መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - እኔ የምለው - ስደት ከአትሌት እስከ ባልቴት - እስከ መቼ?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
07 April 2013 ተጻፈ በ 

ስደት ከአትሌት እስከ ባልቴት - እስከ መቼ?

በቦጋለ ንጋቱ

ስደት ዜጎች የሚኖሩበትን አገር ድንበር አልፈው፣ በማያውቁት ማኅበረሰብና ባህል ውስጥ ለመኖር የሚገደዱበት አስከፊ ማኅበራዊ ችግር ነው፡፡

በዘርፉ የሚደረጉ ጥናቶች ለስደት የሚዳርጉ ሁኔታዎችን ገፊ ምክንያት (push factor) እና ሳቢ ምክንያት (pull factor) እንዳሏቸው ይገልጻሉ፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ለስደት የሚዳረጉት ደግሞ ከደሃ አገሮች፣ በጦርነት ከሚታመሱ ምድሮች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነትን ከሚገፉ መንግሥታት ግዛቶች መሆኑን ስናይ በትክክል በምክንያቶቹ መተማመን እንችላለን፡፡

አገራችን ‹‹ቅዱስ ምድር››፣ ‹‹የተባረከች የሐበሻ ማደሪያ›› እየተባለች በቅዱሳን መጻሕፍት ስትጠቀስ ኖራለች፡፡ እኛም ብንሆን ‹‹የዳቦ ቅርጫት››፣ ‹‹ለምለሚቷ ኢትዮጵያ››… እያልን በተስፋ ስንዘምርላት ኖረናል፡፡ ‹‹ዓባይን ያላየ…›› እንዲሉ ሌላው ዓለም የደረሰበትን ደረጃና ያለውን ፀጋ ሳናገናዝብ የእኛዋን ደሃ አገር ስንክብ መኖራችን የውርደት ዘመናችንን ለማራዘሙ መጠራጠር አይቻልም፡፡

በዚህም ምክንያት በርካታ ዜጎች አገራቸው ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ ሲረዱ፣ ሌላው ዓለም የደረሰበትን ሀቅ ሲገነዘቡ እግሬ አውጭኝ ማለት ጀምረዋል፡፡ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያወጣው አንድ ጽሑፍ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በውጭ አገር ይኖራሉ፡፡ (ይህ መረጃ በሕጋዊ መንገድ የሚሄደውን የዳያስፖራ አኀዝ ብቻ እንደሚካተት ልብ ይሏል)፡፡ በተመሳሳይ ገለልተኛ ምሁራን የስደተኛው ሕዝብ ቁጥር እስከ አራት ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል እያስረዱ ነው፡፡ (በቅርቡ ከወጣ የኢንርኔት ጽሑፍ እንዳየነው)፡፡ የኢትዮጵያዊያን ስደተ ምክንያቶች ግልጽ ናቸው፡፡ ደርግ ‹‹ቀይ ሽብር ይፋፋም›› ብሎ ሰይፍ ሲመዝ በቦሌ፣ በባሌ፣ በሞያሌና በመተማ የወጣው በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ወጣት ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በፖለቲካ ልዩነት ሥጋት፣ በነፃነት እጦትና በእርስ በርስ ጦርነት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ስለሆነም በደርግ ሥርዓት የተካሄዱ ስደቶች ዋነኛ መነሻ ፖለቲካዊ ግፊት መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ (የኢኮኖሚ ስደት ያለ ቢመስልም የርዕዮተ ዓለም ለውጥ በፈጠረው የባለሀብት ልጆች ስደት የሚገለጽ ነው)፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲህም የስደተኛው ቁጥር የቀነሰ አይመስልም፡፡ በተለይ ካለፉት 12 ዓመታት ወዲህ አገሩን ትቶ የሚወጣው አምራች ኃይል በእጥፍ እየጨመረ ነው፡፡ በቅርቡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ በየዓመቱ እስከ 300 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚሰደዱ አረጋግጧል፡፡ ቀደም ሲል የስደተኞች ማረፊያ አሜሪካና አውሮፓ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን አሁን ግን ደረጃው ወርዷል፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ሱዳንና ጂቡቲ ሳይቀሩ ኢትዮጵያዊያን የሚመኟቸው አገሮች ሆነዋል፡፡

