መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ልዩ ልዩ - ዝንቅ - የአዲስ አበባው ጎርፍ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
25 August 2013 ተጻፈ በ 

የአዲስ አበባው ጎርፍ

መሰንበቻውን በሩቅ ምሥራቅም ሆነ በአካባቢው አገሮች ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ሕይወትን ጨምሮ ለከፍተኛ ጥፋት እንደዳረገ በኢትዮጵያም በቅርቡ በደቡብ ወሎ ከሚሴ አካባቢም ሕይወትን የቀጠፈ አደጋም ደርሶ እንደነበር መገናኛ ብዙኀኑ ዘግበውታል፡፡

በአዲስ አበባ የከፋ አደጋ ባይፈጥርም በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መስመር) ሜሪዲያን ሆቴል ፊት ለፊት ባለፈው ሳምንት የጣለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በአካባቢው ለመተላለፍ አደጋ ሆኖ ነበር፡፡ የውኃ መተላለፊያ ቱቦዎች በመዘጋታቸው የከተማይቱን የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ባለሙያዎች ዕርዳታ አስፈልጎ ነበር፡፡ 

(ፎቶ በናሆም ተስፋዬ)

ያቺ መንደር

የትም ተሰደን ብንኖር እርቀን ከእናት አገር፣ 

ይሸተናል ውብ ጠረኗ ያደግንባት ያቺ መንደር፣

ጭቃ ያቦካንባት የልጅነት ትውስታ፣ 

መች ይጠፋል ስለራቅን የማምዬ የአፈር ሽታ፣ 

ማን ሊያወጣው ከልባችን የትኛው ድሎት ሊያስረሳ?

ጭራሽ ያብሳል እንጂ እንደ ግርሻ እየተነሳ፣ 

በሽቦ የሰራነው መኪና፣ የጨርቅ አሻንጉሊቱ፣ 

አንበጣ እየተከተሉ ‹ና ቡና ጠጣ!› ማለቱ፣ 

አባሮሹ፣ ጢባጢቤው፣ ሰኞ ማክሰኞ ጨዋታ፣ 

ቅልልቦሽ፣ ገመድ ዝላይ፣ እቴሜይቴ የሎሚ ሽታ፣ 

‹አኩኩሉ ነገ አልነጋም› ተደብቆ ፍለጋ፣ 

የጨርቅ እና የላስቲክ ኳስ እስኪቦጫጨቅ ሲለጋ፣ 

ጎሉ በድንጋይ ተሰርቶ ዋንጫው በበረኪና 

ድጋፍ ጩኸቱ ሲደምቅ ጨዋታው ሲጀመር ገና 

አቧራው ሲቦን ጎል ሲገባ - ዜማ ግጥም ሲንበለበል፣ 

ማታ ነው ድሌ! ሲባል ለእኛ ሌላው ሰፈር ሲብጠለጠል፣ 

ኧረ ስንቱ!... ይታወሳል የሰፈራችን ትዝታ፣ 

መቼ ያልቃል? ቢያወሩትስ ቀን ጀምረው እስከማታ!

-ሳምሶን ይርሳው ጌትነት ‹‹ምልክት›› (2005)

****************************

ዳኛቸው ስለ በዓሉ

በሕይወት የሌሉት ኹለቱ ስመጥር ደራስያን በዓሉ ግርማና ዳኛቸው ወርቁ በተመሳሳይ ዘመን ባቀረቧቸው ልቦለዶቻቸው ‹‹ካድማስ ባሻገር›› (የበዓሉ) እና ‹‹አደፍርስ›› (የዳኛቸው) ጎልተው ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ፈርጥ ኾነውም አልፈዋል፡፡ ሥራዎቻቸውም ዘመን ተሻጋሪ ኾነዋል፡፡ በዓሉ ኹለተኛውን ልቦለዱን ‹‹የህሊና ደወል›› ሲያሳትም ከመጽሐፉ ሽፋን ጀርባ አስተያየት ከ30 ዓመት በፊት ነበር፡፡ ከልቦለዱ ይዘት ተነሥቶ ያሰፈረው ምልከታ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

