መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - በህግ አምላክ - የውክልና ሕግ ሌላ የባንኮቹ አሠራር ሌላ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
17 March 2013 ተጻፈ በ 

የውክልና ሕግ ሌላ የባንኮቹ አሠራር ሌላ

ባንኮች በተጭበረበረ ሰነድ ጉዳት ሲደርስባቸው መስማት አዲስ አይደለም፡፡ በአገራችን የሰነዶች የምዝገባ ሥርዓት በወጥነት ስለማይደረግ፣ ምዝገባውም ለሦስተኛ ወገኖች በፍጥነት ተደራሽ አለመሆኑ መጭበርበሩን ያጠናክራል፡፡

ለባንኮች የሚቀርቡ የባለቤትነት የምስክር ወረቀት፣ የጋብቻ ሁኔታ ማስረጃ፣ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ፣ የውክልና ማስረጃና የመታወቂያ ወረቀት በአብዛኛው ለመጭበርበር የተጋለጡ ሰነዶች ናቸው፡፡ ይህንን ሥጋት ለመቅረፍ በማሰብ ባንኮቹ የሚወስዱት ዕርምጃ ደግሞ የደንበኞችን ጥቅም የሚጎዳና ሕጉ ሊደርስበት ያሰበውን የንግድ ልውውጥን በፍጥነት የማከናወን ዓላማ እያደናቀፈ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የባንክ አሠራር ባንኮች የውክልና ሥልጣን ለማረጋገጥ የሚሄዱበት ረዥም ጉዞ ነው፡፡

ባንኮች በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተረጋግጦና ተመዝግቦ የመጣን ውክልና በእያንዳንዱ ግብይት ወደ ተቋሙ በመመለስ እንዲጣራላቸው የሚጠይቁበት አሠራር በስፋት ሲተገበር እናስተውላለን፡፡ በዚህ ጽሑፍ የባንኮቹ አሠራር በሕግ ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም? የባንኮቹ አሠራር በባለ ድርሻ አካላት ላይ ምን አንድምታ አለው? ለችግሩስ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ማነው? የሚሉትን ነጥቦች እንመለከታለን፡፡ የባንኮችን ስጋትና መፍትሔውን በሌላ ጊዜ ካልሆነ በዚህ ጽሑፍ አንመለከተውም፡፡

መነሻ ነገር
መስፍን አዲስ አበባ ላይ ያለውን የንግድ ሥራ የሚያከናውነው በውክልና ነው፡፡ እርሱ በአብዛኛው የሚኖረው ጎንደር ከተማ ነው፡፡ ለዚህ ያመቸው ዘንድ በጎንደር ወረዳ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ተረጋግጦ የተመዘገበ ውክልና ለወንድሙ ለፋሲል በመስጠት የንግዱን ሥራ ያከናውናል፡፡ ውክልናው መስፍን የባንክ ሒሳብ ከከፈተበት የግል ባንክ ገንዘብ እንዲያወጣ፣ እንዲያስገባ፣ እንዲያንቀሳቅስ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ ወኪሉ ይህንን ውክልና በመጠቀም የባንክ ዕዳ ይከፍልለታል፣ ንግዱን ያከናውንለታል፣ ግብር ይከፍልለታል፡፡ በዚህ ሰሞን በአንድ የግል ባንክ የገጠመው ነገር ግን ባዕድ ስለሆነበት ግር ብሎታል፡፡ ፋሲል የመስፍንን የግብር ዕዳ ለመክፈል ከመስፍን ሒሳብ በውክልናው መሠረት ገንዘብ ለማውጣት ሲሄድ የባንክ ሠራተኞቹ ውክልናው እስከሚረጋገጥ አናስተናግድህም፣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ተመለስ ይሉታል፡፡

