መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - እኔ የምለው - መሳሳት እንጂ ማሳሳት አይቻልም
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
25 August 2013 ተጻፈ በ 

መሳሳት እንጂ ማሳሳት አይቻልም

በወንድወሰን ክንፈ 

‹‹የሚሠራ ሰው ይሳሳታል፣ የማይሳሳት የሞተ ብቻ ነው፤›› የሚል አባባል አለ፡፡ መሳሳት የሚቻለውም ለሥራ ካለ ክብር አንፃር እንጂ የተሳሳተ ሐሳብ ማሰብም ትክክል ነው ለማለት አይደለም፡፡

ማሳሳት ግን በምድርም ሆነ በሰማይ ትክክል አይደለም፡፡ በምድራዊ ሕግ ብንወሰን አውቆ ማሳሳት ወንጀልም ነው፡፡ በሞራል ደግሞ ነውር ነው፡፡ ይህን እንድል ያስቻለኝ በቅርብ ከመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበርነት የተሰናበቱት አቶ ጥላሁን እንደሻው በሥልጣን ጊዜያቸው ማገባደጃ ለሪፖርተር የሰጡትን ቃለ መጠይቅ አንብቤ፣ ትክክል አይደለም ባልኩት ጉዳይ ለአንባቢያን ትክክለኛውን ማስጨበጥ አለብኝ ብዬ በማሰቤ ነው፡፡

በመድረክ ውስጥ አቋም ያልተያዘባቸው ጉዳዮች እንዳሉ እሙን ነው፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች አንዱ የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ አቶ ጥላሁን ግን እንዳሻቸው፣ ‹‹የመድረክ አስተሳሰብ ግን እንደ ሕገ መንግሥቱ ነው፤›› ብለው አረፉት፡፡ መድረክ አስተሳሰቡ እንደዚህ ከሆነ መድረክ አቋም አልያዘበትምን ምን አመጣው? የመድረክ የወቅቱ ስብሳቢ ስለነበሩ የእሳቸው አስተሳሰብ የመድረክ አስተሳሰብ መስሏቸው በስህተት ከሆነ ይቅር ልንላቸው እንችላለን፡፡ 

ነገር ግን አውቀው እንዳልሆነ የሚያሳብቅባቸው መሸጥ መለወጥ አለበት የሚለው አንድ ፓርቲ ነው ብለው ወደ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ እጃቸውን ይቀስራሉ፡፡ የአንድነትን ፓርቲ ፕሮግራም እንዲያነቡ የሚያስገድድዎት ደንብ ባይኖር እንኳን በያዙት ኃላፊነት የሚመጥን አስተያየት ለመስጠት የሞራል ግዴታ አለብዎት፡፡ የአንድነትን ዝርዝር የመሬት ፖሊሲ ከፕሮግራሙ ላይ አንብበው ከእንደዚህ ዓይነት የማሳሳት ተግባር እንዲቆጠቡ መምከር ተገቢ ነው፡፡

በጣም የሚያበሳጨው ግን ይህን የተሳሳተ መነሻ ይዘው፣ ‹‹መሸጥ መለወጥ ወደ ገባር ሥርዓት የሚመልስ በመሆኑ፣ መሸጥ የሚለው አስተሳሰብ ዕውቅና ሊሰጠው አይገባም፡፡ ያለፈውን ሥርዓት የሚያሰፍን ነው፤›› ብለው ከኢሕአዴግ አፍ ተውሰው ይሳደባሉ፡፡ ይህን አስተሳሰብ ይዘው የኢሕአዴግን የሊዝ ፖሊሲ ይቃወማሉ፡፡ አንድ ጥያቄ ግን ልጠይቅዎት፡፡ ለገጠሩ ሕዝብ መሬቱን መሸጥ ልክ አይደለም ብለዋል፡፡ የእርስዎን መኖሪያ ቤት (ካለዎት) ሸጠው እንዳያጠፉት ካርታው ቀበሌ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበሩ እጅ ይቀመጥለዎት ቢባሉ ምን ይሰማዎታል? በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ይህ ነው፡፡ እኔ እንዲህ ብባል ከስድብ ለይቼ አላየውም፡፡ ውርደት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ነው እየተባለ ያለው በቅጡ ከገባዎት፡፡ ለመሰደብ ከፈለጉ ምርጫዎ ቢሆንም ይህ ግን ተገቢ አይደለም፡፡

