መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - እኔ የምለው - ኳታር - አዲሲቷ የኢትዮጵያ ወዳጅ?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
07 April 2013 ተጻፈ በ 

ኳታር - አዲሲቷ የኢትዮጵያ ወዳጅ?

በኤርጎጎ ገለቶ

ኳታር በጂኦግራፊ አቀማመጧ ከሳዑዲ ዓረቢያ በስተደቡብ የምትገኝ ሲሆን፣ አጠቃላይ የመሬቷ ስፋት የኦሮሚያን አራት በመቶ ያህላል፡፡

አገሪቱ በፐርሽያ ባህረ ሰላጤ ተከባ ባህሬንን አሻግራ ማየት በሚያስችል የቅርብ ርቀት ላይ የምትታይ የትንሽ ትልቅ አገር ናት፡፡ ጸሐፊዎች የስሟን አነሳስም ከወደብ ጋር ያገናኙታል፡፡ የኋላ ታሪኳ ሲዳሰስ ኳታር በርካታ ከቅርብና ሩቅ ከመጡ ጠላቶቿ ጋር ተፋልማለች፡፡ እ.ኤ.አ ከ1871 እስከ 1971 በኦቶማን ቱርኮች ቅኝ ግዛት በኋላም በእንግሊዝ ሞግዚትነት ቆይታለች፡፡ ነፃነቷን እ.ኤ.አ በ1971 ከተቀዳጀች ጀምሮ በኤሚር ማለትም በአል-ታታኒ ቤተሰብ እየተመራች የቆየች ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ከሚታወቁ አራት አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡

ኳታር ነፃ አገር ከሆነች በኋላ ልዓላዊነቷን የመነጠቅ ሥጋት ሰንጎ የያዛት አገር ነበረች፡፡ አጠገቧ የሚገኙት ባህሬንና ሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናትን የሚሰይሙላት የበላይ ጠባቂዎቿ ነበሩ፡፡ የፈለጉትን የመሾም፣ ቀልባቸው ያልወደደውን የመቀየርና የማስቀየር ሚና በየተራ ይጫወቱ እንደነበር የኳታር ታሪክ ያወሳል፡፡ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ሰላምና ፀጥታ በራቀው  በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘዋ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ለሰላሟና ለልማቷ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን በመቀነስ ፈጣን ዕድገትን ለማምጣት የምታደርገው እንቅስቃሴ ከኳታር ጋር ያመሳስላታል፡፡

ሁለቱም አገሮች ያሉባቸውን ሥጋቶች ለመቀነስ የሚከተሉዋቸው መርሆች ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ ለዚህም ይመስላል በተለይ አሁን የሚመሯት ኤሚር ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የኳታርን የዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ በአንድ ማስቀመጥ ይከብዳል የሚባለው፡፡ አወዛጋቢ፣ አነጋጋሪና የማይጣጣሙ የሚመስሉ የግንኙነት አማራጮችን ትከተላለች፡፡ ግጭቶች በተፈጠሩበት በተለይም ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አገሮች ኳታር በአስታራቂነት ስም ብቅ ማለቷ የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ በማባባስ ወይስ በማስታረቅ? የሚለው ሰፊ ትንታኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ለሌላ ጊዜ እናቆየው፡፡ ኳታር እ.ኤ.አ. በ1991 የባህረ ሰላጤው ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ሚና ነበራት፡፡ ከኢራቅ ጦር ጋር ይዋጋ ለነበረው የሳዑዲ ዓረቢያ ብሔራዊ ሠራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ ካናዳ ባደረገችው እንቅስቃሴ የጦር ኃይል በማዋጣት ጥቅሟን አስጠብቃ ወዳጅ ማፍራቱን ገፍታበታለች፡:

