መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - እኔ የምለው - ምነው አንድ ጊዜ በወጣልን?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
31 March 2013 ተጻፈ በ 

ምነው አንድ ጊዜ በወጣልን?

በመዝገበቃል አየለ ገላጋይ

ባልና ሚስቱ በአንድ ቤት ውስጥ የአብሮነት ሕይወት መሥርተው ይኖራሉ፡፡ በአብሮነት መኖራቸው የጋራ ሕይወት መመሥረታቸው መልካም ነው፡፡

ምነው ለብዙዎቻችን ኑሮ ላጤዎችም ባደረገልን፡፡ ነገር ግን ማጀታቸው በመለሰ ደጃፋቸው በጎረሰ ለአብሮነታቸው አደጋ የሆነ አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡ የችግሩም መንስዔ እንዲህ ነበር፡፡ ሚስትየዋ በቆመች፣ በተቀመጠችና በተንቀሳቀሰች ቁጥር የማኅበረሰቡን ባህልና ወግ ማክበሩን ዘንግታ በመቀመጫዋ መጥፎ ጠረን ያለው ትንፋሽ አበክራ ትተነፍሳለች፡፡ የጉዳዩ መደጋገም ያሳሰበው ባልም ከእሱ አልፎ እግር በጣለው እንግዳ ፊትና ከቤት ውጭ ባለ ማኅበራዊ ግንኙነቷም እንዳይከሰት ስጋት ፈጥሮበት በሁኔታው ይብሰለሰላል፡፡ አይገስፃት በይሉኝታ ታንቋል፤ ዝም አይላት ደግሞ በጉዳዩ አሳፋሪነት ተሳቋል፡፡ እሷ ግን አሁንም በጉዳዩ እንደቀጠለች ናት፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ባል ሁኔታው ትርጉም ሊሰጠው የማይችል አግራሞት ፈጥሮበት ፈገፍ ይላል፡፡ የባሏን በሷ ድርጊት ምክንያት ፈገግ ማለት የተመለከተችው ሚስትም ‹‹መሳቁ ነው! ጠንቋይ ተሂዶ አይጠየቅልኝ፤ ገብስማ ዶሮ ለመድኃኒት አይገዛልኝ፤ መታመሜ ለናቴ አይነገርልኝ፤ እንትን እንደ ደም እየወረደኝ፤›› ትለዋለች፡፡ የሚስቱን ንግግር ያዳመጠው ባልም ‹‹ለካስ ባለቤቴ ታማለች ማለት ነው?›› ይልና ለጤንነቷ መፍትሔ ለመጠየቅ በአካባቢው አለ ወደሚባል ጠንቋይ ይሄዳል፡፡ ጠንቋዩም ‹‹ምን ሆነህ መጣህ? ይለዋል፡፡ ባልም ‹‹ሚስቴን አሟት›› በማለት ይመልሳል፡፡ ጠንቋዩ አሁንም መልሶ ‹‹እንዴት ነው የሚያደርጋት?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ባልም ‹‹በተንቀሳቀሰች ቁጥር በመቀመጫዋ ያስተነፍሳታል›› ጠንቋዩም የባልየውን መልስ ካዳመጠ በኋላ ሁኔታውን አሰብ አድርጎ ‹‹የኔ ወንድም አጉል ላትድን አትድከም፤ የተለከፈችው ከባቄላው ቶፋ ነው፤›› ይለዋል፡፡

በጠንቋዩ የጥንቆላ ፍርድ የተደናገጠው ባልም ተነስቶ ወደ አማቱ ቤት ይሄዳል፡፡ አማቲቱም ለአማች የሚመጥነው ሰላምታ ከሰጡ በኋላ ‹‹ልጄ ሰላም ናት? እንዴት ብላ ሰነበተች?›› በማለት የልጃቸውን ሰላም መሆን ይጠይቃሉ፡፡ አማችም ‹‹ኧረ እናቴ እሷንስ አሟት ሰነበተ›› ሲል ይመልሳል፡፡ ‹‹ወይ ልጄ እንዴት አደረጋት?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹በተንቀሳቀሰች ቁጥር በመቀመጫዋ ያስተነፍሳታል›› ሲላቸው አማትም በልጃቸው የሕመም ዓይነት በጣም ያፍሩና ‹‹ኧረ ይቺ አሳፋሪ ከዘራችን እንኳን እንዲህ ዓይነት በሽታ ያለበት የለ ከየት አመጣችው?›› ይሉና አማቻቸውን እንጀራ ጋግረው ለማስተናገድ ምጣድ ሊጥዱ ከምድጃው ለጥ ብለው ጉልቻ ሲያስተካክሉ የእርሳቸው የመቀመጫ ትንፋሽ ደግሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያመልጣቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የሁኔታው ክንውን ያይን እማኝ የነበረው አማች ‹‹ምነው እንደርስዎ አንድ ጊዜ አንድ ጊዜ በወጣላት?›› አለ ይባላል፡፡