ሌላው ያስገረመኝ አንድ ነገር፣ ‹‹እኛ ሥልጣን ብንይዝ ለኢሕአዴግም ሆነ ለሌሎች የተሳትፎ ዕድል እንሰጣለን ማለት ነው፤›› የሚለው ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንዲያስቀጥል ነው? ወይስ የመድረክን ፕሮግራም እንዲያግዝ? ምን ያህል ቀልደኛ እንደሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግ እንደማይፈልግም በተደጋጋሚ መግለጹን አያውቁም ማለት ነው፡፡ በዚህ ኢሕአዴግ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ አንድነት ከኢሕአዴግ ሥልጣን አልፈልግም ሲል የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ፕሮግራም ለማስፈጸም የሚያስፈልግ ሥልጣን አልፈልግም ማለቱ ነው፡፡ መድረክም ይህን እያለ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ሊቀመንበሩ ግን እንዳሻቸው እንዲሉ የቱ ሕገ ደንብ እንደፈቀደላቸው አላውቅም፡፡

ሌላው ማሳሳት አይቻልም ያልኩበት ምክንያት፣ ‹‹በአንድ የመድረክ ስብሰባ ላይ አንድነት ይህን ያህል ጨምሬ ልክፈል ሊል ይችላል፤›› በሚል መነሻ በጋዜጣው ላይ ያሉትን ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ አንድነት እንደዚህ ያለበትን ሙሉ ገጽታ ለመግለጽ አልደፈሩም፡፡ የአቶ ጥላሁን ድርጅትና ሌሎች አጋሮቻቸው በብሎክ ድምፅ አሰጣጥ ችግር ስለፈጠሩ፣ የመድረክ ደንብ ማሻሻያ ውይይት ላይ አማራጭ አቅርበናል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ችግር አሁንም አለ፡፡ ድምፅ አሰጣጥ እንዴት ይሁን ሲባል አንድነት የተለያዩ አማራጮችን አቀረበ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ድርጅታዊ መዋቅር፣ የአባላት ብዛትና ሌሎች መስፈርቶችን አቀረብን፡፡ ብዙ ድምፅ ያለው ብዙ መዋጮም ይከፍላል፡፡ ያቀረብናቸውን በጎ ነገሮች በሙሉ ወደ ጎን ትተው አንድነት ገንዘብ አለኝ ብሎ ሊገዛን ነው፡፡ እንደ ድሮ ጭሰኛ ሊያደርጉን ነው አሉ፡፡ አንድነት በመድረክ ውስጥ ሕውሐት ሆነ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ፡፡  ይህንና ሌሎች ዝርዝር ትተው ጉዳዩን በቁንፅል አቅርበው አውቀው ማሳሳት ያዙ፡፡ የእንደሻው ልጅ አቶ ጥላሁን፡፡ አይጠራጠሩ ብዙ አባል ያለው ብዙ ገንዘብ አለው፡፡

አቶ ጥላሁን ድፍረታቸው ልክ ያጣ ነው፡፡ ‹‹አንድም ድርጅት የራሱን ሥራ አይሠራም፡፡ የመድረክ አባል እስከሆነ ድረስ ለመድረክ ነው የሚሠራው፤›› ይላሉ፡፡ በማስከተልም፣ ‹‹አሁን አሁን  ከአሠራርና  ከደንብ  ውጪ  የሆኑ አንዳንድ ክስተቶች  እያየን ነው፡፡ … መድረክ ዕቅድ ባልያዘባቸው ቦታዎች አባል ድርጅቶች ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ከመድረክ ጋር በመነጋገርና በማሳወቅ ነው መሆን ያለበት፤›› ይላሉ፡፡ ለምን? ቢባሉ መልስ የላቸውም ከድፍረታቸው ውጪ፡፡ አንድነት የአባላቶቹ እንጂ የመድረክ እንዳልሆነ ተጠሪነቱም፣ ተጠያቂነቱም ለአንድነት አባላት እንደሆነ ማን በነገራቸው? ምን ያድርጉ ምን እየሠሩ ነው? ብሎ የሚጠይቃቸው አባላት ስለሌሉ ጊዜያቸውን አንድነት ምን እየሠራነው ብለው ጊዜ ያባክናሉ፡፡ 