በአጭሩ በጠይምነት አትገለጽ ኢትዮጵያዊት አይደለች፣ መላ ቅርጿ አይወራ ወዳጅ እንጂ የአገሬ ኮረዳ ባለመሆኗ ዓይኗንና ከናፍሯን አትጠይቁኝ፡፡ የቅርብ ሩቅ፣ የማታጥር፣ የማትረዝም የመካከለኛው ምሥራቅ አገር አዲሲቷ ‹‹ወዳጄ›› ወዳጃችን ኳታር ዓረቦች እንደሚጠሯት ‹‹ቃጣር›› ትባላለች፡፡

በውጭ ግንኙነት ረገድ ኳታር እንደ አገራችን አባባል ‹‹ሁለት ጉድጓድ ያላት...›› እንደሚባለው አወዛጋቢና አጨቃጫቂ የማይጣጣሙ አማራጮችን እየተከተለች እንደምትጓዝ ውሎ ያደረ ሀቅ ነው፡፡ በመጠን ትንሽ በራዕይ ግን ትልቅ የማይተገበሩ የሚመስሉ ህልሞችን ዕውን ወደማድረጉ ተቃርባለች፡፡ ለዚሁ ይሆን በርካታ የዘርፉ ጠቢባን ከምዕራቡ ዓለም ስመ ጥሩዋ ኖርዌይ ጋር የሚያመሳስሏት?

አሁን የምናወራላት በሀብት ድልቅቅ ያለችዋ ኳታር እ.ኤ.አ በ1971 ሙሉ በሙሉ ነፃነቷን ከተጎናፀፈች ጀምሮ በአል-ታታኒ ቤተሰብ እየተመራች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችንም ልዑዓላዊነቷን ያስጠብቅልኛል ባለችው መንገድ እየከለሰች ቆይታለች፡፡ እንግሊዝ በፐርሽያ ባህረ ሰላጤ አካባቢ የነበራትን ሞግዚትነት ትታ ጦሯን ለማስወጣት ይፋ ባደረገች ጊዜ እ.ኤ.አ በ1968 ኳታር ከባህሬንና ከሌሎች ሰባት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር በፌዴሬሽን ለመቀላቀል ሐሳብ አቅርባ ተቀላቅላም ነበር፡፡ አካባቢያዊ ግጭቱ በመባባሱና ባሰበችው መንገድ ባለመሆኑ ደኀንነቴ ይሻለኛል ብላ ‹‹በአሚር›› መተዳደሯን ተያያዘችው፡፡

ኢንቨስትመንት
የአገሪቱ መንግሥት ከአገር ውጭ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት መጠነ ሰፊ ገቢ እንዲያስገኝ በኢንቨስትመንት ባለሥልጣኑ በኩል በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአገር ውስጥ ሀብት ማበልፀጉ፣ የንግድ ትስስሩንና የረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት ዕቅድ በማውጣት ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱ ይነገራል፡፡ በቅርቡ በወጣ የአገሪቱ የገቢ መሥሪያ ቤት መረጃ መሠረት አንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ተቋሙ በዓለም ትልቅ ከሚባሉት የኢንቨስትመንት ተቋማት አንዱ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የሚገኘው ገቢም በአገር ውስጥና በውጭ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በማፍሰስ ኳታር የምታገኘው ከ75 በመቶ በላይ የአገሪቱን ገቢ የሚሸፍነው በነዳጅ ላይ ብቻ የተንጠለጠለውን ኢኮኖሚ መታደግ መሆኑን አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2008 ይፋ ያደረገችውና ከ2012 እስከ 2016 ያወጣችው የልማት ስትራቴጂ ያብራራል፡፡ ለዚህም መገለጫ  ‹‹ሐሮድስ›› የተባለ የቅምጥሎች ሆቴል አሉ በተባሉ ከተሞች ለንደን፣ ኳላላምፑር፣ ኒውዮርክ፣ ፓሪስና ቻይና በማስፋፋት የፓተንት ባለቤት ለመሆን እየሠራች መሆኑ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡

ታዲያ በአገሯም ሆነ በአካባቢዋ ያላትን ፖሊሲም ሆነ በቅርብ ጊዜ ያላትን ሚና ለራሷ በመተው ኢትዮጵያም ግንኙነቷን ማደሷ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ እንዲህ አሉ በተባሉ አገሮች ተወዳዳሪና የገቢ ምንጭ የሚሆን ኢንቨስትመንት ማስፋፋት የቻለችው ኳታር ኢትዮጵያ እያራመደች ካለው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንፃር ብዙ ባለሀብቶች ልትልክልን ትችላለች፡፡ ከፍ ብሎ እእንደተጠቆመው ኳታር ያላት መሬት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ለግብርና ብዙም የሚጠቅም ስላልሆነ፣ ሕዝቧ አሁን ባለበት ደረጃ የሚፈልገውን ዓይነት ምርት በፍጥነት እያመረቱ ለማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑና እኛ ጋ ካለው ጥሩ የአየር ሁኔታ፣ ሥራ ላይ ያልዋለ መሬት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ካላት ቅርበት አኳያ አንዱ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡

በግብርናው ረገድ መቼም ተፈጥሮ ሁሉን አታድልምና ኳታር ድንጋይማ መሬቷ በአሸዋ ተሸፍኖ ከዝናብ እጥረቱ ጋር በመዳመር ፍሬ የሚቋጥር አይደለም፡፡ በመሆኑም ከአካባቢው የአየር ሁኔታጋር ከሚጣጣሙ የፍራፍሬ ዛፎች በስተቀር ብዙም በአገር ውስጥ ማምረቱ የሚያስኬዳት አይመስልም፡፡ እንደ ‹‹Arab Center for Research & Policy Studies›› ግብርናው ለጠቅላላ ገቢው የሚያበረክተው ከአንድ መቶ አያልፍም፡፡ ስለዚህ አገሪቱ የምግብ ፍላጎቷን ለማሟላት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ሆናለች፡፡ ተሳክቶ ኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፋሰስ ከጀመሩ የሚኖረው ፋይዳ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ኳታር ከአገር ውጭ 60 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንዳደረገች የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ይፋ አድርጓል፡፡ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባለፈ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ እጦት ሚና እንደነበራት ይታወቃልና በመልካም ግንኙነት አገራችን ለአካባቢው ሰላም ለምታደርገው ጥረት አጋዥ ልትሆን ትችላለች፡፡ ባታግዝም አሉታዊ ሚናዋ ከቆመም ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ ባለፈው መስከረም የግብፁ ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ በሶሪያ ላይ አወዛጋቢ የሚባል መግለጫ ካወጡ በኋላ ኳታር ወደ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በግብፅ ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድ እንዳላት ተገልጿል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ከኳታር ከመራራቅ ይልቅ በመቀራረብ መሥራቷ አደጋዎችን ቀድሞ ከመቀነስ አንፃር የብልህ መላ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ትንሽቷ ሀብታም አገር በዓረብ ሊግም ሆነ በዓለም የተለያዩ መድረኮች ያላት ሚና እየጨመረ በመምጣት ላይ ስለሚገኝ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታው ቀላል አይሆንም፡፡ በአንፃሩ አገራችን በምሥራቅ አፍሪካ እያደረገች ያለው የተመሰከረለት እንቅስቃሴ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በተለይ የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ ከምሥረታው ጀምሮ እስካለንበት ወቅት በአኅጉረ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን፣ ዲሞክራሲ እንዲያብብ በተለይም መሠረተ ልማት እንዲስፋፋና ክልላዊ ድርጅቶች ተጠናክረው የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር የምትጫወተው ሚና የጎላ መሆኑ አይካድም፡፡ ይህን እውነት ከተቀበልን ኳታርም ጥቅሟን በይበልጥ ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን መፈለጓ አይቀሬ መሆኑ አሳማኝ ይሆናል፡፡