ባንከሮቹ በአንድ ሳምንት ውክልናውን ወደ ጎንደር በመላክ ከፍትሕ ጽሕፈት ቤት እንደሚያረጋግጡና ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠይቁት ገለጹለት፡፡ እርሱም በዚህ መልስ በመበሳጨት ለባንኩ ሕግ ክፍል አቤቱታ ያቀርባል፡፡ ሆኖም የሕግ ክፍሉ ነገረ ፈጆች የውክልናውን ይዘት በመመልከት ተወካዩ በውክልና ሥልጣኑ መሠረት ከወካዩ የባንክ ሒሳብ ገንዘብ ማውጣት ይችላል ያሉ ቢሆንም፣ የውክልናውን ትክክለኛነት ማረጋገጥና አለማረጋገጥ የቅርንጫፉ ሥራ ነው በማለት፣ አከራካሪ የሆነውን የሕግ ጥያቄ የሕግ ባለሙያ ላልሆኑት ባንከሮች መርተውታል፡፡ በዚህ የባንኩ አሠራር የተበሳጨው መስፍን በአንድ ቀን በአውሮፕላን በመምጣት ገንዘቡን በሙሉ ከባንኩ አውጥቶ ተመልሷል፡፡ በመስፍን አገላለጽ ውክልና መስጠቴ በአካል እንዳልመጣ ካልጠቀመኝ ምን ያደርግልኛል በማለት የባንኮቹን አሠራር ወቅሷል፡፡ በቁጠባ ድርቅ (Liquidity Risk) ለተመቱት የግል ባንኮች ጠቀም ያለ ገንዘብ በአንዴ መውጣቱ የማይፈለግ ቢሆንም አሠራሩን ቀጥለውበታል፡፡ በሌላ የግል ባንክ አዲስ አበባ የተሰጠ ውክልና ይዞ አዲስ አበባ ባለ ቅርንጫፍ ለመጠቀም የሄደ ባልንጀራዬ ከአንድ ቀን በኋላ ተመለስ መባሉ እንዳናደደው ተሞክሮውን ነግሮኛል፡፡

ይህ የባንኮች አሠራር በብዙ ባንኮች ተፈጻሚ የሚሆን ልማድ መሆኑን በባንኮች በውክልና የሚጠቀሙ ደንበኞች ያስተውሉታል፡፡ ጸሐፊው በተወሰኑ ባንኮች ያደረገው ማጣራት የልምዱን በስፋት  መኖር አመላክቷል፡፡ ውክልናው አዲስ አበባም ይሰጥ በክልል፣ ኢትዮጵያም ውስጥ ይሰጥ በውጭ አገር ባንኮቹ ማረጋገጥ አለብን የሚል አባዜ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ለመሆኑ የውክልና ሥልጣንን የማረጋገጥ የባንኮች ግዴታ ሕጋዊነትና የማጣራት ወሰን ምን ድረስ ነው? የሚለውን መመርመር ይገባል፡፡

የውክልና ሕጉ አቋም
 የውክልና ውል በሕጋችን ግልጽ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2199 “ውክልና ማለት ተወካይ የተባለ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሥራዎች በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ማለት ነው፤” ሲል ተርጉሞታል፡፡ የውክልና ዋና ዓላማ ወካዩ በአካል በመገኘት ለማከናወን የማይችለውን ሥራ በተወካዩ አማካይነት እንዲፈጽም ማስቻል ነው፡፡ አንድ ሰው በአካል ጉዳዩን ሊያከናውን ካሰበበት አካባቢ በመራቁ ወይም ጊዜ ከማጣቱ የተነሳ ወይም በሌላ ምክንያት እርሱ የሚሠራውን ሥራ ተወካዩ እንዲሠራ ማስቻል የውክልና ዓላማ ነው፡፡

ውክልና በሕግ ፊት የፀና እንዲሆን ማሟላት ያለበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ውል እንደመሆኑ መጠን ሁለቱም ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ውክልናው በወካዩና በተወካዩ ሙሉ ፈቃድ የተከናወነ፣ ይዘቱ ከሕግና ከሞራል የማይቃረን ሊሆን ይገባል፡፡ ሌላው ወሳኝ ሁኔታ የምዝገባ መስፈርት ነው፡፡ የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 334/1995 በአንቀጽ 5 እንደሚደነግገው የውክልና ሥልጣን መስጫ ሰነዶች ካልተረጋገጡና ካልተመዘገቡ ሕጋዊ ውጤት አይኖራቸውም፡፡ በብዙ አገሮች ውክልናን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብ ሰነዶች የማረጋገጥና የመመዝገብ ኃላፊነት ለመንግሥት ተቋማት የሚሰጡ ሲሆን፣ አንዳድ የኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች ለግል ድርጅቶች ወይም ጠበቆች የሰነድ የማረጋገጥ ሥልጣን ይሰጣሉ፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስነው አዋጅ በመግቢያው እንደገለጸው “የሰነድ ማረጋገጥ ሥራ እምነት የሚጣልበት ማስረጃ የሚያስገኝ፤” ነው፡፡ ውክልናው ከውጭ አገር የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ በውጭ አገር ባለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተረጋግጦ ሊመዘገብ ይገባል፡፡ ከእነዚህ ባንዱ ካልተረጋገጠ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሰ/መ/ቁ 59568፣ የሰ/መ/ቁ 32282 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰጠቱን ልብ ይሏል፡፡
 
ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው የውክልና የቅቡልነት መስፈርቶች ከተሟሉ ተወካዩ የውክልናውን ማስረጃ በመጠቀም በወካዩ ስምና ለወካዩ ጥቅም በውክልናው ሰነድ የተፈቀዱለትን ሥራዎች ማከናወን ይቻላል፡፡ እነዚህ መስፈርቶች ማሟላታቸውን የሚያረጋግጠውና የሚመዘግበው ደግሞ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በመሆኑ፣ ባንኮች ሰነዱ ሲቀርብላቸው ሰነዱ ከጽሕፈት ቤቱ መውጣቱን በውክልናው ገጽ ማህተም መኖሩን፣ መፈረሙን ከመመልከት በስተቀር ማህተሙ ወይም ፊርማው ትክክለኛ ስለመሆኑ የማረጋገጥ ኃላፊነት ሕጉ አይጥልባቸውም፡፡ አዋጅ ቁጥር 334/1995 በአንቀጽ 27 “በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የተረጋገጠ ሰነድ በውስጡ ስለሚገኘው ይዘት ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የተረጋገጠ ሰነድን መቃወም የሚቻለው ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ሲፈቅድ ብቻ ነው በማለት ይህንኑ ሀቅ በአጽንኦት ደንግጓል፡፡

የባንኮች ግዴታ
በሕጉ ውክልናን የማረጋገጥ ግዴታ የተጣለባቸው ውክልናን የሚመዘግቡ የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትና የክልል የፍትህ ቢሮ/ጽሕፈት ቤት ውክልናን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ሌሎች አካላት ባንኮችን ጨምሮ ውክልናው ከእነዚህ አካላት መውጣቱን እንጂ ይዘቱን፣ የተዋዋዮችን ፈቃድ፣ ወይም ትክክለኛነቱን የማጣራት ግዴታ የለባቸውም፡፡

ባንኮች የውክልና ማስረጃው ከእነዚህ የመንግሥት አካላት የወጣ መሆኑን የሚያረጋግጡት ደግሞ የውክልናን ዓላማ (ንግድን የማሳለጥ ዓላማ) በማያደናቅፍ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ ባንኮቹ በአካል መዝጋቢ አካላት ጋር የሚሄዱ ከሆነ፣ ውክልናውን መልሰው በመላክ ለማረጋገጥ ከሞከሩ፣ ቀናት/ሳምንታት በመቅጠር ካላረጋገጥን አናስተናግድም ካሉ የውክልና ዓላማ ሳይሳካ ይቀራል፡፡ ባንኮች የውክልና ዓላማን በጠበቀ መልኩ ውክልናው ከተቋማቱ መውጣቱን የሚያረጋግጡት የውክልናውን ገጽ (face Value) እና ዓውድ (ንባብ) በመመልከት ብቻ ነው፡፡ የውክልናውን ማህተም፣ የባለሥልጣኑን ፊርማ፣ በጀርባው የሚሰጠውን የቴምብር ቀረጥ፣ ማረጋገጫ፣ ወዘተ በዓይናቸው በመመልከት የሚያጠራጥር ሁኔታ (ለምሳሌ የመዝጋቢ አካሉን ስም በአግባቡ ያልተያዘ፣ ማህተሙ ያልተስተካከለ፣ የጎደለ፣ የጠፋ፣ የተሰረዘ፣ የተደለዘ፣ ወዘተ) ካላገኙ በስተቀር በውክልናው መሠረት ደንበኛውን ሊያስተናግዱ ይገባል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከባንኮች ሰነዶችን የማረጋገጥ ግዴታ ጋር በተያያዘ ሁለት ዓይነት መልዕክቶች ያሏቸው ገዥ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው በቀጥታ ውክልናን የሚመለከት ሲሆን፣ ችሎቱ ባንኮች ውክልናው የወጣው ከመዝጋቢው አካል መሆኑን ማህተሙንና ፊርማውን በመመልከት ከሚያረጋግጡ በቀር ጠበቅ ያለ ምርመራ ማከናወን አይጠበቅባቸውም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ፍርድ ደግሞ ሐዋላን፣ መታወቂያን፣ ወዘተ በተመለከተ ባንኮች ክፍያ ከመፈጸማቸው በፊት የተለመደውን የባንክ አሠራርና ልማድ የሚጠይቀውን ጥንቃቄ በማድረግ ክፍያ ከፈጸሙ ሰነዶቹ የተጭበረበሩ (Forged) ቢሆኑ እንኳን ኃላፊነት አይኖርባቸውም የሚል ነው፡፡ የገዥ ፍርዶቹን ይዘት ዘርዘር አድርገን ለመመልከት እንሞክር፡፡