አሁን በደንብ መፈተሽ ያለበት ዜጎችን ለስደት የሚዳርገው ገፊ ምክንያት የትኛው ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በህዳር ወር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በርካታ ስደተኞች ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እየተሰደዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዚህ ስደት መንስዔው ግን የተሻለ የማግኘትና የኢኮኖሚ አቅምን የማሳደግ ፍላጎት እንጂ ፖለቲካዊ መንስዔ አይደለም ነበር ያሉት፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን ግን በዚህ አይስማሙም፡፡

አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በአንድ ወቅት እንደነገሩኝ የኢትዮጵያዊያን ስደት ገፊ ምክንያቶች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሆናቸው ገሃድ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው አብዛኛው ዳያስፖራ የፖለቲካ ስደተኛ ነው፡፡ (በደርግ ጊዜ ወጥቶ በዚያው በርግጎ የቀረውን ጨምሮ)፣ ከምርጫ 97 ወዲህ እንኳን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ተፈጥረዋል፡፡ ስማቸው ከኦነግ፣ ግንቦት 7 እና ኦብነግ ጋር የሚነሱ ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኢሕአዴግ ያኮረፉ (ያልተግባቡ) ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ስደት እየተበራከተ ነው ይላሉ፡፡

‹‹እነዚህ እውነቶችን ስንፈትሽ ሁሉንም ስደተኛ እንጀራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ አገሮች በባህርና በበረሃ እየተሰደደ ካለው የኢኮኖሚ ስደተኛ ጋር መደመር አስቸጋሪ ነው፤›› የሚሉት መምህሩ፣ ተጠናክሮ እየቀጠለ ያለው የስደት ጉዳይ ጠበቅ ያለ ብሔራዊ መፍትሔ ካልተበጀለት አደጋው የከፋ እንደሆነ ሥጋታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

የኢትዮጵያዊያን የኩራታችን ምንጮች ተደርገው የሚቆጠሩት አትሌቶቻችን እንኳን በስፋት ለስደት እየተጋለጡ ነው፡፡ ገና ዝናቸውን አጣጥመን ያልጠገብናቸው እነዚህ ትኩስ ኃይሎች እግራቸው ለምን ወደ ውጭ አደላ? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡

የዓለም አቀፍ የአማተር አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በድረ ገጹ ባለፉት 15 ዓመታት በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በኦሽኒያ ወደሚገኙ 12 አገሮች 25 አትሌቶች ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን በመለወጥ በሌላ አገር ማሊያና ባንዲራ ሥር የሚወዳደሩበትን ፈቃድ እንዳገኙ አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይ ትልልቅ ኩባንያ በመክፈት ‹‹ልማታዊ ባለሀብት›› እንደሆኑ የተነገረላቸው ሰዎች ሳይቀሩ ወጣ ብሎ መቅረት ጀምረዋል፡፡ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት የነበሩ፣ የሆላንድ ካር ባለቤት የነበሩ፣ የስታር ኩባንያዎች ባለቤቶች፣ ወዘተ. ስደታቸውን ከሚዲያ ማንበባችን ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩበትን ድርጅት በትነውና ሀብታቸውን ሰብስበው ሲሰደዱ አንድ ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ ይኼ ምክንያት ምንድነው? ሌላውስ መንፈሱ ላለመሰደዱ እንዴት እየፈተሽን ነው?