ኳታር እየቆየች ግን እ.ኤ.አ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ በዓለም አቀፍ ተቀባይነቷን በማጎልበት በተለይ ከምድሪቱ ‹‹አለቆች›› ጋር ያላትን የጥቅም ግንኙነት በመጨመር ሥርዓቱን ያለ እንቅፋት ማስቀጠል እየተከተለች ትገኛለች፡፡ አገሪቱ ይህን መርህ መከተል የጀመረችው በወቅቱ ኤሚር ሃማድ ቢን ካሊፋ አልታኒ መሪነትና በቅርቡ አገራችንን በጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃማድ ቢን ጃሉም ኢል-ታኒ ተርጓሚነት መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ በፊት ወሰንተኛዋ በሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ ተፅዕኖ ሥር እንደነበረችና እነኝህ ሰዎች አገሪቱን መምራት ከጀመሩ በኋላ ግን የኳታርን ነፃ አገር መሆን በየአጋጣሚው አጽንኦት ሰጥተው ማወጁን ገፉበት፡፡ ለዚህም በማሳያነት ከሚጠቀሱት ክንውኖች አንዱ የአልጄዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ መቋቋም ነው፡፡ በእርግጥም ቻናሉ በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት መገናኛ ብዙኃን ተርታ መሰለፍ በመቻሉ ያለሙት ተሳክቶላቸዋል ለማለት ያስችላል፡፡

ከዚህ በሻገር እንደ አሜሪካ ካሉ ትላልቅ፣ እንደ ኢራን ካሉት ተፈጥሮአዊ ሀብት ካጣመራት አገሮችና በክልሏ ካሉት አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠሯ የኳታር አንዱ መላ ነው፡፡ ለነገሩ በአካባቢዋ ካለባት የፀጥታ ሥጋቷ አንፃር ከአሜሪካ ጋር ከመወዳጃት አልፋ የመከላከያ ስምምነት በመፈራረም፣ እስከ አል ኡዲድ የአየር ኃይል ማዕከል የኢራንና አፍጋኒስታን ኦፕሬሽንን ማቋቋም ስትደርስ አይገርምም፡፡ በዚህም ዶሃ የአሜሪካ አየር ኃይል በመስፈሩ በአካባቢው ይሰነዘርብኛል ብላ ከምታስበው ማንኛውም ጥቃት እንደሚከላከል ታምናለች፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በዓይነ ቁራኛ የምትከታተለውን መካከለኛውን ምሥራቅ ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና ስለሚኖረው «እከክልኝ ልከክልህን» የተገበሩ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ ከአገር ውስጥ በሚነሱ አንዳንድ ቅሬታዎች የኳታርን መሪዎች መንታ ልብ ማድረጋቸው ባይቀርም፡፡

የመጀመሪያው ያልታሰበበት አጣብቂኝ ኢራን የራሷን የኑክሌር ማበልፀጊያ መገንባት በመጀመሯ በባህረ ሰላጤው አገሮች የበላይነት ፖሊሲን ለማራመድ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚለው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል የኳታርን መሪዎች ያሳሰባቸው አሜሪካ አሊያም እስራኤል የኢራንን ኑክሌር ማብላያ ሊያጠቁ ይችላሉ የሚለው ነው፡፡ ችግሩ የማብላያው መጠቃት ሳይሆን ኢራን ከእነዚህ አገሮች የትኛውም ጫፌን ቢነካ ‹‹ውርድ ከራሴ›› በሚል የአገራችን አባባል ኳታርን በገሃድ ማስጠንቀቋ ነው፡፡ በአካባቢዋ በምንም ዓይነት መንገድ የበላይነትን ከመጎናፀፍ ውጭ ህልውናዋ እንደማይረጋገጥ በመገንዘብ እየሠራችበት እንደምትገኝ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