ጋዜጠኛው አራት ዓመት ምን እየሠራችሁ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምንም የሚል መልስ መስጠት ተስኗቸው ስንመካከር፣ ይኼው ግንባር ደረስን ብለው አረፉት፡፡ አንድነት የጠየቃቸው በአራት ዓመት ተገቢውን ጉዞ አላደረግንም (እዚህ ችግር ውስጥ እኛም አለንበት) ስለዚህ አብረን ጠንክረን እንውጣ ብሎ ይህን ሊያደርግ የሚችል ሰነድ በይፋ አቀረበ፡፡ ‹‹ይህ በቀና መንፈስ ያልተሠራ ሥራ በመሆኑ መድረክ አይቀበለውም፤›› አሉ፡፡ ቀና መንፈስ በሚስጥር የሚሉት የቃላት ድሪቶዎች አልገቡኝም፡፡ መድረክን ለማጠናከር ያሉበት ድክመቶች እነዚህ ናቸው ብሎ በዝርዝር ሐሳብ ማቅረብ (ሁሉም ልክ ላይሆኑ ይችላሉ) ከቅንነት ውጪ ምን ሊሆን ይችላል? በሚዲያ መግለጽ የተቻለን ሰነድ ሚስጥር ማለት ምን ማለት ነው? ሌላው የአንድነት ምክር ቤት ከመድረክ ጋር ያለንን ግንኙነት አጥንታችሁ ሐሳብ አቅርቡ ማለት ሚስጥረኛና ቅንነት ከማጣት ጋር እንዴት ይገናኛል፡፡ መልሱ ለአቶ ጥላሁንና ጓዶቻቸው ጉዳዩ በዝርዝር ተነግሮም ቢሆን ካልገባቸው ችግሩ የመረዳት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ አንባቢያንን ግን ማሳሳት አይቻልም፡፡ 

‹‹አንዱ አባል በጋራ ከመሠረተው ማኅበር መውጣት ከፈለገ ጥሎ መሄድ እንጂ ማኅበሩ መፍረስ አለበት ማለት አይችልም፡፡ አንድነት ማድረግ የሚችለው ይህንን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ምን ዓይነት እብሪት እንደሆነ መግለጽ ያስቸግራል፡፡ ለማንኛውም አንድነት ከመድረክ መውጣት ሲፈልግ ምን ማድረግ እንዳለበት ከአቶ ጥላሁን ምክር አያስፈልገውም፡፡ ነገር ግን ይህ ዕቅድ ለጊዜው የለንም፡፡ አማራጩ ግን በጠረጴዛ ላይ የለም ማለትም አይደለም፡፡ የአንድነት መድረክን ማጠናከር የሚቻለው አባል ድርጅቶች ሲጠናከሩ መሆኑን አጥብቆ ያምናል፡፡ አንድነትም እንደ አንድ አባል ድርጅት በመጠናከር ለሌሎች ሞዴል ለመሆን ወስኗል፡፡ ከዚህ ጉዞ ምንም ዓይነት ጫጫታ እንደማይመልሰው ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድነት አባላት፣ መዋቅር፣ ሕግና ደንብ ያለው ተቋም ነው፡፡ ተጠያቂነትም ያለበት፡፡ መድረክ አቅዶ ሥራ እስኪልክልኝ ብሎ አይጠብቅም፡፡ አንድ ጥያቄ እንደ መውጫ ልጠይቅዎት፡፡ አቶ ጥላሁን ደቡብ ኅብረት ምን እየሠራ ነው? የመድረክን ትዕዛዝ እየጠበቀ ነው እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አባል ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