መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ዝንቅ - ‹‹ኧረ ምን ጉድ ነው?››
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
04 August 2013 ተጻፈ በ 

‹‹ኧረ ምን ጉድ ነው?››

ከአርሲ አካባቢ አዲስ አበባ ጎራ ያሉ ገጠርተኞች፣ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ፣ በማቲ ሲኒማ ስክሪን ላይ የሚታየውን የአንበሶች ፊልም በአግራሞት
ሲከታተሉ ፎቶ/ በሪፖርተር በታምራት ጌታቸው

የሚሆነው ሁሉ ይሁን
እኛን ሲውጠን መከራ
አዎ እናንተማ ዝለሉ ከበሮ ምቱ ዳንኪራ
ቁረጡ ጮማና ጎድን ተራጩ ውስኪና ቢራ
    እሰይ! እናንተ ዝፈኑ ድምፃችሁ
               ያምራል ቆንጆ ነው!!
      እዬዩ ዋይታው ለእኛ ነው
      ሳቁ! ቦርቁ! ፈንድቁ!
      ከአበባና ከጨረቃ፣ ከኮከብ በላይ ድመቁ
      እሬሳችን ላይ ደንሱ አጥንታችንን አድቅቁ
እናንተ ብሉ፣ ጥገቡ፣ ተራጩ ውስኪና ቢራ
እኛ በረሃብ እንሙት ስቃይ እንግልት እናውራ
የእናንተ ሕይወት ይታደስ
የእኛ እንባ ግዴለም ይፍሰስ
የእናንተ ኑሮ ጣፈጠ
የእኛ ዓለምን ግን ኮመጠጠ
    እናንተ ወርቆች፣ አልማዞች
    እኛ ገለባ - እንክርዳዶች
    ይህ ሁሉ ይሁን እንደሻው
             ይሁን የሚሆን በሞላ
ያቺ ቀን እስክትመጣ ያቺ ጽዋ እስክትሞላ
-    ሰሎሞን ሞገስ ‹‹ከፀሐይ በታች›› (2004)‹‹ምንድን ነው እንዴታ?›› - የአኙዋ ተረት
በጥንት ጊዜ አሾል የምትባል አንዲት ልጅ ከአባቷ ጋር ትኖር ነበር፡፡ አባቷ ኦባንግ ይባል ነበር፡፡ ኦባንግ አሾልን በጥሩ ሁኔታ ካሳደጋት በኋላ ከወንድ ጋር ግን ፈጽሞ እንዳትገናኝ ከለከላት፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ጓሮ ስትወጣ ተከትሏት ይወጣል፡፡ ውኃ ለመቅዳት ስትሄድም አብሯት ይሄዳል፡፡ እንጨት ልትሰብር በሄደች ጊዜም እንደዚሁ አብሮ ተከትሏት ይሄዳል፡፡ ብቻዋን መሄዷን ካወቀም ክፉ ነገር ይናገራታል፡፡ ይሰድባታል፡፡ ሁሉጊዜ ይወቅሳታል፡፡ በዚህ ምክንያት አሾል ታስራ በመቀመጧና እንደ ባልንጀሮቿ የወንድ ጓደኛ ሳትመርጥ በመኖሯ በጣም በጣም ትበሳጭና ታዝን ነበር፡፡ እየተበሳጨች በምትገኝበት በዚሁ ሁኔታ ላይ ደግሞ የአገሩ ሰው ‹‹ወንድ ጤፉ›› የሚል ቅጽል ስም አወጣላት፡፡ በዚህ ሁኔታ ዕድሜዋ እየጨመረ ከሄደ በኋላ አንድ የሚወዳት ልጅ አገኘችና በጣም ተደሰተች፡፡