አያድርገውና ዛቻው የሚፈጸም ከሆነ ኳታር ከኢራን ጋር የምትጋራው በዓለም ትልቅ የጋዝ ማምረቻ ተቋም አደጋ ተጋረጠበት ማለት ነው፡፡ በኢራን በኩል እንኳን በዓለም ሁለተኛዋ የጋዝ ክምችት ባለቤት ብትሆንም፣ ጥቅም ላይ ለማዋል እጅ አጥሯታል፡፡ በተቃራኒው ኳታር በክምችቱ ኢራንን ብትከተልም ከመጠቀሙ አንፃር ብዙ ርቀት ተጉዛለችና የጎረቤቷ ሁኔታ ከአጋም ጋር የተጠጋ .... ሆኖባታል፡፡

የውጭ ግንኙነት
በውጭ ግንኙነት ረገድ ኳታር የምትከተለው ሌላው መንገድ በተለያዩ አገሮች የውስጥና የውጭ ግጭቶች በአደራዳሪነት ሚና የዓለምን ትኩረት መሳብ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 በሊባኖስ ውስጥ በተፈጠረው አለመግባባት የተጫወተችውን ሚና ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በወቅቱ ባይሳካላቸውም ሳዑዲ ዓረቢያና ሶሪያ የሊባኖስን መንግሥትና ተቃዋሚ ቡድን ለማግባባት ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ባይሳካላቸውም ኳታር የነበረውን ክፍተት በሒደት በአንክሮ ተከታትላ ለይታ ስለነበር፣ ሁለቱን ወገኖች በማደራደሯ በሊባኖስ የጥምር መንግሥት በመመሥረት እንዲስማሙ አስችላለች፡፡ ፍፁም የተዋጣለት ውጤት ባታገኝም በሱዳን መንግሥትና በዳርፉር አማፂያን፣ እንዲሁም በየመን የነበረውን ቀውስ ለመፍታትም ጥረት በማድረግ የተወሰነ ዕርምጃ ተራምዳለች፡፡ በዚህ የተነሳ ይመስላል በቀጣናው ለዓለም አቀፍ ደረጃ በአስታራቂነት አስፈላጊነቷ እየጨመረ የመጣው፡፡

በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ጎራዎች (ካምፖች) ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ኳታርን ልዩ አንዳንዴም አወዛጋቢ ያስብላታል፡፡ ለምሳሌ ከእስራኤል አልፎ አልፎ፣ ከሃማስ፣ ከሂዝቦላህ፣ ከኢራን፣ የዛሬውን አያድርገውና ከሶሪያ ጋር መልካም ወዳጅነት ነበራት፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባው በዓረቡ ዓለም የተቃውሞ እንቅስቃሴ አገሪቱ የተከተለችውን የአክሮባት ሥልት ነው፡፡ መቼም የገንዘብ መኖር ትልቅ ነገር ነውና ይህቺው የ1.6 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ዓረባዊት አገር በሕዝብ ብዛት ወይም በመሬት ስፋት ቢሆን በብዙ እጥፍ የሚበልጧትን አገሮች በልጣ የተጫወተችው ሚና አይረሳም፡፡ ግብፅን ጨምሮ በቱኒዚያ፣ በሊቢያ፣ በባህሬን በተለያዩ ዘዴዎች ጣልቃ በመግባት ሁለት ተቃራኒ ወገኖችን ሳያስከፉ አስማምቶ የሚያሳልፍ ፖሊሲ ተከትላለች፡፡ የተቃውሞ ሠልፈኞቹን በመደገፍ በኳታርም ሆነ በእስላማዊ አገሮች (በተለይ ሰለፊዎችን) ድጋፍ ስታገኝ፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ጣልቃ የመግባትን ጉዳይ በማቀንቀንና በመሳተፍ ደግሞ የምዕራብ ዓለምን ወዳጅነት ታጠናክርበታለች፡፡ በሶሪያም እያራመደች ያለው ይኼንኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከምትከተለው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንፃር ግንኙነት የምንፈጥርበት አገር የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም፣ የሚያራምደው የውጭ ፖሊሲ ወይም የመንግሥት ቅርፅ ምንም ይሁን ምንም ለፀጥታችን ሥጋት እስካልሆነ፣ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እስካልገባና በሚደረገው የልማት ርብርብ አንዳች ፋይዳ ካለው ወዳጅ ይሆነናል፡፡ በዚህ መሠረት ከኳታር ጋር እንደገና የታደሰው ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ሊያመጣ የሚችለውን ፋይዳ ማየት ይቻላል፡፡