ኢትዮጵያዊያን እናትና አባቶች (አዛውንቶች) ከአገር መሰደድ አይደለም ከትውልድ ቀያቸው የመራቅ ልምድ እንኳን የላቸውም፡፡ ‹‹እትብቴ ከተቀበረበት…›› ከሚለው ብሂል በመነሳት ይመስላል እዚያው ኖሮ መሞት እንደ ክብር ይቆጠር ነበር፡፡ ከዚህም በላይ እንግሊዛዊው አገር ጐብኚ ሊዝና ኬት እንኳን፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን የትም አገር ያላገጠመን እጅግ እንግዳ ተቀባይና አስተናጋጆች ናቸው፡፡ ከአገር መሰደድ አይደለም ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር ፍላጎት እንኳን የላቸውም፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው በሰሜን ተራራዎች ላይ የሰፈረው ሕዝብ በውስን መሬት ሲኖር በሌላው ሜዳማና በረሃ መሬት ላይ ደግሞ እጅግም ሊሠራ የሚችል ኃይል የላቸውም፣›› ብሎ ከ100 ዓመታት በፊት የታዘበውን መጻፉ፣ ‹‹የኢትዮጵያዊያን ማንነት በባዕዳን ቅኝት›› የሚለው መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዚህ ቀደም በስደት የሚኖሩ ልጆቻቸውን በመጠየቅ ስም በርካታ እናቶችና አባቶች አገር ጥለው እየተሰደዱ ነው፡፡ ‹‹የእገሌ እናት ግሪን ካርድ ተገኘላቸው›› ማለት ሎተሪ ወጣላቸው እንደማለት እየሆነ ነው፡፡ ‹‹በተከበሩበት አገር ኖሮ መሞት›› የሚለው የኩሩ ባህል መገለጫችን እየተሸረሸረ ለመሆኑ የስደት ገጽታችን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ተሄዶ ተሄዶስ ማብቂያው መቼ ይሆን?

‹‹የጻፍኩት ደብዳቤ ደርሷል ወይ ከቤቴ፣
እኔ አለሁ በጤና እንዴት ነሽ እናቴ፤›› የሚለው ግጥም እየተቀየረ ይመስላል፡፡ እናትም ልጅም ከተሰደዱ ደብዳቤውስ ለማን ይጻፋል? ማንስ ይናፈቃል? የኢትዮጵያዊያን አባቶች (በተለይ ከተሜው) በጉብኝት መልክም ሆነ ባህር በመሻገር ቀዬያቸውን ለቀው ለመሄድ ከተመኙ አዲስ የታሪክ ክስተት እንደሆነ መታየት አለበት፡፡

በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው የኢሚግሬሽን መሥርያ ቤት ዘወትር ሰው አያጣውም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሠልፍ የያዙ የገጠር ሴቶችና ባልቴቶች ሳይቀሩ ተዳክመው ቆመው የሚውሉበት ሥፍራ ሆኗል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ስደተኛ›› የሚያደርገቸውን ሕጋዊ መታወቂያ (ፓስፖርት) ለማውጣት ነው፡፡ ዛሬ የፓስፖርት ማውጫ ዋጋ ጨምሯል፡፡ ወረፋውም ቢሆን እስከ ስድስት ወር እየፈጀ ነው፡፡ በዚያ ላይ በክልል ከተሞችም ማውጣት ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ፍላጎቱ ተባብሶ ነው የቀጠለው፡፡ በእርግጥ ሁሉም ዜጋ ፓስፖርት ቢኖረውም ይሰደዳል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ አሁን ያለው ዝንባሌ ግን የመውጣትና የመሰደድ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

አቶ በላይ ገዛኸኝ ቀደም ባሉት ዓመታት በጉዞ ወኪል/ኤጀንሲ ይሠሩ ነበር፡፡ የስደት ጉዳይን በተመለከተ የሚሰማቸውን እንዲህ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በርካታ ኢትዮጵያዊያን የገጠር ወጣቶች አገር ጥለው መውጣትን ይፈልጋሉ፡፡ በተለይ ከወሎ፣ ከጂማ፣ ከሐረር፣ ከአርሲ ቀደም ሲል ተሰደው ጥቂት ጥሪት የላኩ ሰዎችን በማየት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄዶ መሥራት ይፈልጋሉ፤›› በማለት የስደትን ገጽታ ይናገራሉ፡፡

‹‹ብዙዎቹን ለምን እዚሁ በአገራችሁ ሥራ አትሠሩም? ብለህ ስትጠይቃቸው አይደሰቱም፡፡ በገጠር የመሬት ጥበትና ገቢ ማግኛ ሥራ ማጣት፣ በከተማም ከእጅ ወደ አፍ አልፎ ሕይወት የሚቀየር ሥራ ስለሌለ፣ ተላይ ከተሳካ ያልፍልሃል፣ ካልሆነም እዚያው ያልፍብሃል፤›› እንደሚሉዋቸውም ነው የሚያስረዱት፡፡ መንግሥት የነደፋቸው ጉልበት ተኮር በርካታ ዘርፎችም አይስቧቸውም፡፡