‹‹ሐዲስ ሣህሌ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ ለአንድ ዓመት በማስተማር ራሱን ለመርዳት የተሠማራ ቢሆንም በገጠሩ ችግር ምክንያት ራሱን ለሕዝቡ እንዲሰዋ የተገፋፋ ወጣት ነው፡፡ ያለፈውን ትውልድ ሥራና ክንውን በማውጠንጠንና ከሚገባው በላይ ታላቅነቱን በማጋነን በትዝታ ተውጦ አይባንክንም፡፡ በትዝታ የሚባክን ትውልድ በራሱ የማይተማመን የሚኖርበትን ዘመን ችግሮች መቋቋም ያልቻለና መኖር ያቃተው መሆኑን የተገነዘበ ይመስላል ሐዲስ ለኢትዮጵያ አዲስ ፍጡር ነው፡፡ በወሬ አይፈታም፤ ዓላማው በሙሉ ሠርቶ ለማሳየት ነው፡፡ መሰናክሎች ይገጥሙታል፡፡ ፈተና ይደርስበታል፤ ለሕይወቱ ያሰጋበትም ጊዜ ነበር፡፡ እንዴት ሊወጣው ቻለ?

‹‹ጥንታዊውን ሳያሞካሽ ወይም ሳያንጓልል፤ ዘመናዊውምን ሳያጋንንና ሳያካኪስ በተደላደለ መንፈስ የቀረበ ውብ የሆነ ልብ ወለድ ጽሑፍ ነው፡፡ ከ‹አድማስ ባሻገር› ይታይ የነበረው ወጣት በኅሊና ደወል ከአድማስ ወዲህ ተከሰተ፡፡››

*************************************

የመነጽር አያያዝ

ስኮትላንዳዊው ባለቤቱን ሲመክራት፣ ‹‹የምታዬው ነገር ከሌለ አዲሱ መነጸርሽን ማውለቅ አትዘንጊ›› አላት ይባላል፡፡ 

* * *

ምፅዋት

የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቱ አብቅቶ መዘምራኑ ማራኪ መዝሙሮችን እያሰሙ ምፅዋት በመሰብሰብ ላይ ሳለ አንዷ አገልጋይ ሙዳየ ምፅዋቱን ይዛ ወደ አዛውንቱ ስኮትላንዳዊ ቀረበችና፣ ‹‹አብዬ፣ ለጌታችን የሚሆን አንድ ፔንስ (ሣንቲም) ምፅዋት ይስጡኝ›› አለቻቸው፡፡ 

‹‹ዕድሜሽ ስንት ነው፣ ልጄ?›› 

‹‹አሥራ ስድስት፡፡››

‹‹እንግዲያውስ›› አሉ እየሳቁ፤ ‹‹እኔ ዘጠና ዓመት ሞልቶኛል፡፡ ስለዚህ ፈጣሪያችንን ካንቺ ቀድሜ ስለማገኘው ለርሱ በእጁ እሰጠዋለሁ፡፡››

**************************************

ማን በለጠ?

እንግሊዛዊው፣ አየርላንዳዊውና ስኮትላንዳዊው ጩኸት የበዛበትና በጭስ የታፈነ በርካታ ሰዎች የተሰበሰቡበት መጠጥ ቤት ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ የእንግሊዙ ተወላጅ ‹‹የአገሬ የእንግሊዝ መጠጥ ቤቶች ምርጦች ናቸው፡፡ አንደ ነገር የጠጣ ሰው ሁለተኛውን በነፃ ይጋበዛል!›› አለ፡፡ ጠጪዎቹ በመገረም ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡

አየርላንዳዊው በበኩሉ፣ ‹‹በኔ አገር አንድ ነገር የወሰደ ሰው ሁለት በነፃ ይጋበዛል›› በማለቱ ጠጪዎቹ ይበልጥ በመደነቅ አጨበጨቡ፡፡ 