እውነቱን ነው! የማይጠቅም የዘር ቋጠሮ ምን ሊፈይድ ተጠራቅሞ ይቀመጣል? አለባብሰን ባረስነው የሕይወት ሁዳዳችን ላይ አጎንቆሎ የሚወጣው ክፉ ሰርዶ እኮ ነው መልካሙን ዘራችንን እያጫጨና ፍሬ አልባ እያደረገ በባዶው እየሸኘን ያለው፡፡ ፈርዶብን አለባብሰን እናርሳለን ተገደን በአረም እንመለሳለን፡፡ የተጣባን ዘርፈ ብዙ ችግራችን ተጠርጎ ከውስጣችን አልወጣማ፡፡

ሐሳቡ ከሐሳባችን፣ ፍልስፍናው ከፍልስፍናችን፣ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ከርዕዮተ ዓለማችን ጋር ካልተመሳሰለ አዘናግተን በአፍ ጢሙ ደፍተን ስብርብሩ ሲወጣ ካላየነው አንረካም፡፡ የእኩይነት ዛር ሰፍሮብን ለካዳሚነት እጅ ሰጥተናላ፡፡ አገግሞ መነሳቱ እንኳ የማያስደስተን እኮ ‹‹አይቶ ዝም ሰምቶ ዝም፣ ከሆድ ያለ አይነቅዝም›› በሚል ብሂል ጥርሳችንን እየቀረጨጭን ከንፈራችንን እየነከስን ያሳደግነው አላስፈላጊ የበደል ፅንስ ከአዕምሯችን ማህፀን ውስጥ በወቅቱ ተጠርጎ ስላልወጣና በደግነት እሴቶች መተካት ባለመቻሉ ነው፡፡

ለብርሃኑ ተፈላጊነት የጨለማው ንፅፅራዊ ውለታ አይታየንም፡፡ ለማር ጣፋጭ መባል የኮሶ መኖር አስፈላጊነት ይዘነጋናል፡፡ እያፈነደደና እያጎበደደ ‹‹እሺ›› ለሚለን እንጂ ምክንያታዊ ሆኖ ‹‹ለምን?›› የሚለን ያባታችን ጠላት ነው፡፡ ሁሉም ነገር እኛን መስሎ ዩኒቨርስ ልሙጥ ካልሆነ በስተቀር ልዩነት ውበት መሆኑን አንገነዘብም፡፡ በሰብዕናችን  ማሰሮ ውስጥ ያለው የዕብሪትና የተአብዮ አተላ ተሟጦ አልተደፋማ፡፡

የትውልድ ቀጣይነት የሚያሳስበን፣ የታሪክ ተወቃሽነት የማያስደነግጠንና ‹‹ዛሬ ልብላ ደረቴ ይቅላ›› በሚል ፈሊጥ ተጠፍንገንና በግላዊነት እግረ ሙቅ ታስረን የመኖራችን ሚስጥር እኮ ከእንቦቃቅላነታችን ጀምሮ ባጠራቀምነው የክፉ አስተሳሰብ አንቡላና ብሪንጥ ህሊናችን ስለተሞላና እሱን መድፋት ቢሳነን ነው፡፡

በሰበብ አስባቡ ሳያስፈልግ ለአበል ሲሉ የመስክ ሥራ የሚፈጥሩ፣ ያልተጠቀሙበትን ወጭ አሳብጠው ለማወራረድ አዕምሯቸውን የሚያስጨንቁና አግባብ ያልሆነ ጉርሻ ካላገኙ ፈጣን አገልግሎት ባለመስጠት ደንበኛን የሚያጉላሉ ባለሙያዎች መበርከት፣ ሽቅብ አንጋጠው የሚመለከቷቸው ‹‹አይከኖቻቸው›› የተምሳሌትነት ውጤት ስለሆነ አይደል? ታዲያ ይኼ ክፉ የዘር ቋጠሮ መቼ ይሆን ከውስጣቸው አንድ ጊዜ ተጠርጎ የሚወጣላቸው? የሚወጣልን?