የመጀመሪያዉ በሰበር መዝገብ ቁጥር 20890፣ ሐምሌ 10 ቀን 1999 ዓ.ም. በአመልካች ልማት ባንክ እና በተጠሪ ወ/ሮ አለምነሽ ኃይሌ መካከል በተደረገ ክርክር የተሰጠ ፍርድ ነው፡፡ ችሎቱ በተጭበረበረ ውክልና የተፈጸመ ግብይት ላይ የተነሳ  ክርክር በምን መልኩ መዳኘት እንዳለበት የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ተጠሪ ለተወካይ የውክልና ሥልጣን ያልሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ ተወካይ በተጭበረበረ የውክልና ሰነድ መሰረት አመልካች የተጠሪን ቤት መያዣ በማድረግ የሰጠው ብድር ፈራሽ እንዲሆን በመጠየቅ በሥር ፍ/ቤቶች የተከራከሩ ሲሆን የስር ፍ/ቤቶች ውክልናው በፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ሐሰተኛ በመሆኑ መያዣው ፈራሽ ነው ሲሉ ወስነዋል፡፡ ሆኖም የፌዴራሉ ሰበር ሰነዱ በባለሥልጣን ተረጋግጦ እስከቀረበ ድረስ በሰነዱ መሠረት ግዴታ የሚገባው ወገን ማረጋገጥ ያለበት ፊርማውንና ማህተሙን በመመልከት ሰነዱ በባለሥልጣን ፊት መረጋገጡን ብቻ እንጂ ከዚህ አልፎ የሰነዱን ትክክለኛነት ሊሆን አይችልም ሲል ትንታኔ በመስጠት የሥር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ በመሻር ገዥ ፍርድ ሰጥቶአል ፡፡

ሰበር ችሎቱ በሰጠው ዝርዝር ሐተታ ምክንያቱን እንዲህ ገልጿል፡፡
“…በመሠረቱ በባለሥልጣን ፊት ያልተደረጉ ጽሑፎች (Non-authentic deeds) ተዋዋዮች በግል ችሎታቸው የሚያዘጋጇቸው ውልን የሚመለከቱ ሰነዶች ናቸው፡፡ በባለሥልጣን ፊት የሚደረጉት ደግሞ ለዚሁ ሥራ ተብሎ የተሰየመ ባለሥልጣን ሰነዱን የተመለከታቸውና ምስክርነቱንም የሰጠባቸው ናቸው፡፡ ሰነዱ በባለሥልጣን ተረጋግጦ፣ እስከቀረበ ድረስ በሰነዱ መሠረት ግዴታ የሚገባው ወገን ማረጋገጥ ያለበት ፊርማውንና ማህተሙን በመመልከት ሰነዱ በባለሥልጣን ፊት መረጋገጡን ብቻ እንጂ ከዚህ አልፎ የሰነዱን ትክክለኛነት ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ላይ ተጠሪ በሰነዱ ላይ ያለው ፊርማ በፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ ተመርምሮ የተጠሪ ፊርማ እንዳልሆነ ቢረጋገጥም ከላይ እንደተመለከትነው አመልካች (ባንኩ) ማጣራት የሚጠበቅበት ውሉ በባለሥልጣን ፊት መደረጉንና ባለሥልጣን ምስክርነቱን የሰጠበት ስለመሆኑ እንጂ የፊርማውን ትክክለኛነት ማጣራት የሚጠበቅበት አይሆንም፡፡”

ከዚህ ፍርድ የተወሰኑ ጠቃሚ ነጥቦችን መገንዘብ እንችላለን፡፡ ሲጀምር ባንኮች የውክልና ሰነድ የተጭበረበረ ወይም ፎርጅድ መሆኑን ለማረጋገጥ ገጽን ከማየት፣ ማህተሙንና የባለሥልጣኑን ፊርማ ከማረጋገጥ ያለፈ ግዴታ ያልተጣለባቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህም አሁን በተግባር ባንኮች ውክልናን ወደ መዝጋቢ አካል በመላክ የሚያረጋግጡበት ዘዴ የተሳሳተ መሆኑን አስረጂ ነው፡፡ ሁለተኛው ባንኮች ይህንን ግዴታቸውን ተወጥተው የውክልና ሰነዱ የተጭበረበረ በመሆኑ ደንበኛው ጉዳት ቢደርስበት ደንበኛው መዝጋቢውን አካል (የመዝጋቢው አካል ወይም ሠራተኞቹ ተሳትፎ ካለ) እና በሒደቱ የተሳተፉ ሰዎችን ከሚጠይቅ በቀር ባንኮችን መጠየቅ አይችልም፡፡