በመጨረሻ ስኮትላንዳዊው፣ ‹‹የናንተ መዝናኛ ሥፍራዎች ጥሩ ቢሆኑም እንደ ስኮትለንድ ሊሆኑ ግን አይችሉም፡፡ ስኮትላንድ ውስጥ አንድ መለኪያ በሒሳባችሁ ከጠጣችሁ፣ ሦስት በነፃ ትጋበዙና ባክብሮትና በፍቅር ቤታችሁ ድረስ ትሸኛላችሁ!›› አለ፡፡ 

እንግሊዛዊው በሸቀ፡፡ ‹‹አታጋን እባክህ፤ አሁን የተናገርከው አጋጥሞህ ያውቃል? በዓይንህ በብረቱ አይተሃል?›› በማለትም በቁጣ ጠየቀው፡፡ 

ስኮትላንዳዊው እየሳቀ፣ ‹‹እኔን ባያጋጥመኝም፤ እህቴን አጋጥሟታል›› አለው፡፡

-አረፈዓይኔ ሐጎስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች (2005)

*************************************

ከታ

(ይህ ታሪክ ከከታ ምድር ተነሥቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስለገባ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ይተርካል፡፡ ያ ወጣት እኔ ነኝ…)

ይህ የእኔ የክንዴ ቅንጭብ ታሪክ ነው፡፡ 

ጉዞ……. 

ከአዲስ አበባ ተነስተው፣ ቃሊቲን ሰንጥቀው፣ አቃቂን አቋርጠው፣ ዱከምን ከኋላ ጥለው ቢሾፍቱ ለመድረስ የተወሰነ ርቀት ሲቀርዎ ወደ ቀኝ ይታጠፉ፣ ወደ ቀኝ ታጥፈው ብቻ እንዳይቆሙ አሁንም ይጓዙ፣ ይጓዙ፤ ሸንተረሮች፣ ተራራዎች… ቢያጋጥምዎ እንዳይበገሩ፣ ትንንሽ ጅረቶች ቢያቋርጡ እጅ እንዳይሰጡ፡፡ አሁን በዛ አሉ? ግዴለም ትንሽ ነው የሚቀረን ደርሰናል፡፡ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከከፈሉ በኋላ የት የሚደርሱ ይመስልዎታል ከኔ የትውልድ መንደር ከታ!

ወደ መንደራችን እየቀረቡ ሲመቱ ‹‹እህህህ… ለመንደሩ እንግዳ ነህ?›› የሚሉ በዕድሜ ጠና ያሉ አረጋዊ ካጋጠሙዎ እሳቸው የገረሱ አባት ጋሸ በዳዳ ናቸው፡፡ እሳቸውንም ሰላምታ ሰጥተው እንዳለፉ… ምናልባት እድለኛ ከሆኑ እናቴ ከደጅ ተቀምጣ ምሳ እያሰናዳች ይሆናል፤ ዕድልዎን እያመሰገኑ በአድአ ነጭ ጤፍ የተሽሞነሞነ ምሳዎትን በልተው ሊመጡ ነው ደስ ይበልዎ! የእናት ነገር ሆኖብኝ እሷን አስቀደምኩ እንጂ ከአጎቶቼ አንዱን አግኝተው እርጎ የሆነ ጠላ ተጋብዘው ሊመጡ ስለሚችሉ ከታ ድረስ ለምን ደከምኩ ብለው እንደማያማርሩ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከታም ደሞ የት ነው እንደሚሉ አልጠራጠርም፤ ከታን በዓለም ላይ ልዩ የሚያደርገውስ ምንድነው? ብለው እንደሚጠይቁም በድጋሜ አልጠራጠርም፡፡ ባለመጠራጠሬም ጥያቄዎን ለመመለስ እጣደፋለሁ፡፡