በሰሞኑ ወዳጅነትን ያደስንላት አገር ምንም እንኳን በነዳጅና በጋዝ ሀብት ከሩሲያና ከኢራን ቀጥሎ መሪ ብትሆንም፣ የሚመራት መንግሥት በእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የተንጠለጠለውን ኢኮኖሚ መተማመን ለመቀነስ፣ ሌሎች የምርታማነት መስኮች በዓይነትና መጠን አድገው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ለመሆኑ በርካታ አብነቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

በግብፅ 18 ቢሊዮን ዶላር፣ ብዙ ሥጋቶች ቢጋረጡባትም እንኳን ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሱዳን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ፣ በሞሮኮ፣ በፍልስጤም፣ በሶሪያ ለኢንቨስትመንት ኳታር ያዋለችው ገንዘብ (እንደ ዓለም አቀፉ ንግድና ልማት መድረክ 2008 ሪፖርት) ከሆነ 228 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋ ነበር፡፡ አሁንም አጠናክራ እየሠራች በመሆኑ ከሳዑዲና ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ቀጥሎ በያዘችው ደረጃ ላትቆም ትችል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያም መልሶ ከኳታር ጋር መወዳጀት ከዚህ የልማት ገፀ በረከት ለመቋደስ መሆኑ ግልጽ ነውና ይበረታታል፡፡

ፖለቲካ
ኳታር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፖለቲካዊው ባሻገር በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይ በኢንቨስትመንት መንቅሳቀሷ ወደጎን የማይባል ነው፡፡ ለምሳሌ በሱዳን ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በትንሹ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዝብ ኢንቨስት አድርጋለች፡፡ እንደ ‹‹Arab Centre for Research & Policy Study›› የምታተኩረውም በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ፣ በሪል ስቴት፣ በፋይናንስና በቱሪዝም መስኮች መሆኑ ለአገራችን የሚኖራት ትኩረት ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡  ረብጣም ባይሆን የምታመጣውን መጠነኛ ገንዘብ ብሎም ከኢንቨስትመንቱ ጋር የሚመጣውን ቴክኖሎጂ ለምንታትርለት የልማት ትግል የሚያመጣው ጥቅም መልካም መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ ውጭ ትርፋማ ባይሆንም ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን የሚያሳድግ ተግባር ማከናወንም ጀምራለች፡፡ በቅርቡ ከ25 ሺሕ በላይ ሕፃናትን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለማድረስ የሚያስችል የሦስት ዓመታት የትምህርት ድጋፍ ስምምነት ከዩኒሴፍ ጋር ተፈራርማለች፡፡ ወዳጅነት ሲጠናከር ከዚህ ድጋፍ መቋደስ ይቻል ይሆናል፡፡

የአገራችን የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በጥቅሉ ያለንን የዲፕሎማሲ አቅም ተጠቅመን ውጫዊ የደኅንነት ሥጋቶችን በመቀነስ ከተቻለም ማስወገድ ነው፡፡ የግሎባላይዜሽንን አሉታዊ ተፅዕኖ በመቀነስ እየገሰገስንበት ላለነው ሰፊ የገበያ ዕድሎችን፣ የኢንቨስትመንት ማስፋፋት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ማፈላለግ፣ በአገር ውስጥ የሚከናወነውን ከድህነት የመውጣት ትንቅንቅ ማገዝና አቅምን በመገንባት አሁን ያለበትን ተጋላጭነት በማይቀለበስ መልኩ መቀነስ ነውና በዚህ አያበቃም፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ፒተር ሄይንለይን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ያንፀባረቁትም ይህንኑ ነበር፡፡

በቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ከሚመራው መንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደ ዴሞክራሲያዊ አገር ተጠይቀው፣ የውጭ ግንኙነታችን ከርዕዮተ ዓለም ጋር ሳይሆን ለልማታችን አንዳች ፋይዳ ካለው የትኛውም ሥርዓት ጋር ወዳጅነቱን እንደምንፈልገው ከአሜሪካ ዲሞክራት፣ ከእንግሊዙ ሌበር ፓርቲ፣ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ፣ በማለት የመለሱት ይህንኑ የሚያጠናክር ይመስላል፡፡ ስለዚህ ነው በለንደን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የአገሪቱ መሪ ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በመቀጠል ብዙም ሳይቆይ ልዑካን በመላክ የወቅቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በማነጋገር ኤምባሲዎች በሁለቱም በኩል እንዲከፈቱ የተስማሙት፡፡ ከውይይቱ ጎን ለጎን ለኤምባሲው መከፈት ቅድመ ሁኔታአጥኚ ቡድኑ ሥራውን እየሠራ ነበር፡፡ አሁን ኳታር ኤምባሲዋ ተከፍቶ ሥራ ከጀመረ ከሁለት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ቅድመ ሁኔታውተጠናቆና ቢሮ ተደራጅቶ ሰዎች ተመድበው በቅርቡ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ኳታር የብዙዎችን ቀልብ እየሳበች ነው፡፡ በአካባቢዋ ያለባትን ሥጋት ለመቀነስ በተለያዩ የውጭ ግንኙነት መርሆዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ለማትረፍ በስፋት እየሠራች ነው፡፡ ህልሟ ከቅዥትነት አልፎ በተግባር ወደ መረጋገጡ ሲቃረብ ባለችበት የባህረ ሰላጤው (Gulf) አገሮች አለቃ ለመሆን መቃረቧን አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ምንም እንኳን ኳታር የሕዝቧ ብዛት ከ1.6 ሚሊዮን ባይዘልም አዘቅዝቀው የሚመለከቷትን ጎረቤቶቿን በዶላሯ ላይ ተንጠራርታም ቢሆን ለመገርመም እየኳተነች መሆኗ እርግጥ ሆኗል፡፡ ለስኬቱ ደግሞ ቀድማ ለመሠረተቻቸው ወዳጆቿ ቀጥላም በኢኮኖሚ ትብብሩ ለምትወዳጃቸው ባለውለታዎቿ፣ ወደ 18 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅና ቀኝ እጅዋ አልጄዚራ ምሥጋና ይግባቸውና ሙከራዋን መቀጠሏን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በተለይም አልጄዚራ በአገሪቱ የውጭ ፖሊሲ የተቃኘ ይመስላል፡፡ በመጀመርያ የሚዲያ ተቋሙ ዓረቦች በቋንቋቸው ዜና የሚያገኙበት ምንጭ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፌስቡክ ወይም ትዊተር የበለጠ ተቀባይነትን ያገኘና በዓረቡ ዓለም የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ መሪዎቹ የቀረቡትን በመልካም እያነሳ ወዳጅነትን ያጠናክራል፤ ወዳጆችን ያበዛላታል፡፡ ቢያንስ ኳታርን በአሉታ ባለማንሳት መሪዎቹን ይተባበራቸዋል፡፡ ከአሚሮቹ ተቃራኒ የሆነ አገር ወየውለት፡፡ ወትሮ ጎልታ የማትታይ የአገሪቱን አሉታዊ ጉድ እየዘከዘከ ቀድሞ የተወዳጁ ቢኖሩ እንዲጠራጠሩ፣ ለመወዳጀት ወይም ለመደገፍ ያሰቡም ቆም ብለው እእንዲያስቡ የማድረግ አቅም አለው አልጄዚራ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