ባንኮቹ የሰበር ችሎቱን ገዥ ፍርድ መከላከያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በእርግጥ በዚህ መዝገብ የተሰጠው ፍርድ እንከን የለሽ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ባንኩ በውክልና ማስረጃው ይዘት ስርዝ ድልዝ ያለበትና በግልጽ ለመጠራጠር የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉበት እየተመለከተ አለማረጋገጡ ኃላፊነቱን ሊያስቀርበት አይገባውም ነበር፡፡ ይህ ፍሬ ነገር በሥር ፍ/ቤቶች መረጋገጡን ሰበር ችሎቱ በፍርድ ሐተታው ገልጿል። 

በሌላ በኩል የዚህ ሰበር ፍርድ የተፈጻሚነት ወሰን ላይ ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ፍርዱ ተፈጻሚ የሚሆነው መጭበርበሩ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ላይ ከሆነ ነው ባንኩ ማህተምና ፊርማ የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡ እንደነሱ አመለካከት ውክልናው ከጽ/ቤቱ ካልወጣና መጭብርብሩ ባንኩ ላይ ከሆነ ባንኮቹ ተጠያቂ ስለሚሆኑ ውክልናዉን ወደ ጽ/ቤቱ በመላክ ሊያረጋግጡ ይገባል ይላሉ፡፡ ሆኖም ፍርዱ የባንኮችን ውክልና የማረጋገጥ ግዴታ ወሰን ለማመልክት ትንተና የሰጠ በመሆኑ በሁለቱም ሁኔታዎች ተፈጻሚ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡

ሲጀምር ፍርዱ ውክልና የማረጋገጥ ሥልጣን የመዝጋቢ አካላት እንጂ የባንኮች አለመሆኑን በማያሻማ መልኩ ያስቀምጣል፡፡ ቀጥሎ ባንኮች የውክልናን ገጽ (ማህተምና ፊርማ) ከማመሳከር ያለፈ ግዴታ እንደሌለባቸው በአጽንኦት ይተነትናል፡፡ የፍርዱ ዓላማ ሰነድ መዝጋቢ አካል ባለበት አገር በቅን ልቦና በሰነድ የሚገበያዩን ሰዎች መጠበቅ ነዉ፡፡ የፍርዱ ትንታኔ በምንም መልኩ ውክልናን ወደ መዝጋቢ አካላት እየመለሱ ለማረጋገጥ መሠረት ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ቀጥለን የምንመለከተውን ፍርድ ከመረመርን መጭበርበሩ ባንኩ ላይ ቢሆን እንኳን የሰነዱን ገጽ ክመመልከት ባለፈ በውስጥ አሠራሩ የተቀመጠ ደንብን የመከተል ግዴታ ይኖርበታል እንጂ የውክልና ሰነድ እየላከ እንዲያረጋግጥ ግዴታ አይጥልበትም፡፡ ሰነድ እየላኩ ማረጋገጥ ከተጀመረ መቆሚያ የለውም፡፡ የደንበኛ መታወቂያ፤ የፍርድ ቤት ዉሳኔ የመንግሥት መ/ቤት ደብዳቤ፣ የኩባንያ ቃለ ጉባዔ፤ የጋብቻ ማስረጃ ወዘተ ምን የማይላክና የማይረጋገጥ ሰነድ ይኖራል? ባንኮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ተቋማት ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በየዕለቱ የሚመጣላቸውን ውክልና ወደመጣበት በመላክ ሥራ በተጠመዱ ነበር፡፡