ከፍቅረኛዋ ጋር ተዋደው ሲኖሩ አባቷ ፈጽሞ ከወንድ ጋር ትገናኛለች የሚል ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ ሆኖም አንድ ቀን የአሾል ሆድ እየገፋ የመጣ መሰለው፡፡ እየዋለ እያደረ በሄደ ቁጥርም ጥርጣሬው በጣም እየጎላ መጣ፡፡ በኋላ አባቷ በጣም ተናደደና ‹‹አርግዘሻል ወይ?›› በማለት አፋጥጦ ጠየቃት፡፡ እሷም ያበጠው ይፈንዳ አለችና ‹‹እንዴታ!›› ስትል መለሰችለት፡፡ ኦባንግ ይበልጥ ተናዶ ‹‹ምንድነው እንዴታ?›› ብሎ በቁጣ ጮኸባት፡፡ በዚህ ጊዜ አሾል ‹‹አንተ ለምን ነበር እናቴን ያስረገዝክ?›› አለችው እንደገና፡፡ ከዚያም ኦባንግ የባሰ በመናደድ ‹‹እኔማ ልጅ ፈልጌ ነዋ!›› አላት፡፡ እሷም እንደዚያው ‹‹እኔም ልጅ ፈልጌ ነዋ!›› አለችውና አፉን አስያዘችው፡፡ ኋላም ካፈቀረችው ወጣት ጋር ተጋብታ በደስታ ኖረች ይባላል፡፡
-    ባይለየኝ ጣሰው ‹‹የአኙዋ ተረቶች ሌሮ ዎች አኙዋ›› (1995)ፍቅር በሒሳብ
በአንዳች ቅጽበት set ነትሽን አድንቄ ቀርቤ ላወራሽ ብፈልግ ስለፍቅርሽ እኔ ለፍቅር  negative ነኝ ብለሽ ብታስደነግጭኝም እኔ ግን ለፍቅር positvie ሳስብም እኔ radical ውስጥ የገባሁ ነኝ ብትይም ተማመንኩ፡፡ ከcomplex system ላስቀር negative ፍቅርሽን sub set ሆነሽብኝ ፍጹም ብታስቸግሪኝም በsine መስመር ወደ አንቺ ብመጣ የአንቺ ምርጫ በcosine መስመር ሆኖ ቢያስከፋኝም ተስፋ ባለመቁረጥ በhorizontal line ወይስ በsymptote ወደ አንቺ ለመቅረብ አንድ ሐሳብ መጣልኝ፤ ሳሰላስል ድንገት ወስኜ ለራሴ እንደ polynomila በ power በዝቼ rationalize ሆነ inverse ሆኜ በመምጣት እንዳለብኝ ወሰንኩ አንቺን ፈልጌ፡፡

የምር ግን አስቸጋሪ ነሽ ለፍቅር empty set ነሽ፡፡ በሂሳብ ቀመር በ subtracton ኧረ እባክሽ በmultiplication ደግሞም በaddition እኔ ልሆንልሽ የፍቅርሽ division:: የፍቅርሽ ውስብስብነት በlimit “x” goes to beta አለመፈታቱ ቢሆንብኝ ስቃይ በሐሳብ ብዞር በቁጥሮች ጎራ በgraph ዎች መንደር በcircle አደባባይ በquadratic ሰፈር በcalculus እና በመደመር አንቺ ግን ክፋትሽ አሁንም undifined ነሽ፡፡ ግን solve ማድረጊያው የፍቅርሽ መንገዱ sequence አይደለም፤ አቤት ክፋቱ እኔ ግን ተስፋ ባለመቁረጥ logarithm ተጠቅሜ exponentialን አብዝቼ በsolution set ቦታ ሆኜ perimeter ሽን አቅፌ vertical line ሽን አይቼ upper and lower bounedሽን አረጋግጩ remainder ሽን በድካም አግኝቼ square root ሳላበዛ ተስፋ አደርጋለሁ እንደማግኝሽ፡፡ በfunction ቦታ ካልተገኘሽ የፍቅር slope ካልገባሽ የ “x” “y” ዋጋ ካልሆንሽ የምር አሁንም ለፍቅር empty set ነሽ፤ ለፍቅር undefined ነሽ፤ ለፍቅር one over zero ነሽ፤ ሁሌም ነሽ፡፡


የመምህሩ ውለታ
ሳይንስን እያስተማሩ ጎን ለጎን የሳይንስ ፋክሊቲ ዲን በመሆን ኃላፊነታቸውን ይወጡ የነበሩ አንድ መምህር በዚያ ወቅት ለአንድ ተማሪያቸው የዋሉት ውለታ የማይረሳ ነበር፡፡ ያኔ መምህራቸው የዋሉላቸውን ውለታ ጃንዋሪ 5 ቀን 2009 አዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ባደረጉት ምስክርነት የሰጡት ቃል ይህን ይመስል ነበር፡፡

‹‹በእኔና በዶክተር ተወልደ መካከል ያለውን ዝምድና እዚህ ጋር ላነሳ እወዳለሁ፡፡ ቀደም ብሎ እሱ እንደጠቆመው እኔ ወጣት ተማሪ ነበርኩ፡፡ እሱ ደግሞ የተከበረ ወጣት ምሁር ነበር፡፡  በዚያ ወቅት የአፄው ሥርዓት ማክተሚያው ላይ ደርሷል፡፡ በወጣትነታችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እያለን በወቅቱ ከአፄው ሥርዓት ማክተሚያው ላይ ደርሷል፡፡ በወጣትነታችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እያለን በወቅቱ ከአፄው አባቶች ጋር ተፋጠጥን፡፡ የክብር ዘበኛ ጦርም አራት ኪሎና አካባቢዋን ወረራት፡፡ በርካታ ተማሪዎች ታፈሱ፡፡ የተወሰንን ተማሪዎች አምልጠን ወደ ዲኑ ቢሮ ሸሸን፡፡ በወቅቱ የሳይንስ ፋክሊቲው ዲን የነበረው ይኸው ሰው ነው፡፡ ዶ/ር ተወልደ በጥሩ ስሜት ቢሮ ውስጥ ተቀበለን፤ ከዚያም ቢሮው ውስጥ ቆልፎብን ከክብር ዘበኛ አደጋ ተከለልን፡፡ ይህንን ዓይነት ጥላ ከለላ ሊሆነን በመቻሉ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡››
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ
‹‹መለስ ለአፍሪካ የዓለም አቀፍ ጀግናችን››
  ************************