ከታ ከባሕር ጠለል በላይ በምን ያህል ከፍታ እንደምትገኝ ባላውቅም (ማን የባሕር ጠለል ሲፈልግ ይውላል) ዱከምን፣ ዝቋላን እንዲሁም አቃቂን መንደርተኛ አድርጋ የተፈጠረች ስፍራ ናት! ከታን በዓለም ላይ በጣም ለየት የሚያደርጋት ብቸኛ ነገር አለ ከተባሉ እኔ በከታ መወለዴ ነው፡፡ (በሽሙጥ እንደማይስቁ ይማሉልኝ!) ከዚህ ሌላ ከታን ለየት የሚያደርጋት ነገር ይፈልግ ከተባለ በልጅነቴ ሳስበው ይገርመኝ እንደነበረው በጥቁር አፈር ላይ ነጭ ጤፍ ማብቀሏ ነው፡፡ በርግጥ በዕድሜ እየበሰልኩ ስመጣ በጥቁር ላይ ነጭ መብቀሉ የዓለም እውነት ነው ብዬ የቀለም አድልኦን ተፈጥሯዊ በማስመሰል በመፈላሰፍ ጥረት አድርጌያለሁ (ማንም ይኼን ጥረቴን ባያውቅልኝም)፡፡ ለማንኛውም የከታ አርሶ አደር እንደኔ ለመፈላሰፍ ግድ ሳይሰጠው በርትቶ በማረስ ለአዲስ አበባ ሕዝብ የጤፍ ፍጆታ ያቀርባል፡፡ ይህ አምሮበት የምታዩት አዲስ አበባያዊ ለውበቱ ምክንያት የሆነችውን ከታን ሳያውቋት ዘመናት መቆጠሩ በጣም ያሳዝናል እንላለን እኛ የከታ ልጆች! 

-ዮፍታሔ ካሳ ‹‹በአራጣ የተያዘ ጭን›› (2005)

************************************

ጥቁሩ ቁራ

በፕሮፌሰር አህመድ መሐመድ ዓሊ የተተረከ

ቁራ በአንድ ወቅት ሼኪ ወይም ቄስ ስለነበረ ቀለሙም ነጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ አዕዋፋት ሁሉ አቤቱታ አሰሙበት፡፡ እንደዚህም አሉ ‹‹በአንድ ወገን ሥጋ ይበላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍራፍሬ ይበላል፡፡››

ከዚያም ሁሉም አዕዋፋት ተሰባስበው ‹‹አንተ ሼኪ ወይም ቄስ ነህ! ነገር ግን የምትሰራው ነገር ስህተት ነው፡፡ ትንንሾቹ አዕዋፋት ሥጋ መመገብ አለባቸው፡፡ ትልልቆቹ ደግሞ ፍራፍሬ ይብሉ፡፡ አንተ ግን ከሁለቱም ወገን ትበላለህ፡፡›› አሉት፡፡

በሱማሌ ብቻ ሳይሆን በኩሽ ባህል በአጠቃላይ ቁራ የፀሐይ አምላክ የሆነው የዋቅ ተወካይ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ኦሮሞዎችም ጭምር በፀሐይ አምላክ ያምናሉ፡፡ ቁራ የፀሐይ አምላክ ዋቅ የተናገረውን ለሰዎች የሚተረጉምና የሰዎችንም መልዕክት ወደ ፀሐዩ አምላክ የሚያደርስ መሆኑን ያምናሉ፡፡

ቁራውም ሲናገር ‹‹ዋቅ! ዋቅ!›› እያለ ነው፡፡

ሆኖም ቁራው እምነት በማጉደል ሁለቱንም ነገሮች ማለትም ፍራፍሬና ሥጋ ስለበላ ቅጣት ተጣለበት፡፡ ረግመውትም ጥቁር ሆኖ ቀረ፡፡

-የኢትዮጵያ ሶማሌ ተረት ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ የተጠለፈ