 ሁለተኛው ፍርድ በተጭበረበረ ሰነድ የተከፈለን ገንዘብ ይመለከታል፡፡ ሰበር ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 48269 የካቲት 24 ቀን 2002 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ ባንክ በተጭበረበረ መንገድ ለወጣ ገንዘብ በኃላፊነት ሊጠየቅ የሚችለው የተለመደውንና ተገቢውን የባንክ አሠራር ሳይከተል ወይም ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ ከፍሎ ከተገኘ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የባንኩ ደንበኛ የእኔ ባልሆነ ሐሰተኛ ፊርማና ማህተም ከሒሳቤ ገንዘብ ስለወጣብኝ ባንኩ ተጠያቂ ነው ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን፣ ባንኩ ደግሞ በሰነዶቹ ላይ ያለው ፊርማና ማህተም ትክክል አለመሆኑን ለመጠራጠር ወይም ለማወቅ የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የባንኩን የተለመደ አሠራር መሠረት አድርጌ ከፍያለሁ በማለት ተከራክሯል፡፡ በዚህ ፍርድ መሠረት ባንኮቹ በተጭበረበረ ሰነድ ለተከፈለ ክፍያ ኃላፊነት የሚኖርባቸው ክፍያው የተፈጸመው የተለመደ አሠራር ተከትሎ (ፊርማውን ከናሙናው በማመሳከር) ካልተፈጸመ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ ፍርድ ሰበር ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 25306 ህዳር 12 ቀን 2000 ዓ.ም. ከሰጠው ፍርድ በመንፈስ የሚያፈነግጥ ነው፡፡ በዚህ ቀዳሚ ፍርድ ባንክ ከፍርድ ቤት ባልወጣና በተጭበረበረ የፍርድ ትዕዛዝ ገንዘብ ከፍሎ በመገኘቱ ኃላፊ ተደርጓል፡፡ የችሎቱ ምክንያት የተጭበረበረው ባንኩ እንጂ ደንበኛው ባለመሆኑ ጉዳቱንም ሊሸፍን የሚገባው ባንኩ ነው በሚል ነው፡፡ ሆኖም በሰ/መ/ቁ 48269 የተሰጠው ፍርድ የቀደመውን ፍርድም በመተቸት የተሰጠ በመሆኑ የተሻለ አስገዳጅነት አለው፡፡

ይህ ጉዳይ በቀጥታ ከውክልና ማስረጃ ጋር ባይያያዝም ከባንኮች ሰነድ የማረጋገጥ ግዴታ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ በሰ/መ/ቁ. 48269 የተሰጠውን ገዥ ፍርድ በማመሳሰል በመተርጎም (By Analogy) ለውክልና ካዋልነው ባንኮች ተጨማሪ ወይም አጋዥ የባንክ ግዴታን በውስጥ አሠራራቸው በመደንገግ ሊፈጽሙት ይችላሉ፡፡ ሆኖም የባንኩ አሠራር የውክልናን መሠረታዊ ዓላማ የሚያጨናግፍ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የሚሆነው ባንኮች በቅጽበት (በመረጃ መረብ) ወይም በፍጥነት (በስልክ፣ በፋክስ) ከመዝጋቢው አካል በማረጋገጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕጉ ከሚጠይቀው የውክልናን ገጽ የመፈተሽ ግዴታ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነት ፈጣን የማረጋገጥ ዘዴን የሚጠቀሙ ከሆነ ባንኮቹንም ደንበኞቻቸውንም ከሥጋት የሚታደግ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጭ ባንኮቹ ለቀናት/ለሳምንታት የማረጋገጥ ሥራ ላይ የሚተኙ ከሆነ ውጤቱ ቢከፋም «በውክልና አናስተናግድም» በማለት በራቸው በላይ ቢለጥፉ እረፍት ያገኛሉ፡፡

የባንኮቹ አሠራር አንድምታ
ባንኮቹ ማጭበርበርን ለመከላከል በሚል የተለያዩ አማራጮችን ሲወስዱ ይታያሉ፡፡ የተለመደው ከላይ የተመለከትነው በደንበኛው ወጪ ከመዝጋቢ አካላት ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወካይና ተወካይ በአካል እንዲመጡ በማድረግ የተወካዩን የውክልና ማስረጃና ፎቶግራፍ ከባንኩ ሒሳብ ጋር በማያያዝ ወደፊት ሲመጣ ያለ ችግር እንዲስተናገድ ማስቻል ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በስልክ በመደወል ከወካዩ የሚያረጋግጡበት ሁኔታ አለ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የባንክ አሠራሮች የሚመነጩት ባንኮች ውክልናን በማረጋገጥ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ ካለማወቅ ወይም ከመዘንጋት ነው፡፡