የትምህርት ሥርዓታችንም ቢሆን እነዚህንና መሰል ኢ ሥነ ምግባራዊ የሕይወት አሰርና እሴቶቻችን ሙሬ ሆኖ ከውስጣችን ጠርጎ ሊያስወግድልን አልቻለም፡፡ ይህ የመማር ማስተማር ሥርዓታችን፣ ንድፈ ሐሳብና ተግባር እንዴት እንደሚዋሀዱ ለመረዳት ባያስችለንና በሕይወታችን የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ባያግዘን፣ በዚች ምስኪን አገር እየኖርን የነጮችን ነጭ መሬት ለመርገጥ ደጋግመን ከመናፈቅ ነፃ ሊያወጣን አልቻለም፡፡ የውጩን ዓለም የሕይወት መስተጋብር እንደተሸከመ ተገደን የምንጋተው እንጂ የእኛን እውነተኛ ማኅበራዊ ሁኔታና አገራዊ ቀለም የተላበሰ አይደለማ፡፡ ይህ ደግሞ የስደተኛነት፣ የጥገኝነት፣ የዘመናዊ ባርያነትና ለራስ ጥሩ ግምት ያለመስጠት ደዌ መንስዔ የሆነው ቫይረስ ከአዕምሯችን ውስጥ ጥልቅ መሠረት ይዞ እንዲቀመጥ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

መማራችን የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትና ሕይወታችንን የመቀየሪያ ሒደት ከመሆን ይልቅ፣ በሰበሰብናቸው የዲግሪ መረጃዎች ብዛት ታች ከሚባለው ሠፈር አብረን እንዳንደክም፣ የይሉኝታ ሸክም ተሸካሚ ባሪያዎች እንድንሆንና ቆርሶ ለማያጎርሰን ክብር እንድንገደር አድርጎናል፡፡ ምክንያቱም የምንማረው ትምህርት በፍላጎት ላይ የተመሠረተና የየግል ማንነታችንን ጥያቄ የሚመልስ አይደለማ፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኮ የድህነትን አስቀያሚ ስሜት በውል ሳይገነዘበው የቀረ አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም እንደ እግር እሳት እያንገበገበው ከመኖሩ በላይ ለድንቁርናና ለውርደት ያጋለጠውና እያጋለጠው ያለ ብርቱ ጠላቱ መሆኑን ያውቃል እንጂ፡፡ መሸሸጊያ ጓዳው መሸሻ ሜዳው ቢሰወርበት ነው የባዕድ አገር ሰቆቃ ኑሮን መርጦ ማዶ ማዶ ለማየት የሚገደደው፡፡ በእርግጥ ጥቂት ዘመን ወለድ ግዙፋንና ክቡዳነ መዝራዕት ሆዳቸው በጀርባቸው እስከሚዞር በልተው ያድሩ ይሆናል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን በየጓዳው ምንዳቤና ጠኔውን በጀርባው ተሸክሞ እሹሩሩ እያለ ያሞላቅቃል፡፡

ከራሳችን ባህል፣ የአኗኗር ሥርዓት፣ የኢኮኖሚ ደረጃና ማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ያላተኮረው የትምህርት ሥርዓታችን የውጩን ዓለም የባህል አተላ ገንቦ ተቀብለን ሳናጠል የመጋት አባዜው ከውስጣዊ አስተሳሰባችን ሊፋቅ አልቻለም፡፡ የውጩን ዓለም ልጋግ እየላስን የመኖር አባዜያችን አሁንም እንደተጣባን ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ታዲያ ይኼ ክፉ የዘር ቋጠሮ መቼ ይሆን ከውስጣችን አንድ ጊዜ ተጠርጎ የሚወጣልን?