ጊዜን በስላቅ
የሥዕል አስተማሪ ክፍል ውስጥ ይገቡና ለተማሪዎቻቸው የክፍል ሥራ ይሰጣሉ፡፡ መምህሩ ተማሪዎቻቸው ስለው እንዲያሳዩዋቸው የጠየቁት በሀዲዱ ላይ የሚጓዝ ባቡር ወይም ባቡሩን ከነሀዲዱ ቁጭ እንዲያደርጉላቸው ነው፡፡ ክፍለ ጊዜው ከማለቁ በፊት እንዲታረምላችሁ በፍጥነት ሥሩ ይሉና ወደ መቀመጫቸው ያመራሉ፡፡ ቁጭ እንዳሉ እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋቸውና ክፍለ ጊዜው ሊያልቅ 5 ደቂቃ ሲቀረው ይነቃሉ፡፡ ወዲያውም ተማሪዎቻቸው የሠሩትን በየተራ እየተመለከቱ ሲያርሙላቸው ከተማሪዎቹ መካከል አንደኛው ሐዲዱን ብቻ ሥሎ ያሳያል፡፡ መምህሩ ሲመለከቱት ባቡሩ የለም ሀዲዱን ብቻ ይመለከቱና ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ መምህሩ፡- ስላችሁ አሳዩኝ ያልኳችሁ በሀዲድ ላይ የሚጓዝ ባቡር ነው፣ አንተ የሣልከው ደግሞ ሀዲዱን ብቻ ነው፤ ባቡሩስ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ተማሪ፡- አይ ቲቸር እርስዎ እኮ እንቅልፍ ወስዶዎት እያለ ባቡሩ አልፏል፡፡ ለዚህ ነው ሀዲዱን ብቻ የሚመለከቱት ብሎ አሸነፋቸው፡፡
  ************************

በዩኔስኮ የተመዘገቡ የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች
-    ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችና ቅርሶች ባለቤት የመሆኗን ያህል በተለይም ከአፍሪካ አገሮች በተሻለ ሁኔታ ቅርሶቿን ለዓለም ሕዝብ ያበረከተችና ዕውቅና ያገኘች አገር ነች፤
-    በዩኔስኮ ከተመዘገቡ 9 ቅርሶቻችን በተጨማሪ በሥነ ጽሑፍ ታሪክም 12 የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኩል አስመዝግባ ለዓለም ኅብረተሰብ አበርክታለች፤ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-
1.    ግብረ ሕማማት (በ15ኛ ክፍለ ዘመን የተፃፈ)
2.    የሸዋው ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ለእንግሊዝ ንግሥት የፃፉት ደብዳቤ
3.    ታሪከ ነገሥት (በ20ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
4.    የዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ (በ19ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
5.    ዐርባዕቱ ወንጌል (በ14ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
6.    ፍትሐ ነገሥት (በ19ኛ ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
7.    አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶርያ የፃፉት ደብዳቤ
8.    መጽሐፈ ሔኖክ (በ15ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
9.    የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት (በ15ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
10.    ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ለመስኮብ ንጉሥ ኒኮላስ ቄሳር 2ኛ የፃፉት ደብዳቤ (በ19ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
11.     መጽሐፈ ቅዳሴ (በ17ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
12.    መዝሙረ ዳዊት (በ16ኛው ክፍለ ዘመን) የተፃፈ
- ቱባ መጽሔት


አባባሎች
•    ከጸጉራችን ቀድሞ የሚያረጀው ውስጣችን ነው፡፡
•    ሁለት ውሾች በአንድ አጥንት ተስማምተው አያውቁም፡፡
•    እድለኛ ሰው ውሃ ውስጥ ቢወረውሩት አሳ ይዞ ይወጣል፡፡
•    እኛ የምናደንቀው ጨረቃ ላይ የወጡትን ሳይንቲስቶች ሳይሆን ጨረቃ ላይ እንዲወጡ ያስተማሯቸውን መምህራን ነው፡፡
ሪቻርድ ኒክሰን /የአሜሪካን ፕሬዝዳንት/
•    ለማስተማር የሚደፍር መማርን መዘንጋት የለበትም
ጆን ኮቶን ዳና
•    የመማር ፍላጎት ሳይቀሰቀስ ለማስተማር የሚነሳ መምህር ካልጋለ ብረት ስለትን ከሚሻ ቀጥቃጭ ጋር ይመሳሰላል፡፡
ሆራስ ማን