የባንኮቹ ሕጉን ያልተከተለ አሠራር ራሱን የቻለ አንድምታ አለው፡፡ ሲጀምር እያንዳንዱን የውክልና ሰነድ ከመዝጋቢው አካል ማረጋገጥ የመዝጋቢው አካልን ሥልጣን መጋፋትና መጠራጠር ነው፡፡ ሕጉ የሕዝብ ሰነድን የማረጋገጥ ከባድ ኃላፊነት ለመንግሥት ተቋማት መስጠቱ ሕዝብ በመንግሥት ተቋማቱ ላይ ባለው ከፍተኛ አመኔታ ነው፡፡ ባንኮች መዝጋቢ አካላት ሰነዶችን ለማረጋገጥና ለመመዝገብ የተሰጣቸውን ሥልጣን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባንኮች የውክልና ሥልጣንን ድጋሚ ማረጋገጥ ይገባናል ካሉ ግን የመዝጋቢ አካላቱ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡

ሌላው የባንኮቹ አሠራር በተደጋጋሚ እንዳልነው የውክልናን ዓላማ ያፋልሳል፡፡ ውክልና ዋና ዓላማው በአካል ተገኝቶ ግብይት ማድረግ ያልቻለን ወካይ ሰው በተወካዩ አማካይነት እንዲያከናውን ማስቻል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ውክልና የወካዩን ችግር ያቃልላል፣ የንግድ ልውውጥንም ያፋጥናል፡፡ ዳግም የውክልናን ሰነድ ወደ መዝጋቢ አካል መላክ ግን ሰዎች በውክልና እንዳይገበያዩ የመከልከል ውጤት አለው፡፡ በመነሻ ነገሩ እንደተመለከትነው ሰዎች ከርቀት ውክልና ከመስጠት ይልቅ በአካል መጥተው ያለፍላጎታቸው የንግድ ልውውጥን ለማከናወን በመገደድ አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ ይዳረጋሉ፡፡

የተወካይን ፎቶ በመቀበል ማስተናገድም ችግሩን በዘላቂነት አይቀርፍም፡፡ ሲጀምር ወካዩና ተወካዩ በአካል መጥተው፣ ተወካዩ ፎቶውን ሰጥቶ መስተናገዱ ተጨማሪ ግዴታ ከሌለው የሰነዱን ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ወካይና ተወካይ በመመሳጠር ለሚፈጽሙት የተጭበረበረ ሰነድ መከላከያ የመሆን አቅሙ አናሳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ወካይ በአንድ ግብይት ከአንድ የበለጡ ተወካዮችን የመወከል ሥልጣኑ በሕግ ዕውቅና ስላለው የአንዱን ተወካይ ፎቶ መለጠፉ የወካዩን ነፃነት የሚጋፋ ነው፡፡ ሁለተኛ ተወካይ ሒሳብ ለማንቀሳቀስ ሲመጣ “ፎቶህ ስላልተለጠፈ አናስተናግድም” የሚል ዘዬ ሊመጣ ነው፡፡

የውክልና ማስረጃን ለመዝጋቢ አካላት በመመለስ የማረጋገጥ የባንኮች አባዜ ሌላም አንድምታ አለው፡፡ ይህ አሠራር በሌሎች ሰነዶችም (የፍርድ ቤት ውሳኔ፣ የጋብቻ ማስረጃ፣ መታወቂያ፣ ወዘተ) መፈጸሙ ስለማይቀር ግብይትን በጥርጣሬ እንዲሞላ ያደርጋል፡፡ በፍርድ ቤት መብቱ ተረጋግጦለት የመጣን ደንበኛ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትክክለኛ (Genuine) ስለመሆኑ ሳናረጋግጥ መብትህን ልንፈጽምልህ (ገንዘብ ልንከፍልህ) አንችልም ሊባል ነው፡፡ ይህ ችግር ከሥጋት ባለፈ በተግባር በአንዳንድ ባንኮች መፈጸሙን ጸሐፊው ያውቃል፡፡

 ይህም የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ የመቃወም ውጤት ስለሚኖረው ከልካዩን ግለሰብም ሆነ ባንኩን ለፍትሐ ብሔርና የወንጀል ኃላፊነት መዳረጉ አይቀርም፡፡ በውክልና የጀመረው ሥጋት ወደ ሌሎች የሕዝብ ሰነዶች የሚቀጥል ከሆነ ባንኮች ተቋማቱን (ፍርድ ቤቶች፣ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ቀበሌ፣ ወዘተ) ወክለው እስካልሠሩ ድረስ በማረጋገጥ ጥረታቸው አይረኩም፡፡ ይህም የመንግሥት ተቋማት አመኔታ እንዳይኖራቸው በማድረግ ባንኮች የጥርጥር መልሕቅ በሕዝብና በመንግሥት መካከል በመሰንቀር አፍራሽ ሚና እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፡፡
ወካዩ ስልክ ላይ በመደወል ማረጋገጥም ተጨማሪ (Subsidiary) መተማመኛ ካልሆነ በቀር ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ ወካዩ ስልኩን ቢቀይር፣ ሌላ ሰው ቢያነሳው፣ መልስ መስጠት ፈቃደኛ ባይሆን፣ ወዘተ ባንኮች የተነሱበት የተሳሳተ የምክር ሐሳብ ይመክናል፡፡ ወካይ ወዶና ፈቅዶ በወከለው ጉዳይም ዳግም በስልክ ማረጋገጥ ወካዩን መጠራጠርና ማመናጨቅ ይሆናል፡፡