እስኪ የዚህ የትምህርት ሥርዓታችን ውጤት የሆነውንና በየተቋማቱና በየቢሮው በህሊና ግልሙትናና በነፍስ እድፍ ገጸ ባህርያት የሚከናወን ትራጄዲ፣ ኮሜዲ አልያም ሜሎ ድራማ ተውኔት እንደ ታዳሚ ሆነን እንመልከት፡፡ በአጥንት፣ በሥጋና በደም እየተጠራሩ፣ በጥቅም እየተሳሰሩና አንዱ ድልብ ንፁሀን ዜጎችን አሰቃቂ፣ ሌሎች ትንንሾች ደግሞ ያሳቃቂው እንባ ጠባቂ ሆነው የቦናፓርቲዝምን ኩነተ ድርጊት የሚያካሂዱ፣ አርቀው የማይመለከቱ፣ በጠባብ ሠፈር የታጠሩ፣ ጠል አልባ ደመናዎችንና የደረቁ ወንዞችን የሚመስሉ ዜጋ በል ዜጎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ጭብጥ የተሸከመ እኮ ነው፡፡

ስለተቋማቱ የሀብት አጠቃቀምና አላስፈላጊ ወጪ ቁጠባ በየስብሰባው ይደሰኩራሉ፡፡ ዙሪያው ግን በተቋማቱ የሥራ ሰዓት የተቋማቱን ንብረት ለግል ሥራቸው ያውላሉ፤ በጎምቱ ህሊና ሰፋፊ አዕምሯቸው ተሸፍነዋላ፡፡ እነዚህ ሽምቅ ተዋንያን ዝምድናንና የጥቅም ትስስሮሽን መሸሸጊያ ጓዳና የእውነት ጠራራ መከላከያ ጃንጥላ አድርገው በመጠቀም አደገኛ የትውልድ ክፍተት እየፈጠሩ እኮ ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ክፉ የዘር ቋጠሯቸው መቼ ይሆን ከውስጣቸው አንድ ጊዜ ተጠርጎ የሚወጣላቸው?

እነዚህ የቦናፓርቲዝም ሥርዓት አራማጆች በጎደፈ ህሊናቸው ሲደነግጡና ኦና ላይ በፍርኀት ሲያፈጡ ሰው ከመሆን ጎራ ይወጡና ለጥቅማቸው ሥጋት መስሎ የታያቸውን ሲነቅሉ፣ በአንፃሩ ደግሞ የእነሱን እንባ ጠባቂ ከመልካሙ ማሳ ላይ ሳይገባው እንዲገባው አድርገው ሲተክሉ፣ ሠራተኛን እያፈናቀሉ ቤተሰቡን ሲበትኑ፣ የግል ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅና እንደ ፍላጎታቸው ትውልዱን ለመበወዝ በየጊዜው ድርጅታዊ መዋቅር ሲለዋወጡ እንድናይ መገደዳችን እኮ፣ የአምባገነንነት አብሮ አደግ ውቃቢያቸውን አንድ ጊዜ ጠርጎ ከውስጣቸው የሚያስወጣላቸው የመፍትሔ ፀበል ቢጠፋ ነው፡፡

ሌላው በጣም የሚገርመው ነገር እነዚህ የቦናፓርቲዝም ሥርዓት አራማጆች ትውልዱን በክፉ ጥርሳቸው ነክሰው ከያዙ በቀላሉ የማይለቁ፣ ይቅር የማይሉና የቂም ጠፍር ሲያኝኩ የሚኖሩ፣ እንዲሁም በትውልድ ዘንድ ያለውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት የማያስቡ፣ ግን መልካም ዘር ባልዘሩበት ማሳ ላይ የፍፅምና ፍሬን የሚጠብቁ መሆናቸው ነው፡፡ በእነሱ ዘንድ መሪነት ማለት ግራ የተጋባ ተከታያቸውን ትክክለኛ የግብ አቅጣጫ ከፊት ሆኖ እንደ አቋመ ፅኑው ሙሴ ማሳየት ሳይሆን፣ እንደ ክፉ እረኛ ከኋላ ሁኖ በክፉ ጅራፍ እየገሩ መንዳት ይመስላቸዋል፡፡