መጋቢት 2005 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሳምንት ላይ የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በጋራ ዓውደ ጥናት አዘጋጅተው ነበር፡፡ በስደተኝነትና ችግሮች ላይ ባተኮረውና በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደው መድረክ 400 የሚደርሱ በስደት የተጎዱ ወገኖችና ቤተሰቦች፣ የጉዞ ወኪሎች፣ የግል ላኪ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተገኝተው ነበር፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ከመድረኩ የመካከለኛው ምሥራቅ ስደት (በሕጋዊም፣ በሕገወጥ መንገድም) ተባብሶ የቀጠለ መሆኑን መስማታችን ነው፡፡

‹‹ብዙዎቹ የገጠር ስደተኞች ዘመናዊ ምግበ ማብሰል ቀርቶ የራሳቸውን ንፅህና እንኳን በወጉ የሚጠብቁ አይደሉም፡፡ አለማወቃቸው፣ ፅዳት የሌላቸው አለመሆናቸውና ጎታታነታቸው ተደማምሮ ከአሠሪዎቻቸው ጋር ያጣላቸዋል፡፡ በዚህም እንደ ዕቃ እየቆጠሩ ይጥሏቸዋል፡፡ ወይም የከፋ አደጋ ያደርሱባቸዋል፤›› ነበር ያሉት በርካታ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ ሌላው ቀርቶ ዕድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናት ሴቶች በሐሰተኛ መታወቁያ ያለዕደሜያቸው ፓስፖርት አውጥተው በአውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ሲጉላሉ መመልከት፣ በበረራ ወቅት ልብሳቸው ላይ እስከመፀዳዳት የደረሰ ውርደት መታየቱን፣ በዕለቱ ከቀረበው ጽሑፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ በላይ የአገር ገጽታን የሚያበላሽና የሁሉንም ዜጋ ስሜት የሚጎዳ ‹‹የውርደት ማቅ›› ሊኖር አይችልም፡፡ ግን መላው ሕዝብም ሆነ መንግሥት ችግሩን ለመቀልበስ እየሠሩ ያሉት ሥራ ምንድን ነው?

ቀደም ሲል በተገለጸው መድረክ ላይ ሲነሳ የነበረው ‹‹መንግሥት ስደትን ለማስቆም እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አይደለም፡፡ እየተባለ ያለው ዜጎች እንዴት በሕጋዊ መንገድ ይሰደዱ እንጂ፣ ስደትን በምንና እንዴት እናቁም የሚል አይደለም፤›› የሚሉ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በርካታ አምራች ኃይሎች በበረሃ፣ በዱር ገደሉና በየባህሩ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳረጉበት ሕገወጥ ጉዞ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ የስደትና ዳያስፖራ ጉዳይን በተመለከተ የሚከታተሉ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ ይነገራል፡፡ ግን ምን ውጤት እየተገኘ እንደሆነ መገምገም አለበት፡፡

የአገራችንን ዜጎች ለስደት እየገፋ ያለው (push factor) ግን ኢኮኖሚያዊ ችግር ብቻ ነው የሚለው ድምዳሜ አሳሳች ነው፡፡ ፖለቲካዊ ገጽታ ያላቸው የመውጫ በሮች በርካታ ናቸውና፡፡ ዛሬ ‹‹ከቃሊቲ ስደት ይሻለኛል ብዬ መጣሁ እንጂ ማን እንደ አገር›› ከሚሉት ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛ፣ ምሁራንና ሌሎች ዳያስፖራዎች ጀምሮ በየበረሃው እየተንጠባጠ እስከሚቀረው አርሶ አደር ስደተኛ ድረስ ተመልካች ሊያገኝ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ እነቺሊና ቬትናም ከአምስት አሥርታት ዓመት በፊት እንዳደረጉት ብሔራዊ ጥሪና ሕዝቡን ያሳተፈ ‹‹የስደት ይቁም!›› አብዮት መቀስቀስ አለበት፡፡ ከዚያም በላይ መንግሥት ድኅነትን፣ ቤት አልባነትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ኑሮ ውድነትንና ተስፋ መቁረጥን የመሳሰሉ ችግሮችን በተጠናከረ መንገድ የሚቀፍፍበትን ስልት መንደፍ ይኖርበታል፡፡ ያኔ ሁሉንም እያዳረሰ ያለው ስደት ጋብ ይል ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