መፍትሔ ቢሆን
ባንኮቹ በአሠራር ያመጡትን ችግር ሊያሻሽሉት የሚችሉት በዋናነት ራሳቸው ናቸው፡፡ የባንክ ሠራተኞች ባንኮች የውክልና ሥልጣንን በማረጋገጥ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ የሚያውቁ አይመስልም፡፡ ከላይ በጽሑፉ እንደተመለከተው ባንኮች የውክልናውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የጽሕፈት ቤቱን ማህተምና ፊርማ በመመልከት፣ የውክልናውን ገጽ በማየት ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የዘለለ ምርመራ ማከናወን ግዴታቸውም አይደለም፤ ሕጉም አይፈቅድላቸውም፡፡ ስለዚህ በተግባር ውክልናን ወደ መዝጋቢ አካላት መላክ፣ በፖሊስ ፎረንሲክ ማስመርመር፣ ስልክ መደወል፣ ወዘተ ስህተት መሆኑን መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ለውጥ ለማምጣት ባንክ ውስጥ የተቀመጡ የሕግ ባለሙያዎች መነሳሳቱን ካልወሰዱ ሌላ ባለሙያ ቀዳሚ የሕግ ማስከበር ሥራ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የሕግ ባለሙያዎቹ ዝርዝር መመሪያ ማስተላለፍ፣ ሥልጠና መስጠት፣ ከዚያም አልፎ አስተያየት ሲጠየቁ በድፍረት ሕጉ የሚለውን ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሥጋቱ ከፍተኛና ቅርብ ከሆነ ደግሞ የማጣራቱን ኃላፊነት በቅጽበት ወይም በፍጥነት ለማከናወን ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር በመረጃ መረብ ለማረጋገጥ የሚቻልበትን አሠራር ማዘጋጀትና መተግበር፤ ካልተቻለ ደንበኛው ሳያውቅ በተለይ ብዙ ገንዘብ ለሚያወጡ ተወካዮች፣ በስልክ ከጽሕፈት ቤቱ ለማረጋገጥ መሞከር፣ የማጣሪያ ጥያቄዎችን ማቅረብ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈጣን አሠራር በአንድ በኩል የውክልና ንግድን በፍጥነት የማሳለጥ ዓላማ አያደናቅፍም፣ በሌላ በኩልም ባንኮች በሕጉ ከሚጠበቅባቸው ግዴታ በተጨማሪ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረጋቸው ያለባቸውን ሥጋት ያርቃል፡፡ ይህ አማራጭ የምዝገባ ሥርዓታችን ደካማ በሆነበት አገራችን እስከተወሰኑ ጊዜያት ሊጠቅም ይችላል፡፡

ባንኮቹ ከሕጉ ዓላማ ውጭ ውክልናን የመጣበት አካባቢ ድረስ ዳግም በመመለስ ጊዜ ማባከንና ደንበኞች ላይ ጉዳት ማድረስ የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ባንኮቹን ተጠያቂ ከማድረግ ውጭ ሥጋቱን የሚከላከል አይሆንም፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ባንኮች በውል ወይም ከውል ውጭ ኃላፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ደንበኛው ገንዘቡ በጊዜው ባለማውጣቱ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት ባንኮቹ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ መሪ ደንብ “ማንም ሰው ከራሱ ጥፋት የተነሳ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ላደረሰው ጉዳት ኪሣራ መክፈል አለበት፤” ሲል የደነገገውን መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡ በባንኮቹ ተገቢ ያልሆነ አሠራር በአካል ካለበት መጥቶ ገንዘቡን አሟጥጦ ከመውሰድ ባለፈ ባንኩ ላይ ክስ መስርቶ የሚያስፈርድበት ሁኔታ መኖሩን ማወቅ አይከፋም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