ደግሞ እኮ እነዚህ የቦናፓርቲዝም ሥርዓት አራማጆች በዚህ ብቻ አይበቃቸውም፡፡ ይልቁንም ያረጀና የጋጄ ወቅት ያስተናገደው ፀሊም ታሪካችንን እየነቀሉ ለራሳቸው የህልውና ርዝማኔ ሲሉ እንደ ወተት እየጋቱ ዘር ቆጣሪ፣ አጥንት አበጣሪና ለብሔርተኝነት አቀንቃኝና ዘማሪ ያደርጉናል፡፡ ብንፋቀር አንድነት ይኖረናላ፡፡ በአንድነት ተባብረን ብንተፋ ደግሞ አይረቤ ትቢያችንን በምራቃችን ጎርፍ መጥረግ እንደምንችል ያውቁታል፡፡ ለጥ ብለን ለእነሱ እስካጎነበስን ድረስ ብቻ ነው በእነሱ ዘንድ ትክክለኛው ኢትዮጵያዊነት ያለው፡፡ ቀጥ ብለን ‹‹ለምን?›› ማለት ስንጀምር ኢትዮጵያ የሚለው ጭንብል ተገልብጦ ብሔርተኝነት ቦታውን ይረከባል፡፡ ታዲያ ይህ ትውልድ እንዳይናገር ቢኖር ነገር፣ ዝም እንዳይል በቁጭት ቢብሰለሰልና ‹‹ቢሰናከል መንገድ ጣለኝ ከወንበዴ›› ቢሆንበት፡-

ካ’ጋሙ ከቀጋው
ሄዶ ተጠግቶ
ወይኑ ፍሬ አፍርቶ
ተንዠርግጎ አሽቶ
ይታያል ጎምርቶ፡፡
ዳሩ ብርደ ፈሱ ሞቀሞቅ ባቄላ
ቢጋግሩት ምራቅ ቢጠምቁት አተላ
ዘመን የቀረሽው ብሪንጥና አንቡላ
ተበልቶ አያጠግብ አንጀትን አይሞላ
ብስናት ብስናት አለው ትውልዱን ጠቅላላ፡፡
የክረምት የበጋው
መከር ያልጠራቸው
ፀደይ ያልዋጃቸው
የገብስ ጎሳዎች
የስንዴ እንክርዳዶች
የባቄላ አሉማ
የጓያ ብናኞች
ከተመረጠው ዘር አብረው ተቀላቅለው
በነፋስ እፍታ መርዛቸውን ነፍተው
የትውልዱን ጉልበት የሚያሽመደምዱ
ትውልዱን ለጋውን የንብርክክ ያስኬዱ
ትውልዱን ለጋውን የቀነጣጠሱ
እፍኝ እፍኝ እንባ ካ’ይን የሚያስፈስሱ
አሉ ከትውልዱ፣
የታሪክ ልማሞች የሻገቱ እርሾዎች
የጠራራ መብረቅ ጠል አልባ ክረምቶች
አሉ ከትውልዱ፣
ኑረው የማይኖሩ ሞተው የማይሞቱ
ግማሽ ሞት የሞቱ እንደ ተጎለቱ
አሉ ከትውልዱ፣
ሞተ ከዳ ሲያዩ ጥንብ የሚጓተቱ
ተግማምተው ያገሙ ሸተው ያሸተቱ
አሉ ከትውልዱ፣
የትውልዱን ጉዞ በ’ነሱ ዕርምጃ ልክ እየቆጠሩ
ትውልዱ እንዳይፈጥን ኮድኩደው ያሰሩ
አሉ ከትውልዱ
አሉ… አሉ… አሉ…
ኑረው የማይኖሩ ሞተው የማይሞቱ
ግማሽ ሞት የሞቱ እንደተጎለቱ፡፡
በማለት ማንጎራጎሩን አማራጭ አድርጎታል፡፡ ታዲያ ይኼ ክፉ የዘር ቋጠሮ መቼ ይሆን ከውስጣችን አንድ ጊዜ ተጠርጎ የሚወጣልን? መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎቹ ልተውና ለጊዜው እዚህ ላይ ይብቃኝ፡፡