሌለው ግምገማውን የሚያካሂደው በየካፌው ስለሆነ እኮ ነው፤›› ብሎ ይመልሳል። ነገረ ሥራቸው የሚያስደንቁ ዓይነት ናቸው። ከወዲያ ኋላ መቀመጫ፣ ‹‹የግለሰብ ትዳር በቤት ዕጦት ይመጥናል ከተባለ የአገር ፖለቲካና ታሪክ በምን ሰበብ ይሆን ታዲያ ሲከሽፍ የኖረው?›› ብላ ስትጠይቅ አንዲት ወይዘሮ ትሰማለች። ነገርን ነገር ሲፈትለው ትዝብትን ትዝብት እየገመደው ጉዟችን ማቆሚያም የለው። መልሱ ጥቂት ሆነ እንጂ ጥያቄስ ሞልቶ ነበር፡፡         

ጎተራን እያለፍን ነው። ‹‹አገሩ በሙሉ በቃ መንገድ ብቻ ሆነ እኮ፤›› እያለ አንዱ በማሳለጫው መንገድ ይገረማል። ‹‹ኔትወርኩ ጠፋ እንጂ መንገዱስ ነበረ። ምን ታደርገዋለህ? በዚያው ልክ ምን መንገዱ ቢሰፋ ግፊያው ይብስበት ጀመር። ቅድሚያ ለአገር መስጠትን የሚያውቅበት ስለጠፋ ይኼው ሙስና አሁን ያለበት ደረጃ ደረሰ። አሁን መንገዶች ሁሉ ወደ እሱ ሲያመሩ ስታይ በጣም ታዝናለህ፤›› ይላዋል ሌላው። ከወዲያ ደግሞ፣ ‹‹እንደልብ አያስኬድም እንጂ እኮ ኢሕአዴግ መንገድ በመቀየስና በመገንባት መቼ ይታማል?›› ይላል። ‹‹ምናልባት ሠርተን አንጨርስ ብሎስ እንደሆን?›› ትጠይቃለች ከጎኔ ያለችው ወጣት። ‹‹እንዲያ ከሆነ ታዲያ ልማት ውስጥ ዲሞክራሲን ምን ዶለው?›› መልሶ ይጠይቃታል ጎልማሳው። 

ጨዋታው ጥቂት በትካዜ በተወሰዱ ሰዎች ምክንያት ጋብ አለ። ከወዲያ ከኋላ መቀመጫ፣ ‹‹እንዲያው ግን ዘንድሮ የዚህ የሰበር ዜና ነገር አይገርማችሁም?›› ሲል አንዱ ጨዋታ ጀመረ። ‹‹እንዴት?›› ትጠይቀዋለች ወጣቷ።  ‹‹አታይም እንዴ የቢቢሲና የአልጄዚራን ውሎ? ድሮ ሰበር ዜና ሲባል ቅስማችን አብሮ እንደሚሰበር ነበር የማስታውሰው። አሁን ከኢቲቪ ሌላ ሰበር ዜና ቢል የሚያስደነግጠን የቴሌቪዢን ጣቢያ እኮ የለም፤›› ይላል። ይህን ከማለቱ ቀበል አድርጋ ወይዘሮዋ፣ ‹‹ነውጠኛ፣ ጭፍን ተቃዋሚና አምባገነን በሞላበት ዓለም ውስጥ ሰበር ዜና በዝቶ ባንለምደው ምን ይገርማል? በተለይ የግብፅንና የሶሪያን ሁኔታ በተከታተልኩ ቁጥር ልቤ ይዝላል። ለምንድን ነው ግን ሰው ከታሪክ ተምሮ ግጭቶቹን በሰላም መፍታት እያቀተው የመጣው?›› ብላ ማንን እንደምትጠይቅ ሳናውቅ ተናገረች። ዝምታው ሲያይል ለእውነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት መስዋዕት የሚሆኑ ሕዝቦችን ለማሰብ የሚደረግ የህሊና ፀሎት መሰለ፡፡ 

 ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹መኖር ደጉ አያ እርጅና ስንቱን ያሳያል?›› እያሉ አዛውንቱ ለብቻቸው ሲነጋገሩ ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ኧረ በጣም ከዘመን ዘመን እየተሻገሩ መኖርን የመሰለ ነገር ምን አለ?›› አላቸው። ይኼኔ አዛውንቱ የተሰማቸውን ለመግለጽ ዕድል ስላገኙ ደስ እያላቸው፣ ‹‹ይገርምሃል እንዲህ ከዘመን አፋፍ ላይ ቆመህ ያለፈውን ስታይ ለማመን የሚከብዱህ ነገሮች መብዛታቸው። እኔ በዕድሜዬ ከቶ በዚህ አገር እንዲህ የለውጥና የሥራ ማዕበል አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ምንም እንኳ መሥራት ያለብንን ያህል ባለመሥራታችን ትናንት ከኋላችን የነበሩ አገሮች ጥለውን ቢሄዱም፣ ምንም እንኳ ልማቱ የአንድ እጅን ጡንቻ ብቻ ማዳበር እየሆነ ቢሄድም እዚህ መድረሳችን ትልቅ ነገር ነው፤›› ብለው የግል ትዝብታቸውን ሲያጋሩት እኛም እንሰማለን። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ መልዕክት ይሰማናል፡፡ ከታክሲ የሚሰማው ሬዲዮ ለመጪው እሑድ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚደረግ ይናገራል፡፡ ወጣቷ፣ ‹‹የምን ሠልፍ ነው?›› ብላ ስትጠይቅ፣ ወያላው ‹‹አክራሪዎችን ለመቃወም ነው በሉ መጨረሻ፤›› ብሎ የጉዞውን ማብቃት ነገረን፡፡ አዛውንቱ ከዘራቸውን ተደግፈው እየወረዱ፣ ‹‹የሚከር ነገር ደግ አይደለም፡፡ ማክረርና ውጥረት እንዲረግቡ እንጂ እንዲባባሱ ማድረግ ለማንም አይበጅም፡፡ ስለዚህ ወገኖቼ ደህና ዋሉ ውጥረትን አርግቡ፤›› ሲሉን በየተራ እየወረድን ወደ ጉዳያችን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ!