መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ዓለም - የአወዛጋቢዋ ማርገሬት ታቸር ሕልፈት
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

የአወዛጋቢዋ ማርገሬት ታቸር ሕልፈት

‹‹አለመስማማት ሲኖር መስማማትን እንድናመጣ፣ ስህተት ሲኖር እንድናርም፣ ጥርጣሬ ሲኖር እምነት እንድናሳድር፣ ተስፋ መቁረጥ ሲኖር ተስፋ እንድንፈነጥቅ እርዳን፤›› በሚለው የቅዱስ ፍራንቼስኮ ፀሎታቸው ይታወቃሉ፡፡

ለእንግሊዝ የመጀመርያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ በእንግሊዝ የወግ አጥባቂውን ፓርቲ እ.ኤ.አ. ከ1975 እስከ 1990 መርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1979 ጀምሮ በፈቃዳቸው ሥልጣን እስከለቀቁበት 1990 ድረስ ደግሞ አገሪቷን በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሦስት ተከታታይ ምርጫዎች ያሸነፉ ብቸኛዋ ፖለቲከኛም ናቸው፡፡ ላለፉት 150 ዓመታት በእንግሊዝ ለረዥም ጊዜ አገር የመሩ ብቸኛዋ መሪ መሆናቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ወይ ፍንክች በሚለው የፖለቲካ አቋማቸውና የመምራት ብሂላቸው አንድ የቀድሞዋ የሶቭየት ኅብረት የመከላከያ ጋዜጠኛ ‹‹አይረን ሌዲ›› የሚል ቅፅል ስም ሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹አይረን ሌዲ›› በሚለው ቅፅል ስማቸው ሚዲያዎች የሚጠሯቸው ባሮነስ ማርገሬት ሂልዳ ታቸር ይህችን ዓለም የተሰናበቷት ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በ87 ዓመታቸው ነበር፡፡
ለ11 ዓመታት እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ሚስ ታቸር በ1980ዎቹ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ከአገራቸው አልፈው በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የታቸር ተቀናቀኝ የነበሩት የሌበር ፓርቲው ቶኒ ብሌር እንዲሁም የቀድሞዋ የሶቭየት ኅብረት መሪ ሚኻኤል ጐርቫቾቭ የእንግሊዝን ኢኮኖሚ ከሥር መሠረቱ በመቀየር የነፃ ገበያን ጽንሰ ሀሳብ የተገበሩ፣ እንዲሁም ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ታላቅ መሪ ነበሩ ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ በጠንካራ ሠራተኝነታቸው የሚታወቁት አንደበተ ርቱዋ ሚስ ታቸር የሚወደዱም የሚጠሉም መሪ ነበሩ፡፡ ከብሪታንያ የማክሰኞ ጋዜጦች መካከል ዴይሊ ሜይል ‹‹እንግሊዝን ያተረፈች ሴት›› በማለት ሲጽፍ ዴይሊ ሚረር ደግሞ፣ ‹‹ሕዝቡን የከፋፈለች ሴት›› በማለት አስፍሯል፡፡

ሚስ ታቸር በእንግሊዝ የንግድ ማኅበራትን የበተኑ፣ የመንግሥት ኢንዱስትሪዎችን ወደግል እንዲዛወሩ ያደረጉ፣ የእንግሊዝ ወዳጅ ከነበሩ የአውሮፓ አገሮች ጋር የተናቆሩና የፎክላንድ ደሴቶችን ከአርጀንቲና ለማስመለስ ጦርነት የገጠሙ መሪ ናቸው፡፡

ቀዝቃዛውን ጦርነት ለማርገብ ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ጋር ጠንካራ ግንኙነት የፈጠሩ፣ እ.ኤ.አ. በ1991 የኢራቅ ኩዌትን መውረር ተከትሎ አሜሪካ የባህረ ሰላጤውው ጦርነት ስትከፍት የመጀመሪያውን ጆርጅ ቡሽ የደገፉ፣ እንዲሁም ከሚኻኤል ጐርቫቾቭ ጋር አብሮ መሥራት እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩም ነበሩ፡፡

የአገራቸውን የፖለቲካ ምኅዳር ብቻ ሳይሆን የዓለምን ጭምር የቀየሩ መሪዎች ይጠቀሱ ቢባል የማርገሬት ታቸር ስም ገዝፎ ይነገራል፡፡ በዓለም ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም ሲሉም እ.ኤ.አ. ከ1997 እስከ 2007 የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቶኒ ብሌር ይገልጿቸዋል፡፡

የወቅቱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ‹‹ትልቅ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር አጥተናል፡፡ ማርገሬት የመራችው አገር ብቻ አልነበረም፡፡ አገራችንን አትርፋለች፤›› ብለዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ደግሞ ‹‹አሜሪካ ትልቅ ወዳጇን አጣች፤›› በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአርጀንቲናውያን ዘንድ ብዙም የማይወደዱት ታቸር በፎክላንድ ደሴት ነዋሪዎች ዘንድ ‹‹የእኛ ዊንስተን ቸርችል›› በመባል ይሞገሳሉ፡፡ የነፃነት ተምሳሌት ናቸው በመባል በደጋፊዎቻቸው በኩል የሚሞካሹት ሚስ ታቸር፣ ከሚተቹባቸው ጉዳዮች አንዱ እሳቸው እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚመሩበት ወቅት በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መኖሩ ነበር፡፡ አልጄዚራ እንደዘገበው ታቸር ከነፃነት በኋላ የመጀመርያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካን የነፃነት ታጋዮች ‹‹አሸባሪ›› በማለት ይጠሯቸው ነበር፡፡

በአየርላንድ ሪፐብሊካኖች ዘንድ ታቸር በግትርነታቸውና በብሪታንያ እስር ቤት የረሃብ አድማ አድርገው ሕይወታቸውን ባጡ 10 አይሪሾች ምክንያት ይኮነናሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ እ.ኤ.አ. በ1984 በግራንድ ሆቴል ከተሞከረባቸው የቦምብ ግድያ ተርፈዋል፡፡

ሚስ ማርገሬት ታቸር በሕይወት እያሉም ሆነ ካለፉ በኋላ አከራካሪነታቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ በእንግሊዝ የመንግሥት ኢንዱስትሪዎችን ወደግል በማዛወር ነፃ ገበያን አጠናክረዋል፡፡ ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲን ተግብረዋል ቢባሉም፣ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ ለእንግሊዝ ውድቀትን ትተው አልፈዋል ይሏቸዋል፡፡

የሌበር ፓርቲ የቀድሞ መሪ የነበሩት ሎርድ ኪኖክ የሚስ ታቸር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብሪታንያን በቀላሉ ልትወጣው ወደማትችለው ውድቀት ከቷታል ብለዋል፡፡ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጐርደን ብራውን ስለጥንካሬያቸውና የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸው ሲያወሱ፣ የሌበር ፓርቲው ኤድ ሚልባንድ ሚስ ታቸር የተለየ ሰብዕና ያላቸውና የጠቅላላውን ትውልድ የፖለቲካ አመለካከት መልክ ያስያዙ ናቸው ብለዋቸዋል፡፡

የሚስ ታቸርን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቃወም ራሳቸውን ከሥልጣን ያገለሉት ወግ አጥባቂው ሎርድ ሎውሳን ‹‹ታቸር አምባገነን ነበረች›› ብለዋል፡፡ የነፃ ኢኮኖሚን ፖሊሲ በማስፈን ከተቀሩት የሶቫሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ተከታይ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲላተሙ የነበሩት ሚስ ታቸር የእንግሊዝን የኢንዱስትሪ ምኅዳር ወደ ዘመናዊነት የቀየሩ ነበሩ፡፡ ይህን በመቃወም በአገሪቷ የተለያዩ ብጥብጦችና ሠልፎች ይከናወኑ የነበረ ቢሆንም፣ ታቸር ዓላማቸውን ከግብ ሳያደርሱ አልቆሙም፡፡ በዚህም አንዳንዶች ግጭትን የምትመርጥ ሲሉ ሲያብጠለጥሏቸው ከርመዋል፡፡ ሚስ ማርገሬት ታቸር ግን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መምራት የቻሉ ነበሩ፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ባለቤት ናንሲ ሬገን፣ ሮናልድ ሬገንና ሚስ ታቸር ለኮሙዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም በነበራቸው ጥላቻ የተነሳ የተለየ ግንኙነት ነበራቸው ብለው፣ ‹‹ሬገንና ማርገሬት የፖለቲካ መንፈሳቸው የተጣመረ ነበር፡፡ ታቸር ብዙዎች ጀልባውን መቅዘፍ በሚፈሩበት ወቅት ዓላማዋን ከግብ ለማድረስ ጠንካራና ቁርጠኝነት ያሳየች መሪ ነበረች፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

የፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቲዊተር ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹የማትፈራ የነፃነት ታጋይ፣ ነፃ የሆነ ሕዝብ እንዲኖር የቆመችና ዓለም ቀዝቃዛውን ጦርነት እንዲያሸንፍ የረዳች፤›› ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል፡፡

የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ከሌበር ፓርቲው ጋር ብዙ የሚለያይባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ የሌበር ፓርቲው ቶኒ ብሌር ታቸር የነበሩ አሠራሮችን ይዞ ይጓዝ ለነበረው ሌበር ፓርቲ ፈተና መሆናቸው ጥሩ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ለእንግሊዝ ያደረገችው አስተዋጽኦም ቀላል አልነበረም፤›› ይላሉ፡፡ ለእንግሊዛውያን ሕይወት መለወጥ የነበራቸውን አስተዋጽኦና ባህሪ ማክበር ይገባል ሲሉም ይናገራሉ፡፡

ሆኖም በብሌር አነጋገር ሁሉም አይስማሙም፡፡ የሚስ ታቸር ሕልፈተ ሕይወት እንደተሰማ ደስታቸውን ለመግለጽ በግላስጐውና በለንደን አደባባይ የወጡም ነበሩ፡፡ በታቸር ፖሊሲ የተሽመደመደው የማዕድን አውጭዎች ብሔራዊ ማኅበር ለታቸር ቤተሰቦች ሐዘኑን ከመግለጽ ይልቅ በእሳቸው የፖለቲካ ውሳኔ ምክንያት በማኅበሩ ላይ ስለደረሰው ውድመት ነበር የገለጸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1926 በእንግሊዝ ግራንታም የተወለዱት ማርገሬት ታቸር በሥልጣን ዘመናቸውና ካለፉም በኋላ የዓለምን አመለካከት ከፍለው መያዝ የቻሉ አወዛጋቢ መሪ ሆነዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1951 ከነጋዴው ሚስተር ዴኒስ ታቸር ጋር ጋብቻ በመፈጸም ሁለት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በስትሮክ ምክንያት እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